Saturday, 14 April 2012 12:33

ለምን ባላቶሊ ብቻ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ጥቁሩ ጣሊያናዊ ማርዮ ባላቶሊ በሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጭ በሚያደርጋቸው አወዛጋቢ ተግባራትና ሁኔታዎች የውድድር ዘመኑ አነጋጋሪ ተጨዋች ሆኗል፡፡ ማርዮ ባላቶሊ ከኤሪክ ካንቶና በኋላ የመጣ የኳስ ሜዳ ሰይጣን እንደሆነም እየተገለፀ ነው፡፡ ከ3 ዓመት በፊት በኢንተር ሚላን ሲጫወት የጁቬንትስ ደጋፊዎች‹የጣሊያን ኔግሮ ብሎ ነገር የለም›  በሚል በስታድዬም ከሰደቡት ግዜ አንስቶ የባላቶሊ ሁኔታ በርካታ አወዛጋቢ ክስተቶችን እያስተናገደ እስከ ዛሬ ቀጥሏል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ባላቶሊ የኢንተርሚላን ተጨዋች ሆኖ ባንድ ወቅት በቴሌቭዥን ባደረገው ቃለምልልስ ላይ የቀረበው የኤስሚላንን ማልያ ለብሶ ነበር፡፡ በልጅነቴ የኤሲሚላን ደጋፊ ስለነበርኩ ነው ብሎ በወቅቱ በኢንተር ደጋፊዎች ለደረሰበት ወቀሳ ይቅርታ በመጠየቅ ማስተባበያ አድርጓል፡፡ ከሶስት ሳምንት በኋላ ግን በቂ ልምምድ እንደማይሰራና በሚያሳየው የስነምግባር መጓደል ሳቢያ በሞውሪንሆ ቡድን የተጠባባቂ ወንበር እንዲያሞቅ የተፈረደበት ማርዮ ባላቶሊ በሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ኢንተር የስፔኑን ባርሴሎና አሸንፎ ዋንጫውን ሲወስድ የኢንተር ሚላን ደጋፊዎችን የሚያበሳጭ ተግባር አሳየ፡፡

በወቅቱ በሳንሲሮ የነበሩ የክለቡ ደጋፊዎችን አብሻቂ ንግግሮችን  ሲሰማ የለበሰውን የኢንተር ሚላን ማሊያ አውልቆ  ሜዳ ላይ በመጣል  የሚወቅስበትን ጥላቻ አባባሰ፡፡ በወቅቱ በኢንተር ሚላን የነበረው ኢብራሞቪች እንደተናገረው ጣሊያናዊው ማርኮ ማቴራዚ በተግባሩ ተናድዶ ባላቶሊን ሊደበድበው ሞክሯል፡፡ ከወር በኋላ እዚያው ጣሊያን ውስጥ በኮፓ ዲ ኢታሊያ ኢንተር ሚላን እና ሮማ ሲጫወቱ ልማደኛው ባላቶሊ የሮማውን አምበል ፍራንቸስኮ ቶቲ አናደደ፡፡ ቶቲ በሜዳው ውስጥ ባላቶሊን 25 ያርድ ድበማሳደ ሊደበድብው አሯሩጦ የቀይ ካርድ ሰለባም ነበር፡፡ ባላቶሊ በወቅቱ ‹አንት የማትረባ ኒግሮ ሺት› በማለት እንደተሰደበ ቢገልፅም ቶቲ ለዚህ ማረጋገጫ አልሰጠም ነበር፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎችና ሌሎች አወዛጋቢ ክስተቶች ባላቶሊን በጣሊያን ሴሪኤ እንዳይቀጥል አድርገውታል፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ ማንሲቲ ሲዛወር አወዛጋቢ የእግር ኳስ ክስተቶችና ስብዕናዎችን በሚያራግቡት የእንግሊዝ ታብሎይዶች ቤስተ ለእምቦሳ ነበር የተባለው፡፡ ስለሆነም ባላቶሊ እንግሊዝ ከገባ በኋላ አወዛጋቢነቱ እና አነጋጋሪነቱ ይባስ ተፋፍሟል፡፡

በሙሉ ስሙ ማርዮ ባርውሃ ባላቶሊ ተብሎ ይጠራል፡፡ የተወለደው በጣሊያን ፓሬልሞ ሲሆን አሁን 21 ዓመቱ ነው፡፡ ባላቶሊ በኳስ አጨዋወቱ ያለው ፍጥነትና ጉልበት፤ ጠንካራ ሹቶቹ፤ አስደናቂ የአብዶ ችሎታውና ብልህነቱ የሚለይ ሲሆን በፊት መስመር በየትኛውም የጨዋታ መስመር በውጤታማነት በመሰለፍ አድናቆት ያተረፈ ነው፡፡ በቅጣት እና በፔናሊቲ የሚገኙ የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብ በመቀየርም ከሮናልዶና ከሜሲ እኩል በሚያነፃፅር ብቃቱም ይገለፃል፡፡

የመጀመርያ ሁለት ጎሎቹን በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲቲ ዌስት ብሮምን ሲያሸንፍ  ቢያስቆጥርም ከዩሱፍ ሙላምቡ ጋር በፈጠረው ግጭት ከሜዳ ተባረረ፡፡  በቀጣይ ወር ደግሞ እሱን በልጦ በፊፋ የዓለም ምርጥ ወጣት ተጨዋች ጃክ ዊልሼርን አላውቅም ብሎ ተናገረ፡፡ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሮበርቶ ማንቺኒ ባህርይውን እንዲያሻሽል ለመጀመርያ ግዜ በይፋ ያሳሰቡት ይሄኔ ነበር፡፡ ከሳምንት በኋላ ግን ባላቶሊ አስቶንቪላ ላይ ሃትሪክ ሰራ፡፡  2011 ሲገባ ደግሞ በማንችስተር ታዳጊ ስፖርተኞች ላይ ዳርት ወርውሮ ተከሰሰ፡፡ በዩሮፓ ሊግ ጨዋታ በቀይካርድ መሰናበቱን ተከትሎ ማንቺኒ በቁጣ “ስቱፒድ” አሉት፡፡ ወር ሳይሞላ ግን ማን ሲቲ በሎሳንጀለስ ከኤልኤ ጋላክሲ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያገኘውን የግብ አጋጣሚ በተረከዝ አገባለሁ ብሎ በመሳቱ ከሜዳ ቀይረው አስወጡት፡፡ የመኖርያ ቤቱ ባኞ ውስጥ እሳት ተነስቶ የእሳት አደጋ ብርጌድ ተጠራበት፡፡ በማግስቱ በማንችስተር ደርቢ ላይ ጎል አግብቶ በደስታ ገለጻው ማልያውብን አውልቆ ‹ዋይ ኦል ዌይስ ሚ›የሚለውን ፅሁፍ አስነበበ፡፡ በወቅቱ በኦልድትራፎርድ ሁለቱ የማንችስተር ክለቦችን ባፋጠጠው የመጀመርያው ዙር የሊጉ ደርቢ ጨዋታ ላይ  ሲቲ 6ለ1  በሆነ ውጤት ዩናይትድን ካሸነፈ በኋላ ባላቶሊ በክፍት መኪናው በማንችስተር ጎዳናዎች በመዘዋወር የቀያዮቹን ሰይጣኖች ደጋፊዎች ለማብሸቅም ሞክሯል፡፡ በማን ሲቲ ከክለቡ አሰልጣኝ ሮበርቶ ማንቺኒ ጋር ብቻ ሳይሆን ከደጋፊዎቹ ጋር በተደጋጋሚ እሰጥ አገባ እየገባ አጋጥሟል፡፡ በፕሪ ሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ከተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ጋር በመጋጨት እና በሆነ ባልሆነው እየተነጫ ነጩ የሚበጠብጠው ባላቶሊ ከሲቲ የቡድን አጋሮቹም ጋር ቅጣት ምት እመታለሁ በሚል ክርክሩ በተደጋጋሚ የመጨቃጨቅ አባዜውን ሲያሳይ ሰንብቷል፡፡

በሲቲ ክለብ ውስጥ የተቀመጠውን ሰዓት እላፊ በመተላለፉ 120ሺ ፓውንድ የተቀጣው ደግሞ ከወር በፊት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ባላቶሊ በሲሲሊ ከሚታወቅ ማፍያ ጋር ይሰራል በሚል ታምቷል፡፡ ባላቶሊ ማንችስተር ሲቲ ከገባ በኋላ  5ሺ ፓውንድ ጥሬ ገንዘብ ይዞ መኪና ሲያሽከረክር ተገኝቶ ለቅጣት ተዳርጓል፡፡ በመኪና አደጋና የትራፊክ ህግ በመተላለፍ ተደጋጋሚ ጥፋቶች እያደረሰ ተይዞ ተቀጥቷል፡፡ የሴቶች እስር ቤት ያለፈቃድ ሲጎበኝ ተይዟል፤ በነዳጅ ማዳያ ቆሞ 20 ፓውንድ ለአላፊ አግዳሚው ሲሰጥም አጋጥሟል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከሩኒ ጋር ግንኙነት የታማች ሴት በፍቅር አንገብግቧል ተብሎ በእንግሊዝ ታብሎይዶች የፊትና ጀርባ ማድመቂያ ሆኗል፡፡ ባላቶሊ በቀይ ካርድ ተባርሮ በወጣባቸው ሁኔታዎች ሊጫወት የሚገባውን 8 የሲቲ ጨዋታዎች አልተሰለፍ፡፡ ከበርከታ የቡድኑ ተጨዋቾች ጋር አይሰማም ፤ ከማንሲኒ እና ከረዳቶቻቸው ጋርም ሁሌ  መቃቃሩን አልተወም፡፡ ከሲቲ ተቀናቃኝ ክለቦች ደጋፊዎች ጋር በሚፈጥረው ግብግብ ችግር ፈጣሪ ተብሏል፡፡

በውድድር ዘመኑ አራተኛውን ቀይ ካርድ አርሰናል 1ለ0 ሲቲን ባሸነፈበት ጨዋታ የወሰደው ባላቶሊ በወሳኝ ሰዓት ከሜዳ ውጭ ሆኗል፡፡ ከዚሁሀ ክስተት በኋላም ተጨዋቹ በቀጣይ የውድድር ዘመን በሲቲ መቆየቱ አጠራጣሪ መሆን ጀምሯል፡፡ በሳምንት 200ሺ ፓውንድ የሚከፈለው ማርዮ ባላቶሊ በክለቡ አሰልጣኝና ባለሃብቶች ብስጭት በጊዜ ከማንሲቲ ሊሰናበት መቻሉም እየተነገረ ነው፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች በሜዳ ላይ ከሜዳ ውጭ በመልበሻ ክፍልና በልምምድ ሜዳዎች የሚፈጥረው ረብሻ ባላቶሊ ማንችስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ካጣ ዋናው ሰበብ ይሆናል ብለዋል፡፡በ2010 ኦገስት ወር ላይ ማርዮ ባላቶሊ ለማንችስተር ሲቲ ለ5 ዓመታት ለመጫወት ፈርሞ ነበር፡፡ ከ1ዓመት ከ6 ወር በኋላ ግን ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል እየተወራ ነው፡፡ ፈላጊዎቹ የቀድሞ ክለቡ ኢንተር ሚላንና በልጅነቴ የምደግፈው ክለብ ያለው ኤሲ ሚላን ናቸው፡፡ አንዳንድ የስፖርት ተንታኞች በበኩላቸው ማርዮ ባላቶሊ ለአርሰናል ቢጫወት ብለው ተመኝተዋል፡፡

45 የማንችስተር ሲቲ ማሊያው ቁጥር

ከ2007 እስከ 2010 በኢንተርሚላን 59 ጨዋታዎች 20 ጎሎች

ከ2010 ጀምሮ በማንሲቲ 38 ጨዋታዎች 19 ጎሎች

300ሺ ፓውንድ እንግሊዝ ከገባ በተለያዩ ክሶች የተቀጣው

24 ሚሊዮን ፓውንድ ኢንተርን በመልቀቅ ማንችስተር ሲቲ የገባበት

166 የሴት ጓደኞቹ

27 በመኪናው አደጋ የደረሰበት

975 ፓውንድ በማንችስተር በ3 ሚሊዮን ፓውንድ የገዛው መኖርያ ቢኖረውም ማንችስተር ውስጥ በሚገኝ ሂልተን ሆቴል በተደጋጋሚ መኝታ እየተከራየ ያድራል፡፡

 

 

Read 5726 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 12:38