Sunday, 19 November 2017 00:00

የሙጋቤ ከሥልጣን መውረድ ኮ/ል መንግስቱን አያሰጋቸውም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(29 votes)

   ዚምባቡዌን ላለፉት 40 ዓመታት ገደማ የመሩት የ93 ዓመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ሰሞኑን በአገሪቱ ወታደራዊ ሃይል ከሥልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ፣ በዚምባቡዌ ለ26 ዓመታት በጥገኝነት የኖሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ዕጣ ፈንታ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የዚምባቡዌ ወታደራዊ ሃይል በሙጋቤ ላይ የወሰደውን እርምጃ “መፈንቅለ መንግስት አይደለም” በማለት ያስተባበለ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ፤ መፈንቅለ መንግስቱን በፅኑ እንደሚያወግዝ በመጠቆም፣ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ውይይት ተደርጎ፣ ለውጥረቱ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲበጅ ወታደራዊ ሃይሉን አሳስቧል፡፡
ሙጋቤ ከሥልጣን መገለላቸውን ተከትሎ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩትና በሌሉበት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም ቤተሰቦችን አግኝተን አነጋግረናል ያሉ የመረጃ ምንጮች፤ ኮሎኔሉ “በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙና መፈንቅለ መንግስቱም ለህልውናቸው እንደማያሰጋቸው” መረዳት እንደቻሉ አስታውቀዋል፡፡    
በመፈንቅለ መንግስቱ ላይ ከተሳተፉት ወታደራዊ ክንፍ አባላት ጋርም ኮሎኔሉ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ከመረጃ ምንጮቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሮበርት ሙጋቤ በአሁኑ ወቅት በቁም እስር ላይ የሚገኙ  ሲሆን  ቀጣይ የሃገሪቱ መሪ እንደሚሆኑ ሲጠበቁ የነበሩት ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ፣ ከአገሪቱ ሸሽተው እንደወጡ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዚምባቡዌ ወታደራዊ ሃይል፤ “ዓላማዬ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ አይደለም፤ ሮበርት ሙጋቤን ተከልለው አገሪቷን ሲቦጠቡጡ የኖሩ ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ ነው” ሲል የቆየ ቢሆንም ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን ማንሳቱን ይፋ አደርጓል፡፡
“ጉዳዩ አሳስቦኛል” ያሉት የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሙሣ ፋኪ በበኩላቸው፤ ህብረቱ መፈንቅለ መንግስቱን እንደሚያወግዝ ጠቁመው፣ ሁሉም የአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች ወደ ድርድር በመምጣት፣ ለውጥረቱ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲዘይዱ አሳስበዋል፡፡

Read 13191 times