Sunday, 05 November 2017 00:00

“መንገደኛ” መፅሐፍን በስደት አገር እንዳነበብኩት

Written by  ዳዊት ንጉሡ ረታ(ከደቡብ ኮሪያ ሶል ከተማ)
Rate this item
(2 votes)

 ለአንድ መፅሃፍ የተዋጣ መሆን መቼት (መቼና የት) ያለው ዋጋ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ የልቦለድ አፃፃፍ አለባውያን አስረግጠው ቢነግሩንም እኔ ደግሞ አንድን መፅሃፍም በልዩ ሁናቴ ለማንበብ ራሱ፣ መቼት ያለው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ከተመክሮዬ በመነሳት እመሰክራለሁ፡፡
በደቡብ ኮሪያ እገኛለሁ፡፡ አንድ ዓመት አለፈኝ። በስደት ላይ ሆኜ ስለ ስደት የሚያትት መፅሐፍ የመውጣቱን ዜና ከሰማሁበት ቀንና ሰዓት አንስቶ መፅሐፉን ለማግኘትና ቶሎ አንብቤ፣ ከአንድ ዓመት የስደት ቆይታዬ አንፃር ልመለከተው በማሰብ፣ ወዳጆቼን ላኩልኝ ስል ተማፀንኩ፡፡ “መንገደኛ” መፅሐፍ ቶሎ ተገኝቶ ሊላክልኝ አልቻለም። ምክኒያቱም የመጀመሪያው ዕትም ገበያ ላይ ባለመገኘቱ ነበር፡፡ የደራሲው የቅርብ ወዳጅ እኔ ወዳለሁበት ከተማ ለስራ ጉዳይ በመጣች ጊዜም ከደራሲውም ቢሆን አፈላልጋ እንድታመጣልኝ ቃል ባስገባትም ሊሳካ አልቻለም፡፡ የሆነው ሆኖ በቅርቡ እጄ ገብቶ በስስት አንብቤ ጨረስኩት፡፡ ስደት ላይ ተሁኖ፤ ስለ ስደት የሚያትት ሊያውም ጥናትን መሰረት አድርጎ የተሰራ መፅሐፍ አንብቦ ዝም ማለት ተገቢ ባለመሆኑ፣ የነቢይ መኮንን መንገድን ተከትዬ እኔም እይታዬን እንዲህ ላጋራ፡፡
ከፀሃፊው ማንነት አንፃር፡- የመፅሐፉን ሽፋን ተንተርሶ በተቀጠለ ገፅ ላይ ፀሃፊው የምጣኔ ሀብት፤ የሥነ-ሕዝብና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ እንደሆነና በሥነ-ሕዝብ፤ በአካባቢ ጥበቃ፤ በወጣቶችና በስደት ዙሪያ ከዚህ ቀደም የምርምር ስራዎች እንደሰራ ያወቅሁ ጊዜ “መንገደኛ” መፅሐፍ በትክክለኛው ሰው እንደተፃፈ አመንኩ፡፡ ብዙ ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ዘርፈ ብዙ ሙያዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከሙያና ከተመክሮአቸው የሚያገኙዋቸውን ዕውነታዎች፣ እንዲህ ወደ መፅሐፍ ለውጠው ስለማያስነብቡን በርካታ ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የትናትና የምርምር ስራዎች የመደርደሪያ ማድመቂያ ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከዋና ዘርፋቸው ባሻገር ወደ መፅሐፍቱ መንደር ጎራ እያሉ ያሉትን እንደነ ዶ/ር ምህረት ደበበና ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ዓይነቶቹን በቅድሚያ በርቱልን ማለት ያስፈልጋል፡፡
የመፅሃፉ መታሰቢያነት፡- ፀሃፊው የመፅሐፉን መታሰቢያነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጉዋዙና በአገሪቱ ሲተጉ ህይወታቸውን ላጡ እንዲሁም እነርሱ ሳይኖሩ ሌሎች እንዲኖሩ ቤዛ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማድረጉ ትክክለኛነትና ሚዛናዊነት፣ ለመፅሐፉ የሰጠሁትን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል፡፡ እነዚያ ያልተዘመረላቸው መንገደኞች፤ አስታዋሽ ማግኘታቸውንና ዛሬ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚጫወተውን ገንዘብ የሚልኩት በምን ዓይነት የህይወት ውጣ ውረድ እያለፉ እንደሆነ በተገቢው ሁናቴ ለአንባቢ ማሳየቱ ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡
መረጃዎችና ገጠመኞች፡- ደራሲው ከሙያና ከስራ ልምዱ እንደዚሁም በዋነኛነት መፅሐፉን ለማሰናዳት ካደረገው ሰፊ ዝግጅት፣ ስደትና መሰል ጉዳዮችን በተገቢው መንገድ ለመተንተን ችሎአል፡፡ ለዚህም በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ ቀላል የማይባሉ መረጃዎች መቅረባቸውን በዋቢነት መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ቁጥሮች፤ ቀናትና የሌሎች ፀሐፍት ጥናቶችም በሚገባ ተካተውበታል፡፡  ፀሃፊው በዋናነት ትኩረቱን አድርጎ የተነሳበት ርዕሰ ጉዳይ ስደት ቢሆንም ይህንኑ ለማዘጋጀት ባደረጋቸው ጉዞዎቹ ያጋጠሙትን ገጠመኞች እያዋዛ ያቀረበበት መንገዶች፣ የመፅሐፉ ሁነኛ ውበት ሆነው ታይተውኛል፡፡ በተለይም በተለያዩ ጊዜያት በደቡብ አፍሪካ፣ ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ያደረጋቸው ውሎዎች የማይረሱ ናቸው፡፡
ፀሐፊው፤ ”ይህ ሁሉ መከራና በደል እየደረሰ ቢሆንም አሁንም ሰዎች በልባቸው ጥሩ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡”  ብላ ልክ እንደ አና ፍራንክ የምታምን በጆሃንስበርግ የምትኖር የጎዳና ተዳዳሪን አስደናቂ ዕይታ ሲያጋራንና “ጥቁር የአሜሪካ መሪ በነጮች ቤተ-መንግስት!” ብሎ የኦባማን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን ያጣጣለ የሌላ የጎዳና ልጅ ጥልቅ እይታን ገጠመኙ አድርጎ ሲነግረን፣ መፅሐፉን ሳንሰለች እስከ ዘለቄታው እንወርደዋለን፡፡
ስደት! የመፅሃፉ አጠቃላይ ጭብጥ፡-
ቀላል መስሎን ነበር ከቤት ስንወጣ
ሊማሊሞን ስናልፍ አላማጣ መጣ፡፡
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን በዋቢነት በመጥቀስ፣ በገፅ 162 ላይ በመግቢያነት ፀሐፊው ያሰፈረው ከላይ የተነበበው ስንኝ፣ ለእኔ የመፅሐፉን ጭብጥ በሚገባ የሚገልጽልኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በተለይም በምዕራፍ ሁለት ላይ የሚተረከው የኢዛና የህይወት ውጣ ውረድ በዚህ ስንኝ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይስተዋላል፡፡
ስደት ለአብዛኞቻችን ቀላል መስሎን ነበር ካገር ስንወጣ ነው፡፡ ስለ ውጪ አገራት አልጋ ባልጋነት እየተሰበክን ኖረን፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሆነን ከመፈጠር፣ ውጪ አገር ዛፍ ሆነን ብንፈጠር ይሻለናል” ብለን ስንቀልድ አድገን፣ “እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል” እያልን ስንተርት ኖረን፣ “ያልተገላበጠ ያራል” ብለን ስንፎክር ከርመን፣ “የተስፋይቱ ምድር” እያልን ስናልም ኖረን……. ድንገት ቀላል ይመስለንና ካገር ባንድም በሌላም አጋጣሚዎች እንወጣና እንሰደዳለን፡፡ ታዲያ ከስደት ዕውነታዎች ጋር የዕውነቱን መፋጠጥ የምንጀምረው ገና እግራችን በሌላ አገር ለመገኘት ባደረግናቸው ሙከራዎችና ተሳክቶም ድንገት ራሳችንን በሰው አገር ያገኘነው ጊዜ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ወዳጅ ዘመዶቻችን የሰው አገር ባህር ዳርቻዎች ጋር፣ ፎቅና መኛፈሻዎች አካባቢ፣ በምርጥ ልብሶች ተውበው የተነሱዋቸው ዓማላይ ፎቶግራፎች ውስጣቸው የኢዛናን አሳዛኝ የታሪክ ቀንበር እንደተሸከሙ የሚገባን ገና የሳምንታት ዕድሜን በተሰደድነበት አገር ማስቆጠር ስንጀምር ነው፡፡ ህይወትን ከዜሮ ለመጀመር ጥረት ሲደረግና መያዣ መጨበጫው ሲጠፋ፤ ተስፋ የተሰቀለ ዳቦ ሆኖ እሱን ለማውረድ ያለው መባዘን ዕልህ አስጨራሽ እንደሆነ መረዳት ስንጀምር፤ ማንም ማንንም መርዳት በማይችልበትና የቀደመ ያሸንፍ! መርህ ድንገት የህይወት መመሪያችን ሆኖ ቁጭ ሲል፤ የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ ጨካኝ ነውን? ብለን መፈጠራችንን እስክናማርር ድረስ የጭካኔን ጥግ ያየን ጊዜ…. ወዘተ ያንጊዜ የነጋድራስን የግጥም ስንኝ ለራሳችን ጮክ ብለን እንላታለን፡፡
ቀላል መስሎን ነበር ከቤት ስንወጣ ….ሊማሊሞን ስናልፍ አላማጣ መጣ፡፡
ስደት በርካታ ያልተነገረለት ዕውነታ አለው። በመፅሐፉ ላይ የሚተረከው የኢዛና ዕውነተኛ ታሪክ ቀላል መስሎን ነበር ብሎ ካገር ለሚወጣ ሰው፣ ሳይወድ በግድ ልብ የሚያስገዛ አስደንጋጭ ዕውነታ አለው፡፡ የሰው ልጅ ሊያልፍበት ይችላል ብለን የማናስባቸው ነገር ግን በስደት ዓለሙ ዘወትር ሊከሰቱ የሚችሉ ዕውነታዎች በመፅሐፉ ሲተረኩ አይናችንን አስጨፍኖ ያንዘፈዝፈናል፡፡ በውሃ ላይ የምትሄድ መርከብ በሻርክ ስትናወጥ፣ ሻርኩን ፀጥ ለማሰኘት ድንገት በመርከቡዋ ከተሳፈሩ ሰዎች አንዱን ወጣት አንስቶ ወደ ውሃው ሲወረውረው ማየት….ከዚያም ሻርኩ ፀጥ ሲል “እናንተ እድለኞች ናችሁ…ከዚህ ቀደም እኮ ከአስር በታች ሳንሰጠው ፀጥ አይልም” ሲባል ማዳመጥ….ሊማሊሞን ስናልፍ አላማጣ… ያስብላል፡፡
የአገር ልጅ ዕውነታ፡- በመፅሐፉ በጥሩ ሁናቴ የተተነተነው፣ መንገድ አሻጋሪዎች ከሆኑት ውስጥ የራሳችን የአገር ልጆች የሚያሳዩት የጭካኔ ጥግ ነው፡፡ እንደ ፀጋዬ አይነቶቹ የጭካኔ አውራዎች፣ ከኢትዮጵያዊ ማንነትና ስነ-ልቦና ፈፅሞ በማይጠበቅ መልኩ በገዛ ወገናቸው ላይ የሚፈፅሙት ግፍና ተንኮል፣ አብዛኛው ስደተኛ ባገሬ ልጆች ይደርስብኛል ብሎ ፈፅሞ የማያስበው ነው፡፡ ዕውነታው ግን በስፋት በመፅሐፉ ተተንትኗል፡፡ እነ ፀጋዬ የስደት ዓለሙ መንግስት ለመሆን ችለዋል። ያስራሉ፤ ይገርፋሉ፤ ያስርባሉ፤ ይዘርፋሉ፤ በል ሲላቸው ገንዘብ በመቀበል መንገድ ያሻግራሉ፡፡ ይህ ዕውነታ በመፅሐፉ በመቅረቡ፣ ለስደት ያቆበቆበ ቢኖር ማድረግ የሚገባውን ጥንቃቄ አስቀድሞ ይረዳና ወገኔን ካገኘሁማ ከሚል ሞኝነት ራሱን ቢያንስ ሊከላከል ይችላል፡፡ በዚያው ልክም የአገር ልጅም የአገር ልጅ ያልሆኑ የሌላ አገር ዜጎችም ባልታሰበና ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ህይወታችን ገብተው፣ ድንገት ሲረዱንና ህይወታችንን ከአደጋ ሲታደጉን እናነባለን፡፡ ይህም በስደቱ ዓለም የሚታይ  የህይወት ሌላኛው ገፅታ ነው፡፡
ጥቁር በጥቁር ላይ፡- ከደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ፣ ህይወትን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ አስደናቂ ነው፡፡ በመፅሐፉ ላይ በአፓርታይድ ዘመን ጥቁሮችን ሲጨፈጭፍ የነበረ የአንድን ነጭ ሃውልት ለማስፈረስ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ስንት ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳልወጡ፣ አንድ ጥቁርን አቃጥለው ወይም በድንጋይ ወግረው ለመግደል ግን ሰከንድ እንደማይፈጅባቸው እናነባለን፡፡ ጥቁር በጥቁር ህዝብ ላይ እንዲህ የነገሰበት አምባገነናዊ ስርዓት፣ ከአገር መንግስታት አልፎ በወንድማማች ህዝቦች መካከልም ሰፍኖ በጉልህ እየታየ፣ የታላቁዋ አንዲት አፍሪካ ምስረታ የቁም ቅዠት ሆኖ ይታያል። ያም ሆኖ በመፅሐፉ ገድላቸው የሚተረክላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በደቡብ አፍሪካ ምድር በየደቂቃና ሰከንዱ መጤ ከሚሉዋቸው የአገሪቱ ነዋሪዎች ጋር የሚያደርጉት የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ትግል፣ ምን ያህል መንፈሰ ብርቱዎች እንደሆንን የሚያስመሰክር ሃቅ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ለማመን በሚያስቸግር የኑሮ ዓለም ውስጥ ሆነው ንግድ ለማስፋፋት፣ አዳዲስ አሰራሮችን ለማስተዋወቅ፣ ከተማ ለማሳደግ፣ ማህበራዊ ኑሮ ለመመስረት፣የአገር ቤት ንግዶችን ለማስተዋወቅ… ወዘተ የሚያደርጉት ጥረት በዕውነት ኢትዮጵያውያን ዕድሉና አጋጣሚው ቢያመቻቸው ምን ዓይነት ዜጎች እንደሚወጣቸው የሚያሳይ ሃቅ ነው፡፡
አለመገዛት! ዕድሜ ለአያቶቻችን፡- እኔ በምኖርበት በደቡብ ኮሪያ፣ ኢትዮጵያውያን ለአገሪቱ የችግር ጊዜ ያደረግነው ውለታ ታስቦ የሚያስገርም ሃውልት ተሰርቶልናል፡፡ ይህ መሆኑ የሚሰጠን የስነ-ልቦና ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ በቅኝ ግዛት ባለመያዛችን ምክኒያት በአገሪቱ ተሰደው ከሚገኙ ከማናቸውም የአፍሪካ አገራት ዜጎች የበለጠ አንገታችንን ቀና፣ ደረታችንን ነፋ አድርገን እንደምንኖር ለአንድ ዓመት ያህል አስተውያለሁ። እኛ ኢትዮጵያውያን ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጨርሶ በማይገኙባቸው፣ ነጮች ብቻ አዘውትረው በሚገኙባቸው የመዝናኛና የጉብኝት ስፍራዎች ወዘተ-- ከነጮች እኩል እየተጋፋን ስንጓዝ የሚሰጠው የውስጥ እርካታ የተለየ ነው፡፡
ይሕ ዕውነታም የኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በደቡብ አፍሪካ ሲፈፅሙት በመፅሐፉ ሲታይ፣ ዕድሜ ለአያቶቻችን ያስብላል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ራሳቸው ዜጎቹ የማይሞክሩትን ንግድ በመጀመር፣ የራሳቸውን ከተማ በማስፋፋትና በማሳደግ፣ ከዚያም ሲያልፍ ለነዋሪው ዱቤ በመስጠት አዳዲስ አሰራሮችን ኢትዮጵያውያን ሲያስተዋውቁ፣ ጠጅና ጠላን ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ነገሮች ለገበያ ሲያቀርቡ፤ ዱርየዎችንም ተባብረው ሲያሯሩጡ እናነባለን፡፡ ይህ በደም የተላለፈ የሚመስል ዕውነታ ምንም እንኳን በስደት ላይ ብንሆንም፣”ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ”ን ያስታውሳል፡፡ ያም ሆኖ በደቡብ አፍሪካ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ በሆኑና በቡድን በሚደራጁ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው በደልና ሰቆቃ ተቆጥሮ የማያልቅ እንደሆነ ከመፅሃፉ እንረዳለን፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ “መንገደኛ” መፅሃፍ ያስደምመናል፡፡ በመጨረሻም ስደትን በተመለከተ ምን መደረግ እንደሚገባው ፀሐፊው እንደ ባለሙያነቱ የመፍትሄ ሃሳቦችንም ያቀርባል፡፡ በመፅሐፉ ላይ የተመለከትኩዋቸውና ቢስተካከሉ ብዬ የማስባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ላነሳ እወዳለሁ።
ርዕሱ፡- “መንገደኛ” ከሚባል በሽፋን ስዕሉ ላይ እንደሚታዩት በርከት ያሉ ሰዎች፣ “መንገደኞች” ቢባል መልካም ይመስለኛል፡፡ ምክኒያቱም በመፅሃፉ የቀረበው ታሪክ፤ የአንድ ሰው ሳይሆን የብዙ፣ ታሪካዊ ተምሳሌቱም ለሁላችንም በመሆኑ፣ ከነጠላ ይልቅ በብዙነት ቢወከል ከሚል የመነጨ ነው፡፡
አላስፈላጊ፡- አብሬ ጫት ቃምኩ፤ ሜክ ኤ ፕላን /ሙስና/ ሰጥቼ ጉዳዬ ተሳካልኝ ወዘተ ዓይነት ታሪኮች፣ የደራሲው ዕውነታ ቢሆኑም በመፅሐፉ የመካተታቸው አስፈላጊነት አይታየኝም፡፡ ለአንባቢ ሌላም አሉታዊ ትርጉም ሊሰጡ ስለሚችሉም፡፡
ያልተቃኙ፡- ደራሲው በወጣቶች ዙሪያ ብዙ ምርምር እንደማድረጉ የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ለወጣቶች ዝግ መሆኑ፤ ፈልቅቀው የገቡትም ስደት ዕጣ ፈንታቸው እንደሆነ፤ ፖሊሲዎችና አተገባበራቸው ለየቅል በመሆናቸው የወጣቶች ስደት እንደተባባሰ፤ በተለይም ደግሞ ደራሲው የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ባለሙያ እንደመሆኑ፣ የህዝብ ቁጥር መብዛት ዋንኛ የስደት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል በስፋት አለመተንተኑ በእኔ ዕይታ የመፅሐፉ ውስንነቶች ናቸው ብዬአቸዋለሁ፡፡ መንግስት ስደትን ለመከላከል እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት፣ ከዘመቻ ስራ ያላለፈ መሆኑን ለመመስከር ፀሐፊው በመፅሃፉ ማካተት ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ምንም እንኩዋን ስደትን በተመለከተ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚ/ሩ የሆነ አንድ አደረጃጀት ቢኖርም ያን ጊዜ በሊቢያ የታረዱ ወንድሞቻችን ዜና በተሰማበት ወቅት አንዳንድ የሚዲያ ውይይቶችን ከማካሄድ ባለፈ በተጨባጭ የሰራው ስራ ምን እንደሆነ ተፈትሾ ቢካተት ለሚመለከተው ሁሉ ትልቅ ግብዓት ይሆን እንደነበር አምናለሁ፡፡
ምስጋና፡- ፀሐፊው በምስጋና ገፁ ላይ በርካታ ግለሰቦችን እንደየ አስተዋፅዖዋቸው ያመሰገነ ቢሆንም በመፅሐፉ እያንዳንዱ ምዕራፍ መግቢያ ላይ ግጥሞቻቸውን ለተጠቀመባቸው ደራሲያን ምስጋና መስጠት ተገቢነት ነበረው እላለሁ። በተረፈ “መንገደኛ” መፅሐፍ፣ ከመፅሐፍነቱ ባሻገር፣እኔም የደቡብ ኮሪያ ቆይታዬን በተመለከተ እንድጽፍ ንሸጣን ጭምር ይዞልኝ የመጣ መልካም ዕድሌ ነው እላለሁ፡፡
ቸር ያገናኘን.... መልካም ሰንበት!

Read 2680 times