Sunday, 05 November 2017 00:00

‘ዲቫሉኤሽን’ እና ዋጋ በአናት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)


       “--ግራ የገባን ደግሞ…እንደ ሁሉም ነገር ማለት ነው…የኤኮኖሚስቶች ‘ትንተና’ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ችግራችን ገብቷቸው
አንጀታችንን ያርሱናል፡፡ አለ አይደል…ልክ እነሱ ውስጥ ገብተን እኛ የተናገርን ይመስለናል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ይህ ከየመጽሐፉ
የወጣ ቋጥኝ፣ ቋጥኝ ቃላት…እንደገና ደግሞ የዘመኑን ቋንቋ እየደረደሩ፣ “በሰዉ ኑሮ ላይ ይህን ያህል ጫና አያመጣም” ይሉናል፡፡
መሶባችንን ያዩ ይመስል!--”
   
     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ዘንድሮ “እንዴት ሰነበታችሁሳ!” መባባሉ ራሱ እየከበደ ነው፡፡ እንዴት እየሰነበትን እንደሆነ ትንሽ ትንሽም እያወቅን “እንዴት ሰነበታችሁሳ!” ማለት “ሰውዬው ያመዋል እንዴ!” ቢያስብል አይገርምም፡፡
እኔ የምለው…ያቺ የፈረደባት ቲማቲም ስንት ደረሰች? ልክ ነዋ…ከፈለገ ጓሮ ተቆፍራ ብትወጣስ! ‘ዲቫሉኤሽን’ ማለት ‘ዲቫሉኤሽን’ ነው፡፡
የአትክልት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ… የተለያዩ አትክልቶች ራሳቸውን እየካቡ ነበር፡፡
ብሮኮሊ (ማእድ አበባ) - “እኔ ልክ ዛፍ እመስላለሁ” አለ፡፡
ዋልነት (ዋጓንጉሌ) - “እኔ የሰውን አንጎል እመስላለሁ” አለ፡፡
እንጉዳይም- “እኔ ጥላ እመስላለሁ” አለ፡፡
ይሄን ሁሉ ዝም ብሎ ሲያዳምጥ የቆየው ሙዝ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ይሄ ውይይት እኔ ደስ አላለኝም” አለና አረፈው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…“እንዴ ጭራሽ ሠርታችሁ አትብሉ ነው እንዴ የሚሏቸው!” እንላለን፡፡ “ይሄን ሁሉ ከፍለው ቤተሰባቸውን በምን ያስተዳድሩ፣ ልጆቻቸውን እንዴት ያሳድጉ!!” እንላለን፡፡ እነሱ “እሪ!” ባሉ ቁጥር እኛም አብረን “እሪ!” እንላለን…ሰብአዊነት ነውና፡፡  “ለአንድ ሊትር ነዳጅ ይሄን ያህል ከተጠየቁ ምኑን ሠሩት!” ብለን ለባለ ሚኒባስ ታክሲዎች እናዝናለን፡፡
“ነጋዴ ላይ ግብር ተቆለለ፣ ሁለት መቶና ሦስት መቶ ይከፍል የነበረው አስርና ሀያ ሺህ ተጠየቀ” ሲሉ ስንሰማ እከሌ ብለን የምንጠራው ባይኖረንም እናዝናለን፡፡ የገንዘብ ችግርን ነገር እናውቃታለና!
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንዲህ ስናዝንላቸው ነጋዴዎቹም፣ እሺ… “ብድር መላሽ ያድርገን” አይበሉ፣ እሺ፣ “ለእኛ እንዳሰባችሁልን ፈጣሪ ለእናንተም ያስብላችሁ” ቢሉ ጥሩ፡፡ ከዚህ  ይልቅ መጀመሪያ የሚታያቸው የእኛ ንጹህ ልብ ሳይሆን የሳሳ ቦርሳችን እየሆነ ተቸግረናል፡፡ እንዴት አይነት መጨካከን ነው የመጣብን!
ስሙኝማ…መቼም ማንም ንግድ ውስጥ የሚገባው ለነፍሱ ሳይሆን ለትርፍ ነው፡፡ (“ኮሌጅ የከፈትነው የአገሪቱን የትምህርት ስርአት ለማሳደግ በማሰብ ነው” አይነት አንጀት ላይ መጎዝጎዝ አልፎበታል፡፡) እናማ… እስከሚችሉት ያትርፉ፣ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ያትርፉ፡፡ ግን…ይቺም ኑሮ ሆነችና በተገኘ አጋጣሚ፣ ያለምንም ምክንያት በዋጋ ላይ ዋጋ መቆለል ምን የሚሉት የቢዝነስ ስትራቴጂ ነው!
እግረ መንገዴን… የንግድ ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ባለሱቁን… “ትናንት እዚህ መጥቼ ኃይል ቆጣቢ አምፖል ገዝቼ ነበር፡፡ ግን ቤት ወስጄው ላብራህ ብለው እምቢ አለ” ይለዋል፡፡
ባለሱቁ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ታዲያ ምን ሊሆንልህ ነበር፤ ከበራ እንዴት አድርጎ ኃይል ሊቆጥብ ይችላል!” ብሎት አረፈ፡፡
እናማ…አሁን የሰሞኑን የዶላር ምንዛሪ ጭማሪ እዩልኝማ! ገና እንኳን አዲስ እቃ ሊገባ…አለ አይደል… እቃ የሚያመጡት መርከቦች ከወደብ ባልተንቀሳቀሱበት ሁኔታ እንዴት ነው ዋጋ ጭማሪ የሚኖረው፡፡
አንድ ወዳጄ ማርማላት ሊገዛ ሄደ፡፡ ከወር ምናምን በፊት ሠላሳ ሰባት ብር ነበር የገዛው፤ አሁን ግን ሀምሳ ብር ተባለ… “አሁን የመጣ ነው እንዴ?” ብሎ ሲጠይቅ የተሰጠው መልስ “ከፈለግህ ግዛ…” የሚል ነው፡፡ “ካልፈለግህ ተወው…” መሆኑ ነው። እናማ… ‘ችግር ደረሰብን’ ባሉ ጊዜ ያዘንላቸው ሰዎች፣ “ደጉን አምጣላቸው!” ብለን የጸለይንላቸው ሰዎች፣ “መከራቸውን አቅልላቸው፣” ያልንላቸው ሰዎች---መልሰው እኛኑ!  ለምን መጫወቻ ኳሳቸው ያደርጉናል!
ስሙኝማ… ‘ዲፕሎማቲክ’ የሚሉትን ነገር ለመሆን፣ አሁን የምናወራው… “ሁሉንም ነጋዴዎች የሚመለከት አይደለም” ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥም ሁሉንም አይመለከትም። “ጥቂቶች በፈጠሩት…” ምናምን እንዳንል ሸመታ በሄድንበት ቦታ ሁሉ ዋጋ ያለ አግባብ እየተቆለለብን የምን “ጥቂቶች…” ብሎ ነገር ነው! “ጥቂቶች…” የሚባለው እኮ እዚህ ቆልለው ከዋጋ በላይ በመቶ ብር የሸጡልንን፣ እዛኛው በሀቅ ስድሳ አምስት ብር ሲሸጡልን ነው፡፡ እና “ጥቂቶች…” ለማለት ቸግሮናል፡፡ ‘ጥቂቶች’ የሚባለው እንደ በቀደሙ የአዲስ አበባ ስታዲየም ግርግር፣ አብዛኛው ሰው በሰላም ተቀምጦ ጥቂቶች ‘ሲቀውጡት’ ነው፡፡
“ለምን እንትና ሱቅ አትሄድም፣ እሱ በዋጋው ነው የሚሸጥልህ” መባባል ናፈቀንሳ!
ለምሳሌ ነዳጅ በጨመረ ቁጥር “እንደው ምኑን ከምኑ ሊያብቃቁት ነው!” የምንላቸውን ባለ ሚኒባስ ታክሲዎችን ተመልከቱልኝማ! ይኸው በብር ከሰባ አምስት፣ በሁለት ብር ከሰባ አምስት የተባልነውን መንገድ፣ ድፍን ድፍኗን መክፈል ከጀመርን ስንት ጊዜያችን፡፡ መጀመሪያ ሰሞን “ስሙኒ መልስ አለኝ” እንል ነበር፡፡ አሁን፣ አሁን ግን ትተናል፡፡ አንዳንድ የታከሲ ረዳቶች፤ “ስሙኒ የሚባል ነገር ከያዝክ ውጉዝ ከመአርዮስ!” ምናምን የሚል ግዝት ነገር ያለባቸው ይመስላል፡፡ እኔ የምለው ስሙኒዋ ለሆነ ኮብልስቶን መንገድ መዋጮ ነች?! ቫት ነች!? “ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው…” ምናምን ነገር ነች?!  ከተወሰደችብን አይቀር ቢያንስ ያመስግኑና!
ግራ የገባን ደግሞ…እንደ ሁሉም ነገር ማለት ነው…የኤኮኖሚስቶች ‘ትንተና’ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ችግራችን ገብቷቸው አንጀታችንን ያርሱናል፡፡ አለ አይደል… ልክ እነሱ ውስጥ ገብተን እኛ የተናገርን ይመስለናል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ይህ ከየመጽሐፉ የወጣ ቋጥኝ፣ ቋጥኝ ቃላት… እንደገና ደግሞ የዘመኑን ቋንቋ እየደረደሩ፣ “በሰዉ ኑሮ ላይ ይህን ያህል ጫና አያመጣም” ይሉናል፡፡ መሶባችንን ያዩ ይመስል!
ስሙኝማ… ሀሳብ አለን፣ …የስፖርት ጋዜጠኞች በዘገባቸው የዘመኑን ቋንቋ የማይጠቀሙሳ! “እከሌ የተባለው ተጫዋች ከቡድን አጋሩ ከክንፍ በኩል የተሻገረለትን ኳስ፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ተቀብሎ በስኬታማ መልኩ ለውጤት በማብቃት፣ የቡድኑን ግብ የማግባት ዕቅድ ሀያ አምስት በመቶ አሳክቷል፡፡ በቀሪዎቹ ሀምሳ ስምንት ደቂቃዎች ቀሪዎቹን ሦስት ጎሎች በማስቆጠር፣ ቡድኑን በዓመቱ መጀመሪያ ጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም፣ በቁርጠኝነት ለማስቻል በመንቀሳቀስ ላይ ነው” ይባልልን፡፡ ከረዘመም ውሀ እየጠጡ፣ ዓረፍተ ነገሩን መጨረስ ነው! ከጊዜ ጋር አብሮ መሄድ ነዋ! (በእርግጥ… አብሮ መሄድ ማለት አብሮ መድረስ ላይሆን ይችላል!)
እናማ… ትንታኔ፣ መግለጫ፣ ማብራሪያ ምናምን ሲሰጥ ግልጽ እንዲሆነ እያደረጉልን ይሁንማ። በአረፍተ ነገር ርዝማኔና በመፈክር ቃላት ግራ እንዲገባን አያድርጉና! ስለ ግልጽነት ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ሁለት ጓደኛሞች ሲያወሩ አንዱ እንዲህ አለ፡- “ቤት ከሥራ ስመለስ ሚስቴ ስስ የሌሊት ልብስ ለብሳ ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ ነበር፤ ከዛም ‘ጥፍር አድርገህ እሰረኝና የፈለግኸውን አድርግ አለችኝ”
 ጓደኝዬውም በስሜት ተውጦ…
“እና!...አሰርካት?”
“አዎ፣ አሰርኳት”
“ከዛስ!”
“በቃ፤ አሰርኳትና ቢራዬን ልጠጣ ወጣሁ”
እሷሰ ብትሆን፤ “እሰረኝ” “ጠፍረኝ” ቅብጥርስዮ ከማለት የምትፈልገውን ‘በማያሻማ ቋንቋ’ አትናገርም እንዴ! ረጅም ነገር ለመቀነትነት እንጂ ለወሬ አይሆንም፤ ቂ…ቂ…ቂ…
ሌላ ደግሞ…እሷ ባሏን፤ “ጎረቤቶቻችን በጣም ደስ ይላሉ፡፡ ባልዬው ሁልጊዜ ሚስቱን ያንቆለጳጵሳታል፣ ያቅፋታል፣ ይስማታል፡፡ አንተስ ለምን እንደ እሱ አታደርግም?” ትለዋለች፡፡
ባል ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “አንቺ ምን ነካሽ፤ እኔ ሴትዮዋን የት አውቃታለሁ!” አላትና አረፈው፡፡ ግልጽነት! ግልጽነት! “እኔ መታቀፍ አማረኝ”፣ “መሳም አማረኝ” ብትል ዓለም አያልቅ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…ይሄ ‘ዲቫሉኤሽን’ የሚባለውን ነገር ለቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ እንደሚመች ሳይሆን፣ አለቆች እንዳይቆጡ በማለት ሳይሆን፣ “ደግሞ እንዳልጠቆር” በሚል አይነት ሳይሆን…እውነቱንና እውነቱን ንገሩን፡፡ ነገ፣ ከነገ ወዲያ የአገልግሎቶችና የምርቶች ዋጋ በምን ያህል ሊጨምር ይችላል? ‘ዲቫሉኤሽን’ ከብሩ ጋር እኛንም ቁልቁል ይዞን የሚሄድ እንደሆነ እቅጩን ንገሩንማ፡፡
ደግሞ በሰበብ አስባቡ ዋጋ በላይ በላይ የምትጭኑብን የንግድ ሰዎች… ትንሽ አስቡልንማ! ‘ዲቫሉኤሽን’ ለእኛ የጨጓራ አሲድ መጨመር፣ ለእናንተ ደግሞ የትርፍ መጨመር ሲሆን ለሰማይ ቤት ክርክርም አያመቻችሁም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5330 times