Sunday, 05 November 2017 00:00

በልዩነት ውስጥ ምን ይታየናል? ውበት ወይስ መድልዎ?

Written by  ዶ/ር ዳዊት አሰፋ (የኢትዮጵያ የአዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት)
Rate this item
(0 votes)

 ልዩነት ባለበት ቦታ ሁሉ ውበት አለ። ተፈጥሮም እንዲህ ድንቅ ሆና የተሰራችው፣ ልዩነትን በህብረት ውብ አድርጎ የመግለጥ ሚስጥር ውስጥ ይመስለኛል፡፡ የምናየው፣ የምንሰማው፣ የምንዳስሰው የምንቀምሰውና የምናሸተው ሁሉ አንድ አይነት ብቻ ቢሆን፣ እንዴት አለም ጎደሎ ትሆን ነበር!
በአንፃሩ ግን በልዩነት ውስጥ ውበት ነጥሮ የሚወጣውን ያህል መድልዎም በጓሮ በር በኩል ሾልኮ ብቅ ይላል፡፡ መድልዎ በተለያየ ቅርፅና ገፅታ፣ በሁሉም ቦታና ሁኔታ ውስጥ ከሰው ልጆች ጋር አብሮ የሚኖር ክፉ ደዌ ነው፡፡ በሽሙጣችን፣ በጥቅሻችን፣ በሳቃችን፣ በሀዘናችን፣ በትንፋሻችን ውስጥ እንኳ ሳይቀር ሾልኮ ይመጣል፡፡ በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጤና፣ በፆታና በሌሎችም ልዩነቶች ውስጥ የመድልዎ ክፉ መንፈስ ያጠላል። ስለዚህ የልዩነት ትርጉሙ እንደ ተመልካቹ ነው ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡ የታደሉት በልዩነት ውስጥ ውበትን አይተው ያደንቃሉ፡፡ ያላደላቸው ደግሞ መድልዎን በልባቸው ያነግሳሉ፡፡
በዚህ ፅሁፍ “የምናጠልቀው መነፅር”፤ በእኛም ይሁን በሌሎች ህይወት ላይ የሚፈጥረውን አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳስሳለን፡፡ በተለይም የመድልዎን አስከፊ ገፅታ ለማሳየትና አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም እሞክራለሁ።
“ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ”
ልዩነትን በመድልዎ አይን መመልከት ስንጀምር፣ ከእኛ የተለዩና የእኛ ያልሆኑ ብለን የፈረጅናቸውን ነገሮች ሁሉ ለማጥፋት እንነሳለን። ከረጅም ጊዜ በፊት በአንደኛው የአገራችን ክፍል፣ አንድ ሰውነቱ የሳሳ፣ ፀጉረ ልውጥ ሰው ብቻውን ሲዘዋወር፣ የአካባቢው ነዋሪዎች አግኝተውት፣”ኤድስ ወደ አገራችን ገባ” በሚል ሰበብ ደብድበው ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት በስፋት ይወራ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ችግሩን ከችግረኛው ለይቶ ባለማየት የሚፈፀም ጥፋት ነው፡፡ ለተጠቂውም ድርብ በደል ነው፡፡ የመድልዎን ችግር አጉልተን ለማየት እንዲያመቸን አንድ ሌላ ምሳሌ ልጨምርላችሁ፡፡
በዚህች የልዩነት ድንቅ መገለጫ በሆነችው አገራችን ውስጥ በሐመር ጎሳዎች ባህል፣ ህፃናት ጥርስ ሲያበቅሉ የላይኛው ጥርሳቸው ቀድሞ ከወጣ ሚንጊ (የተረገሙ ልጆች) ተብለው በጎሳው ሽማግሌዎች ይፈረጃሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተረገሙ በመሆናቸው ለህዝቡ መቅሰፍት ያመጣሉ ተብሎ ስለሚታመን በጫካ ይጣላሉ ወይም ወደ ወንዝ ይወረወራሉ፡፡
በእርግጥ ከዚህ በተቃራኒው ሌሎች ብዙ አኩሪ ባህሎች ያሉት የሐመር ህዝብ፤ ይህንን የሚንጊ ልጆችን የማግለል ልምዱን ቀስ በቀስ እየቀነሰ መሄዱን ወደ ኋላ ላይ እንመለከታለን፡፡
የቁልቁለቱን ጉዞ በምናባችን ስንቃኘው
በልዩነት ምክንያት መድልዎ ሲነግስ፣ በመድልዎ መደላድል ላይ መገለል ሲታነፅ፣ መገለልም ለጥቃት በር ከፍቶ የህይወትን ጣር ሲያበዛው፣ በመጨረሻ ተጠቂው ግለሰብ፣ በማህበረሰቡ የኑሮ እርከን ደረጃ ወደ ታች እየተንሸራተተ ይወርዳል፡፡ ይህ ክስተት የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች፤ “ሶሻል ድሪፍት” (Social drift) የሚሉት ነው፡፡ በተለይም በከባድ የአእምሮ ህመም የተጠቁ ወገኖቻችን ዕጣ ፋንታ ይህ እንደሚሆን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ህመሙ ከሚያስከትለው ጉዳት ባሻገር በማህበረሰቡ የሚደርስባቸው መገፋት የቁልቁለት ጉዞውን ያፋጥነዋል፡፡
ይህንን አሳዛኝ ጉዞ በምናቤ ሰዳስሰው፣ ለእኔ የተከሰተልኝ ምስል የሚከተለው ነው፡፡ የበሽታው ስቃይ በላይህ ላይ ተጭኖ ያቅበዘብዝሀል፤ ማህበረሰቡ ይንቅሀል፣ ይፈራሃል፤ በመጨረሻም ያገልሀል፡፡ በዓለም ላይ ከተገነቡት የኑሮ ዑደቶች ውስጥ ስፍራህ እየጠበበ፣ የተቆናጠጥከው መሬት ቀስ በቀስ እየከዳህ ትሄድና፣ አንድ ቀን ሳይታወቅህ፣ ሰውም ሳያውቅልህ፣ እራስህን ሰዎች በእግራቸው ከሚረግጡት ትቢያ እንኳን ያነስክ ሆነህ ታገኘዋለህ።
ሰዎች ይረሱሀል፡፡ ምናልባት ለጊዜውም ቢሆን መረሳቱ በሀፍረት እየተሸማቀቁ ከመኖር የምትደበቅበት ዋሻህ ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ እንደመረሳት ያለ ክፉ እድል የለም፡፡ ከመረሳትስ ይልቅ መናቅ ወይም መጠላት ሳይሻል አይቀርም። ቢያንስ ለመናቅና ለመጠላት የሚያበቃ ዋጋ አግኝተሀል ማለት ነው፡፡ መረሳት ግን ባዶ መሆንን የሚያሳይ አስፈሪ ገጠመኝ ነው፡፡ መረሳትህ ከህያዋን ማህደር መፋቅህን፣ ከሙታንም የናፍቆትና ትዝታ መዝገብ ውስጥ መጥፋትህን ይጠቁምሀል… እናም ያስፈራል፡፡
ለዚህ የምናብ ጉዞ ማጣቀሻ እንዲሆን አንድ ታሪክ ላካፍላችሁ….
የዛሬ ሰባት ወይም ስምንት አመት ገደማ ይሆናል፡፡ ሰውነቱ በጉስቁልና የጫጨ፣ ጠይም፣ አሳዛኝ ገፅታ ያለው፣ፀጉረ ሉጫ ወጣት በሰዎች ተይዞ ለህክምና ቀረበ፡፡ ከቤተሰቦቹ ሸሽቶና የሁለተኛ አመት የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ፣ ከአመት በላይ ተሰውሮ ቆይቷል፡፡ በአጋጣሚ በሰፈር የሚያውቀው የከባድ መኪና ሾፌር፤ መንገድ ዳር ከውሾች ጋር ሲላፋ አግኝቶት ነው ወደ ቤተሰቦቹ የመለሰው፡፡ በኋላም በህክምና ለመረዳት በቃ፡፡ ከሁለትና ሶስት ሳምንታት ህክምና በኋላ አቅሉን መግዛት ሲጀምር ታሪኩን በዝርዝር አጫወተን፡፡
… በርካታ ወራትን በጫካ ውስጥ አሳልፏል፡፡ ቀን ቀን ውሾች ሲከተሉት ይውላሉ፡፡ ማታም ከበውት ያድራሉ፡፡ አንዳንዴ እርስ በርስ ሲጣሉ መሀል ገብቶ ለመገላገል በሚሞክርበት ወቅት ንክሻ ያጋጥመው እንደነበር አጫወተን፡፡ እውነትም ሱሪውን ወደ ላይ ሲሰበስበው፣ በለምጥ የተሽለመለመ ገላው ብቅ አለ፡፡ ባቱ በነበረበት ቦታ ላይ የጎደጎደ ጥቁር ለምጥ ይታያል፡፡
“ይህን ሁሉ ስቃይ እንዴት መቋቋም ቻልክ?” ስንል ጠየቅነው፡፡
“በመጀመሪያ አካባቢ በጆሮዬ የሚያንሾካሹክ ድምፅ ከአካባቢው ርቄ እንድሄድ ይነግረኝ ነበር። ድምፁን እየተከተልኩ ወደ ጫካ የገባሁ ይመስለኛል። ከሰው መሸሹ የተሻለ ነው ብዬ አስቤም ሊሆን ይችላል፡፡ በኋላ ላይ ብቸኝነቱን እየለመድኩት ሄድኩ፡፡ በእርግጥ በጣም ይርበኝና ይበርደኝ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የዛፍ ቅርፊት፣ ቅጠልና የወዳደቁ ነገሮችን ስመገብ ኖሬያለሁ፡፡ ብዙ ስቃይ አለው፡፡ በጆሮዬ ላይ የሚያወራው ድምፅም ይረብሸኝና ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ግን ንጉስ የሆንኩ ይመስለኝ ነበር፡፡ ዙሪያዬን የከበቡኝ ውሾች ደግሞ እኔን የሚጠብቁ አንበሶች ናቸው ብዬ አምን ነበር፡፡--”
ይህ ወጣት ከወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ጤናው ተመልሶለት፣ ትምህርቱን ለመቀጠል ጥረት እያደረገ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አሁን የት ይሆን? ምናልባትም ዛሬ ትምህርቱን ጨርሶ በሥራ ላይ ተሰማርቶ ይሆናል፡፡
ፍቅር ያድናል
የመድልዎ መገለጫ ውስብስብ የመሆኑን ያህል መፍትሄውም እንዲሁ ቀላል እንደማይሆን እንረዳለን፡፡ በእርግጥም ቀላል ቢሆንማ ኖሮ አለማችን ምን ያህል ሰላማዊና ፍትህ የሰፈነባት ትሆን እንደነበር አስቡት፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰዎች መድልዎን ለመቀነስ ይረዳሉ ብለው ያመኑባቸውን ዘዴዎች ከመሞከር አልቦዘኑም፡፡
አንደኛው ዘዴ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥና በጉዳዩ ላይ እውቀት እንዲኖረው ማብቃት ነው፡፡ እውነትም ይህ የመፍትሄው አንዱ አካል ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን። ለአብነት ያህል በዚህ ፅሁፍ ላይ እንደ ምሳሌ ያነሳሁት የሀመርን ሚንጊ ልጆችን የመጣልን ባህል በተመለከተ ልጆቹ ቢያድጉ በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው መቅሰፍት እንደሌለ በተግባር በማስተማር የተወሰነ ለውጥ እየመጣ መሆኑ ይነገራል፡፡ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችም ሚንጊ ልጆችን በማደጎ መልክ እየወሰዱ በማሳደግ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአንፃሩ ደግሞ እውቀት ብቻውን መድልዎን የማይቀንስበት ሁኔታዎች እንዳሉ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የአእምሮ ህሙማን ስለ ህመሙ ምንነት ከፍተኛ እውቀት አላቸው በሚባሉ የህክምና ባለሙያዎች ሳይቀር መድልዎና መገለል እንደሚደርስባቸው የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ፡፡ እንግዲህ እውቀት ብቻውን ሙሉ መፍትሄ እንደማይሆን፣ ነገር ግን የመፍትሄው አንዱ አካል እንደሆነ እንቁጠረውና ወደ ሁለተኛው አማራጭ እንሂድ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የምናየው ህግን ነው፡፡ ህግ ያለ እውቀት አንካሳ ነው፡፡ እምነት ካልተጨመረበት ደግሞ ከንቱ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ እውቀትና እምነት ጋር ያልተጣጣመ ህግ፣ ተፈፃሚነቱ አጠያያቂ ይሆናል፡፡ በቀላሉ እንኳን ስንት የማንፈፅማቸው ሕጎች እንዳሉ በልቦናችን እንመርምረው፡፡ እናም መድልዎን በህግ ለመከላከል ስንሞክር ችግሩ ከዚህ ይጀምራል - ማህበረሰቡ ካለው እውቀትና እምነት አንፃር፡፡
በተጨማሪም የመድልዎ መገለጫዎች በህግ ማዕቀፍ ለመሰብሰብ የሚያስቸግሩ፣ በሚታይ ድርጊት የማይገለፁ የስሜት ውጣ ውረዶችን ያዘሉ ናቸው፡፡ መድልዎ በሳቃችን፣ በሽሙጣችን፣ በሀዘናችን፣ በጥቅሻችን፣ በትንፋሻችን ውስጥ ሁሉ አለ ብለን የለ? ይህን ታዲያ እንዴት በህግ ለመቆጣጠር ይቻላል፡፡ የህግ ልዕልና የነሰገባት አገር ተብላ በምትሞካሸው አሜሪካ ውስጥ እንኳን የከፋ የዘር መድልዎ እንዳለ ጥቁር አሜሪካውያን በምሬት እየገለፁ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡
በመሆኑም ህግም ሆነ እውቀት በፍቅር ድልዳል ላይ ካልተቀመጡ በስተቀር እይታችን የተንሸዋረረ ከመሆን አይድንም፡፡ ሁለቱም በጎ ተፅዕኖ የሚያመጡት የፍቅር እርሾ ሲኖር ነው፡፡ የፍቅር መነፅር ያጠለቀ ሰው፤ እውቀቱ ውበትን መመልከቻ ብርሃኑ ይሆናል፡፡
ከእኛ የተለየውንና የእኛ ያልሆነውን እንደ ራሳችን ቆጥረን እንድንቀበለው የሚያደርገን፣ ከውድድርና ከፉክክር መንፈስ አውጥቶ ወደ ትብብር ማማ ከፍ የሚያደርገን ሚስጥር ፍቅር ብቻ ይመስለኛል፡፡
ከወዳጅ ተርፎ ለጠላትም የሚበቃ ፍቅርን ይስጠን!!

Read 1705 times