Sunday, 05 November 2017 00:00

ከሃሳብ ሙላት … የምናብ ሙላት!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

 ... ፅሁፍ ለመፃፍ ስነሳ… ራሴን አዳምጣለሁኝ፡፡ የማደምጠው የምናብ መጠኔን ለመለካት ብቻ ነው፡፡ የምናብ “ጌጄን” ብቻ ነው የምለካው፡፡… ልክ ማርሎን ብራንዶ እንዳለው፣ “ለመተወን ስመጣ ውስጤ ያለውን አቅም አጤናለሁ፡፡… አቅሜ መቶ ፐርሰንት መስሎ ከተሰማኝ…መድረክ ላይ ወጥቼ ሰባ አምስት ፐርሰንቱን እተውናለሁ፡፡ ሰባ አምስት ፐርሰንት ይዤ የመጣሁ ከመሰለኝ ሀምሳ ፐርሰንቱን እሰራበታለሁ፡፡… ይዤ የመጣሁት አቅም ሰላሳ አምስት ከሆነ… መድረክ ላይ አልወጣም፤ ፊቴን አዙሬ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ” (ተዋናዩ የተናገረውን የጠቀስኩት ቃል በቃል አይደለም፡፡ ጥቅል መንፈሱ ግን እዛው ገደማ ነው፡፡
የእኔም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከምፅፈው ነገር በፊት የምናብ ሙላት መኖሩን አረጋግጣለሁ፡፡ ምናቡ ካለ ስለ ምንም ነገር መፃፍ ይቻላል፡፡ ከምንም ነገር ተነስቶ የትም መድረስ ይቻላል፡፡ የማይያያዙ ጉዳዮችን ምናብ ካለ ማጋባት አልያም ተጋብተው የኖሩትን መለያየት ይቻላል። ሰባኪ ብቻ ነው አጀንዳ ይዞ የሚመጣው፡፡ አጀንዳ ይዞ ለሚመጣ፣ ምናብ ብዙ አያገለግለውም፡፡
ጥበብ ከፍ ያለ የሚሆነው የሰበካ ሸክም ቀንሶ፣ የምናብ አቅም ከፍ ያለ እንደሆነ ነው፡፡ ቅርፃዊያን እንደዛ ያምናሉ፡፡ እርግጥ ቅርፅና ይዘት እንደማይለያዩ የታወቀ ቢሆንም …ቅርፁ ሲታቀድ ባልታወቀ መንገድም ቢሆን ይዘት አብሮ መፀነሱ ባይቀርም… እኔ ግን ይሄ የከረመ እውነት እንደማያገባኝ ችላ ብዬ የምናቤን መጠን ብቻ ለክቼ እነሳለሁኝ፡፡ አንዱን ቅርፅ በተወሰነ ሀሳብ ላይ ተመስርቼ እጀምርና.. ሀሳቡ ወደ አንድ ጥግ እያደላ የመጣ ሲመስለኝ አቆመዋለሁኝ፡፡… በአንድ ፅሁፍ ላይ አንድ እምነትን እያመነዥግሁ ከምሰብክ ቅርፁ ላይ ብመሰጥ ይሻላል፡፡
…ለመሆኑ ድምዳሜ ምንድነው?... ከሀሳብ አለም የሚመጣ እርግጠኝነት ነው?...ወይንስ ከተሞክሮ የተገኘ የማይሻር እውነት?
መጀመሪያ ዳርዊን ነው ስለ ዝግመተ ለውጥ ፅንስ ሀሳብ አጥንቶ ያቀረበው፡፡ ግን ጥናቱ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ የሚጠቁመው ብዙ ልኮች መፍረስ እንዳለባቸው ነው፡፡
የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥና በተፈጥሮ ምርጫ እየነፀረ የመጣ ከሆነ… የተፈጥሮ ምርጫ ደግሞ ጠንካሮችን እያሳለፈ ደካሞቹን የሚጥል ከሆነ… ዝርያ ወይንም ዘር መሰረታዊ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቶማስ ጋልተን (የራሱ የዳርዊን አጎት ልጅ ነው)…በዘር ማዳቀል ላይ መሰረት ያደረገውን ፍልስፍና (eugenics) ከዳርዊን ጋር አያይዞ መስበክ ቀጠለ፡፡
ዳርዊን በሀልዮው ለማሳየት እንዳጣረው፤ ዝርያዎች (species) አንዱ ከሌላው እየተለያየ እና እየተመረጠ የዘለቀው፣ ጠንካራው ዘር ከጠንካራው ጋር ሳይከለስ መዝለቅ ከቻለ ነው ብሎ ጋልተን ደመደመ፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ ጠንካራና ደካማ ዘር የሚለውን ራሱ የሚወስነው ከሌላ ቅድመ እምነት ተነስቶ ነበር፡፡ ልክ እንደ ከብትና የእህል ዝርያ፣ ጥሩው ከጥሩው መደቀል ይገባዋል አለ፡፡ የከብትና የእህል ዝርያን በማዳቀል የግብርና ምርታማነታችንን እንዳሻሻልነው፣ የራሳችንንም ዘር በጥንቃቄ በማዳቀል ከጥሩ ወደ በለጠ ጥሩ፣ የሰው ልጅን ዝግመተ ለውጥ እናሳድግ… ማለቱ ነው፡፡
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1885… ለዚህ ሀሳቡ መጠቅለያ እንዲሆን “eugenic” የሚባለውን ቃል ፈጠረ፡፡ ወይንም “ኮይን” አደረገ፡፡ “eugenics”፡- ማህበረሰባዊ የዳርዊኒዝም አተገባበር ተብሎም ተጠርቷል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዝርያ ምርጥ አድርጎ በዝግመተ ለውጥ ፉክክሩ ወደ ፊት ማራመድ…በግል መፍጨርጨር ሳይሆን በማህበረሰብ ደረጃ አንድ ላይ ምርጥነትን ማስቀጠል ነው አላማው፡፡
ካርል ፓርሰን ይኼንን የጋልተን ሀሳብ ወስዶ ወደ ሀገር አውድ…በሀገር በሚመሰል ማህበረሰብ ላይ ተረጎመው “It is not the individual that must be eugenic; it is the nation…”
ካርል ፓርሰን ከሀገሩ የእንግሊዝ ነዋሪ ዜጎች ምርጥ የሆኑትን ቢያዳቅል፣…ብሪቴን… በአለም ላይ የበላይነቷን እንደያዘች ትዘልቃለች… ከዘወትር ባላንጣዋቿም ትጠበቃለች…በማለት አሰበ፡፡ ይኼንን ሀሳቡን በጊዜው የነበረውም መንግስት ደገፈው፡፡
“At its birth eugenics was nto a politicised science; it was a scienceised political creed” ይላል ማት ሪድሊ፡፡
ለምሳሌ፤እንግሊዝ ደቡብ አፍሪካ ካሉ ነጮች ጋር በ1908 የ“Boer War” ተብሎ የሚታወቀውን ለመዋጋት ዘማቾችን ስታዘጋጅ…ወታደሮቹ ዝርያና አስተዳደጋቸው መመዘን አለበት በሚል ብዙ ክርክር አድርጋለች፡፡ (ዊኒስተን ቸርችል በዚህ ጦርነት እንደተሳተፈ መጥቀስ አስፈላጊ ባይሆንም ዝም ብዬ ብጠቅሰው ምን ይለኛል?.. በሚል ጠቅሸዋለሁኝ)
በዛው ዘመን አካባቢ ከጀርመንም ተመሳሳይ አቅጣጫ እየተያዘ ነበረ፡፡ በኒቼ ፍልስፍና ምክኒያት ይሆን ወይንም የኧርነስት ሀይክል (Ernst Haeckel) “የባዮሎጂያዊ እጣ ፈንታን በራስ መወሰን” የሚል አስተሳሰብ… ብቻ ጀርመንም ከእንግሊዝም በበለጠ… የባዮሎጂ ሳይንስን ሀገር ወዳድነት (Nationalism) ጋር ደባልቃው ህዝባዊ እንቅስቃሴ አደረጉት፡፡
የሚያሳዝነው ግን፤ ይኼ እንቅስቃሴ በሁለቱም ሀገሮች አቅጣጫውን ቀይሮ… “ምርጥ ዝርያን አዳቅሎ” ማሳደግ ከሚል አዝማሚያ ይልቅ “ምርጥ ያልሆኑ ዝርያዎችን” እንደ አረም ቀንሶ ወደማጥፋት አሳበረ፡፡
ምርጥ ብለው የሚያምኑት እነማንን እንደሆነ መግለፅ አያስፈልግም፡፡ በወቅቱ የፖለቲካና የማህበረሰብ ልጓም የጨበጠን…ወይንም ኮርቻን የተፈናጠጠ “ምርጥ” ብለው ራሳቸውን እንደሚስሉ አያጠያይቅም፡፡ ባያጠያይቅም፤ “ምርጥ ያልሆኑ ዝርያዎች” ናቸው ብለው ባስቀመጡት ትርጉም ውስጥ “ሰካራሞች፣ የሚጥል በሽታ (epiletics) ያለባቸው፣ የአእምሮ ዝግመት ተጠቂዎች…ወዘተ” የሚል ፍረጃ ላይ ደረሱ፡፡
እንግዲህ ፍረጃው ራሱ…የፈራጁን ሥነልቦና ግልባጭ ነፀብራቅ ነው፡፡ “reverse psychology” እንዲሉ ፈረንጆቹ፡፡ ማለትም ከማህበረሰቡ የመሪነት ማማ ላይ ያሉት የሚያምኑት…ወይም የሀገሪቷ ችግር ብለው ከሚያስቡት ፖለቲካ በመነሳት “ምርጥ” እና “ውዳቂውን” ለይተው ለመምታት ይጠቅማቸዋል፡፡… ቅድም እንዳልኩት “ኢዮጄኒክስ” የሚባለው ሳይንስ፣ ከሳይንስነቱ ፖለቲካነቱ ያይላል፡፡
በዛው ዘመን አካባቢ አሜሪካ ቀድመው የገቡ የአንግሎ ሳክሰን ዘር ይዘናል የሚሉት የኢዮጂኒክስ ሳይንስን ስብከት አጨብጭበው የተቀበሉት … ከደቡብ አውሮፓ በፍጥነት ወደ አሜሪካ እየፈለሰ ያለውን ስደተኛ… በዚህ ፅንሰ ሀሳብ ለመዋጋት ይቻላል ብለው ስላሰቡ ነው። እ.ኤ.አ በ1924 የፀደቀው ፀረ ስደተኛ አቋምን የያዘው የህግ ረቂቅ፤ “የስደተኛ እገዳን” የሚደነግግ የሆነው ከዚሁ ሳይንስ መነሻ ነው፡፡ ወደ 1911 ዓ.ም ገደማ በአሜሪካ ያሉ ክልሎች፣ የአእምሮ በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዳይራቡ የሚያደርግ…የህግ አንቀፅ በፍትህ ሥርዓታቸው ላይ አስገብተው ነበር፡፡ … ህጉ ወንጀለኛን በሞት ፍርድ የመቅጣት ሀላፊነት የሚያከናውን ከሆነ የመራባት መብትንም መስጠትና መከልከል መብቱ ነው ተብሎ፣ ከህዝብም ብዙ ተቃውሞ አልገጠመም፡፡
አሜሪካ የግለሰብ ነፃነት እስከ ጥግ ድረስ የተከበረባት የምትባለው ሀገር፣ በእነዚህ አመታት (በቨርጂኒያ ለምሳሌ ምርጥ ያልሆኑትን የማኮላሸቱ ተግባር እስከ እ.ኤ.አ 1970 ድረስ በህግ ከለላ ስር ሆኖ ይከናወን ነበር)… ወደ 100,000 ገደማ የሚሆኑ የሀገሪቱ ነዋሪዎች፣ “አእምሯችሁ ዘገምተኛ ነው” በሚል ምክኒያት እንዳይራቡ ተደርገዋል፡፡ እንደ ከብት ተኮላሽተዋል፡፡
አሜሪካ በማኮላሸቱ ሂደት በቁጥር ከተሰላ መሪ ብትሆንም በሌሎች አለማት ያሉ መንግስታትም ተመሳሳይ ድርጊት በህግ ከለላ ስር ሆነው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ወይንስ ጀርመን ናት በአለም ላይ የማኮላሸቱን ሬከርድ በመሪነት የተቆጣጠረችው?... ጀርመን በመጀመሪያ ላይ ወደ 400,000 ዜጎቿን እንደ ከብት ቀጥቅጣ አኮላሸች፡፡ በኋላ ከተኮላሹት ብዙዎቹን ገደለቻቸው፡፡
እንግሊዝ ግን፤ ምንም እንኳን የኢዮጄኒክስ ሳይንስ የፈለሰፈች ብትሆንም ህግ አድርጋ ሳታፀድቀው ቀጥላለች፡፡ ምናልባት ህግ ያላደረገችበት ምክኒያት የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ፈርታ ነው ይባላል፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤ/ክ ጠንካራ መሰረት በጣለባቸው ሀገራት (ወይንም ተፅዕኖ ማድረግ አቅም ባለበት ሀገራት) የዚህ የኢዮጄኒክስ ሳይንስ ህጋዊ አልተደረም፡፡
ሶሻሊስቷ ራሽያ ህጉን ተግባራዊ አላደረገችውም፡፡ እንዲያውም ሶቪየቷ ራሽያ ምርጥ ጭንቅላት ያላቸውን ነበር እያደነች የምትገድለው፡፡ የአእምሮ ዘገምተኝነት ካለባቸው ይልቅ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ለስርዓቱ አደጋ መስለው ይታይዋት ነበር፡፡ ስለዚህ ህጉን በፍትህ መፅሐፍት ላይ አላሰፈረችም፡፡
…አሁን አሁን…ዘርን በማዳቀል ማሻሻል (eugenics) የሚለው ሳይንስ፣ እንደ “ሀሳዊ ሳይንስ” (Pseudoscience) እየተቆጠረ መጥቷል፡፡ ግን መጥቷል ወይ? ብዬ እንድጠራጠር የሚያደርጉ የዜና ሽውታዎችን እሰማለሁ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው አንድ ሰው በአንዲቷ የስካንዴኒቪያ ሀገር፤ “ስደተኞችን ብቻ እየለየ የሚያጠቃ በሽታ ተከስቷል” ሲለኝ… ምናልባት ይሄ ነገር አሁንም በአዲስ መልክ ተሻሽሎ ቀጠለ እንዴ? ብዬ እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡
…እና ዘንድሮ ኢዮጄኒክስ በጄኔቲክስ ሳይንስ ተተክቷል፡፡ ይዘት በይዘት ተቀይሯል… ብዬ ልያዘው፡፡ ወይንስ ስብከት በስብከት፡፡… ለዚህ ነው እኔ ስብከት አልወድም ያልኩት፡፡ ሁሉም ሳይንስ በመሰረቱ በግርድፍ ሀሳብ ወይንም እምነት የሚነሳ ነው፡፡ “Premise” ብለው ይጠሩታል፡፡ ግርድፉ ሀሳብ ስህተት ካለው የሚደረስበት ድምዳሜ ደግሞ የበለጠ የተሳሳተ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መለስ ብለን ስናየው፣ በስህተቱ ምክኒያት የተፈፀመውን ልብ ስንል እንሸማቀቃለን፡፡
…ለዚህ ነው፤ ቅድም ስጀምር፤ “እኔ የቅርፅ አራማጅ ነኝ” ያልኩት፡፡ ተደራጅቶ የሚመጣ ሀሳብ እና… ውትወታ… ያስፈራኛል… ፕሮፓጋንዳ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከሀሳብ ሙላት የምናብ ሙላት…ይበልጥብኛል…ስል አስባለሁ፡፡
…እናም አንባቢዎች…ዛሬ አጀንዳ ይዤ አልመጣሁም፡፡ አጀንዳ በሀሳብ እና ሳይንስ…በምርምር እና ልክ የሚገለፅ ከሆነ… ወደ ድምዳሜ በቀላሉ አያመራም፡፡ ምርምሩን ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንዲሆን በስሜታዊነት አሳልፎ አይሰጥም፡፡
… ሳይንስም እንደ ጥበብ መንገድ ነው፡፡ ድምዳሜ ግንብ ነው፡፡ በድምዳሜ ተጉዛችሁ ግንቡ ጋር ስትደርሱ…ትልቅ ማስፈራሪያ አልያም ማስጠንቀቂያ - ቃለ አጋኖ ጮሆ ይቀርብላችኋል፡፡ ይኼ ግድግዳው ላይ ያለ ድምዳሜ “ስብከት” ተብሎ ይጠራል፡፡
ከሰባኪው ሳይንስ ምናባዊው ለእኔ ይቀርበኛል፡፡ አልፌው ልሄድ እችላለሁኝ፡፡ ሳይንሱም እኔን እንደዛው፡፡ ሁለመናው በይዘት ያልተጨናነቀ ቅርፅ፣ ከድምዳሜ ይልቅ ለምርምርና መረዳት ብዙ ክፍተት አለው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ እያሰብኩ የቅርፅ ቅንፉን ሳልዘጋ… ክፍት እተወዋለሁኝ፡፡… ምክኒያቱም፤ መጣጥፌ በይዘቱ ሳይሆን በቅርፁ እንዲያዝ ስለምሻ ነው፡፡  

Read 946 times