Print this page
Monday, 13 November 2017 09:43

መድረክ “ስር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ” እንደሚያስፈልግ ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

   “የህዝቡ ጥያቄና የመንግስት ምላሽ አልተጣጣመም”

    ሀገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ለማውጣትና ከሚያንዣብበው አደጋና ጥፋት ለመታደግ ብቸኛው አማራጭ “ስር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ” ማምጣት መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ ለውጡን ለማምጣትም ኢህአዴግ ከመድረክ እና ከሃቀኛ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ድርድር ማካሄድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
መንግስት በሀገሪቱ የተፈጠረው የህዝብ ቅሬታ የገዘፈ መሆኑን መረዳት እንዳቃተው የገለፀው መድረክ፤ የህዝቡ ጥያቄና የመንግስት ምላሽ ባለመጣጣሙ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየለዋወጠ መቀጠሉን ጠቅሷል፡፡
“ችግሩን በስር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ከመፍታት ይልቅ ወታደራዊ ኃይልን አማራጭ አድርጓል” ሲል ገዥውን ፓርቲ በመግለጫው የሚተቸው መድረክ፤ “ሁኔታው በህዝብ ዘንድ ቅሬታን እየፈጠረ፣ ሀገሪቷ በታሪኳ አይታ ወደማታውቀው የትርምስና ጥፋት አቅጣጫ እንዳታመራ ከፍተኛ ስጋት አድሮብኛል” ብሏል፡፡  የህዝቡን የፖለቲካ ጥያቄዎች ወደ መልካም አስተዳደር እጦት ደረጃ ዝቅ በማድረግ “በጥልቅ ተሃድሶ እፈታለሁ” በማለት ኢህአዴግ በራሱ የውስጥ ፓርቲ ጉዳይ ተጠምዶ መቆየቱን የጠቆመው መድረክ፤ በዚህም የተነሳ የህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል ብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በኮሬ፣ በቡርጂ ህዝቦች ላይ በተለያየ መንገድ ጥቃት መድረሱን የጠቀሰው መግለጫው፤ እነዚህ ብሄር ተኮር ግጭቶች እየተከሰቱ ያሉት የግዛት ማስፋፋት ባነገቡ የኢህአዴግ ካድሬዎች አደራጅነትና አነሳሽነት ነው ሲል ወንጅሏል፡፡

Read 3568 times