Monday, 13 November 2017 09:58

ሁለት ኪሎ ስኳር የነፈገን “ባለሁለት ዲጂት ኢኮኖሚያችን”!!

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(0 votes)

ስኳር ስኳር ስኳር፣
ስኳር ነሽ ጣፋጭ፡፡
የልጅነት ትዝታ እንደተጣባን እነሆ እስከ ሽበት እየዘለቅን ነው፡፡ የቤተሰባችን የጋራ “ተወዳጅ አባል” የነበረችው የፊሊፕሷ ብርቄ ሬዲዮናችን፣ ነጋ ጠባ ይህን ዝነኛ ስኳር አወዳሽ ሙዚቃ ታስደምጠን የነበረው ከአምስት አሠርት ዓመታት በፊት ነበር። እኛም ህፃናቱ ይህንን “ስኳር! ስኳር! ስኳር!” የምንዘምረው በቄንጥ ነበር፡፡ ነበር አያኮራም ቢባልም፡፡
ይሄው ጣፋጭ ዜማ በግሩም ሁኔታ በላስቲክ ከረጢት ታሽጎ፣ በአስር ሳንቲም ይሸጥ ለነበረው የወንጂ ስኳር ማስተዋወቂያነት ይውል እንደነበርም ትዝ ይለኛል። ብዙው ሰው የስኳርን ጣዕም ገና በስፋት ማጣጣም ደረጃ ላይ ባልደረሰበት በዚያ ዘመን፣ ወንጂ ስኳር ይተዋወቅ የነበረው በካሚዮን፣ ሠፈር ለሠፈር እየዞሩ፣ የልመና ያህል በተፈላ ቡና በሚያባብሉ “አቅማሾች” አማካይነት ነበር። አቅማሾቹ የእኛን የውሪዎቹን ቀልብ ይማርኩ የነበረው አንዴ ተልሳ የምታልቅ የመዳፍ ላይ ስኳር በመቸር ሲሆን ለታላላቆቻችን ደግሞ አንድ አቦል ቡና ከአንድ ከረጢት ወንጂ ስኳር ጋር በመለገስ ነበር፡፡ እውነትነቱን ተጠራጥረው፣ “ተረት ተረት” ለሚሉኝ ተረበኞች መልሴ፣ “ደጉ ዘመን” የሚል ይሆናል፡፡
በዝነኛው የእናታችን ጠጅ ቤት በማር ስልቻ መሃል፣ በኩንታል ተጎልቶ አስታዋሽ ያልነበረው ስኳር፤ ዛሬ ለወገኔና ለሀገሬ ባዕድ ሆኖ ከወርቅ ዋጋ እኩል መስተካከሉን ሳስተውል፣ አዬ ዘመን! እያልኩ፣ ዘመኑን ያከፋውን ፖለቲካችንን መታዘቤ አልቀረም። በተለይ ደግሞ “መላው ዓለም አፉን በእጁ ላይ ጭኖ የተደነቀበት በፈጣን የዕድገት እሽቅድድም ላይ ያለው ባለሁለት ዲጂቱ ኤኮኖሚያችን” ቢያንስ ለአንድ ቤተሰብ የወር ፍጆታ፣ ሁለት ኪሎ ስኳር ማቅረብ ተስኖት፣ ሕዝብ ሲያነባ መመልከት፣ እንደምን አንጀት እንደሚያሳርር ለቀባሪው አላረዳም፡፡ ዳሩ የስኳር እጥረት ሊከሰት የቻለው፣ “ስኳር ተጠቅመው የማያውቁ ወገኖቻችን፣ ይህን ጦሰኛ ማጣፈጫ ከተወዳጁ በኋላ” እንደሆነ በጎምቱ መሪዎቻችን አንደበት፣ ከማስጠንቀቂያ ጋር የተነገረን ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ ፋብሪካውም እንደ ዜጎች ቁጥር ጣሪያ እየነካ ነው በሚባልባት ሀገር፣ “በአሁኑ ሰዓት ስኳርን ከገበያ ላይ ከመፈለግ ይልቅ አልማዝ ለሸመታ ቢጠየቅ” ሳይቀል የሚቀር አይመስለኝም፡፡
ይህንኑ “እንደ መድኃኒት የተፈለገ” የስኳር ፍጆታ ለማሟላት፣ ነባሮቹን ሳይጨምር ከአስር ያላነሱ ግዙፍ የስኳር ፋብሪካዎች እንደሚገነቡ “የትራንስፎርሜሽኑ ሀገራዊ ህልማችን” አስጎምጅቶን ነበር፡፡ እኔም ለምስክርነት አንድ ሦስቱን ፕሮጀክቶች ገና ከጅምሩ ለማየትም በሉት ለመጎብኘት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል? የስኳር ፕሮጀክቶቹ ገና ወደ ምርት ሳይገቡ፣ ለብዙ ጎምቱ ሹማምንቶቻችን “ቀን መውጫ፣ ከድህነት ማምለጫ፣ የሀብት ማከማቻ፣ የግል መንደላቀቂያ” ሆነው እንዳረፉ በቅርቡ ያረዳን፣ የሙሰኞቹ የፍርድ ቤት ውሎ ምስክር ነው፡፡
ከስኳር ፕሮጀክቶቹ ጋር በተያያዘ ምን ያህል የሀገር ሀብት እየባከነ እንዳለ፣ ምን ያህል ሀብት እንደተዘረፈ፣ ዜናውን ስንሰማ ጭንቅላታችንን ይዘን፣ ኡኡ ማለት ነበር የቀረን፡፡ የሀገር ሀብት ነዋ! ከደመወዛችን ላይ የምንገሸለጠው ታክስ ነዋ! መፃኢው ትውልድ ከየትም አምጥቶ ይክፈለው ብለን በጭፍን በመፍረድ፣ ከባለጠጎቹ ሀገራት ላይ የተበደርነው ገንዘብ ነዋ! የሕዝባችንን የፀጉር ልክ ያህል የውጭ ዕዳ ተሸክመን ለጎበጥነው ለእኛ መሰሉ ሕዝብ፣ የሀገር ሃብት በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፍ እያየን፣ “የሀገር ያለህ” እያልን የኡኡታ መዋጮ ባናዋጣ “የኢትዮጵያ አምላክ በመጨረሻው የፍርድ ሰዓት ለፍትህ እናት አሳልፎ መስጠቱ” የሚቀር አይመስለኝም፡፡
የፓርላማ ወንበረተኞቻችን አንድ ሰሞን ከስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ ጉድ የሚያሰኝ አስደንጋጭ ውይይት አስደምጠውን፣ ጉዳዩን ከምን እልባት ላይ እንዳደረሱት የመጨረሻው ውጤት እንደናፈቀን፣ ጉዱ በጓዳ ተድበስብሶ የቀረ መስሎናል። ውጤቱ ታውቆ ከሆነም አልተገለፀልንም፡፡ ስለዚህም እንደ ዜጋ ኡኡታ ሲያንሰን ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ የወንበረተኞቻችን ቋሚ ኮሚቴ፣ የስኳር ኮርፖሬሽንን ሥራ ገመገምኩ ባለበት መድረክ ላይ የተደመጠው መለሳለስ እንደ ዜጋ በግሌ አሳፍሮኛል። አስገንፍሎኛል፡፡ “ኬኒያ ሊገባ የታሰበው ስኳር እንዴት ከድንበር ላይ ሊመለስ ቻለ?” ተብለው የተጠየቁት የኮርፖሬሽኑ ሹም፣ እራሳቸውን ከደሙ ንፁህ አድርገውና ተረጋግተው፣ “በእኛ በኩል እንጃ፣ ላኪና ትራንስፖርተርስ ነጋዴዎቹን መጠየቅ ይሻላል፡፡ ይሄ ጉዳይ በፍፁም የስኳር ኮርፖሬሽንን አይመለከትም” የሚል በፈገግታ የታጀበ መልስ ብጤ ሲሰጡ፣ “የተከበሩት ወኪሎቻችን” በአንፃሩ፤ “ነው እንዴ? ከሆነ እሺ!” ዓይነት እንደ ዘበት ማለፋቸውን፣ ከሕዝብ የተኳረፈው የዜና መስኮታችን፣ ጭራውና ቀንዱ በማይለይ ሁኔታ የውይይቱን ሃሳብ ቆራርጦ አስደምጦናል ወይንም አስገርሞናል፡፡ “መስከረም ሳይጠባ ጉድ አይሰማም” ብለን ለመተረትም ድፍረት ሰጥቶናል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው፣ እኛ ብዙኃኑ ዜጎች እንዳንሰማው ተቆራርጦ የቀረ ዝርዝር ሃሳብ ካለ፣ ያንን “አይሞሌ” ሚዲያችንን ገስፆ፣ ዝርዝር ውይይቱን ቢያስደምጠን አንጠላም፡፡ “በነዲድ ሃሩር ሲንከራተት ከርሞ እያነባ ወደ ሀገሩ የተመለሰው” የስኳር መጠን፣ አራት ሺህ ቶን (አርባ ሺህ ኩንታል) መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ የሂሳብ ስሌቱ ቀላል ነው፡፡ በሙቀት ምክንያት ምን ያህሉ ቀልጦ፣ ምን ያህሉ ለሀገሩ እንደበቃ በውነቱ መረጃው አልተሰጠንም። የስኳር እጥረት እያንፈራፈረን ባለበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት (ሀገሪቱ ምን ዶላር ቢያስፈልጋት፣ የታሰበው ዶላር በእውነትም ልማት ላይ የሚውል ከሆነ) ቅድሚያ መሰጠት የነበረበት ለማን ነው? አራት ሚሊዮን ኪሎ ስኳር በሀገር ውስጥ ቢያንስ ለአንድ ቤተሰብ ወርሃዊ ኮታ ሁለት ኪሎ ስኳር ቢከፋፈል ኖሮ፣ ለሁለት ሚሊዮን ቤተሰብ ይደርስ ነበር፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሦስት አባላት እንኳ ቢገኙ ስድስት ሚሊዮን ሕዝባችን ተጠቃሚ በሆነ ነበር፡፡ መቼም በሂሳብ ስሌቱ የሚሳለቁና የሚራቀቁ ወገኖች እንደሚኖሩ ይገባኛል፡፡ አይ ሀገር! አይ ሀገር! አይ ሀገር!   
የስኳር ጉዳይ ናላውን ያዞረውና የልብ ድካም ያለበት ወገኔ፣ ይህንን ያህል ቁጥር ሰምቶ  ገላፈቻ እንዳይልብኝ ስለሰጋሁ መጠኑን የገለፅኩት እያለሳለሰኩ ነው፡፡ ይሄንኑ ሰሞኑን በድንበር በኩል አፈትልኮ ሊሰደድ ነበር የተባለ ስኳር መታገት በተመለከተ፣ቀድመን መርዶውን የሰማነው፣ ከዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች እንደነበር ይታወሳል፡፡ የእኛዎቹ መንግሥታዊ ሚዲያዎችማ “ተከድነው ይረሩ” ተብሎ ስለተፈረደባቸው በምን እዳቸው ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን ተብዬው መንግሥታዊ ተቋም፣ “እኔ የለሁበትም” በማለት በጲላጦስ ሣህን አጁን የተለቃለቀበት ይህ አሳፋሪ ጉዳይ፣ ለዜና ማሰራጫዎቹ ትኩስ ዜና፣ ለእኛ ደግሞ ትኩስ መርዶ መሆኑን ማን በነገራቸው፡፡    
ይህንን መሰል ሀገራዊ መርዶ ሲጋት የከረመው ወገኔ፣ እንባው ሰማይ ሰማያት ደርሶ አሲድ ለማዝነብ በሚያጉረመርምበት  የትናንቱ አንድ ቀን፤ “እማማ ይፈልጓችኋል” ተብሎ ከእናታችን ቤት ስልክ ተደወለልን። ፈጥነን ደረስን፡፡ እማማ አዝነዋል፤ ተክዘዋል፡፡ የሀዘናቸው ምክንያት ደግሞ የብዙውን ሰው ቆሽት እያደበነ ያለው ይሄው የጋራ ሀገራዊ ጉዳይ ነው። የስኳር ጉዳይ፡፡ የተደወለልን ከቤታችን ያለውን ስኳር አራግፈን ይዘን እንድንመጣ ጭምር ነበር፡፡
ታዳጊዎቹ የእናታችን የልጅ ልጆች፣ስኳር ከቤትም ከሰፈር ገበያም ከመጥፋቱ የተነሳ፣የቁርስና የመክሰስ ላይ ሻሂያቸው ስለተጓደለባቸው፣”ትምህርት ቤት አንሄድም” ብለው ለቀናት አድማ  መትተዋል፡፡ ትምህርት ቤት ላለመሄድ የወሰኑት ለተወሰኑ ቀናት ብቻ ሳይሆን ስኳር እስካልቀረበላቸው ድረስ ለሁልጊዜም እንደማይሄዱ ጭምር ወስነዋል፡፡ “አብዮታዊ አቋማቸውን” የገለፁት ደግሞ የመማሪያ ደብተሮቻቸውንና መጻሕፍታቸውን ከቦርሳቸው ውስጥ እያወጡ በመበተን፣እንቢታቸውን በማጠናከር ጭምር ነበር፡፡ ልጆቹ በቁንጥጫ ስላላደጉ መባለጋቸው አይደለም፡፡ እኛ ትልልቅ ተብዬዎቹ፣ በሀገራዊ ጉዳይ አንጀታችን እርር ሲል የስሜታችንን የቁጣ ወላፈን ያለ ገደብና ያለ ይሉኝታ እንደምንዘረግፈው ሁሉ ህፃናቱም የፈፀሙት የተቃውሞ ድርጊት፣ ዕድሜያቸው የሚፈቅደውን ስለሆነ አይወቀሱም፡፡ ይህ እውነት ተረትም ግነትም የለበትም፡፡
ከቤት እንደደረስን እማማ የጠየቁን የመጀመርያው ጥያቄ፤ “ስኳሩ የታል?” የሚል ነበር፡፡ ባለቤቴም ፈጠን ብላ በተከፋ ስሜት፤ “እንኳን እኛ ቤት ከሀገር ጭምር ስኳር ከጠፋ ሰንብቷል” የሚል መልስ ለእናቷ ሰጠቻቸው፡፡ የእማማ ተስፋ ከመቅፅበት ሲዳፈን ታውቆኛል፡፡ ለካስ ልጆቹን ያረጋጉት፣ እኛ ስኳር ይዘን እንደምንመጣ ዋስትና በመስጠት ነበር። “ስኳር አላመጣንም” የሚለውን መልስ እንደሰሙ፣ ከእማማ ዓይን የፈሰሰው እንባ፣ ለአንድ ሟች ዘመድ ተቆጥቦ ቢቀመጥ ኖሮ፣ ጥሩ የፍቅር ስንቅ ይሆን ነበር፡፡ እንባቸውን እያበሱ ዞረን እንድንፈልግና በተገኘው ዋጋ ገዝተን እንድንመጣ ፣ቀጭን የእናትነት ትዕዛዝ ተሰጠን። ቃላቸውን ማክበር ስለነበረብንም “የስኳር ያለህ” እያልን፣ ከተራ ኪዮስክ እስከ ሱፐር ማርኬት፣ ከመርካቶ እስከ ሾላ ገበያ፣ ከዋናው አስፓልጽ እስከ ጉራንጉር  ሰፈሮች በተወደደ ቤንዚን እየተሽከረከርን፣ በአራቱም አቅጣጫ፣ ከተማችንን በማሰስ ተንከራተትን።
“የግለሰቦችን መብት በሚገባ ያስከበረው ልማታዊው ዲሞክራሲያችን” በትንሽ በትልቁ ለፍረጃ ይጣደፋል የሚል ግምት ስለሌለኝ  የዛሬን አያድረገውና፣ በዚያ “በመልከ ጥፉ” የደርግ ዘመን ቢሆን ኖሮ፣ አንድ ኪሎ ስኳር ዋጋው  ሁለት ብር ከአስራ አምስት ሣንቲም ስለነበር የባከነውን የቤንዚናችንን ዋጋ ስናሰላው፣ አንድ ኩንታል አሸክሞ ይመልሰን ነበር፡፡ የማያባራ የጦርነት ፍዳ የተሸከመው ደርግ ቢያንስ፣ “የቀለህ መግዣው ናላውን ቢያዞረውም” እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ስኳር በኮታ ያቀርብልን እንደነበረ ማስታወሱ፣ “ጦርነት ናፋቂ” አሰኝቶ እንደማያስገመግም ተስፋ  አደርጋለሁ፡፡
ለማንኛውም የማታ ማታ አንድ አካባቢ አንዱ ኪሎ ስኳር በጥቁር የጭለማ ስሌት፣  ከሃምሳ አምስት ብር እስከ ሰባ ሁለት ብር እንደሚሸጥ ተጠቁመን፣ ይገኛል የተባለለት ቦታ ደረስን፡፡ እንኳን ሰባ ሁለት ብር፣ ሰባት መቶ ብር ቢጠሩም፣ ንብረት አሲዘንም ቢሆን ለመግዛት ዓይናችንን የምናሽ አይመስለኝም። ለማንኛውም የተባለው ቦታ እንደ ደረስን በልባችን እየፀለይን፣ በልምምጮሽ ቋንቋ፣ “ፍልቅልቁንና ሽቁጥቁጡን ነጋዴ”፣ አንድ ሁለት ኪሎ ስኳር እንዲሸጥልን ተማፀንነው። ነጋዴውም በሙሉ ፈገግታ ታጅቦ፤ “ጋሼ እኔ እኮ አድናቂህ ነኝ!!! ለአንተ ሁለት ኪሎ ቀርቶ ኩንታሉን ብሰጥህስ ምን ይጎዳኛል፡፡ አዝናለሁ፤ ስኳር የሚባል ሸቀጥ በሕይወቴ ነግጄም አላውቅም፡፡ እንዴት ወደ እኔ ሊመሩህ ቻሉ? ጠላቶቼ ናቸው ይህንን የሚያስወሩብኝ” ብሎ ወሽመጣችንን በጠሰው፡፡ ለካስ በዚያ በማያልፍለት የቴሌቪዥን መስኮት አማካይነት አስታውሶኝ ኖሯል፡፡ በኋላ እንደተረዳሁት፣ ለጥቆማ እንደሄድኩ ሳይጠራጠር አልቀረም፡፡ ብጠቁምስ ዳሩ… “አይ አለመተዋወቅ!” አለ አሉ፤ ሌቦ ሣህሉ፡፡
መድረስ አይቀርምና ባዶ እጃችንን እያጨበጨብን ቤት ደረስን፡፡ አብዮተኞቹ ህፃናት አኩርፈው እንደተዶረሩ አገኘናቸው፡፡ መጽሐፋቸውና ደብተራቸው እንደተዝረከረከ ነው፡፡ ባለቤቴ የስኳር እጦቱን መርዶ እንድታረዳ እኔ ደግሞ “አብዮተኞቹ ህፃናት” በተቃውሞ የበተኑትን ደብተራቸውንና መጽሐፋቸውን፣ መክሬያቸው እንድሰበስብ ሥራ ተከፋፍለን፣ ወደየተግባራችን ተሰማራን፡፡ ተግባሬን ጀምሬ የተበታተነውን መጽሐፍ ለመሰብሰብ ጎንበስ ስል፣ በአንድ መጽሐፍ ላይ የራሴን ስም አየሁት፡፡ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መማሪያ መጽሐፍ ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት ለትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍሎች ያሉትን የመማሪያ መጻሕፍት ያዘጋጀነው በቡድን ነበር፡፡ በመጻሕፍቱ ሽፋን ላይ ስማችን አፍጥጦ ተቀምጧል፡፡ በተለይ እኔ የጻፍኩት ምዕራፍ፤ “የሀገር ፍቅር” የሚለውን ነበር፡፡ አዬ ጉድ!!
በምዕራፉ ውስጥ ወጣቶች ታዳጊዋንና በዲሞክራሲ ጎዳና ላይ የምትገኘውን ሀገራቸውን እንዲወዱና ለሕዝባቸው ታማኝ አገልጋይ እንዲሆኑ ያልጠቀስኩት ምሳሌ፣ ያልሰበክሁት ስብከት፣ ያልደሰኮርኩት ዲስኩር አልነበረም፡፡ ተማሪዎቹ የዜግነት ግዴታቸውን በትጋትና በቅንነት እንዲወጡ፣ መንግሥትም ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚያከብር ደመቅ አድርጌ መጻፌ ትዝ ይለኛል፡፡ ዛሬ ፊት ለፊት የተላተምኩት ከእዚህን መሰሉ ቲዎሪና መራር እውነታ ጋር ነው፡፡ ልጆቹ ስኳር ጠይቀዋል፡፡ ይህ ትንሹ የመብታቸው ክፍል ነው። “ነፍስና ሥጋቸውን” እንዲጠብቅላቸው አደራ ለሰጡት መንግሥት፣ ቢያንስ ለእኛ ኢምንት፣ ለእነርሱ ግን ግዙፍ የሆነ “የስኳር መብት” ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ቤተሰባቸው በኑሮ ውድነት ሲናጥ፣ የትምህርት ቤት ክፍያቸውና ወጭአቸው የቤተሰቡን ናላ ሲያዞር ነጋ ጠባ እያደመጡ ነው፡፡ በትምህርት ቤታቸው ደግሞ እኔና ብጤዎቼ  በጻፍኩት መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሀገር ፍቅር ይማራሉ፡፡ በአንፃሩ አንድ ማንኪያ ስኳር ከቤታቸው ማጀት በመጥፋቱ ወላጆች ሲማረሩ እየሰሙ ነው፡፡ “የኢኮኖሚያችን እድገት ያመጣው የፍላጎት መጨመር ውጤት ስለሆነ ታገሱ” ማለት ለእነርሱ ትርጉም አልባ ተረት ነው፡፡ እግዚኦ ተቃርኖ!!
እማማ እንባቸውን እንዲያብሱ ያልመከርኩትን ያህል፣ ጉዳዩ የእኔን ህሊና በአርጩሜ መቅጣት ሲጀምር፣ አይኔም ልቤም እየተደጋገፉ ተላቀሱ፡፡ ሀገሬ በእውነት ሀገር አላት? (በዚህ ርዕስ ከአሁን ቀደም አንድ ጽሑፍ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡) መሪዎቻችንስ ብሶታችን ይገባቸው ይሆን? እንደው ለነገሩ በመሪዎቻችን ቤት ስኳር ጠፍቶ ያውቃል? የመሪዎቻችን ሚስቶች፣ እንደኛ ሚስቶች ከገበያ ሲመለሱ፣ ከኑሮው ውድነት የተነሳ ከገዙት ዕቃ በበለጠ ክብደት ፌስታል ሙሉ ምሬት ተሸክመው ይመጡ ይሆን? ለነገሩስ ገበያውን ያውቁታል? ልጆቻቸውስ ስኳር ቆጥቡ ተብለው ተመክረው ያውቃሉ? ሀገር ውስጥ ይማሩ ከሆነስ፣ እንደ እኛ ልጆች “የትምህርት ቤት ክፍያ በጊዜው ካልከፈላችሁ ትባረራላችሁ” ተብሎ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ያውቃል? በእግር እንደሚኳትኑት እንደ እኛ ልጆች እንደነ ጂጆ፣ እንደነ ሮዳስ፣ እንደነ ሌዊ፣ እንደነ አቢጌኤል “የአለቆቻችን ልጆችስ” ስኳር አጥተው ያውቃሉ?  ስኳር በማጣትስ ትምህርት ቤት አንሄድም ብለው፣ በቤተሰቦቻቸውንና በሾፌሮቻቸው ላይ አምፀው ያውቃሉ?  አያድርግባቸው! «ምን በወጣቸው ይቸገሩ? ችግርን የለመዱት የእኛው ልጆች እንደ ቢጤታቸው ቢኖሩ ይሻላል፡፡» የሀገራችን የገበያ ንረት ከአስራ አምስት ፐርሰንቱ ግሽበት በፊትም ሆነ በኋላ እንደ ስፑትኒክና እንደ አፖሎ መንኮራኩሮች፣ ሰማይ ሰማያት ሲወነጨፍ ምድር ላይ ቁጭ ያሉት መሪዎቻችን፣ እዮታችንን እያደመጡ ይሆን? እንጃ! እንጃ! እንጃ!
ከመኖሪያ ቤታችን ፊት ለፊት የሸማቾች ሱቅ አለ። ከሁለት ሦስት ቀናት በፊት ስኳር መጥቷል ተብሎ ተነግሮ ስለነበር ይታይ የነበረውን ትርዒት መመልከት በእጅጉ ይሰቅቃል፡፡ ሁለት ኪሎ ስኳር ለመግዛት ሰልፉ የተጀመረው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ነበር። እናቶች፣ እህቶች፣ አባቶች፣ ጎልማሶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች--- በጋቢና በካፖርት ተጠርዘው፣ በጥቅምት ብርድ፣ በእኩለ ሌሊት እንደ ሰማይ ክዋክብት ሜዳ ላይ  ፈሰው ማየት፣ እንኳን የሰውን ልጅ በደመ ነፍስ የሚመሩትንም እንስሳት ያራራ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ሌሊቱን በብርድ ሲቀጡ ካደሩት መካከል ምን ያህሉ እንደተሳካላቸው አዋቂዎቹ፣ ሸማቾቹና አንድዬ ብቻ ናቸው፡፡ ለመሆኑ እነዚያ ወረፋ ጠባቂ ግፉዓን፣ በዚያ እኩለ ሌሊት የጭውውታቸውና የፀሎታቸው ርዕስ ምን ሊሆን ይችላል? “ረዥም ዕድሜ ለመንግሥታችን? የተባረከ ጤንነት ለመሪዎቻችን?” የሚል ይሆን? እንጃ! እንጃ! እንጃ!
እንደው መላ ሲጠፋ የጅል ሃሳብ መታሰቡ የተለመደ አይደል? ሃኪሞቻችን ለእኛ ለአዋቂዎቹ  ጤንነት በመጠንቀቅ ከሦስቱ ነጫጭ ገዳዮች (The three white killers) ከጮማ፣ ከጨውና ከስኳር እንድንታቀብ ማስተማሩን ቢበረቱበት ይሻል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እኛ ወላጅ ተብዬዎች፣ ሦስቱን ነጫጭ ገዳዮች እንድንፈራቸው እንደተደረገ ሁሉ፣ ልጆቻችንም በተለይ ስኳሩን እንዲፈሩትና “አብዮት እንዳያስነሱብን”  የየግላችንን ካሪኩለም ቀርፀን  በየቤታችን እያስፈራራንም ሆነ በትጋት እያስተማርን “ከስኳር ወረፋ ጠባቂነትና ከምሬት” መገላገሉ ይሻል ይመስለኛል፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽናችንም የሥራ ጫና ሊቀንስ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ የስኳር ቀበኞችንም ቁጥር ለመቀነስ ጥሩ ስትራቴጂ ይሆናል። ይህ ፕሮጀክት ከተሳካ “ስኳር፣ ስኳር” ዝማሬን ወደ ሌላ የአሸናፊነት አብዮታዊ ዝማሬ መለወጡ አይገድም፡፡ እንዲህ፡-
“አብቅቷል ለስኳር መንከራተት፣
አብቅቷል እያጣፈጡ መጠጣት፣
አብቅቷል ከሸማቾች ደጅ መዋል፣
አብቅቷል በስኳር ናጦ መክበር፡፡”
እንግዲህ ቸር እንሰንብት!!

Read 984 times