Monday, 13 November 2017 09:51

“ገንፎ እፍ እፍ ቢሉሸ ሊውጡሽ ነው እውነት አይምሰልሽ!”

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እጅግ የሚያምር ልጅ፤ ከአሸዋ ላይ አንዲት ትንሽ ጉድጓድ ቆፍሮ፣ እዚያች ውስጥ ከባሕሩ ውሃ በትንሽ ዛጎል ሳያቋርጥ ቶሎ ቶሎ እያመላለሰ ይጨምር ነበር፡፡ ውሃውን ለማቆር እየሞከረ ነው ማለት ነው፡፡
አንድ የተማረና የተመራመረ በጣም የረቀቀ ቅዱስ፤ ያንን ልጅ ባየ ጊዜ ሀሳቡ ተሳበ። ወደ ልጁ ቀረበና፤
“አንተ ልጅ ምን እያደረግህ ነው? እዚች ትንሽዬ ጉድጓድ ውስጥ ውሃ ለመጨመር ይህን ያህል አዕምሮህ እስቲጠፋ ድረስ የምትደክመው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
ልጁም፤
“ባህሩን አጠንፍፌ ውሃውን ሁሉ እዚህ ጉድጓድ ውስጥ ለመጨመር እፈልጋለሁ” ሲል መለሰለት፡፡
ቅዱሱም፤
“ያንን ለማድረግ ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ባሕሩ ምን ያህል ትልቅና ሰፊ መሆኑንና እንደዚች ባለች ትንሽ ቀዳዳ ውስጥ ይህንን ስፍርና ልክ የሌለውን ውሃ ለማግባት እንደምን እችላለሁ ብለህ ታስባለህ? የማይቻልን ነገር ለማድረግ መሞከርስ ትርፉ ድካም መሆኑን መገንዘብ እንዴት ያቅትሃል?” አለው ቅዱሱ ሰው፡፡
ልጁም፤ እጅግ የረቀቀ ትርጉም ባለው አስተያየት ትኩር ብሎ ተመለከተውና ወዲያው፤
“እኔ ባሕሩን ለማጠንፈፍና ከዚች ጉድጓድ ውስጥ መክተት ዕውን አልችልምን? ለምን ሙከራዬን ታናንቅብኛለህ? አንተ ከባሕሩ ሚሊዮን ጊዜ የሚበልጠውን የሥላሴዎችን ምስጢርና ባሕሪያቸውን ለማወቅ ትፈልግ የለምን? እዚህ አሸዋ ላይ ካደረግኋት ከትንሿ ጉድጓድ ይልቅ ወሰን ከሌለውና ይህ ይቀረዋል ከማይባለው የአምላክ ዕውቀት፤ በጣም ያነሰውን ናላህ ውስጥ አኑረህ ለመሸከም ጥረት ታደርግ የለምን?” ሲል ጥያቄያዊ ምላሽ አቀረበለት፡፡ ከዚያም ልጁ የሰማይ ብርሃን ተጎናፅፎ ወዲያው ተሰወረ፡፡ ይህ ህፃን የአምላክን ትልቅ መልዕክት ለቅዱሱ ሊናገር የተላከ ነበር ይባላል!
*       *      *
ትልቁ ነገር የሀገርን ትልቅ ስዕል ማየት ነው! ምንጊዜም ትናንሽ ችግሮች ይኖሩብናል። ልንፈታቸው የሚገባን ግን ትልቁን የሀገር ስዕል ካስተዋልን ነው! አያሌ መንገዶች ወደ መፍትሔ ሊመሩን ይችላሉ፡፡ ከመንገዶች ሁሉ የተሻለውን ለመምረጥ ግን ልዩ ዕይታን ይጠይቃል፡፡ ትልቁ ቁምነገር ጥመትን አስቀድሞ ከላይ ማስወገድ ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወ/መስቀል እንዲህ ይሉናል፡-
“ምንም ወፍጮ መፍጨት፣ ውሃ መቅዳት፣ እንጀራና ዳቦ መጋገር፣ ወጥ መስራት፣ ለሴት የተለመደ የዘወትር ተግባሯ ቢሆንም፤ ማታ ማታ ባሏን እራት ካበላች በኋላ ጥጧን አቅርባ በእሳት ዳር ሆና ትፈትላለች፤ በቡልጋ ድርና ማጉን ፈትሎ እዚያው በሚገኘው ሸማኔ አሰርቶ ለቤተሰብ አስፈላጊ የሆነውን ልብስ ማዘጋጀት የተለየ የሴቶች ባልትና ነው፡፡ በዚህም ጊዜ እንዲህ ስትል ታንጎራጉራለች፡-
“ባሰላው ባሰላው እንቢ አለኝ እንዝርቱ
 ከታችም አይደለ ከላይ ነው ጥመቱ”
ጥመቱ ከላይ ሲሆን፣ ብልሽቱ ከላይ ሲመጣ፣ አደጋው የትየለሌ ነው፡፡ ታች ድረስ ይሰማል፡፡ ይናጋል፡፡ የሥርዓት መናድ ያስከትላል፡፡ ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ጊዜ፣ የሰው ኃይልና አንጡራ - ሀብት መውጣት ይኖርበታልና የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ነው! አያሌ ችግሮች አሉብን- የላይኛው መዋቅር መዛባት፣ የፍትሕ መዛባት፣ የዲሞክራሲ መቃወስ፣ የሀብት ክፍፍል መላ - ቅጥ መጥፋት፣ የገዢና ተገዢነን አግባብ ማጣት፣ የነባራዊ ሁኔታና የህሊናዊ ሁኔታ አለመጣጣም- ወዘተ… የሥርዓት መናጋት ሥራዬ ብሎ አለማጤን፤ ለሁሉም ወገን አለመረጋጋት ይዳርጋል፡፡ ከሁሉ በላይ የሥልጣን ገዋ (Power vacuum) ቢፈጠርስ ማለትም ደግ ነው! ጉዳዮችን በመልክ በመልካቸው ሰድሮ ለማየት ቅንነትና ከተንኮል - የፀዱ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ቀናት ብቻውን፣ ያለ ፖለቲካ ብስለት የትም አያደርስም፡፡ ምክንያቱም ቀናነት ወደፈለጉት አቅጣጫ አጣመው ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ እኩያን ሊኖሩ ይችላሉ!
የይስሙላ ፍቅር፣ የይስሙላ አጋርነት፣ የይስሙላ ጓድነት እጅግ ጊዜያዊ ዕድሜ ያለው፤ “ላያዘልቅ ፀሎት ለቅስፈት” የሚባለውን አይነት ነው፡፡ ለወጉ “ዘላቂነት ዘላቂነት” ብንል …መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መፈክር ከመሆን አያልፍም፡፡ ያለንበት የሚመስለን ኳስ ጨዋታ ለተለዋጭነት (ለቤንችነትም) የማያበቃን ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ “የት ይደርሳል የተባለው ባህር ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው፡፡” ከመባል አያልፍም። ነኝ የምንለውን ነገር፣ በእርግጥ ነን ወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ፈጣን ተለዋዋጭ ሁኔታ (Volatility) ያለ ነገር ነውና እርግጠኝነት ወደ ፍፁምነት አድጓል ብሎ መፈጠም የዋህነትም፣ አዳጋችም ነው፡፡ “ገንፎ እፍ እፍ ቢሉሽ ሊውጡሽ” ነው፤ ዕውነት አይምሰልሽ!” የተባለው ተረት ቁም ነገሩ ይኸው ነው!

Read 6900 times