Monday, 13 November 2017 09:33

ለብሄር ተኮር ግጭቶች የፖሊሲ መፍትሄ ያስፈልጋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    በጌድኦና በሀረር የተከሰቱ ብሄር ተኮር ግጭቶችን መርምሮ ሰሞኑን ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)፤ በሀገሪቱ ብሄር ተኮር ግጭቶች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁሞ የማያዳግም የፖሊሲና የአፈፃፀም መፍትሄዎች ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ቋንቋና ብሄርን መሰረት ያደረገው የሀገሪቱ የፌደራል ስርአት ከተዋቀረ ላለፉት 26 ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ ከ40 በላይ የብሄር ግጭቶችና ጥቃቶችን አጣርቶ ሪፖርት ማቅረቡንም ሰመጉ አስታውሷል፡፡
ሰመጉ እነዚህን ሪፖርቶች ሲያቀርብ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ይጠቁም እንደነበረ አውስቶ በመንግስት በኩል ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱንና ከግጭቶቹ በቂ ትምህርት አለመወሰዱን መገምገሙን አስታውቋል፡፡
“ከብሄር ጥቃትና ግጭቶች ጋር በተያያዘ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተገቢ ትኩረት ባለማግኘታቸው ዛሬ የደረሰበት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ያለው ተቋሙ፣ በጉዳዩ ላይ መንግስት አዳዲስ የፖሊሲ መፍትሄዎችን እንዲያስቀምጥ አሳስቧል - በቸልተኝነት የሚቀጠል ከሆነ ለሀገሪቱ ህልውና አሳሳቢ መሆኑን በመግለፅ፡፡
ሰመጉ በዚህ በ143ኛ ልዩ የምርመራ ሪፖርት መግለጫው፤ በጌድኦ ዞን መስከረም 2009 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው የብሄር ግጭት፣ 31 ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውንና 101 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቷል፡፡
በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት በስፋት የዘረዘረው የሰመጉ መግለጫ፤ በጌድኦ ዞን ጨለለቅቱ ከተማ በሁለት ቀናት ጥቃት የአንድ መቶ ሰላሳ አራት ግለሰቦች ንግድ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን፣ እያንዳንዳቸውም ከ36ሺህ ብር እስከ 11 ሚሊዮን ብር እንደሚገመቱ ጠቁሟል፡፡ በይርጋጨፌ ከተማ ደግሞ የሶስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሰዎች ቤትና የንግድ ተቋማት መውደማቸውን አመልክቷል፡፡
ከወደሙት መካከል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የቡና መፈልፈያ ፋብሪካዎችና መጋዘኖች ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው መስከረም 27 እና 28 ቀን 2009 ዓ.ም በተፈፀመ ጥቃት መሆኑንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተጎጂዎች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑንና በተስፋ መቁረጥና በጤና ማጣት የተነሳ አስር ያህል አባወራና እማወራዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጫለሁ ብሏል ሰመጉ፡፡ በስደት ቀዬአቸውን ለቀው ድጋፍ የሚሹትም በርካቶች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የክልሉ መንግስት ዜጎችን ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አድንቆ ሂደቱ በቂ አይደለም ሲል ተችቷል፡፡
በሌላ በኩል ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም በሃረር ከተማ ግለሰቦች ብሄር ተኮር ድብደባና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈፀመባቸው ማጣራቱን ሰመጉ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡  

Read 1732 times