Saturday, 04 November 2017 12:57

ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶችን ተረክቦ የሚሸጥ ድርጅት ተቋቋመ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

- ድርጅቱ መወገድ ያለባቸውንና ዋጋ የማያወጡ ንብረቶችንም ያስወግዳል
           - በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ30 ሚ.ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማስወገዱን ገልጿል
         
   በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ውስጥ የሚገኙና አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን ከጥቅም ውጪ ከመሆናቸው በፊት ተረክቦ የሚሸጥ ድርጅት ተቋቋመ፡፡
“እንደራስ አሴት ማኔጅመንት” የተባለው ይኸው ድርጅት፤ የተለያዩ ቋሚና ተንቀሳቃሽ  ንብረቶችን ከባለቤታቸው ተረክቦ፣ በሽያጭና በሌሎች መንገዶች የሚያስወግድ ነው፡፡ የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ፈለቀ ትናንት በካራቫን ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ የተለያዩ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፣ የንግድ ህንፃዎችን፣ ፋብሪካዎችን፣ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችን፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንና የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን ተረክቦ በመሸጥ ተቋሙ የሚደርስበትን ከፍተኛ ኪሣራ ለማስቀረት ይሰራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የንብረት ግምት ስራ፣ ከጥቅም ውጭ የሆኑና አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ንብረቶችን የማስወገድ ሥራ እንዲሁም የገበያ ጥናትና የማማከር ሥራም ይሰራል፡፡
በተለያዩ መንግስታዊና የግል ተቋማት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ሳይችሉ ቀርተው የከተማቹ በርካታ ንብረቶች የቆይታቸው ጊዜ እየረዘመ በሄዱ ቁጥር ከጥቅም ውጪ የመሆናቸው ዕድል እየጨመረ እንደሚሄድ የተናገሩት አቶ አንተነህ፤ ድርጅቱ የእነዚህን ንብረቶች የቆይታ ጊዜ በማሣጠር በወቅቱ አገልግሎት መስጠት ለሚችሉበት አካል በሽያጭ እንዲተላለፉ በማድረግ፣ ተቋሙን ከከፍተኛ ኪሣራ እናድናለን ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማስወገዱንም ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸው ከዚህ አገልግሎት የሚያገኘው የኮሚሽን ክፍያ መሆኑንና ሥራው አዲስ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችና በውጪ አገራትም ጭምር ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸውም አቶ አንተነህ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 1406 times