Saturday, 04 November 2017 12:46

በዶ/ር መረራ ጉዲና ጉዳይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተደመጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ሁለቱን ምስክሮች ፖሊስ በአድራሻቸው ሊያገኛቸው አልቻለም ተብሏል

   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌን በመተላለፍ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተከሰሱት ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ አቃቤ ህግ ከቆጠራቸው አራት ምስክሮቹ መካከል ሁለቱ ትናንት የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በፖሊስ ተፈልገው ባለመገኘታቸው መቅረብ እንዳልቻሉ አቃቤ ህግ አስረድቷል፡፡
በእለቱ ቃላቸውን የሰጡት ሁለቱ ምስክሮች፤ በማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ፣ ዶ/ር መረራ ጊዲና የላፕቶፓቸውን የይለፍ ቃል (password) ተጠይቀው ከሰጡ በኋላ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ ፅሁፎች ፕሪንት ተደርጎ ሲወጣና እሳቸውም ፅሁፎቹ የራሳቸው ስለመሆናቸው በፊርማቸው ሲያረጋግጡ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በመለስ ፅሁፎቹ ምን ይዘት እንዳላቸው እንደማያውቁ ገልፀዋል-ምስክሮቹ፡፡
በፖሊስ ተፈልገው አልተገኙም የተባሉት ቀሪ ሁለት ምስክሮችን ለማዳመጥም ፍ/ቤቱ ለህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛና የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ በፓርላማ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ግንቦት 7 አመራሮች ጋር ተገናኝተው በመወያየት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌን ተላልፈዋል በሚል ነው የተከሰሱት፡፡ ሌላው የቀረበባቸው ክስ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት እንዲከሰትና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ የአመፅ ጥሪ አስተላልፈዋል በሚል ነው፡፡

Read 2539 times