Print this page
Sunday, 05 November 2017 00:00

“ልማድ ሲሠለጥን ተፈጥሮ ይሆናል!”

Written by 
Rate this item
(23 votes)


   አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ትልቅ ቴያትር ቤት ፊት ለፊት አንድ ወጣትና አንዲት ወጣት ቆመዋል፡፡ የቆሙበት ቦታ የቴያትር ቤቱ ኮሪደር ነው፡፡ ሰው ቴያትር ለመግባት የሚሠለፈው እዚሁ ኮሪደር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው እየመጣ ከወጣቱና ከወጣቷ ጀርባ መሰለፍ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ ሰልፉ በጣም እየረዘመ ወደ ዋናው የግቢው በር እየደረሰ ሄደ፡፡
የቴያትሩ መጀመሪያ ሰዓት ደርሶ ተዋንያኑ መልበሻ ክፍል ገብተው ተዘጋጅተዋል፡፡ ሰው ግን ትኬት እየቆረጠ አይደለም፡፡ የቴያትር ቤቱ ዳይሬክተር ግራ ገብቶታል፡፡ ሲጃራውን በላይ በላዩ እየለኮሰ ያጨሳል፡፡ ወደትኬት መቁረጫው ክፍል መጥቶ፤
“ለምንድን ነው ሰው ማስገባት ያልጀመራችሁት?” ሲል ጠየቀ፡፡
ትኬት ቆራጯ፤
“ኧረ እኛ ዝግጁ ነን፡፡ ሰው ግን ወደ እኛ አልመጣም፡፡ ለምን እንደማይመጣ አላውቅም!”
ዳይሬክተሩ ወደተሰለፈው ህዝብ ሄዶ፤
“ለምንድን ነው ትኬት ቆርጣችሁ የማትገቡት?” ሲል ጠየቀ፡፡
ከፊት የተሠለፉት ሁለቱ ወጣቶች፤
“ኧረ እኛ አዲስ ፍቅረኛሞች ነን፤ እዚህ ጋ ተቃጥረን ነው!” አሉ፡፡
“ሌሎቻችሁስ” አለ ዳይሬክተሩ፡፡
ሌሎቹ፤
“እኛ እነሱን ዓይነት ነው”
ዳይሬክተሩም፣ ለወጣቶቹ፤
“በሉ እናንተ መንገድ ልቀቁ፤ ሌሎቻችሁ ግቡ”
አስገባቸው፡፡
* * *
የመንገኝነት ችግር የሁልጊዜ ችግራችን ነው፡፡ ሌሎች ሲሰለፉ መሰለፍ፣ ጫማ ቤት ሲከፈት ካየን ጫማ ቤት መክፈት፣ አንዱ ኬክ ቤት ሲከፍት ሌላውም ኬክ ቤት መክፈት ልማዳችን ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በሼክስፒር ሀምሌት ውስጥ፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣
ወይ ለነገ ይለምድብሻል፤
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣
ወይ ይጠፋል፣ ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሠለጠነ እንደሁ፣
ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል!”
ይለናል፡፡
የለመድነውን ነገር ለመለወጥ አንችልበትም፡፡ ለለውጥ ሁሌም አዲስ የምንሆነው ለዚህ ነው፡፡ የሚገርመው ለውጥ እንደማይገባን አለመረዳታችን ነው።
“እናውቃለን
ብንናገር እናልቃለን”
… የሚለውን አባባል ዝተን-ዓለማችንን ስንደጋግመው ኖረናል፡፡ እስከ ዛሬም አልለወጥነውም፡፡ ቢሳካልን፤
“እናውቃለን
ባንናገር እናልቃለን”
… ማለትንም ብንማር መልካም ነበር፡፡
“ፊት የተናገረን፤ ሰው ይጠላዋል ፊት የበቀለን፤ ወፍ ይበላዋል” ስንባባል ከርመናል፡፡ ይሄንንም ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡ ምነው ቢባል፤ አስቀድሞ ያወቀ አስቀድሞ ማሳወቅ ይገባዋልና! በዘልማድ አንዴ የተዋሀዱንን አባባሎች ተሸክመን መጓዝ የለብንም፡፡ ተገቢ ሆኖ ሲገኝ መለወጥንም መልመድ ቢያንስ ከወግ-አጥባቂነት ያድናል፡፡ ልማዶቻችንን እንፈትሻቸው! ክፉውን ከደጉ እንለይ፡፡ ደጉን ለማዘመን ዝግጁ እንሁን፡፡ የሚተካውን እንተካ! የሚሻሻለውን እናሻሽል- ባለበት-ሀይ እያልን በተለመደው መንገድ ብቻ መዳከሩ መንቀዝን ያስከትላል፡፡ መታደስና መለወጥ እንጂ መንቀዝ ክፉ ልማድ ነው፡፡ Regeneration, not degeneration  እንዲሉ ፈረንጆቹ፡፡ “ልማድ ሲሠለጥን ተፈጥሮ ይሆናል” የሚባለው ለለውጥ ዝግጁ ያልሆነን ህብረተሰብ አመላካች ነው፡፡ ለውጥ የእፎይታን ያህል ነው ይላሉ፤ የፖለቲካ ጠበብት፡፡ “a change is as equal to rest” ብለው ቀድሞ ጠቁመውናል! ዐይናችንን እንከፈት፡፡

Read 8140 times
Administrator

Latest from Administrator