Monday, 13 November 2017 13:32

የሰከሩ፣ “የአረንጓዴ ልማት እቅዶች”!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(14 votes)

 1 የሰከረ የአረንጓዴ ልማት እቅድ ቁ1።
   .መንግስት ኤሌክትሪክ ለመግዛት፣ ለአውሮፓ ኩባንያ 500 ሚ. ዶላር ይከፍላል። ውል አዘጋጅቷል።
   .ከዚያስ? በ400 ሚሊዮን ዶላር ለነሱዳን ለነኬንያ ይሸጣል። ወደ ተግባር እየተለወጠ ያለ እቅድ ነው።
   .(1000 “GWH” የኤሌክትሪክ ሃይል በ75 ሚ.ዶላር ሂሳብ ገዝቶ፣ በ60 ሚ.ዶላር መሸጥ ማለት ነው!)።
2 የሰከረ  የአረንጓዴ ልማት እቅድ ቁ2።
   .21 ሚሊዮን በሬዎችን መቀነስ! ላሞችም ይቀነሳሉ። ለምን? እበት የዓለምን ዓየር ይበክላል!
   .ከአገራችን የገበሬ ቤተሰቦች መካከል ግማሾቹ፣ አንድም በሬ የላቸውም።
   .ከ9 ሚሊዮን በላይ የገበሬ ቤተሰቦች፣ በሬ የላቸውም!
3 የሰከረ  የአረንጓዴ ልማት እቅድ ቁ3።
   .የቤት መኪናና ታክሲዎችን መቀነስ! የኤሌክትሪክ መኪኖችን መጠቀም! ወጪው ግን እጥፍ ነው።
   .እኮ ለምን? የዓለምን ሙቀት ለማቀዝቀዝ! የቤት መኪኖችና ታክሲዎች ዓየርን ይበክላሉ! ተብሏል።
   .ባጠቃላይ፣... የአቃቤ ህግ የሙስና ክሶች፣ ከአረንጓዴ ልማት ቅሌቶች ጋር ሲነፃፀሩ፣ ተራ ክሶች ናቸው።
. እንደ ጀስቲን ቢበርና እንደ ዲካፕሪዮ ልንሆን ነው?
የኢትዮጵያ ወገኛ ቢሮክራቶች፣ደካማ የኤሌክትሪክ መኪኖችን፣ “በእጥፍ ወጪ” ለማስመጣት እቅድ ይዘዋል? አየ ወግ!
ሚሊዮነር የአለማችን ዘፋኞችና አክተሮች፣ እነ ጀስቲን ቢበርና ዲካፕሪዮ... ወገኛ ቢሆኑ የራሳቸው ጉዳይ ነው። 7ሺ ባትሪዎች የተገጠመለት፣ ግን በደንብ የማይሰራ የኤሌክትሪክ መኪና ይግዙ - 80 ሺ ዶላር! በራሳቸው ገንዘብ ነው የሚቀልዱት።
በእርግጥ ወጪያቸው ይሄ ብቻ አያበቃም። ባትሪ መለወጥ የዋዛ ጣጣ አይደለም።
“ርካሿ” የ32ሺ ዶላር የኤሌክትሪክ መኪና እንኳ፤ የ6ሺ ዶላር ባትሪ ያስፈልጋታል። የነዲካፕሪዮ መኪናማ፣... ቢያንስ ቢያንስ የ21ሺ ዶላር ባትሪ ያስፈልጋታል። በየእለቱ ለ8 ሰዓታት ቻርጅ የሚደረግ ባትሪ ማለት ነው። ታዲያ፣ ቻርጀሩም ራሱ ውድ ነው - እንደ አይነቱ ከ500 ዶላር እስከ 20 ሺ ዶላር ይፈጃል። በዚያ ላይ፣ የባትሪ ነገር፣... በሞባይል ታውቁታላችሁ። የመኪና ባትሪም፣ የተለየ አይደለም። ሺ ባትሪዎችን የመጠቀም ጉዳይ
ስለሆነ፣ ወጪዎቹና ችግሮቹም ሺ ናቸው። ለዚህም ነው፤ ባትሪ ከመግዛት ይልቅ መከራየት የተጀመረው። ኪራዩ፣ በወር ሲሰላ፣ ከ100 ዶላር እስከ 500 ዶላር ነው። ታዲያ ለቤት መኪና ከሆነ ነው እንጂ፣ ብዙ ኪሎሜትር ለሚጓዙ መኪኖች...
ለምሳሌ ለታክሲ ከሆነ... የባትሪ ኪራይ ይጨምራል። ምናለፋችሁ፣ የባትሪ ኪራይ፣ ከነዳጅ ወጪ ይብሳል። ስለዚህ፣ “የኤሌክትሪክ መኪና በመግዛት የነዳጅ ወጪን መቀነስ” የሚለውን የወገኞች ስብከት እርሱት። ባትሪ ለመቀየር የባሰ ወጪ
ያስፈልጋልና። ለዚያውም የዶላር ወጪ!
በአጭሩ፣ በአማካይ በ10 ሺ ዶላር ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ የቤት መኪኖችን፣ 30ሺ ዶላር በሚፈጁ ደካማና አስቸጋሪ
የኤሌክትሪክ መኪኖች ለመተካት ነው የታቀደው። አሁን ይሄ ምን የሚሉት እቅድ ነው?
የሰከረ እቅድ ነው - የድሃ አገር ሃብትን በከንቱ የሚያባክን እቅድ!
. ገበሬ፣ በሬ ባጣበት አገር፣ በሬ የመቀነስ እቅድ!
ከዋና ዋናዎቹ “የአረንጓዴ ልማት እቅዶች” መካከል ትልቁ፤ የከብቶችን ቁጥር ለመቀነስ የወጣው እቅድ ነው። ለዚህም ነው፣

በሰነድ ተዘርዝረው የቀረቡት። ማለትም...   
ሀ. 7 ሚሊዮን በሬዎችን በእጅ መሳሪያ መተካት! 4 ሚሊዮን በሬዎችን በማሽን መቀየር!
ለ. በከብት አርቢዎች አካባቢ፣ መኖ በማሻሻል 4 ሚሊዮን ከብቶችን መቀነስ!
ሐ. 14 ሚሊዮን ላሞችን መቀነስ!
መ. “17 ሚሊዮን ከብቶችን መቀነስና በዶሮ መተካት”።
... እነዚህ እቅዶች፣ ቃል በቃል “የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ” የተሰኘው ዝነኛ ሰነድ ውስጥ የሰፈሩ አባባሎችና መረጃዎች ናቸው።
ግን ለምን? ማሽኖችንና መሳሪያዎችን መጨመር እየተቻለ፣ በሬዎችን መቀነስ ያስፈለገው ለምንድነው?
ለሌላ ምክንያት አይደለም። “እበት የዓየርን ይበክላል! የከብቶች እበትና ከሆዳቸው የሚወጣ ጋዝ፣ ለዓለም ሙቀት መጥፎ
ነው” ሲሉ ፅፈዋል የአገራችን ወገኞች። ያወጡት እቅድም፣ የከብቶችን ቁጥር በግማሽ ለመቀነስ ያለመ እንደሆነ በዝርዝር
ገልፀዋል።
ያኔ፣ የወገኞቹ እቅድ የወጣ ጊዜ...
በሬ የሌላቸው የአገራችን ገበሬዎች ስንት ነበሩ?
5 ሚሊዮን!
ዛሬ ከ7 ዓመት በኋላ...
በሬ ያጡ ገበሬዎች ስንት ናቸው?
9 ሚሊዮን!
በሌላ አነጋገር፣ ከአገራችን ገበሬዎች መካከል፣ ግማሾቹ አንድ እንኳ በሬ የላቸውም!
እንዴት ነው ነገሩ? እና የመንግስት ኤክስፐርቶች ምንድነው የሚያወሩትና የሚያቅዱት? ምንድነው አላማቸው? “ካርቦን
ልቀት”... ምናምን እያሉ የሚያነበንቡትስ ለምንድነው?
. የ“ካርቦን ልቀት” ወገኞች፣ በርካታ ፋብሪካዎችን ዘግተዋል።
ባለፈው ሳምንት የአለም ባንክ ያሰራጨውና በሰፊው ሲዘገብ የሰነበተውን አዲስ መረጃ ተመልከቱ - ከማነፃፀሪያው።
በዓመት የሚመነጨው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ (ሲኦ2) መቀነስ አለበት በሚል መፈክር፣ ለ30 ዓመታት የእሪታ ዘመቻ
ቢካሄድም፣ አልቀነሰም። እንዲያውም፣ በእጥፍ ጨምሯል።
በዓመት የመነጨው ሲኦ2፣  በአዲሱ መረጃ እንደተገለፀው፣ 36138 ሜትሪክቶን ሆኗል።
ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ስንት እንደሆነ ገምቱ። 12 ብቻ!
(የድሃ ድሃ የሆነ አገር ብዙ ነዳጅ መጠቀም አይችልም። ብዙ መኪኖች የሉም። በዙ ፋብሪካዎች የሉም)።    የኢትዮጵያ ድርሻ፣ ወደ “0”፣ ወደ ባዶ ቢቀንስ፣ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚያመጣው ቅንጣት ለውጥ የለም።
(የዓለም የሲኦ2 ጋዝ፣ 36126 ቢሆን አልያም 36138 ቢሆን ለውጥ የለውም።)
የኢትዮጵያ ድርሻ፣ በአንዳች ተዓምረኛ የኢኮኖሚ እድገት አማካኝነት፣ በአምስት እጥፍ ቢጨምርስ?  ይሄኛውም ለውጥ
አያመጣም።
ኢትዮጵያውያን፣ “መኪና እንዳትጠቀሙ” ተብለው ወደባሰ ኋላቀርነት ቢመለሱ፤ የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ
እንደሚያደርገው፣ “ፋብሪካዎች ይዘጉ” ቢባልና ኢትዮጵያውያን ወደ ባሰ የስራ አጥነትና የድህነት ትርምስ ቢዘቅጡ፣...
“የከብቶች እበት የዓለም አየርን ይበክላል፤ ይወብቃል” ተብሎም፣... ከነአካቴው፣ ኋላቀሩ የበሬ እርሻ ወደ ባሰ የመኮትኮቻ
እርሻ... ከሳር ጎጆ፣ ወደ ባሰ የዋሻ ኑሮ፣ ችግርና ከተደጋጋሚ ረሃብ ወደ ባሰ የረሃብ እልቂት፣...
ከዚያም አልፎ፣... “ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንዳትተነፍሱ” ተብለው ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ ከምድረገፅ እንዲጠፉ
ቢፈረድባቸው፣... ያኔ ዓለማችን ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ነፃ ብትሆን፣ ትርጉሙ ምንድነው? በካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ላይ
ምንም ለውጥ የማያመጣ ሲሆን ደግሞ አስቡት።
የ1000 ዓመታት የኢትዮጵያ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ድርሻ ቢደመር፣ ከቻይና የአንድ ዓመት የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ጋር
እኩል ነው።
ቻይና ውስጥ ጥፋት እየተሰራ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም በተቃራኒው፣... ስራ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፋብሪካ፣ መኪና
መበራከቱ መልካም ነው። የኢኮኖሚ እድገትና የተሻሻለ ኑሮ.... መልካም ስኬት እንጂ በጭራሽ እንደ ጥፋት ሊታይ
አይገባውም ነበር።
ወገኞቹ የኢትዮጵያ በርላታ ባለስልጣናትና በርካታ ምሁራን ግን፣ “ሲሉ ሰምታ ታንቃ ሞተች” እንደሚባለው፣ “የካርቦን
ልቀት፣ የዓለም ወበቅ፣... የአየር ፀባይ ለውጥ፣ የምድር ዋልታዎች በረዶ መቅለጥ... እያሉ እንደ ድግምት እየለፈፉ፣ ይቅርታ
የማይደረግለት ጥፋትና ክፉ ሃጥያት ይሰራሉ።
በድሃ አገር ውስጥ፣ ፋብሪካዎችን መዝጋት ምን ማለት ነው? ይሄ፣ “በሃሳብ ደረጃ” የተነገረ አይደለም። በአዲስ አበባ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ፣ ከ12 በላይ ፋብሪካዎች እንዲዘጉ ተደርገዋል፤ ግንባታቸው ታግዷል።
በድሃ አገር ውስጥ፣ በ10 ቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ሃብትን፣... በከንቱ ማጥፋትና ማባከንስ ምን ማለት ነው? ይሄም “በሃሳብ ደረጃ” ላይ ብቻ የሚገኝ ክፉ ምኞት አይደለም።
. የ10 ቢሊዮን ሃብትን እንደዘበት የሚጠፋ ብክነት ላይ፣... የባሰም መጣ!
“የአካባቢ ጥበቃ”፣ “የካርቦን ልቀት”... ምናምን እየተባለ፣ እስካሁን ለነፋስ ተርባይኖች የወጣው 770 ሚሊዮን ዶላር፣ አንዱ
የብክነት ምሳሌ ነው። በዛሬ ምንዛሬ፣ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው።
ይህንን ወጪ እስካሁን ከተገነቡት የሃይል ማመንጫ ግድቦች ወይም ከአዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ጋር አነፃፅሩት። ለምሳሌ፣
ከጨሞጋ 1 ጋር።
ጨሞጋ1 የሃይል ማመንጫ ግድብ፣ በ270 ሚ.ዶላር ወጪ የሚገነባ ተቋም ነው። የሚያመነጨው የሃይል መጠን ግን፣ እስከዛሬ ከተተከሉት የነፋስ ተርባይኖች ድምር ሁሉ ይበልጣል። በጣም ይበልጣል። ለነፋስ ተርባይኖቹ የወጣው ወጪ ግን፣
770 ሚ. ዶላር ነው። ማለትም፣... በ500 ሚ.ዶላር ይበልጣል። በዛሬው ምንዛሬ፣ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በከንቱ ባክኗል ማለት ነው።
እንዲባክን የተደረገው፣ በተራ ስህተት አይደለም።
ከ20 ቢሊዮን ብር ውስጥ 13 ቢሊዮን ብር እንደዘበት እንዲጠፋ የተደረገው፣ ባለማወቅ አይደለም።
ይሄ የነፋስ ተርባይኖች ቅሌትስ ምን ይባላል? አሁን ደግሞ የባሰ መጥቷል።
. የአቃቤ ህግ የሙስና ክሶችና “የነፋስ ተርባይን፣ የእንፋሎት ሃይል” ቅሌት  
እስከዛሬ ያየናቸው የአቃቤ ህግ የሙስና ክሶች፣ ከአረንጓዴ ልማት ቅሌት ጋር ሲነፃፀሩ፣ ተራ ክሶች ናቸው።
“ብድር ተመልሷል፤... ግን የተመሰው ዘግይቶ ነው” የሚል ክስ፤ “ግንባታው ተካሂዷል፤... አገልግሎትም እየሰጠ ነው፤... ግን ያለ በቂ ጥናት የተካሄደ ግንባታ ነው” የሚል ክስ... እነዚህ ሁሉ ክሶች፣... እውነት መሆናቸው ከተረጋገጠ፣ ተገቢ ክሶች ሊሆኑ ይችላሉ።
በከንቱ ከጠፋው 13 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀሩ ግን፣ የእስከዛሬዎቹ ክሶች፣ ቀላል የህፃናት ስህተቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው ማለት ይቻላል።
ይህ ያነሰ ይመስል፤... መንግስት ከውጭ ኩባንያዎች፣ የኤሌክትሪክ ሃይልን በዶላር በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት እየተዋዋለ ነው...
እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ። አንደኛው ውል፣ ኮርቤቲ የእንፋሎት ሃይል ፕሮጀክትን የሚመለከት ነው። ሁለተኛው ውል ደግሞ፣ ገና በጨረታ ከተሰጠ ወር ያልሞላው የመተሐራ የፀሃይ ሃይል ፕሮጀክትን የሚመለከት ነው።
እነዚሁ የቅሌት ውሎች፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ከፀደቁ፣... የፌደራል አቃቤ ህግም “ይሁን” ብሎ ከተስማማ፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ኤሌክትሪክ በየዓመቱ የመግዛትና ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የመክፈል ግዴታ ውስጥ ይገባል። በየዓመቱ እንደሆነ አትርሱ።
“ምናልባት ብክነት ላይሆን ይችላል። ኤሌክትሪክ ገዝቶ፣ ወደ ኬንያ ወደ ጂቡቲና ወደ ሱዳን ኤክስፖርት በማድረግ ለማትረፍ አስቦ ሊሆን ይችላል” ብላችሁ ትገምቱ ይሆናል።
እዚህ በዶላር ገዝቶ፣ ወደ ውጭ በዶላር ለመሸጥና ለማትረፍ?
ግምታችሁ ስህተት ነው። በስንት ዋጋ ለመግዛት እንደሚዋዋልና በስንት ዋጋ ለመሸጥ እንደተዋዋለ ተመልከቱ።
1000 “GWH” የተሰኘ የኤልክትሪክ ሃይል በመሸጥ፣ 60 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ይችላል መንግስት። ለዚህም የአራት ተከታታይ ዓመታት መረጃዎችን ከብሄራዊ ባንክ የየዓመቱ ሪፖርት ማረጋገጥ ትችላላችሁ።
በ60 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ፣ በስንት ዋጋ መግዛት አለበት። ባነሰ ዋጋ መሆን አልነበረበትም?
ግን አይደለም።
በ75 ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ነው የተዋዋለው። ለአውሮፓ ኩባንያ፣ 75 ሚ. ዶላር በመስጠት፣1000“GWH” ኤሌክትሪክ ለመግዛት!
ከዚያስ? በ60 ሚሊዮን ዶላር ለነሱዳን ለነኬንያ ይሸጣል።
ይሄ እቅድ፣ የለየለት ስካር ነው ብትሉ፤ አዎ ስካር ነው።
ግን በሚስጥር የተያዘ ድብቅ ስካር አይደለም። በተደጋጋሚ በይፋ የተገለፀ የስካር እቅድ ነው።
ይሄው ነው እውነታው። ቅንጣት ስህተት የሌለው፣ እውነተኛ መረጃ።
ለምንድነው ታዲያ፣ ዝም ዝም የተባለው?
እንደተለመደው፤ ነገርዬው እስኪስፋፋ ድረስ ነው? ኪሳራውና ብክነቱ፣ ጥፋቱና ወንጀሉ ተባብሶ፣ አገር ምድሩ በውድቀት
እስኪተራመስ ድረስ ዝም-ዝም ማለት በአገራችን የተለመደ ነው።
ከሁለት ከሦስት ዓመት በኋላ፣... ነገሩ ሁሉ በውድቀት ትርምስ ሲቃወስ፣... ድንገተኛ ዱብዳ የወረደባቸው ይመስል፣ ከዳር ዳር እሪታ ይበራከታል። ጣት መቀሳሰል፣ መወነጃጀል፣ “ሙስናና ዝርፊያ” እያሉ መጯጯህ ይመጣል።

Read 4154 times