Sunday, 05 November 2017 00:00

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት - በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 · ፖለቲካችን እየወደቀ ባለበት፣ኢኮኖሚያችን እየተነቃቃ ነው ማለት የማይጣጣም ነው
           · አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ፣ወታደሩ እጁን ሊያስገባ ይችላል ብዬ እሰጋለሁ
           · ለፌደራል መንግስት ግብር አልከፍልም የሚል ክልል ሊፈጠር ይችላል
           · ከእንግዲህ የብሔርና ጎጠኝነት ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይጠቅምም

   አገሪቱ በፖለቲካ ቀውሶች ዳግም እየተናጠች፣ከዕለት ወደ ዕለት አስጊ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በተቃውሞና “የብሔረሰቦች ግጭት” በሚል ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለመፈናቀል እየተዳረጉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከመንግስትም ሆነ ከተቃዋሚው ጎራ አሊያም ከምሁራኑ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችል አዲስ መላ ወይም ሃሳብ ሲሰነዘር ጨርሶ አይሰማም፡፡ ለመሆኑ ለአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄው ምንድን ነው? እንዳይከሰት ከሚፈራው የእርስበርስ ግጭትና መበታተን መዳኛው መንገድ ምንድን ነው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደን በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

    ኢዴፓ አገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዴት ይገመግመዋል?
ኢዴፓ ብዙ ጊዜ ሦስተኛ አማራጭ በሚል፣ የሠላም ሀሳቦችን ነው የሚያስቀድመው፡፡ ፕሮግራሞቹ በዚህ የተቃኙ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ግምገማዎቹ የሠላም ሀሳብ ላይ ያጠነጥናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እኔም እንደ ምሁር፣ ኢዴፓም እንደ ፖለቲካ ድርጅት የምንረዳው፣ ወጣ ያለ አካሄድ መኖሩን ነው፡፡ ይሄ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም የህዝብን ስሜትና ትኩሳት ስናዳምጥ፣ መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶች እንዳሉ ነው የምንገምተው፡፡ መነሻዎቹ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በፖለቲካው አንጻር ስንመለከት፣ ባለፉት 25 ዓመታት ኢህአዴግ የሄደባቸው መንገዶችና ፖሊሲዎች አሁን ላይ የማይሰሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችለናል። ሪፎርም ያስፈልጋል ቢባልም በጥልቀት ስላልተሰራበት ህዝብ አሁንም በጥርጣሬ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። ነገሮችን ማስተካከል በሚገባው ደረጃ ማስተካከል አልተቻለም፡፡ መንግስት የካቢኔ ለውጥ አደረግሁ ቢልም የፖሊሲ ለውጥ አላደረገም፡፡ ይህቺ ሀገር ደግሞ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እፈታለሁ ብሎ የሄደበት መንገድም ውጤት አልባ ነው የሆነው፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ፖለቲካው አልተረጋጋም። ለዚህ አለመረጋጋት ደግሞ ሀገሪቱ የምትከተለው ፌደራሊዝም ችግር እንዳለበት ከሁነቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚገባው ፌደራሊዝሙን እንደገና መፈተሽና ማዋቀር እንዲሁም ህገ መንግስቱንም መፈተሽ ነው። የክልሎች አወቃቀር እንደገና መታየትና መጠናት እንዳለበት ነው የምንረዳው፡፡
በሌላ በኩል፤ በህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ውስጥ “ልዩ ኃይል” የሚባል የፖሊስ አደረጃጀት የለም፡፡ በህግ የተቀመጠው ወይ ፖሊስ ነው ወይ የመከላከያ ኃይል ነው እንጂ ልዩ ኃይል የሚባል ነገር የለም፡፡ በዚህ ልዩ ኃይል እየታገዙ ክልሎች እርስ በእርሳቸው ጥርጣሬ ውስጥ የመግባትና ፀብ ፍለጋ አይነት ይፋዊ ንግግሮችንም እያየን ነው፡፡ ይሄ ለሀገሪቱ ጠቃሚ አይደለም፡፡ ኢዴፓ የወቅቱን ሁኔታ እንዲህ ነው የሚረዳው፡፡
በፌደራሊዝም ሥርዓቱ ላይ በግልፅ የሚታዩ ጉድለቶች ምንድን ናቸው?
የፌደራሊዝሙ አወቃቀር ብሔር ብሔረሰቦችን ትኩረት ያደረገ በመሆኑና ማንነትን መሰረት በማድረጉ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎች ምንጭ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ስልጣን በታጣ ቁጥር ስልጣኑን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት፣ የማንነት ጥያቄን መነሻው ያደረገ ግጭት ነው እየፈጠረ ያለው። ሁለተኛ የኢኮኖሚ ትስስሮሽ በዚሁ የፌደራል ሥርአት ውስጥ ገና አልተፈጠረም፡፡ ሀገሪቱ ሀብት ቢኖራትም ሀብትን ወደ ምርት በመቀየሩ ረገድ ገና ናት፡፡ በዚህ የተነሳ በሀብትና ምርት፣ ክልሎች እርስ በእርስ አልተሳሰሩም፡፡ በመሰረቱ ያለው ፖሊሲ ሊያስተሳስር የሚችልም አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት የሀብት ባለቤትነት ጥያቄን ሲያስነሳ እየተመለከትን ነው፡፡ “ከእኔ ክልል የሚመነጨው ሀብት የኔ ብቻ ነው” የሚል ስሜት እየተንፀባረቀ ነው ያለው፡፡ በዚህም የተነሳ በፌደራል ላለመገዛት ጥረት ይደረጋል፡፡ ወደ ፌደራል የሚገቡ የሀብት ምርቶችንና ገቢዎችን እዚያው በክልል ተወስነው እንዲቀሩ የመፈለግ ስሜት ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ያሉ አካሄዶች ደግሞ ልዩነቱን የበለጠ እያሰፉት ይሄዳሉ። ልዩነት ሲሰፋ ደግሞ የኛ የሚለው ቀርቶ የኔ፣ የክልሌ የሚለው አስተሳሰብ ይነሳሳል፡፡ ይሄ ደግሞ የማንነት ጥያቄን አጉልቶ ከመስበክ የመጣ ችግር ነው ብለን እናምናለን፡፡  
የኢኮኖሚ ትስስሮሽ አልተፈጠረም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? እንዴትስ ነው ሊፈጠር የሚችለው?
የኢኮኖሚ ትስስሮሽ የሚፈጠርበት የራሱ መርህ አለው፡፡ የፌደራል ሥርአት በርካታ ሀገራት የሚጠቀሙበት ሥርአት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የተጠቀምንበት የፌደራል ሥርአት አወቃቀር፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሮሽን ሊያመጣ የሚችል አይነት አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ ትስስሮሽ ሊመጣ የሚችለው አማራ ክልል ያለው ሀብት ለኦሮሚያ፣ ኦሮሚያ ላይ ያለው ሀብት ለደቡብ፣ ደቡብ ላይ ያለው ወደ አማራ ክልል፣ አማራ ክልል ያለው ወደ ትግራይ፣ ትግራይ ያለው ወደ ኦሮሚያ ወዘተ--- የሚመጣበት የንግድ ሰንሰለት፣ የአሰራር ስርአትና የመሳሰሉት ሲዘረጋ ነው። ይሄ እስከዛሬ አልተደረገም፡፡ ወጣቶች ከአንዱ ክልል ወደ አንዱ እየተዘዋወሩ መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ቢኖርም አስተማማኝ አይደለም፡፡ በመጠራጠሮች የተሞላ ነው፡፡ የግጭቶችም መነሻ ሲሆን በቅርቡ ታዝበናል። “ይሄን  ቋንቋ ካልተናገርክ እዚህ መስራት አትችልም፣ ያንተ ሀብት አይደለም፣ የኔ ብቻ ነው” የሚሉ አመለካከቶች ናቸው እየተንጸባረቁ ያሉት። “የክልሉ ሀብት ነው” የሚለው እየነገሰ ሄዶ፣ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ትስስሮሽ ጉዳይ ቸል ተብሏል፡፡ የተጫነን ምርት “ወደ ሌላ ክልል ልትወስድ ነው” የሚለው መንፈስ ሁሉ የሚፈጠረው፣ ይህ የኢኮኖሚ ትስስሮሽን የመፍጠር ጉዳይ እውን ባለመሆኑ ነው።
እንደ እኔ፣ አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር አይቻልም። በእርግጥ መንግስት የኢኮኖሚ ትስስሮሽ መፍጠር የሚያስችለኝን ሁኔታ ዘርግቻለሁ ይላል፡፡ ይሄ ግን ተጨባጭ እውነታውን አያሳይም፡፡ አሁን ባለው አስተዳደራዊ መዋቅርና የፌደራል ሥርአት፣ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር እድል የተዘጋ ጉዳይ ነው፡፡ የሚቻል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሪፎርሙ ወጥ የሆነ፣ ሁሉንም ሊያሳትፍ የሚችል ሆኖ ነው መምጣት ያለበት፡፡ ስለ አገራዊ አንድነትና ብሄራዊ ስሜት መስበክ በመጀመር ነው፣ የምንፈልገውን አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት የምንችለው።
ሌሎች ፓርቲዎችም አሁን ያለው የፌደራል ሥርዓት፣ ሪፎርም መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ሪፎርም የሚደረገው ምንድን ነው? እንዴትስ ነው የሚደረገው?
ሪፎርሙ መጀመር ያለበት ዲሞክራሲን ከማስፈን ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝብ በራሱ ጉዳይ ተሣታፊ ሆኖ በነፃነት እንዲወስን ዲሞክራሲ ወሳኝ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ምሁራኑ ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርቡ መጠየቅ አለባቸው። ህዝቡ፣ የየአካባቢው መስተዳደሮች ሃሳባቸውን መጠየቅና ማወያየት፣ ከዚያም ህዝቡ በምን አይነት አከላለል? ከማን ጋር መኖር እንደሚፈልግ ህዝበ ውሣኔ ማካሄድ ያስፈልጋል። ፌዴራሊዝም በዋናነት አላማው ለአስተዳደር አመቺነት ነው መሆን ያለበት እንጂ ባህሉና ቋንቋውን ተዋርሶ የሚኖርን ማህበረሰብ በጎጥ ለመለየት መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥም መታየት አለበት፡፡ ከምንም በላይ ግን ህብረተሰቡ እንዲወስን ነው መደረግ ያለበት፡፡ አሁን ያለው ግን ከህብረተሰቡ የመነጨ ሳይሆን ከላይ የወረደለትን የሚቀበል ነው፡፡ ይሄ አካሄድ ከ25 ዓመት በኋላ ያተረፈው ግጭት ነው፡፡
መንግስት የአገሪቱን ችግሮች በትክክል ተገንዝቦ፣ ለመፍትሄው በትክክል እየተንቀሳቀሰ ነው ማለት ይቻላል?
ሙከራ ቢያደርግም አልተሣካለትም ማለት ይቻላል። ሙስናን የመከላከል ሥራ ነው ጎልቶ የታየው እንጂ ከዚያ በመለስ ምንም አይነት አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አልፈተሹም፡፡ አሁን ችግሩ ያለው በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አዋጆችና ህጎች በአግባቡ እየተተረጎሙ አለመሆናቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች እንደገና መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም እንደተደራጀ መረጃው አለን፤ ነገር ግን እስከ ዛሬ እኛንም ሆነ ሌሎችን ግብአት አልጠየቁም፡፡ ምን ፖሊሲ እንዳሻሻሉም አናውቅም። በአጠቃላይ የአስተዳደር መዋቅሮች ናቸው መለወጥ ያለባቸው። አሁን ሁሉም ነገር ቀዝቅዟል፡፡ በዚህ የተነሣ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ አጋሮች እርስ በእርሣቸው ተቀዛቅዘዋል፡፡ አዲስ ሃሳብ ስለማይመነጭ የመሠለቻቸትና የመናናቅ ነገር ይመጣል፡፡ ይሄ ሲሆን ጫናው በቀጥታ ህዝቡ ላይ ነው  የሚያርፈው፡፡
በሌላ በኩል መንግስት፤ “እየታደስን እንሠራለን፣ እየሠራን እንታደሣለን” በሚል መርህ በተሃድሶ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮችና እየፈታ መሆኑን እየገለፀ ነው፡፡ በእናንተ ግምገማ በዚህ ተሃድሶ ምን ውጤት ተገኝቷል?
በመፈክር ምንም አይነት ለውጥ አይመጣም፤ ዋናው ታች ወርዶ በህግ የተደገፉ ተግባራዊ ሥራዎች እንዴት እንስራ? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ጳጉሜ ውስጥ “የከፍታ ዘመን” ተብሎ ሲዘመር ነበር፤ ግን የዚህ ከፍታ ምንጭና መድረሻ አይታወቅም። ህዝብ መብቴ ተጣሰ ብሎ ሲጮህ፣ ”የከፍታ ዘመን” ምንድን ነው ትርጉሙ? ለህዝብ ጥያቄ በቀጥታ መልስ መስጠት ሲቸግራቸው፣ ወደ አምባገነንነት እየሄዱ ነው ያሉት። ህዝብ መምራት ሲያቅታቸው የማርሻል ህግን ነው የሚጠቀሙት፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ አገዛዝ እንደገና እንዲመጣ እድል እየከፈተ ነው ያለው፡፡ በኦሮሚያ፣ በሻሸመኔ በሌሎችም የሚታዩ ግጭቶች፣ መንግስት ወደዚህኛው አስተሳሰብ እንዲመጣ የሚገፋፉ ናቸው፡፡  
የፌዴራል መንግስቱ የሃይል ሚዛን ከክልሎች አንፃር እንዴት ይታያል?
እስካሁን ባየነው የፌደራል አስተዳደር ውስጥ ጎልቶ ያየነው፣ የሲቪል አስተዳደሩን ሳይሆን የኢህአዴግ ወይም የፓርቲ ስልጣንን ነው፡፡ በክልሎችም በተመሣሣይ። ስለዚህ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ በህዝቡ ተቀባይነት ሲያጣ፣ የፖለቲካ ስልጣኑ ወይም የሲቪል አስተዳደሩም እየላላ ነው የሚሄደው፤ ምክንያቱም አስተዳደሩ እስከታች ድረስ በኢህአዴግ የካድሬ ፖለቲካ የተቃኘ ነው፡፡ ሲቪል አስተዳደር የለውም፡፡ ዛሬ ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይ እንዲሆን እድል የከፈተውም፣ ይህ የመንግስት የሲቪል አስተዳደር እና የፓርቲ ፖለቲካ ድንበር የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ በህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ውስጥ የፓርቲና የመንግስት ስልጣን እንዴት ይለይ የሚለው፣ በፅኑ ህግ እንዲደገፍ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን በተያዘው አቅጣጫ ትንሽ ከቀጠለ ግን ነገ ለፌዴራል መንግስቱ ግብር አልከፍልም የሚል ክልል ሊፈጠር ይችላል። ለዚህ መፍትሄው በአፋጣኝ በፌደራል ሥርአቱ ላይ ሪፎርም አካሂዶ፣ ጠንካራ የእዝ ሰንሰለት መፍጠር ነው፡፡ የመንግስት አስተዳደርና ፖለቲካ መለያየት አለባቸው፡፡
በእርስዎ እይታ የሀገሪቱ የስልጣን ማዕከል በተጨባጭ ማን ጋር ነው ያለው?
ለኔ ስልጣን አሁን ያለው ክልሎች ጋ ነው፡፡ በፊት የፌደራል መንግስቱ ጫና ፈጥሮ ይሰራባቸው የነበሩ የፖለቲካ መስመሮች በሙሉ እየተዘጉ በመምጣታቸው፣ አሁን ትልቁ የሀገሪቱ ስልጣን ወደ ክልሎች ነው እያመዘነ የሄደው፡፡ ወደ ክልሎች እያመዘነ ከሄደ ደግሞ ክልሎች በጋራ ተስማምተው የመሰረቱትን የፌደራል ስልጣን እየተጋፉ ነው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ ያለመግባባት ከተፈጠረ ከኢህአዴግ አባልነትም የሚለይ ፓርቲ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይሄ አደገኛው አዝማሚያ ነው፡፡ ስልጣን ወደ ክልሎች ባመራ ቁጥር የፌደራል መንግስቱ ተንጠልጥሎ የሚቀር ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የሆነ ቦታ ላይ የፌደራል ሥርአቱ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን ስናይ፣ የክልሎች ስልጣን ከፌደራል ስልጣን የሚለይባቸው በትክክል በህግ ማዕቀፍ አስቀምጠው ነው ተግባራዊ የሚያደርጉት። ወደ እኛ ስንመጣ ሰፊ የህግ ክፍተት አለ፡፡ ይሄ የህግ ክፍተት የተፈጠረው ደግሞ ሁሉም ነገር በፖለቲካው ብቻ ታስቦ በመቀረጹ ነው፡፡
እነዚህ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ ካላገኙ ውጤታቸው ምንድን ነው የሚሆነው ?
አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ አስጊ ነው። እኔ ይሄ ስጋት በዚህ መልኩ መቀጠል አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ ነው፡፡ መንግስትም ካቢኔ አለው፡፡ ስለዚህ ሁሉም በየድርሻው ውይይት እያደረገ አስተዳደራዊ መዋቅሩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከክልሎች ስልጣን ጀምሮ እንደገና ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ባጭር ጊዜ ውስጥ ካልተከናወነ፣ የማታ ማታ፣ የመንግስት አስተዳደሩ በአጠቃላይ ሽምድምድ ብሎ የሚቆምበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ያ ደግሞ የነበረውን የኪራይ ሰብሳቢነት ሁኔታ የበለጠ ያባብሰዋል፡፡ በዚህ መሃል ሀገር መምራት አልቻልኩም በሚል ስልጣኑን ለወታደራዊ አገዛዝ አሳልፎ የሚሰጥበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ህመምን እያስታመሙ ብቻ የሚቀጠል ከሆነ፣ ወታደሩ እጅን ሊያስገባ ይችላል የሚል ፍራቻ ነው ያለኝ፡፡
አገሪቱ በፖለቲካ ቀውሶችና አለመረጋጋት ውስጥ ብትሆንም ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቀጠሏን እየሰማን ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደመሆንዎ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ብዙ ጊዜ የዓለም ባንክም ሆነ ሌሎች ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ እድገት ሲናገሩ፣ ከብሔራዊ ባንክና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር መረጃዎችን ወስደው በማጠናቀር ነው፡፡ የራሳቸውን አጥኚዎች አሰማርተው፣ በተጨባጭ መሬት ወርደው እያጠኑ አይደለም ሪፖርት የሚያወጡት። ስለዚህ የተሳሳተ መረጃ ይዘው ነው ሪፖርት የሚያወጡት፡፡ ሌላው ቀርቶ ብሔራዊ ባንክና ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር እጅ ያሉ መረጃዎች የሚጣጣሙ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ የእድገት ፍንጮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ይሄ እድገት ግን በልማት ፖሊሲዎች መታገዝ አለበት፡፡ ልማት ሊመጣ የሚችለው ደግሞ በዲሞክራሲ ሲታገዝ ነው፡፡ ህዝብ በመልካም አስተዳደር መርካት ሲችል ነው ልማት የሚመጣው። በአስተዳደሩ መርካት ሲችል ነው፣ የእኔነት መንፈስ ተፈጥሮ ልማት የሚመጣው፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ብቻ መቀመጡ ዋጋ አይኖረውም፡፡
ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትታትም የእነዚህ ሁኔታዎች ተቃርኖ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሃገር ቤት ይመጣሉ ማለት አይቻልም፡፡ ፖለቲካው መረጋጋት ሲችል ነው ኢንቨስትመንት መምጣት የሚችለው። ህብረተሰቡ ግን አስቀድሞም የእኔነት ስሜት ስላልተፈጠረበት፣ ያ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዳይቀጥል ነው ትግል እያደረገ ያለው፡፡ በዚህ ተቃርኖ መሃል እንዴት ቀጣይነት ያለው እድገት ማምጣት ይቻላል? አይቻልም፡፡ ገዥው ፓርቲ ይሄን ማጤን አለበት። ፖለቲካችን እየወደቀ ባለበት፣ ኢኮኖሚያችን እየተነቃቃ ነው ማለት የማይጣጣም ነገር ነው። ኢንቨስትመንቶች በመጀመሪያ የሚፈልጉት ፖለቲካዊ መረጋጋትን፣ ሠላምን ነው፡፡
ዓምና መጀመሪያ ላይ መንግስት፣ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት፣ ተቃዋሚዎችን እንደሚያሳትፍ ገልፆ ነበር፡፡ መንግሥት ቃሉን ፈጽሟል ማለት ይቻላል?
እርግጥ ነው ፕሬዚዳንቱ በ2009 ዓ.ም የፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ ይሄን ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሃሳብ በህግ ወይም በአሠራር የተደገፈ አልነበረም። ፕሬዚዳንቱ አቅጣጫ ቢሰጡም አስፈፃሚው ክፍል ወደ ተግባር የሚቀየርበት አሠራር የለም፡፡ ባለፈው ዓመት ከተናገሩት ውስጥ በድርድር የምርጫ ስርዓቱን መቀየር የሚለው ብቻ ነው ተግባራዊ የተደረገው። ከዚያ በመለስ ግን በቃላቸው መሠረት፣ ማንንም አላሣተፉም፡፡ ምሁራንን እንኳ አላሣተፉም፡፡ የዚህ ዓመት የመንግስት አቅጣጫን ያመላከተው የፕሬዚዳንቱ ንግግርም ያን ያህል አንኳር ጉዳዮችን የዳሰሰ አይደለም። ተቃዋሚዎችንም ሆነ ምሁራንን ለማሳተፍ የሚያስችል አሠራርም አልተዘረጋም፡፡
ኢዴፓ ህልውናውንም ቢሆን አፍርሶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት በመፍጠር፣ አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ዕቅድ ነበረው፡፡ ይሄ ዕቅዱ ከምን ላይ ደረሰ?
 አንድ ጠንካራ ፓርቲ የመፍጠር ጉዳይ የግለሰቦች አመለካከት ሣይሆን የፓርቲው የፕሮግራም አካል ነው፡፡ ይሄን ሃሳብ ወደ መሬት በማውረድ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መጠናናት ይፈልጋል፡፡ የፕሮግራም ልዩነቶች መጥበብ አለባቸው፡፡ ብዙ ውይይቶችና ንግግሮች ይጠይቃል፡፡ የኛ ፓርቲ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚደረገው ድርድር መቋጫ ካገኘ በኋላ፣ አንድ ጠንካራ ፓርቲ መስርቶ፣ ለሚቀጥለው ምርጫ ለመቅረብ ዕቅድ ይዟል፡፡ ከእንግዲህ የሃገሪቱ ፓርቲዎች በሊበራል፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለሞች ላይ መንከባለል እንጂ የብሔርና ጎጠኝነት ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይጠቅምም፡፡

Read 1556 times