Sunday, 05 November 2017 00:00

ኢትዮጵያን እንዴት ከመፍረስ እናድናት?

Written by  ታምራት መርጊያ
Rate this item
(1 Vote)

 “ሞኝ ከራሱ ውድቀት ይማራል፤ ብልጥ ከሰው ውድቀት ይማራል”
            
    እንደ ፖለቲካ ምሁራን እይታ፤ አንድ ሀገር የጨነገፈ ሊባል የሚችልበት አውድ አሀዛዊና (quantitative) አይነታዊ (qualitative analysis) ትንተናዎች ይኖሩታል፡፡ ይሁንና ይህ ቃል በግርድፉ ሲታይ፥ የጨነገፈ ሀገር የሚባለው የአንድን ሀገር መንግሥት የሚመራው የፖለቲካ ስርዓት፣ ሀሪቱን የመምራት ሀላፊነቱን መወጣት ሲሣነውና ሀገር የማስተዳደር ልዕልናው እንዲሁም ቅቡልነቱ (Erosion of legitimate authority) እያሽቆለቆለ መጥቶ ጭርሱን ሲጠፋ እንደሆነ የዘርፉ ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡
ታዲያ ይህ ከሆነ ዘንድ አንድ የፖለቲካ ስርዐት ቅቡልነቱን አጣ ወይም መንግሥት የመምራት ልዕልናውን አጣ የሚባለው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡
The Fund for Peace የተሠኘ አንድ አለማቀፋዊ ተቋም፣ ይህን አስመልክቶ ባወጣው ጥናታዊ ፅሁፍ፥ አንድ በስልጣን ላይ ያለ መንግሥት፣ መንግስታዊ ልዕልናውን እንዳጣ የሚታወቀው የሚከተሉትን ባህርያት የሚያሳይ እንደሆነ ነዉ ይለናል፡፡
•የሀሪቱን ሉአላዊ ድንበር ማስከበር ሲሣነው (Loss of control of its territory)
•የመንግሥት አገልግሎቶችን በሚገባ መስጠት ሲሣነው (Inability to provide public services)
•መአከላዊ መንግሥቱ ሀሪቱን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ሲያዳግተው እና ግብር የመሠብሠብ አቅሙ ሲዳከም
•ሙስናና ህገወጥነት በሀገሪቱ ውስጥ በእጅጉ ሲንሰራፋ
• አካባቢያዊና ፖለቲካዊ (geopolitical consequences) ስንክሣሮች ሲበራከቱ እንደሆነ ----- ያስረዳል፡፡
እንደ Fund for Peace (FFP) ሪፖርት፥ ሀገራች ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የመጨንገፍ አደጋ (Critical or Warning Categories) ከተጋረጠባቸው 15 የአለም ሀገራት ዉስጥ አንዷ መሆኗን ያመለክታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የሆነዉ እየሆነ፣ ከዛሬ ላይ ደርሰን፣ ሰሞናዊዉን ነባራዊ ሁኔታ ቆም ብለን ስናስተዉልና ከላይ ከተገለፁት ነጥቦች አንፃር ስናገናዝብ፣ “የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና” በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ትጨነግፍብን ይሆን? የሚል አንዳች ክፉ ስጋት ወደ እዝነ ልቦናው ዘልቆ፣ ነብሱ የማትጨነቅ፣ ነብስ ያወቀ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይኖራል ብሎ ማሰብ  እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ታዲያ ይህች የ ሦስት ሺህ ዓመታት የደደረ ታሪክ ባለቤት፥ ከማንም ቀድማ ስርዐተ መንግሥት የገነባችና ለተቀረው ዓለም ስርዓተ መንግሥት ግንባታን ያስተማረች ሀገር፥ እንዴት እንዲህ ጣርዋ ይብዛ?
“ሞኝ ከራሱ ዉድቀት ይማራል፥ ብልጥ በሰው ዉድቀት ይማራል” እንዲሉ አበው፥ እኛም እሩቅ መሄድ ሣይጠበቅብን ግራና ቀኝ የነውጥ፣ የብጥብጥና የትርምስ ማዕበል ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የሚንጣትን፥ እንደ ሀገር መቆም ተስኗት የምትድኸውንና አፍንጫችን ስር ያለችውን ጎረቤት ሶማሊያ ከመሆናችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ጊዜ ላይ መድረሳችን ግልፅ ጉዳይ ነው፡፡ ጃን ቲጅሜን የተባለ አምደኛ ዘ ኢኮኖሚስት በተሰኘው መፅሄት ላይ እ.ኤ.አ. በ2010 ባቀረበው መጣጥፍ፤ ለሶማሊያ ውድቀትና ለተከተለው መዘዝ፣ አንኳር ገፊ ምክንያቶች ከሚባሉት መካከል፡- ደካማ የሆነ ማዕከላዊ መንግስት መፈጠር፣ ተደጋጋሚና ሰፊ ህዝባዊ አመፅ፣ እንዲሁም ቅጥ አልባ የሙስና ድርጊቶች መስፋፋት ተጠቃሽ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥቶ ይገልፃል፡፡ ታዲያ እነዚህ መግፍኤዎች ዛሬ በሀገራችን ኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋሉ አይደሉምን?
በሌላ በኩል ዴቪድ ብሌር የተባለ ፀሐፊ እ.ኤ.አ ጥቅምት  18, 2008 ዘ ቴሌግራፍ በተባለ መፅሄት ላይ ባቀረበው ጽሁፍ፤ ሶማሊያን ለዚህ ማለቂያ አልባ ውጥንቅጥ የዳረጋት በተቀናቃኝ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት መሆኑን ይገልፃል፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው ጉዳይ ግን በጠቅላላው የሶማሊያ ህዝብ፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ የዘር ግንዱ ከአንድ ብሔር የሚመዘዝ፣ አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገርና ተመሣሣይ ሃይማኖት  (የእስልምና እምነት) ተከታይ ህዝብ ሆኖ ሳለ፣ እራሱን በጎሳ በመከፋፈልና የጎሳ ልዩነት (clan rivalries) በመፍጠር፥ ከአንድነት ይልቅ ክፍፍልን፣ ከመከባበር ይልቅ መናናቅን፣ ከሠላም ይልቅ ሁከትና ትርምስን እንዲሁም ከጋራ እድገት ይልቅ የጋራ ጥፋትን ወይም ፈረንጆች እንደሚሉት፣ የተረጋገጠ የጋራ መጠፋፋትን (Mutually asserted destruction)  በማስቀደም፣ ይኸው ዛሬ መቋጫ በሌለው የዉድቀትና የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡
እንግዲህ አንድ ብሔር የሆነው፥ ተመሣሣይ እምነትና አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገረው የሶማሊያ ህዝብ፤ እራሱ ፈጥሮ ባበጀው የጎሳ አጥር መዘዝ፣ ለእርስ በእርስ መጠፋፋትና የጋራ ውድቀት ከተዳረገ፣ ዛሬ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን፥ ወደንም ሆነ ሣንወድ የፈጠርነውን የብሔር፣ የፖለቲካ፣ የዕምነት ወዘተ...አጥር  ስንመለከትና በአሁኑ ወቅት እየታየ እንዳለዉ በተለያዩ አጥሮች ተሸንሽነን፣ አንዳችን አንዳችን ላይ ጣት በመቀሰር ብሎም ጥቃት በመፈፀም የጋራ ዉድቀታችንን ለማሣለጥ ከመረጥን፥ ከጎረቤታችን ሶማሊያ እጅግ የበረከቱና ህልቆ መሣፍርት የልዩነትና የጋራ መጨንገፍ ሊያስከትሉ የሚችሉ ከበቂ በላይ ገፊ ምክንያቶች መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት በሐገራችን በተለይም  ከብሔርና ከፖለቲካ አንፃር ያሉትን ነባራዊ የልዩነት ኩነቶች ስንመለከት ደግሞ ያለ ምንም ጥርጥር ሶማሊያ ወደገባችበት አዘቅት የሚወስደውን ጎዳና ተያይዘን፣ ወደ ጋራ ውድቀትና አዘቅት በፍጥነት እየተነዳን ለመሆናችን ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም። እኛ ኢትዮጵያዊያን ምንም እንኳን ባለፈው ታሪካችን ውስጥ በርካታ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ቅራኔዎች ያስተናገድን ህዝቦች ብንሆንም እንደ ሀገር እና እንደ ህዝብ፣ እረጅም ታሪክና የጋራ ዕሴቶችን ገንብተን፣ ልዩነቶቻችንን ማስታረቅ በመቻላችን፣ ብዙ መንገድ አብረን ለመጓዝ ችለናል፡፡ በመሆኑም ከገዛ ታሪካችን በመማር ልዩነታችንን አስጠብቀንና ተቀብለን፣ ተከባብረን፣ እንደሠለጠነና በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደሚኖር ህዝብ፣  እንደ ሀገር መቀጠልና  የብሔርም ይሁን የፖለቲካ እንዲሁም ሌሎች ልዩነቶቻችንን ወደ ዕድል መቀየር ከቻልን፥ ለሁላችንም የምትመችና ብዝሀነትን የምታስተናግድ የጋራችን የሆነች እንዲሁም ከቀድሞ የተሻለች ሀገር መገንባት እንችላለን፡፡
በነገራችን ላይ ልዩነት እድልም ፈተናም ሊሆን እንደሚችል ግልፅ ነዉ፡፡ ይሁንና እድል ወይም ፈተና እንዲሆን መምረጥ ግን በእጃችን ላይ የሚገኝ፣ እኛው አራሳችን የምንወስነዉ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ከብሔርም ይሁን ከጎሣ እጅግ ከፍ ያለውን የዘር አጥር ይዛና ወደ እድል ቀይራ ዛሬ አለምን የምታሾረውን ልዕለ ሐያሏን አሜሪካን በቀላሉ መመልከት ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው አሜሪካውያን ከተለያዩ ክፍለ አህጉራት ተሰባስበው ሲያበቁ፥ ነጭና ጥቁር የቆዳ ቀለማቸው ሳያግዳቸው፤ እስፓኒሽ፣ ሜክሲኮ፣ ህንድ ወይም አፍሪካ ሳይሉ፥ ይልቁንም ልዩነታቸውን ወደ እድል በመቀየር፣ ዛሬ የጋራ እሴት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገንብተው፣ለሁሉም ዜጎች ምቹ የሆነ አገር ፈጥረዋል። በዚህ ረገድ ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ሀገር፣ ምን አይነት ሀገር መሆን እንደሚችል አሜሪካ ጥሩ ማሳያ ናት፡፡         
ለማንኛውም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን መስቀለኛ መንገድ ከግምት ዉስጥ ስናስገባ፣ ሁሉም በሐገር ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል በተለይም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው ገዢ ፓርቲ፣ ከተለመደው የስሜታዊነትና እስካሁን (ባለፉት 25 አመታት) የሔድንበትን ጊዜዉ ያለፈበት አቅጣጫ በመተው፣ ጊዜው የሚጠይቀውን መፍትሔ ቆም ብሎ በመፈተሽ፣ በእወድቅ አልወድቅ ሰቀቀን የምትንገዳገደውን ሐገር፣ ለመታደግ መትጋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ የማያጠያይቅበት ደረጃ ላይ መድረሳችን ልብ ሊባል የሚገባው ሐቅ ነው፡፡  “ለንቁ ፈረስ ያለንጋ ጥላ ይበቃዋል” እንደሚባለው፥ አሁን በሀገሪቱ ላይ እያንዣበበ የሚገኘው የመጨንገፍ ጥላ ሊያነቃን ካልቻለ፥ እንደ ጎረቤታችን ሶማሊያ የመጨንገፍ አለንጋ ካረፈብን በኋላ ብንነቃ፣”ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ይሆናልና ሳይረፍድብን መንቃት ይጠበቅብናል፡፡
ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር!

Read 1787 times