Monday, 13 November 2017 09:44

ጠ/ሚሩ ለተፈጠረው የስኳር እጥረት ይቅርታ ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(31 votes)

  • ”የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ የሚፈለገውን ውጤት እያስገኘ ነው”
            • ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል

    የስኳር እጥረት የተከሰተው ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ጋር በተያያዘ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ለተፈጠረው የስኳር ችግር ህዝቡን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን በቅርቡ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ የሚፈለገውን ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚም 2.1 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ጠቁሟል፡፡   
ለወራት የዘለቀውና በመላ ሀገሪቱ የተፈጠረው የስኳር እጥረት የተከሰተው በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በስኳር ፋብሪካዎች አካባቢ መዝነቡን ተከትሎ፣ ለአገዳ ቆረጣ ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ከውጭ ሀገር ስኳር ለማስገባት የተደረገው ጥረትም በፍጥነት ባለመከናወኑ እጥረቱ መከሰቱን አስረድተዋል፡፡ “መንግስት ለተፈጠረው የስኳር እጥረት ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ይጠይቃል” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ለውጥ መንግስት የሚፈልገውን ውጤት እያስገኘ መሆኑን የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የኤክስፖርት ምርቶች ገቢ እየጨመረ ነው ብለዋል- በቡና ግብአት ላይ የ20 በመቶ ጭማሪ መታየቱን በመጥቀስ፡፡ በተመሳሳይ ከአየር ትራንስፖርትና ከቱሪዝም የተገኘው ገቢም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  የ12 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
የምንዛሪ ተመን ለውጥ ይህን በጎ ውጤት ቢያመጣም በሸቀጦች ላይ ምክንያት የለሽ የዋጋ ግሽበት መታየቱን ያልሸሸጉት አቶ ኃ/ማርያም፤ ይህንን ለማስተካከልም ያለ አግባብ ዋጋ በጨመሩ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ፈቃድን እስከ መንጠቅና በፍ/ቤት እስከማስቀጣት የሚደርሱ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የብረት ዋጋ ላይ የ39 በመቶ ጭማሪ መታየቱን በመግለጽም፤ “የብረት ነጋዴዎች ዋጋውን እንዲያስተካክሉ ተነጋግረናል፤ ካላስተካከሉ ግን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ  አስጠንቅቀዋል፡፡

Read 6006 times