Monday, 13 November 2017 09:41

በኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን የገንዘብ ምዝበራ ፈፅመዋል የተባሉ ኃላፊዎች ከሥራና ከደመወዝ ታገዱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

  የደብሩ ፀሀፊ በዝውውር መታለፋቸው አስቆጥቷል
               
    የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ፤ በኡራኤል ቤ/ክርስቲን ከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራ ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ኃላፊዎችን ከሥራና ከደሞዝ አገደ፡፡ የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መልዓከ ገነት ተስፋ ፍስሀ፣ የሂሳብ ሹሙ መሪጌታ ሕንፃ ንርዓይ እና የቁጥጥር ሰራተኛው አቶ ዮሐንስ በርሄ ከሥራና ከደሞዝ የታገዱት ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የአስተዳደር ጉባኤ የገንዘብ ምዝበራው መፈፀሙን በመደባቸው የአጣሪ ኮሚቴ አባላት ኣማካኝነት ለማረጋገጥ መቻሉን ጠቁሟል፡፡ ሀላፊዎቹ በቀጣይ በህዝብ ገንዘብ ላይ በደረሰው ምዝበራ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ፅ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይኑ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ከሶስቱ የደብሩ ሀላፊዎች በተጨማሪ ከስራና ከደሞዝ ይታገዳሉ ተብለው የተጠበቁት የደብሩ ፀሀፊ መጋቤ ሥርዓት ልዑልሰገድ ተክለብርሀን በዝውውር መታለፋቸው ምዕመናንን እንዳስቆ ምንጮች ገለፁ፡፡ ፀሀፊው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ደብሮች ተመድበው ሲሰሩ በሚያደርሱት የስነ-ምግባር ጉድለት ከደብር ደብር እየተዘዋወሩና ከደረጃ ዝቅ ብለው እስከ መስራት መድረሳቸውን የገለፁት ምዕመናን፤ ፀሐፊው ከሌሎቹ ሦስት ኃላፊዎች ያልተናነስ ጥፋት እያለባቸው በዝውውር መታለፋቸው ለሌላ ጥፋት ዕድል መስጠት እንደሆነ ምዕመናኑ ተናግረዋል፡፡ “ሰውዬው የትም ተመደቡ የትም ቤተ-ክርስቲያን አንድ ናት፤ አስተዳደሩም እንደዛው” ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፤ አሁንም ዝውውሩ ተሰርዞ ፀሐፊው ከስራም ከደሞዝም እንዲታገዱ የጠየቁት አስተያየት ሰጪው፣ ይህ ካልሆነ በሌላም ደብር የጥፋት ስራቸውን ከመቀጠል እንደማይመለሱ ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይኑ፤ እሰካሁን አጣሪ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ከፍተኛ ምዝበራ እንደተካሄደ የሚያመላክት ትልቅ ክፍተት በመገኘቱ፣ ሶስቱ ሀላፊዎች ከስራና ከደሞዝ ታግደው ምርመራው እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን በቀጣዩ ምርመራ የደብሩ ፀሐፊም ሆነ ሌሎች ከግዢ ጋር ንክኪ ያላቸው የደብሩ ሰራተኞችና ግዢ የተፈፀመባቸው የንግድ ድርጅቶች ጉዳይ እንደሚፈተሽ አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣዩ ምርመራ ተጠያቂ የሚሆኑ ተጨማሪ ሰዎች እንዳሉ የጠቆሙት መምህር ጎይቶም፤ “የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ሰዎቹን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ ከቤተ- ክርስቲያኑ የተመዘበረው ገንዘብ እንዲመለስ ለማድረግ አቋም ይዟል” ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምዕመናን ነገሩን በቅንነት ቢያጋልጡም በሰበካ ጉባኤውም በኩል የአሰራር ክፍተት መኖሩን የገለፁት መምህሩ፤ አንድ እቃ ሲገዛ ከዚህ ቦታ ይገዛ ብለው ከመወሰን ባለፈ ጨረታ አውጥተው፣ ዋጋ አወዳድረውና የግዢ ስርዓቶችን ተከትለው ስለማይፈፅሙ ገንዘቡ ለዝርፊያ ምቹ እንዲሆን አድርገዋል ሲሉ ተችተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ደብሮች እየተስተዋለ ያለውን የሙስና እና የገንዘብ ምዝበራ ለማስቀረትና የተሻለ አሰራር ለመዘርጋት የሀገረስብከቱ ጽ/ቤት ምን እየሰራ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መምህር ጎይቶም ሲመልሱ፤ የጉዳዩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባትና ከፍተኛ ክትትል በማድረግ፣ ከስድስት በላይ በሆኑ ደብሮች በገንዘብም ሆነ በመልካም አስተዳደር ጉድለት ጥፋት ያደረሱ አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውሰው፣ በቀጣይ የተሻለ አሰራር ለመዘርጋት ሰፊ ጥናት እየተሰራ መሆኑንና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ተግባር ላይ ለተሰማሩ አካላት ስልጠና መሰጠቱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በደብረ ፅጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ1.9 ሚ. ብር በላይ የህዝብ ገንዘብ መመዝበሩን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

Read 3999 times