Sunday, 19 November 2017 00:00

በውጥረት የሰነበተው የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መልቀቂያ ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(57 votes)

በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረ ውጥረት ተማሪዎች ከግቢው እየወጡ ነው

    ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ለሣምንታት በውጥረት  የሰነበተው የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እየወጡ ነው ተብሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፤ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከሦስት ሣምንት በፊት የኦሮሚያ ሶማሌ ክልል ግጭትን ተከትሎ፣ “የሶማሌ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ይውጡልን” በሚል እንቅስቃሴ የተጀመረው ውጥረት ቆይቶም “የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎችም ይውጡልን” ወደሚል መሸጋገሩን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት ምንጮች፤ይሄን ተከትሎም ከ120 በላይ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ወደ ጋምቤላ ክልል ሸሽተው መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡  
በዚህም የተነሳ የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት መቋረጡንና በአስተዳደሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባትም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታደሰ ሃብታሙ የሥራ መልቀቂያ መጠየቃቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡  
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት ተማሪ፤ የምግብና የመኝታ አገልግሎት  ባይቋረጥም ከመኝታ ዶርም ወጥቶ ለመመለስ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ናቸው ብሏል፡፡ የፀጥታ ሃይሎች በግቢው አቅራቢያ በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ የጠቆመው ተማሪው፤ ወደ ግቢ ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ ከተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚገጥማቸው ተናግሯል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ተማሪዎች እስርና ወከባ ይደርስብናል ብለው ስለሚፈሩ መሆኑን ተማሪው አስረድቷል፡፡
ከሌላ ክልል የመጡ ተማሪዎችም “ትምህርት ካልተጀመረ እዚህ መሰቃየት አንፈልግም” በማለት ካለፈው ረቡዕና ሐሙስ ጀምሮ ግቢውን ለቀው እየወጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤የክልሉ ባለስልጣናትና የሃገር ሽማግሌዎች፣ተማሪዎችን በማረጋጋት የተቋረጠው ትምህርት እንዲቀጥል  ለማድረግ እየጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በሃረማያና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ መቀጠሉን ያስታወቁት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፤ በመቱና በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረው ችግርም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈትቶ፣መደበኛ ትምህርት ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡  
በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰተ ባለው ተቃውሞና የትምህርት ማቆም አድማ ጉዳይ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው፤ ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በጥቂት ውጤት ማስመዝገብ ባልቻሉ ተማሪዎች መሆኑን ጠቁመው ከዚህ በኋላ ሁከት ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ በህግ ይጠየቃሉ ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከሶማሌ ወደ ኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተቀየሩ ተማሪዎች ጉዳይም ቢሆን ነገሮች እስኪረጋጉ በሚል ዝውውሩ እንደተከናወነ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ወደነበሩበት ዩኒቨርሲቲዎች ሊመለሱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎችን በማቀያየሩ ሂደት የክልሎች ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ አለ የሚባለው ሃሰት መሆኑን በመጠቆምም፤ ሚኒስቴሩ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሱ ውሳኔ ማከናወኑን ዶ/ር ጥላዬ በአፅንኦት ገልፀዋል።

Read 11700 times