Sunday, 05 November 2017 00:00

የሰ/ ኮርያ የኒውክሌር ሙከራ ከ200 በላይ ዜጎቿን ገድሏል ተባለ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ከሰሞኑ ሌላ የሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው ተብሏል

     ሰሜን ከኮርያ በቅርቡ ያደረገቺው ስድስተኛው የኒውክሌር ሙከራ ባስከተለው የመሬት መንቀጥቀጥና የዋሻ መደርመስ አደጋ ሳቢያ ከ200 በላይ የኒውክሌር ጣቢያው ሰራተኞች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የጃፓኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ የአሻይ ዘገበ ሲሆን የሰሜን ኮርያ መንግስት ግን ሃሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
አገሪቱ ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ፑንጌሪ ከተባለውና በሰሜን ምዕራብ ግዛቷ ከሚገኘው የኒውክሌር ጣቢያ ካደረገቺው የኒውክሌር ሙከራ ጋር በተያያዘ በጣቢያው ዋሻ ውስጥ በሬክተር ስኬል 6.3 የመሬት መንቀጥቀጥና ፍንዳታ መፈጠሩንና 100 ያህል ሰራተኞችን ወዲያውኑ መግደሉን የዘገበው ሮይተርስ፤ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በደረሰ ሌላ አደጋም ሌሎች ከ100 በላይ ተጨማሪ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ መነገሩን አመልክቷል፡፡
የሰሜን ኮርያ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባሰራጨው ዘገባ፤ መረጃው መሰረተ ቢስና አገሪቱ በኒውክሌር ፕሮግራም ላይ እያስመዘገበች ያለውን እመርታ ለማጠልሸት ሆን ተብሎ የተሰራጨ ወሬ ነው በማለት ማስተባበሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜናም የደቡብ ኮርያ የስለላ ተቋም፣ ሰሜን ኮርያ በቅርቡ ሌላ የሚሳኤል ሙከራ ልታደርግ በዝግጅት ላይ መሆኗን የሚያመላክት መረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
የስለላ ተቋሙ በሰሜን ኮርያ የሚሳኤል ፕሮግራም ተቋማት አካባቢ አዲስ ሙከራ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተጧጧፈ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 2942 times