Monday, 13 November 2017 10:33

ኖታ የማይፅፈው አቀናባሪ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

 “…ትንሽ ፊት ብሰጥህ ሙዚቃውን የተጫወትኩት እኔ ነኝ” ትለኛለህ… አለ የሲንፎኒ ኖታ ፀሐፊው፡፡ የሲንፎኒ ሙዚቃ ፀሐፊው ራሱ ሞኝ ነው፡፡ ሞኝ በመሆኑ ተሳስቷል፡፡ ሙዚቃን የፈጠረው፣ እሱ በኖታ፣ ወረቀት ላይ ስለለቀለቀ መስሎታል፡፡
እኔ ግን ሙዚቃ፣ ከሙዚቃ አቀናባሪውም… ከሙዚቃ ተጫዋቹም፣ ከሙዚቃ መሳሪያውም ቀድሞ በምድር ላይ እንዳለ አውቃለሁኝ፡፡ ሙዚቃ እንዳለ ለማወቅ ሰው መሆን ብቻ ነው ያለብኝ፡፡
ጠዋት ፀሐዩዋ በመስኮቴ በኩል ስትወጣ…ቀስ ብላ ነው፡፡ እ-እ-እ-እ ዳ-ዳ-እ…
ምናልባት በኖታ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ኖታ አልተማርኩም፡፡ ግን ፀሐይ ስትወጣ የሚነዝር ሙዚቃ ይሰማኛል፡፡ አንዳንዴ በተጋደምኩበት ሆኜ በፉጨት የሚሰማኝን ዜማ ልደግመው እጥራለሁኝ። ፉጨት ትንሽ ይቀጥናል፡፡ ፀሐይ ስትወጣ በቼሎ ውፍረት ነው የምታፏጨው፡፡
ሚስቴ ከአጠገቤ ተነስታ በቁምሳጥኑ መስታወት ፀጉሯን ስታስታካክል፣ በፀሐይዋ ብርሐን ሙዚቃ ላይ በመስታወቱ ነፀብራቅ የሚታየው የእሷ ሙዚቃ ይጨመርበታል፡፡ ቼሎ እና ቫዮሊን፣ ብርሀን እና እንቅስቃሴ ሆነው አብረው ይደንሳሉ፡፡
በተኛሁበት እጄን ጭንቅላቴ ላይ አጣምሬ እመለከታታለሁ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ሚስቴ ባሌ ዳንስ ስትደንስ…ፒጃማዋን አውልቃ…ሰውነቷን ስትዳብስ…ሻውር ለመውሰድ ስታመነታ… ለመውሰድ ስትወስን…በመስታወቱ ሰረቅ አድርጋ እኔን ስትመለከተኝ… እየተመለከተችኝ በእጇ መግፋቱ እያስታወቀ መምጣት የጀመረውን ሆዷን ስትዳብስ…ሙዚቃው እንቅስቃሴ ስታቆም ዝግ ይልና፣ መንቀሳቀስ ስትጀምር እንደገና ይነሳል፡፡ በአይኔ ገብቶ አንጎሌን ያጥለቀለቃል፡፡
መታጠቢያ ቤት ከመግባቷ በፊት ተነስቼ እንድለባብስ ስታስጠነቅቀኝ…ትንሽ ሙዚቃው ላይ የከበሮ ምት ይደባለቅበታል፡፡… ከበሮው ሀላፊነትን፣ ንቃትን… አስታዋሽ ይመስላል፡፡ ሥራ - እና የመሳሰሉትን አሰልቺ ነገሮች፡፡ ግን የግድ ከቫዮሊኑና ቼሎው ጋር መዳበል አለበት፡፡ እንዲያውም ከመዳበል አልፎ መሪም ልሁን ይላል፡፡
የቁምሳጥኑን መሳቢያ እየከፈተች--- የምትለብሰውን የውስጥ ሱሪና የጡት ማስያዣ፣ ራቁቷን ሆና ስትመርጥ…በፒያኖ እና በቁምሳጥን መሀል ያለው ልዩነት ጠፋብኝ፡፡ ቁም ሳጥኑን እሷ ስትስብና ስትመልሰው…ወይም ቁምሳጥኑ ፊት ቆማ ከንፈሯን ወደ መስታወቱ አስጠግታ ስትነካካ… የፒያኖ ቁልፎችን በአዋቂ እጅ፣ ኮርዶቹን ሲጫኑ… ከሚወጣው ድምፅ ጋር አንድ ነው፡፡ ወደ ባኞ ቤት ገብታ የሻወሩ ውሀ መፍሰስ ሲጀመር… ወይም ሻወሩን ከመክፈቷ በፊት ሽንቷን ስትሸና… የፍሉት ድምፅ ነው ከሌሎቹ የቀድሞ ድምፆች ጎልቶ የሚሰማኝ፡፡ ፍሉቱ --- የቼሎውንና የቫዮሊኑን ድምፅ ከጀርባ አድርጎ ብቻውን ጎልቶ ይወጣል፡፡
የሻወሩ ሙቀት ሲሰማት… ሚኒልክ ወስናቸውና ግርማ በየነ አብረው ያቀነቀኑትን የድሮ ዘፈን ማንጎራጎር ትጀምራለች፡፡ እያንጎራጎረች  ድምፅዋ እየጎላ… ከማንጎራጎር ወደ መዝፈን ስትሻገር… የፍሉቱ ዜማም እንደ ቼሎው የፀሐይ ብርሐን- እና ቫዮሊኑ… የሚስቴ እንቅስቃሴ ከኋላ ተከታይ ይሆናል፡፡ የእሷ ድምፅ፤ ድል አድራጊ ሆኖ ይወጣል፡፡ የሻወሩን ውሃ ዘግታ ስትታሽ --- ዜማዋ…. በአስተሻሸቷ --- ታንቡሪን- ክሽክሽታ እየተዋዘ ይቆራረጣል፡፡
ሻወር ከመግባቷ በፊት “ስወጣ ተነስተህ ካላገኘሁህ!” ብላ ያስጠነቀቀችኝን ረስቻለሁ፡፡ በሙዚቃው ተሸንፌአለሁ፡፡ ግድግዳ ላይ ያለው ሰአት ቅድም መስማት ያልፈለግሁት የከበሮ ምትን ሆኖ--- ጥቅሉን የሲንፎኒ ሙዚቃ ይመራዋል፡፡… ፒያኖው ከፋፍታ ትታው የሄደችው ቁምሳጥን ነው፡፡ ሳሳ ያለ ራፕሶዲ መጫወቱን ቀጥሏል፡፡ እሷ እየታጠበች ከምታንጎራጉረው የዜማ ቅኝት ሳይወጣ። በተከፈተው ቁምሳጥን የተጣጠፉት ልብሶቿ ይታዩኛል፡፡ ሁሉንም ልብሶቿን አውቃቸዋለሁ። አንዳንዶቹ ስንተዋወቅ ጀምሮ የነበሩ፣ ሌሎቹ በሂደት የመጡ ናቸው፡፡ … ከእያንዳንዱ አልባሳቷ ጋር የተያያዙ ትዝታዎች አሉ፡፡
...ያኔ እሷን በጣም አሟት የነበረ ሰሞን ያደረገችው ቲ-ሸርት ጫፉ ይታየኛል፡፡ ሙዚቃው ወደ አሳዛኝ የእንባ ወንዝ ዳርቻ ለማምራት የቲ-ሸርቱን ጫፍ ይዞ ሸመጠጠ - በግርግዳው ላይ ባለው ሰዓት መቁጠሪያ ትርታ ታጅቦ፡፡ ልቡ በሙዚቃው ስልምልም ሲል ሌላ የልብስ ጫፍ ደግሞ መለሰኝ። … ይሄ ዋናው የሙዚቃ “ኮዳ” ነው፡፡ በየዕለቱ ከማዳምጠው የተለያየ ሙዚቃ ጨመቅ የሚገኘው ጭብጥ፣ በዚህ እራፊ ጨርቅ ሊመለስ ይችላል፡፡ የምወዳቸውን ነገሮች ሁሉ ትዝታና የምመኛቸውን ሁሉ ነገሮች ተስፋ፣ በዚህ የሙዚቃው ነፍስ ውስጥ ተካተዋል፡፡ የምሰማው ሙዚቃ ሁሉ ሞቲፍ --- ይሄንን ጨርቅ ይወክላል፡፡ እኔ … እሷም ሆነ እሷ ሆድ ውስጥ ያለው ሽል … ህይወት በአጠቃላይ ይሄንን የእሷን ነጠላ ይመስሉኛል፡፡ ይሄንን ጨርቅ አድርጋ ነው የተዋወቅኋት፡፡ እሷን ሳስብ… ይሄንን ነጠላ አድርጋ በእምሮዬ ያነሳሁት ምስል ነው ትዝ የሚለኝ፡፡ የህይወቴ ሙዚቃ አዝማቹ እሷ ከሆነች… ይሄ ጨርቅ ደግሞ ህይወቴ ላይ የሚታየኝን ተስፋ እንደ ሰንደቅ አላማ ይወክላል፡፡
ከተጋደምኩበት ተነሳሁኝ፡፡ አሁን ፀሐይዋ ሙዚቃዋን ወደ ማጠናቀቅ ደርሳለች፡፡ እሷም ሻወሩ መድረክ ላይ የምታቀርበውን ዜማ ጨርሳለች፡፡ ተነስቼ የተከፈተውን መሳቢያ ዘጋሁት፡፡ የፒያኖው ሙዚቃ አለቀ፡፡ አሁን የሰዓቱ ከበሮ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ከከበሮው ምት ጋር እያቀናበርኩኝ… መስቀያ ላይ ትላንት አሰናድቼ የተኛሁትን ሱፍ ለበስኩኝ፡፡
አሁን ከበሮው ብቻ ነው እየደለቀ ያለው፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ የወንድሜ መኪና ይመጣል። እሷና እኔ ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን፡፡ ዛሬ ቀለበት የማደርግበት ቀን ነው፡፡ እኔ እና እሷ የምንፈራረምበት ቀን፡፡ አልነሳም ብላ አስባ እንደሆነ  አይታወቅም፡፡ ቡናውን ምድጃ ላይ ጥዳዋለች… ሲገነፍል የከበሮው ምት ወደ አስፈሪ ታንቡር ተቀየረ፡፡ ቡናውን በቁሜ ቀድቼ ስጠጣ - ሌላ ሙዚቃ ጀመረ፡፡ የሚያረጋጋ ሙዚቃ፡፡ … ቡናውን ፉት እያልኩ ስጎትት… ቫዮሊኑ በክሮቹ ላይ ደጋኑን ወስዶ ይመልሳል፡፡
ከሻወር እንደወጣች ትንሽ ተጨቃጨቅን፡፡ እንደ ራፕ ሙዚቃ በመሰለ አኳሃን፡፡ .. ጭቅጭቃችን ከጭንቀታችን የመነጨ ነው፡፡ ሁለታችንም ምን እንደሚከሰት አናውቅም፡፡ አንዱ እንደሚያውቅ… ሌላው እንዳጠፋ --- ለመወንጀል ትንሽ ራፕ አደረግን፡፡
ሳሎን ቤቱ ውስጥ ሆኜ ቴሌቪዥን ከፈትኩት። ገና ከመከፈቱ ያወጣው ኳኳታና የፖለቲካና የአሰቃቂ ዜና እሩምታ… ካሰርኩት ክራባት ጋር ተጣምሮ አነቀኝ፡፡ ላቤን አመጣብኝ፡፡ ከእሷ ጋር መኖር ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም እቃ በመሰረቱ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ነው የሚመስለኝ … ከዚህ ቴሌቪዥን በስተቀር፡፡ … ስልኩ ሲጠራ… ስልኩም ሙዚቃዬንና ሰላሜን ገዳይ መሆኑ በተጨማሪ ትዝ አለኝ፡፡ … “ስልክ፣. ቴሌቪዥንና ሰዓት - የሙዚቀኝነት አቅሜን ለመረበሽ የተሰሩ ፈጠራዎች ናቸው” … ብዬ ስልኩን አነሳሁት፡፡ እናቴ ናት .. መዘጋጀታችንን ለማወቅ ፈልጋ ነው። ሳሎን ቤት ሆኜ ሚስቴ ትታየኛለች፡፡ በመኝታ ቤቱ መስኮት ከሚገባው ብርሐን ጋር የአበሻ ቀሚሷን አጥልቃ … ጉሮሮዬ ላይ ሳግ መጣብኝ፡፡ ያለቀ የመሰለኝ ሙዚቃ፤ እንደ አዲስ ዞሮ ተመልሶ መጣና ተከለበሰብኝ፡፡ … እሷ ለባብሳ እስክትጨርስ የነካነው እቃ ሁሉ የተለያየ ዜማ እየፈጠረ… በሲቃ ተሞልቼ፣ እንባዬ እስኪፈስ .. የተቀናበረውን ሲንፎኒ አጣጣምኩኝ፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ በወንድሜ መኪና፣ እሷና እኔ ተጭነን፣ የቀጠሮው ቦታ እስክንደርስ፣ ሙዚቃ ማቀናበሬን አላቆምኩም ነበር፡፡ ከዚህች ልጅ ጋር እስከኖርኩኝ ድረስ ብቻ አቀናባሪ ሆኜ፣ እስከ ዕለተ ሞቴ የምቆይ ይመስለኛል፡፡ 

Read 2688 times