Sunday, 19 November 2017 00:00

በዝዋይ በተከሰተ ግጭት ህይወት ጠፍቷል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(23 votes)

በዝዋይ ከተማ የግለሰቦችን ጠብ ተከትሎ፣ ወደ ብሄር ባመራ ግጭት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን ከ480 በላይ የሚሆኑ የወላይታ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በበኩሉ፤ ጉዳዩ በህግ እንዲጣራና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡
ባለፈው ሰኞ ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም በአንድ የኦሮሞ ተወላጅና በአንድ የዎላይታ ተወላጅ መካከል ከተፈጠረ አለመግባባት ጋር በተገናኘ በተከሰተው ፀብ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የሰው ህይወት መጥፋቱን በርካቶችም ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን የገለፀው ፓርቲው፤ ፀቡ ፈፅሞ በኦሮሞ ህዝብና በዎላይታ ህዝብ መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ወንድማማችነትና አብሮ የመኖር ታሪክ የማይወክል ነው ብሏል፡፡
በግጭቱ የተፈናቀሉ ከ480 በላይ የሚሆኑ የዎላይታ ተወላጆችን በወላይታ ሶዶ ከተማ ተቀብለው ካስተናገዱ ግለሰቦች መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ግለሰብ፤ ሐሙስ እለት በግጭቱ ሞተዋል የተባሉ የ3 ሰዎች አስክሬን ሲቀበር መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ50 በላይ በሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ የገቡ ተፈናቃዮችም በከተማዋ በሚገኝ የወጣቶች ማዕከል ተጠልለው እንደሚገኙና የአካባቢው ህዝብ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት ምንጮች፤ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ትናንት አርብ በጉዳዩ ላይ ከኦሮሞ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ጋር ለመምከር ወደ አዳማ ማምራታቸውን ተናግረዋል፡፡
የግለሰብ ፀብን የህዝብ ፀብ በማስመሰል ወደ ብሄር ግጭት ለመለወጥ የሚደረግ ሙከራን እንደሚያወግዝ ያስታወቀው የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በበኩሉ፤ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀው ወንድማዊ አንድነት በዚህና በመሳሰሉ ደካማ ምክንያቶች እንዳይሸራረፍ፣ ሁለቱም ህዝቦች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

Read 8238 times