Saturday, 18 November 2017 12:34

ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያምን ጨምሮ 5 ባለስልጣናት ለምስክርነት ፍ/ቤት ይቀርባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(23 votes)

  የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው እንዲሁም አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳም ይመሰክራሉ

    በእነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ ጉዳይ ለመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 5 ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት፣ ከታህሳስ 17 እስከ 19 ቀን 2010 ዓ.ም በፍ/ቤት ተገኝተው ምስክርነት እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተላልፏል።   ጉዳዩን የሚመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ባለፈው ነሐሴ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ለመከላከያ ምስክርነት የተፈለጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ ምክትላቸው ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳና የለገጣፎ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ ከጥቅምት 27 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ለምስክርነት የሚፈለጉት ባለስልጣናት በዕለቱ ሳይገኙ የቀሩ ሲሆን ፍ/ቤቱም ምስክሮቹ ያልተገኙት መጥሪያ ስላልደረሳቸው በመሆኑ፣ በቀጣይ መጥሪያው እንዲደርሳቸው ተደርጎ በቀጠሮአቸው መሰረት ቀርበው እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚህ የምስክርነት ሂደት የዕድሜ ልክ ፍርደኛው አቶ አንዷለም አራጌም መካተታቸው ታውቋል፡፡
የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፤በተከሰሱበት የወንጀል ህግ መሰረት መከላከያ ምስክሮቻቸው የሚደመጡ ሲሆን የመዝገቡ ተጠሪና የኦፌኮ አመራር አቶ ጉርሜሳ አያኖን ጨምሮ ቀሪዎቹ 16 ተከሳሾች በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል የሚከላከሉ ይሆናል፡፡

Read 6293 times