Sunday, 19 November 2017 00:00

ህወሓት ስብሰባውን መቋጨት ባለመቻሉ ለ3ኛ ጊዜ አራዘመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

አዳዲስ አመራሮች ይመረጣሉ ተብሏል

    የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሠሞኑን በመቐሌ ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ መቋጨት ባለመቻሉ ለ3ኛ ጊዜ ያራዘመ ሲሆን በቀጣይ በሚያደርገው የሂስና ግለሂስ ግምገማ ማጠቃለያ ላይ አዳዲስ አመራሮችን እንደሚመርጥ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ያለበትን ድክመትና ጥንካሬውን በዝርዝር መፈተሹንና መገምገሙን የሚጠቁመው ትናንት የወጣው የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፤ በፓርቲው ነባር ታጋዮች እና አሁን በአመራር ላይ ባሉት መካከል የመመካከርና የመነጋገር ችግር መኖሩን መገምገሙን ጠቁሟል፡፡
በአመራሩ መካከልም በመተጋገል ላይ የተመሠረተ የጠበቀ አንድነት እንደሌለ መገምገሙን የጠቆመው የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ፤ በጎራ የመጠላለፍና አድፍጦ የመሻኮት ፀረ ዲሞክራሲያዊ አስተሣሠብና ተግባር እንዲሁም በማጥቃትና በመከላከል ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መስተዋሉን አስታወቋል፡፡
የአዲሱን ትውልድ ወጣቶችና ምሁራን አቅም አለመገንባት፣ አለማሣተፍና ተጠቃሚ አለማድረግ መታየቱን የገመገመው ማዕከላዊው ኮሚቴው፤ ከእህት የትግል አጋር ድርጅቶቹ ጋር ያለው ግንኙነት ላይም ጉድለቶች ነበሩ ብሏል፡፡ በዚህ ምክንያትም የትምክህትና ጠባብነት ጎራዎች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ መጣላቸውንና ለዚህም በተዘዋዋሪ የድርጅቱ አመራር ድርሻ እንደነበረው ገምግሟል፡፡  
ባለፉት ጊዜያት በትግራይ በገጠርና በከተማ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች እንዳሉ አይካድም ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው፤ ልማቱን ቀጣይነት ያለው በማድረግና የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችን በማሳካት፣ ህዝብን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ድክመቶች መታየቸውን ጠቁሟል፡፡
አሁንም የሂስና ግለሂስ ግምገማውን አለማጠናቀቁን የጠቆመው የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ፤ በሚቀጥለው ሣምንት በሚያደርገው የማጠናቀቂያ ስብሰባ አዳዲስ የአመራር ምደባና ሽግሽግ በማድረግ በተዘረዘሩ ችግሮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ አቅጣጫዎችን በመተለም፣ ድርጅቱ ክልላዊና ሃገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅም ፈጥሮ እንደሚወጣ ይጠበቃል ብሏል፡፡
የስብሰባው ተሣታፊዎች በሶስት የሃሣብ ጎራ ተከፍለው ግመገማ ማካሄዳቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ አንደኛው ወገን አሁን ያለው የድርጅቱ የፖለቲካ አመራር በቂ ነው ብሎ የሚያምን፣ ሁለተኛው ድርጅቱ ደካማም ጠንካራም ስራ ሰርቷል፤ እየሠራም ነው የሚልና በሶስተኛነት የተሠለፉት የፖለቲካ አካሄዱ መልካም ባለመሆኑ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከባድ ሂስና ግለ ሂስ በተደረገበት ወቅትም የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እና የቀድሞ የኢቢሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ስብሠባውን አቋርጠው መውጣታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

Read 9569 times