Monday, 13 November 2017 10:03

የፌደሬሽኑ ጉባዔ የኳሱ ህልውና በሚወስኑ አጀንዳዎች በቂ ውይይት አላደረገም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጥቅምት 30 እና ህዳር 1 ላይ በአዲስ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል  10ኛው  መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ከ45 ቀናት በኋላ በአፋሯ ከተማ ሰመራ እንዲደረግ ወስኗል፡፡
የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር  በምርጫው ሂደት ላይ ችግር መኖሩን በመጥቀስ በፃፈው ደብዳቤ ይራዘም ወይስ ይካሄድ በሚለው አጀንዳ ሰሞንኑን እየታመሰ ነበር፡፡ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ፌዴሬሽኖች ምርጫው እንዲራዘም  ፤የአዲስ አበባና የደቡብ ክልሎች ደግሞ ምርጫው እንዲካሄድ በያዙት አቋማቸው በጠቅላላ ጉባኤው ከተሟገቱ በኋላ በመጨረሻም በ68 የድጋፍ ድምፅ እና በ62 የተቃውሞ ድምፅ እንዲራዘም ሊወሰን በቅቷል፡፡ በጉባዔው የመጀመርያ ቀን    የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫው እንዲራዘም ከተወሰነ በኋላ መቼና የት ምርጫው ይደረግ በሚለው በጉባዔው ሁለተኛ ቀን መርሃ ግብር ውይይት ተደርጓል፡፡ ጉባኤው  ይራዘም የሚለውን አቋም የማይቀበሉ ባለድርሻ አካላት በመጀመርያው የጉባኤው ቀን የተላለፈው ውሳኔ ተቻኩሏል በሚል ተቃውሟቸውን የገለፁት በመተዳደርያ ደንቡ እንደተቀመጠው ሁለት ሶስተኛው የጉባኤው አባላት የድጋፍ ድምፅ ማግኘት ነበረበት የሚል ጥያቄ አንስተው የነበረ ቢሆንም  በመጨረሻም መራዘሙ ተገቢ መሆኑ በጉባኤው ከመግባባት ላይ ተደርሶበት  የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫው ከ45 ቀናት በኋላ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡   በየትኛው ከተማ አስተናጋጅነት ይካሄድ  በሚለው አጀንዳም  ከጅምሩ 10ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ በዋና ከተማው ሰመራ ላይ እንዲያስተናግድ ተመርጦ በድንገት እድሉን ያጣው የአፋር ክልል እንዲያዘጋጀው ከስምምት ላይ ተደርሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዋዜማው ሰሞናት ሲናፈሱ የነበሩት የተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች በጉባኤው የ2 ቀናት መርሐ ግብር የቀዘቀዙ ቢመስልም በተለይ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫው  የኳሱን ህልውና በሚወስኑ አጀንዳዎች በቂ ውይይት እንዳይደረግባቸው  እንቅፋት ነበር፡፡  ስልጣኑን ባገባደደው የእግር ኳስ ፌደሬሽን የቀረቡት የ2009 የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2010 የበጀት ዓመት እቅድ በጉባኤው ጥልቅ ውይይት ቢያስፈልጋቸውም በእግር ኳሱ አስተዳደር የተንሰራፈው የስልጣን ትርምስ እና ውዝግብ  ስር የሰደደ ችግር ሆኖ ተገቢውን ትኩረት አሳጥቷቸዋ፡፡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ  ህልውና ወሳኝ የሆኑ አገራዊ፣ አህጉራዊና፣ ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን የተመለከቱ አጀንዳዎች፤ ከአስተዳደር፤ ከንግድ እና የስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ አቅጣጫዎች፤ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በስታድዬም ስርዓት አልበኝነት ዙርያ የተንሰራፉ ወቅታዊ እና አሳሳቢ ችግሮች፤ ከስፖርት መሰረተልማቶች፤ የአካዳሚዎች እንቅስቃሴን የተመለከቱ ግምገማዎችና ምክክሮች እንዲሁም የስፖርቱን የወደፊት እጣ ፋንታ እና እድገት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች እነዚህ ሰነዶችን መነሻ በማድረግ በስፋት ማወያየት ነበረባቸው፡፡   
በጉባኤዉ 2ኛ ቀን መርሃ ግብር የቀረበው  የ2010 ዓ/ም የበጀት ዓመት ዕቅድና   በቀጣይ አጀንዳ በነበረውም የተሻሻለዉ አዲስ መተዳደርያ ደንቡ ላይ  በቂ ውይይቶች አለመደረጋቸው የፌደሬሽኑ አስተዳደደር በስልጣን ሽኩቻ በከፍተኛ ደረጃ መዘናጋቱን የሚያመለክት ሆኗል፡፡  በጉባዔው አባላት  ውይይት ተደርጎበት እንዲሻሻል የቀረበው የመተዳደርያ ደንብ  ረቂቅን ለማፅደቅ ያልተቻለባቸው ምክንያቶች በናሙናነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመጀመርያ ክልሎች፤ ክለቦች፤ የከተማ መስተዳደሮች፤ ማህበራት እና ሌሎች የጉባኤው ባለድርሻ አካላት በዋዜማዎቹ ሰሞናት የተላከላቸውን ረቂቅ ደንብ  በማጥናት ለውይይት ተዘጋጅተው አልቀረቡም፡፡ የሁሉም ትኩረት በምርጫ አጀንዳዎች እና ውዝግቦች ሳይወተበተብ አልቀረም፡፡  ከአንዳንድ የጉባኤው አባላት የተሰጡት የተለያዩ አስተያየቶች እነኚህን ሁኔታዎች የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቂ ጊዜ ተሰጥቶንና ተዘጋጅተንበት ውይይት ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ፤ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በበኩላቸው ረቂቅ ደንቡ በቀጣይ በአዲስ የስራ ዘመን ለሚመረጠው ፕሬዝዳንት እና ስራ አስፈፃሚ ተሰጥቶ ቢፀድቅ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ እና ከሌሎች አስተያየቶች በኋላ   የተሻሻለዉ መተዳደርያ ደንብን የማፅደቁ ሥራ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ የሚለዉ ሃሳብ   በጉባኤው የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ወሳኙ አጀንዳ ተትቷል፡፡
የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ አጃንዳዎች ባመዘኑበት 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  የተሰራጩት የ2009 የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2010 የበጀት እቅድ ከምርጫው ባሻገር ሌላ የውይይት መድረክ እንደሚያስፈልጋቸው ለመረዳት ይቻላል፡፡  ላለፉት 4 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በመጨረሻ የስራ ዘመኑ የ2009  የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ፌዴሬሽኑ በስትራቴጂ እንዲመራ መደረጉን፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መጠናከሩን፤ የማርኬቲንግ ስራዎች መሻሻላቸውና  ከሌሎች ዓመታት የተሻለ ከፍተኛ ገቢ መሰብሰቡን፤ በርካታ ባለሙያዎች በተለይ በዳኝነት ማሰልጠኑን፤_ የታዳጊ ክልሎች ተሳትፎ እና ተፎካካሪት ማደጉን፤ በአንድ የውድድር ዘመን ከ1600 ላይ ውድድሮች መምራቱን፤ 8 ብሄራዊ ቡድኖቹ በማደራጀት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎዎች ማድረጉን እንዲሁም የድሬደዋ፣ የባህር ዳር፣ የሐዋሳ ስታድየሞች በካፍ እውቅና ማግኘታቸውን ጠንካራ ጎኖች እንደነበሩ ጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ውድድር ተሳትፎ ቢያድግም የብሔራዊ ቡድኖች በአህጉራዊና በዓም አቀፍ ደረጃ ውጤት ማጣታቸው፤ ክለቦች በአዲስ መልክ ቢመሰረቱም ነባሮች መፍረሳቸው፤ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለትን መፍታት አለመቻሉን፤ የገቢ ምንጮችን በማስፋት ከፍተኛ ሀብት አለመሰብሰቡን፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የውድድር ሜዳዎች እጥረት መኖሩን፤ ክለቦችን በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት ብዙ ርቀት ለመጓዝ ማዳገቱን እንዲሁም ለታዳጊዎች የሚሰጠው ትኩረት ማነሱን በፌደሬሽኑ የ2009 የስራ አፈፃፀም ሪፖርት የአስተዳደሩ ድክመቶችና ያጋጠሙት ችግሮች ሆነው መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
የ2009 የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ተብሎ በቀረበው ሰነድ ላይ  ፌደሬሽኑ በስልጣን ላይ ባሳለፈባቸው ያለፉት 4 ዓመታት በተዘረጉ የውድድር መርሐ ግብሮች 9 ክልሎችና 2 የከተማ መስተዳድሮችን በመወከል በዋና ዋና ሻምፒዮናዎች የሚወዳደሩ ክለቦች ብዛት 156 መሆኑ ተገልጿል፡፡ በወንዶች ፕሪሚየርሊግ 16፣ በሴቶች ፕሪሚየርሊግ 20፤ በሀ-20 ወጣቶች ፕሪሚርሊግ 12፣ በሀ-17 ታዳጊ ወጣቶች ሊግ 14  በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 32 እንዲሁም በኢትዮጵያ 1ኛ ሊግ 57 ክለቦች እየተወዳደሩ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 51 ክለቦችን በእነዚህ የፌደሬሽኑ ዋና ዋና ውድድሮች በማስመዘገብ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሲሆን ኦሮሚያ 33 ደቡብ 28፤ አማራ 16 ክለቦችን በማሳተፍ ተከታታይ ደረጃ አላቸው።
በሌላ በኩል በሪፖርቱ በ2009 ዓም መተግበር ከጀመሩ  አበረታች ጅምሮች መካከል የእድሜ ማጭበርበርን ለማስቀረት የተከናወኑ ተግባራት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ስለዚህም የእድሜ ተገቢነት እና ሌሎች የአካል ብቃት ምርመራዎች ተካሂደው ለ675 ተጫዋቾች በቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ የባር ኮድ ያለው መታወቂያ ካርድ /ቲሴራ/ መዘጋጀቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሪፖርቱ ላይ እንደቀረበው  በ2009 ዓ.ም የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ገቢ 95,962,815 ሲሆን ትልቁ ገቢ ከማርኬቲንግ እና ስፖንሰርሺፕ የተገኘው  21,986,373 ነው፡፡ ከክለቦች ለዳኝነትና ለታዛቢነት ክፍያ 26,150,507 ፤_ ከስታድዬም የትኬት ገቢ 18,889,829፤ ከፊፋ የእድገት ድጋፍ 8,455,442 ፤ ከክለቦች ምዝገባና ቅጣት 3,369,845 ፤ ከካፍና የጨዋታ ተሳትፎ  9,582 712 ፤ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ድጋፍ 6,768,213 ፤ ከኪራይ 670,790 እንዲሁም ከሌሎች 79,095 ብር  ሌሎቹ ገቢዎች ነበሩ፡፡  በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የገቢ ዝርዝር ላይ በጠቅላላ ጉባዔ፤ በአስተዳደር፤ እና በተለያዩ የስፖርት መሰረተልማቶች እኩል ውክልና ይገባናል የሚሉት ክልሎች ምንም አይነት የብር ድጋፍ አለመስጠታቸው ተጠቁሟል፡፡ፌደሬሽኑ በ2009 ያስመዘገበው የወጪ መጠን ከገቢው የሚበልጥ ሲሆን 100 683 310 ብር ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከጉባዔው ተሳታፊዎች አንዱ የፌደሬሽኑ ስራ አፈፃፀም ሪፖርት በቀረበት ወቅት የሰጡት አስተያየትም መነሳት ያለበት፡፡ እኝህ የጉባዔው አባል ላለፉት 4 ዓመታት በስልጣን ላይ የነበረው ፌደሬሽን  ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ  ከ320 ሚሊዮን ብር ብቻ ገቢ ማድረጉ በከፍተኛ ሃብት ማሰባሰብ ብዙም ስኬታማ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም የፌዴሬሽኑ የወጪ መጠን ከገቢው የሚበልጥ ሲሆን 100,683,310 ብር ነው፡፡

Read 2232 times