እነሆ መፅሀፍ መደብር፣ ሊትማን ቡክስና ክብሩ መፅሀፍት መደብር በመተባበር በየወሩ መጨረሻ ባሉት ቅዳሜና እሁድ የሚያዘጋጁት የመፅሀፍ ሂስ ጉባኤና አውደ ርዕይ የዛሬ ሳምንት ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ትራኮን ህንፃ ላይ ይከፈታል፡፡
“ሀሳብን በሀሳብ መፈተን” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ የሂስ፤ ጉባኤና አውደ ርዕይ ላይ “የአለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ ገብረ-መሲህ ድርሰቶች (የኦሮሞ ታሪክ ከ1500-1900) የተሰኘው መፅሐፍ ለሂስ የተመረጠ ሲሆን መፅሀፉ በ19ኛው ክ/ዘመን ከተፃፉ መፅሀፍቶች መካከል የአገራችንን የ400 ዓመታት ታሪክና በተለይም የኦሮሞን ህዝብ ታሪክና ባህል በስፋት የሚያስቃኝ ነው ተብሏል ለሂስና ለውይይት የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ሥነ-ጥበባት መምህር አቶ አበባው አያሌው እንደሆኑም የአውደርዕዩ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገልፀዋል፡፡ ቅዳሜና እሁድ አውደርዕዩን የሚጎበኙ የመፅሀፍት እቁብን ጨምሮ ከ25 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸው መፅሀፍት መግዛት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡