Print this page
Sunday, 05 November 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


           “በግማሽ ጎኔ ፍቅሬን፣ በግማሽ ደግሞ አገሬን”
            
   ልዕልት አይዳ በዘመነ ፈርዖን የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበረው የአምኖሶሮ ልጅ ነበረች፡፡ የዚች ልዕልት አስተዋይነት፣ የፍቅር ፅናትና እምነት ጁሴፔ ቨርዲ በደረሰው Aïda (አይዳ) በተሰኘው ሙዚቃዊ ድራማ (Opera) አለም ተደምሞበታል፡፡
… “በዚያን ዘመን ኢትዮጵያና ግብፅ በየጊዜው የሚናቆሩ ታሪካዊ ተቀናቃኞች … ነበሩ” ይለናል ደራሲው፡፡ … ሁለቱ ነገሮች ባደረጓቸው ተደጋጋሚ ጦርነቶች ባንዱ ዕድል የቀናቸው ግብፆች፤ ልዕልቲቷን ማርከው ወደ ከተማቸው ሜሞፊስ አመጧት፡፡ … በቤተ መንግስታቸውም ውስጥ በባርነት ማገልገሏን ይተርክልናል፡፡
ጁሴፔ ቨርዲ ከ1831-1901 የኖረ ጣሊያናዊ የጥበብ ሊቅ ሲሆን ከ “አይዳ” ሌላ “ኦቴሎ”፣ “ፋፈስታፍ”፣ “ዘ ፎርስ ኦቭ ዴስቲኒ”፣ “ሪጎሌቶ” እና ሌሎች ብዙ እስከ ዛሬ ድረስ በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች የሚጨበጨብላቸው ስራዎቹን አበርክቶ አልፏል፡፡ “አይዳ” … ለመጀመሪያ ጊዜ ለመድረክ የበቃው እ.ኤ.አ በ1871 በካይሮ ከተማ ነው፡፡
*       *      *
ወዳጄ፣ “ፍቅር ከምን እንደሚቀመም ወይም የፍቅር ኬምስትሪ (Chemistry of love) ቀመሩ ምን እንደሆነ አይታወቅም” … የሚባለው እውነትነት ያለው ይመስላል፡፡ … ግብፃዊው የጦር መሪ ካፒቴን ራዳመስ በምርኮኛዋ አይዳ ፍቅር ተሸነፈ፡፡ … ብቻዋን ባገኛት ጊዜም ፍቅሩን ከልቡ ገለፀላት - “Heavenly Aïda” እያለ አዜመላት፡፡
አይዳ ምንም እንኳ የልዕልትነት ክብሯ ተገስሶ፣ እንደ ባርያ ብትቆጠርም የምታስደነግጥ ውብ ወጣት ነበረች። … ይቺ ቆንጆ ልዕልት በበኩሏ ራዳመስ እንደሆነው … እሷም ውስጥ ውስጡን ፍቅር አስጨንቋት ኖሯል፡፡ … እንደውም አንድ ጊዜ ራዳመስ ለሌላ ግዳጅ መነሳቱን አይታ፣ “ይቅናህ፣ በድል ተመለስ” በማለት መርቃ ሸኝታው ነበር፡፡ ነገር ግን ዘመቻው በገዛ ህዝቧና ሀገሯ ላይ መሆኑን ስታውቅ ወደ አምላኳ በመዞር ለወገኗና ለፍቅሯ እሚበጀውን እንዲያደርግ ተማፅናለች፡፡ … ወዳጄ፤ ምናልባት በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ ሊሆን ይችላል … “ፍቅር በሁለት የዋሃን ሰዎች የሚፈፀም ወንጀል ነው” የሚባለው፡፡ … መሃሙድ ነፍሴ፤ እውነቱን ነው … “ወይ ፍቅር … ወይ ፍቅር … ወይ ፍቅር ..” እያለ ያዜመው፡፡
ራዳመስ የተዋጣለት ጀግና በመሆኑ አማልክቷ አይሲስ (The Goddess Isis) ሳትቀር ቡራኬዋን ቸራዋለች፡፡ በመጨረሻ ዘመቻቸውም በድል በተመለሰ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ንጉስ አሞናሶሮን (የአይዳን አባት) ጨምሮ ብዙ ምርኮኞችን በማጋዙ ዝናው ገናና ሆኗል። ራዳመስ ከዚህ ዘመቻ መልስ ሜሞፊስ እንደደረሰ፣ ንጉሱ ከዙፋኑ ተነስቶ ከልጁ ልዕልት አምነሪስ ጋር በመሆን የመጣበት ጋሪ ድረስ ሄዶ፣ በታላቅ አክብሮትና ግርማ ተቀብሎታል፡፡ … ከደስታውም ብዛት የልጁ የአምነሪስን እጅ ለጋብቻ ከመስጠቱም በላይ ራዳመስ እንዲያደርግለት የሚፈልገው ነገር እንዳለ በመኳንንቱ ፊት እየደጋገመ ጠየቀው፡፡ በዚህን ጊዜ ራዳመስ ምርኮኞቹ ሁሉ እንዲለቀቁ በመጠየቁ፣ ንጉሱ ቃሉን ጠብቆ ፈቃዱን ሞላለት፡፡ … ከንጉስ አሞናስሮ በስተቀር ሌሎቹ ነፃ ሆኑ፡፡ …
ልዕልት አምነሪስ ራዳመስን ትወደዋለች፡፡ … እሱ ግን ልቡ አይዳ ዘንድ ነበርና አልፈቀዳትም። ራዳመስና አይዳ ሲገናኙ የምታስተውለው ነገር ብግን ያደርጋት፣ ያስቀናት ነበር፡፡ … ዛሬ ግን ለሷ ልዩ ቀን ነው፡፡ አባቷ በአደባባይ ለራዳመስ ሚስት እንድትሆንለት አጭቷታል፡፡ … በደስታም እየፈነጠዘች፣ ወደ አማልክቶቹ ነበር የሮጠችው፡፡፡ … “ምስጋና ይገባቸዋልና!!” .. በማለት፡፡
*       *      *
ወዳጄ፣ “ኦፔራ በጥልቅ ስሜት የሚሞላህ እውነተኛ፣ አስጨናቂና ተዓምራዊ መንፈስ ነው” ይሉታል፡፡ … ድብቅና ግልፅ የሆኑ የፍቅር፣ የጦርነት፣ የበቀል፣ የጓደኝነት፣ የክህደትና የዕምነት፣ የክፋትና ደግነት፣ የጥጋብና ድህነት ታሪኮችን በሚጣፍጥ ሙዚቃዊ አተራረክ (ብዙውን ጊዜ በሶፕራኖ፣ ቴነር፣ ባሪቶን፣ ባስ፣ ኮንትራልቶ ወይም ከነዚህ ድብልቅ የተቀናበረ) ስልት የሚቀርብ፤ አሳዛኝ፣ አስደሳች፣ አስገራሚ ወይ ሁሉን ያካተቱ ገቢሮችን (scene) ያቀፈ ትዕይንት (Act) ነው፡፡
የፍሬዴሪክ ኒች ጥብቅ ወዳጅ የነበረው ሪቻርድ ቫግነርን ጨምሮ ቀደም ካሉት የኦፔራ ጠቢባንና የሙዚቃ ሊቆች ሮዚኒ፣ ፑቺኒ፣ ካርሳኮቭ፣ ስትራውስ፣ ጎኖድ፣ ሞዛርት፣ ቤትሆቨን፣ ሾፐን፣ ሄንድል ሃይደንና የመሳሰሉት የቅርብ ጊዜዎቹን እና ሉቺያኖ ፓቫሮቲን ጨምሮ በጥበባቸው የሰውን ልጅ አእምሮን በማሳደግና ስልጣኔን ከፍ በማድረግ፤ ነፃነትን በማስተማርና መብትን በማሳወቅ የአለምን ባህል ቀይረዋል፡፡
ወደ ታሪካችን ስንመለስ፣ ከዕለታት በአንዱ ቀን ልዕልት አይዳ ከአባቷ ከንጉሥ አሞናስሮ ጋር ተገናኘች። አባቷም፡- “አይዳ ልጄ፤ አገራችን በጠላቶቿ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል የምታደርግበትን ዝግጅት አጠናቃለች፡፡… እኔም የተማረኩት ሆን ብዬ አንቺን ለማየትና የጠላቶቻችንን አቅም ለመለካት ነው። ክብራችንን አስመልሰን የበላይነታችንን ማረጋገጥ ግድ ነው፡፡… እነሱም ይህ ቀን እንዳይመጣ ነቅተው ይጠብቃሉ፡፡…. ከእንግዲህ መቀደም የለብንም፡፡… አንቺንም አገርሽን የምታግዢበት ቀን ዛሬ ነው›› አላት፡፡
ልዕልት አይዳ አዳምጣ ከጨረሰች በሁዋላ፡፡..
“ምን ላድርግ አባቴ? “…ስትል ጠየቀች፡፡
“ራዳመስ እንደሚያፈቀርሽ አውቃለሁ”
“አዎን አበባ፤ እኔም….”
“ፍቅር ካገር አይበልጥም”
“…እምትፈልገውን ብቻ ንገረኝ …”
“እንግዲያውስ ሃሳቡን እወቂ፤ በቅርብ የመዝመት አዝማሚያ ካየሽበት አቅጣጫና መንገዱን ድረሽበት”… በማለት አስረዳት፡፡
አይዳም ራዳመስ ወደ’ሷ በመጣበት ጊዜ አስደሰተችው፡፡ “ና…አብረን እንክነፍ” እያለች አዜመችለት፡፡ አባቷ እንደ ነገራትም አደረገች፡፡… እናም ራዳመስ አብሯት ከነፈ፡፡ የልቡንም አልደበቃትም፡፡…. ይህንንም የንጉሡ ልጅ አምነሪስ በሰማች ጊዜ በቅናት ተነሳሳች፡፡…ወደ ራዳመስም ቀርባ… “ከሃዲ !ከሃዲ! ከሃዲ!” እያለች ጮኸች፡፡ …ወታደሮችም መጡ፡፡ …ራዳመስ ሊጎዳቸው አልፈለገም፡፡ ጎራዴውን ሰጣቸው። እነሱም በአክብሮት ወደ ዳኛ ዘንድ አደረሱት፡፡… ጳጳሱ ፊት እንደቀረበ ጉዳዩን እንዲያስረዳ ተጠየቀ፡፡ መልስ መስጠት አልፈለገም፡፡…ባደባባይ የተሰበሰቡትም “ክሱ ከቅናት የመነጨ ነው”… በማለት አጉረመረሙ፡፡
“ራዳመስ ሆይ፤ ዝም አትበል፣ ራስህን ተከላከል!!” እያሉ ጮኹ፡፡…እሱ ግን በፀጥታ ይመለከታቸው ነበር፡፡… ዝምታው ጥፋቱን የተቀበለ ያህል የተሰማቸው ዳኛም…አስበው፣ አስበው… ከነሕይወቱ እንዲቀበር ፈረዱበት። እዛም የነበሩት ሁሉ አዘኑ፡፡…ልዕልት አምነሪስ እንኳ ሳትቀር ተፀፀተች፡፡…ራዳመስ ሃሳቡ ሁሉ ስለ ፍቅሩ ነበረና የሆነውን ሁሉ ከምንም አልቆጠረም፡፡… ፍርዱ ወደ ሚፈፀምበት ቦታ ሲወስዱት እንኳ በእርጋታ ነበር እሚራመደው፡፡ … ከአይዳ መለየቱን እያሰበ የመቃብር ቤቱን ደረጃ በዝግታ ወረደ፡፡ … ከቦታው ደርሶ እንደቆመም ጣሪያው ሲደፈን ተሰማው፡፡ … ለመጨረሻውም ደንጊያ (The fatal stone) … ማዜም ሲጀምር አይዳ ከጨለማው ውስጥ ብቅ አለች፡፡ … ከሱ ጋር ለመሞት መቃብር ቤቱ ውስጥ ተደብቃ ነበር፡፡ … ሁለቱም በደስታ እየፈሉ “so pure and beautiful” የተባለውን ውብ ዜማ አወረዱት፡፡
ጊዜው ደርሶ ትንፋሻቸው እየደከመ፣ አየር እያጠራቸው መጣ፡፡ ወደ ሞታቸው መቃረባቸውን ሲያውቁ ‹ዓለም ደህና ሰንብች› (Fare well o earth!)ን እየዘመሩ አንዳቸው ባንዳቸው እቅፍ ውስጥ አሸለቡ፡፡ … ኢትዮጵያውያኖቹ አሸንፈው ሲገቡ ለማየት ባይታደሉም የጆሴፔ ቨርዲ ኦፔራ ህያው አድርጓቸዋል፡፡
አየህ ወዳጄ፤ ለአገርም ለህሊናም ታማኝ መሆን እንዲህ እንደ አይዳ እንጂ እንደኛ አገር ‹ሰዎች› ለመንግስት ‹ያሰቡ› እየመሰሉ፣ የራስን ኪስ ማደለብና ወገንን ማሰቃየት፣ የነጋ‘ለት ‹ወየው› … ያሰኛል!!

አቤት እኔ!
ሁለት ሃሳብ
ሁለት ቃል
ሁለት ኪዳን
    ባንዲት ልቤ ሁለት ነገር
    ልሸከመው የማልችለው
    ከራስ የከበደ ቀንበር!!
በግማሽ ጎኔ - ፍቅሬን!
በግማሽ ደግሞ - ሃገሬን!
አቤት እኔ!
ሼክስፒር እግዜር ይይለት
“ከመሆን ወይ ካለመሆን”
አንዱም ምረጭ - ይለይለት”
ብሎ ያለኝ እኔስ ማነኝ?
ባንድ ማተብ አሰርኩለት
ለፍቅሬ ‹ራሴ›ን ሞቼ
ላገሬ ‹እኔ›ን ሆንኩላት!
      (ፀሐፊው እንደ አይዳ)

Read 2613 times