Sunday, 19 November 2017 00:00

ባህል መገርሰስ የተሳነው ፍልስፍና

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

    ይህንን የዳሰሳ ጽሑፍ ለማዘጋጀት መነሻ የሆነኝ አቶ ዓለሙ ኃይሌየተባሉ ፀሐፊ በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መጽሓፍን አስመልክተው የሰነዘሩት ጠንከር ያለ ትችት ነው፡፡ ፀሐፊው ድርሳኑን በተመለከተለተፈጠረባቸው ግርታ ውሃ በማያነሳ የመሞገቻ ስልት የደራሲውን ፍሬ ሐሳብ ለማምከን ሞክረዋል፡፡ ሙግታቸው ግን ዙሪያ ጥምጥም ነበር፡፡ ፍልስፍናዊ ምልከታውን በመሄስፈንታ ስለ ላሊበላ የስነ ሕንጻ ልህቀት ማብራሪያበመስጠት ነው ብዙ የደከሙት፡፡ በአጠቃላይ የሂስ አቅራቢው ፀሑፍ በተዛነፈ ቁምነገር የተጀቦነወይምበስነ-አመክንዮ አጠራር የred herring fallacy ሰለባ ነበር፡፡
የድርሳኑ አንጓ ጭብጥ ከአክሱምና ላሊበላ የስነህንፃ ልህቀት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን አይደለም። እንደውም የአክሱምሀውልትን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነጹት እጆች ለምን ታጥፈው ቀሩ? ሰማይ ጥግ የደረሰ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች ጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን እንዴት እንደ ሌላኛው ዓለምእስካሁን መዘመን ተሳነን? በሚሉት እና በመሳሰሉት ቁጭት አዘል ጥያቄዎች ቆስቋሽነት ነው ቀሪፍሬ ሐሳቦቹ በስፋት የተተነተኑት፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ አክሱምና ላሊበላ በሰምና ወርቅዘይቤ ተሰናስነዋል፡፡ የሁለት ዓለም ወግእንደ ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ እና ዓለማዊነት፡፡ ልክ ታዋቂው እንግሊዛዊ ማቲው አርኖልድ፤ “The Greeks gave us science and philosophy; the Hebrews gave us the Law.” በሚል መነሻነት ሄለኒዝምና ሄብራይዝምን ምልከታን እንደቀመረው ሁሉ አክሱማዊነት እንደ ሄለኒዝም ጥበብን፣ ላሊበላዊነት  ደግሞ እንደ ሂብራይዝም  የመንፈሳዊ ዓለምውክልናን ተጎናጽፈዋል፡፡
ዓለማዊው እና መንፈሳዊው ዓለም በአንብሮ          /thesis/ እና በተቃርኖ /antithesis/ ተመስለውእርስ በእርሳቸው በዲያሌክቲካል ጭውውት መስተጋብር ሲፈጥሩ ማሳረጊያቸው በአስተጽምሮ /synthesis/ መልክ ዘመናዊነትንለዓይነ ሥጋ ማብቃት ይሆናል፡፡ በእኛ ሀገር የዝግመተ ለውጥ ታሪክ ውስጥ ግን ይህ መስተጋብር ፍጹም ባዕድ ነገር ነበር፡፡ መንፈሳዊው ዘይቤ ዓለማዊውን በመሻር ያለ አጣማጅ ሌጣውን እንደናኘ ብዙ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ የደራሲው ብሩህ አለምነህ መጽሐፍ የቆመበት የአመክንዮ ወጋግራ ይህ ነው፡፡
“ሙግት ይውደም፤ መቀበል ይቅደም”
መቀበል ዝግ ሥነልቦናን ያውጃል። ባለበት የሚረግጥ፣ እንደ ኩሬ የረጋ ምንም አይነት የመለወጥ ጭላንጭል አይታይበትም፡፡ ምዕራባዊያን የሮማ ሥርወ መንግሥትን መውድቅ ተከትሎ፣ በዚህ  አውዳሚ ባህል ተቀይደው ለአያሌ ዘመናት አበሳቸውን በልተዋል፡፡ ይህ የጽልመት ዘመንያከተምዘንድ በታሪክ ፊት የተሰለፉ ጥልቅ አሳቢዎች በእየዘመኑ ተፈራረቁ፡፡ የእነኮፐርኒከስና ጋሊሊዮ አጽም የሚኮሰኩሳቸው ጠቢባን እንደሻማ ቀልጠው፣ ትውልዳቸውን ሊያባንኑ አለት ከሆነው ባህል ጋር ፊት ለፊት ተላተሙ፡፡ በጠቢባኑ ርብርቦሽ እንደ ጅብራ ተደንቅሮ ሲቀናቀን የኖረው ባህል የእምቧይ ካብ ለመሆን በቅቷል፡፡ እኛ ግን ለእንዲህ አይነት ታሪካዊ ዝግመት ለውጥ አልታደልንም። የደራሲው ቁጭት የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው። ለምን የሙግት ፣የመከራከር፣ የመጠየቅና የመደመም ባህል ነጥፎ የመቀበል ስነልቦና አለቅጥ ሠለጠነብን? ይላል፡፡
ይህንን ለለውጥ የሚያንገራግር ቀፍዳጅ ባህል ለመናድ ነበር ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ በታሪክ ፊት የተከስተው፡፡ ዴካርት  “I think therefore I am” በሚል ፍልስፍናዊ ምልከታ ለሺህ ዘመን በመላው አውሮፓ ገንግኖ የኖረው የደቦ ጽልመት እንዲገፈፍ ወጋገን በመፈንጠቅ ፋና ወጊ እንደሆነው ሁሉ፣ ዘርዓያዕቆብም ጥልቅ ድብታ ውስጥ የወደቀውን ማኅበረሰቡን ለማንቃት በብርቱ ተውተርትሯል። ልዩነቱ የአውሮፓዊያኖቹ የትውልድ ቅብብል ነበረው፡፡ ህዳሴ፣ አብርሆትና ዘመናዊነት በሚሉ በእየፈርጁ በተከፋፈሉ የዘመን እሳቤዎች ውስጥ ታላላቅ ጠቢባኖች የየድርሻቸውን አበርክቶት አስተዋውቀዋል፡፡
ምናአልባትም በታሪክ ደግነትየጠቢቡ ዘመን ከታላቁ ንጉስ አጼ ቴዎድሮስ የንግስና ዘመን ጋር በአንድነት ገጥሞ ቢሆን ኖሮ የሚፈጠረው ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ የተለየ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ የንጉሱ የቅርብ ረዳቶች ዋልተር ፕላውዴንና ጆን ቤል ለዘመናዊነት ከነበራቸውጥልቅ ፍላጎት ጋር ተዳምሮ የፈላስፋው አስተምህሮት ቢያንስ ለጥቆ ለሚመጣው ትውልድ ትልቅ መነቃቃት ማበርከቱ አይቀርም ነበር፡፡
ዘርዓያዕቆብን ከሁሉም በላይ የሚያስወድሰው ተግባርሁሉ ነገር ዝግ በሆነበት ወግ አጥባቂ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ ግለሰባዊ  የአስተሳሰብ ነፃነትና የመሞገት ባህልን እንደ አዲስ ለማስተዋወቅ የሂደበት ርቀት ነው፡፡ ድግምትን፣ ማነብነብን፣ መሸምደድን፣ መጥቀስንና መገልበጥን የሙጥኝ ያለ፣ ከማወቅ ጋር መሰረታዊ ግንኙነት ያላቸውን መጠየቅን፣ መረዳትን፣ መመራመርንና መፍጠርን የመሳሰሉትን የእውነተኛ የዕውቀት ባህርያት መገለጫ የሆኑትን ነገሮችበህብረተሰቡ ውስጥ ባዕድ ሆነው እንዲኖሩ ጥንታዊው ባህላችን የተመቸ ነበር፡፡ ዘርዓያዕቆብይህ የከረረ ወግ አጥባቂአውዳሚ ባህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲከስምና የሙግት ወይም የመከራከር የስነዕውቀት ዘዴ /socartic method/ በምትኩ እንዲጎመራ ልክ እንደ አውሮፓዊያን የዘመን አቻዎቹ የድርሻውን ጡብ አኑሮ አልፏል፡፡
ወግ አጥባቂው የስነ ዕውቀት ባህላችንን ዞር ብለን ከገመገምነው በታሪክ ፊት ብዙ ነገር አጉድሎብናል። ለአብነት ያህል የ1966 ወርቃማው ትውልድን ማንሳት ይቻላል፡፡ የ66ቱ ወርቃማው ትውልድ ክሽፈት ተጠያቂ መሆን ካለበት ባህሉ ነው። ምንም አይነት የዳበረ ባህላዊ ንጣፍ ሳይኖረው፣ ያ ትውልድ እንደዋዛ ባከነ፡፡ የሶሻሊዝምን ጥቅስ በበቂ ሁኔታ ማነብነብ የዘመኑ ፋሽን ነበር፡፡ ይህ የዕውቀት ዘይቤ ደግሞ የሚቀዳው ከጥንቱባህላችን ነው፡፡ ለጥቅስ ለጥቅስማ እኔም አላንስም ብሎ ደርግ በጓሮ በር ቀደማቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ሊህቃኑ እንኳን የሕዝባቸውን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ መወሰን ተስኗቸው እንደ ዋዛ አከተሙ፡፡
ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብና ተከታዩ ወልደሕይወት የትውልዳቸውን ዕጣ ፈንታ ለማቃናት ደፋ ቀና ብለዋል፡፡ ያ የደከሙለት ትልቅ ራዕይ፣ ፍሬ አፍርቶ ቢሆን ኖሮ በእየዘመኑ የተሰናከልንባቸውን የታሪክ አጋጣሚዎች ለማለፍ አንቸገረም ነበር፡፡ ገጽ 176 ላይ ከሠፈረው በጥቂቱ፡-
“የዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት የባህልና የእምነት ፍተሻ የአብሮሆት ዘመንን በማምጣት አጼ ቴዎድሮስ ላይ ለሚጀምረው የዘመናዊነት ፕሮጀክት የባህል መደላድል የመፍጠር አቅም ነበረ፡፡ የአጼ ቴዎድሮስም ሆነ የአጼ ምኒሊክና የአጼ ኃይለሥላሴ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ያልተሳኩት የተደላደለ የባህል መሠረት ስላለገኙ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወትም ይሄንን ነገስታቱ ሲፈልጉት የነበረውን የተደላደለ የባህል መሠረት ነበር ለማምጣት ሲጥሩ የነበሩት፡፡”
በአጠቃላይ ጠቢባኑ በድቅድቅ ፅልመት ውስጥ ለሚባጀው ወገናቸው እንደ ሻማ ቀልጠው፣ ጭልጭል የምትል ብርሃናቸውን ለማጋራት ታትረዋል፡፡ የፅልመቱ ገናናት  እስከነ አካቴው ደብዛቸውን አጠፋው እንጂ፡፡ በመቀበል መቃብር ላይ የሙግት ባህል ለመዝራት በብርቱ ታገሉ፡፡ ግን አልቻሉም፡፡ ባህሉን እንኳን ሊገረሰሱት መቀናቀን ተስኗቸው ተፈጣጠሙ፡፡
እንደ ድክመት የሚወሰዱ ነጥቦች
የመጽሐፉ ገዢ ርዕስ ከፍልስፍናዊ መሠረታዊ ጭብጥ ጋር ይጣረሳል፡፡ ፍልስፍናን በአካባቢ ወይም በብሔር መቀንበብ የፍልስፍና ባህሪም ተፈጥሮም አይደለም፡፡ አፍሪካዊ ፍልስፍና ላይ ከሚነሳው የሠላ ሂስ አንዱ ፍልስፍናን ያለ ተፈጥሮዋ የብሔራዊ ስሜት ሰለባ ማድረጉ ነው፡፡ ፍልስፍና ቅጥያ አልባ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ራሱ ትልቅ ብሔር ነው፡፡ ምናልባትም ደራሲው “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” በማለት ፈንታ “ፍልስፍና በኢትዮጵያ” የሚለውን ለአርዕስትነት ቢጠቀም የፍልስፍናን እውነተኛ ባህሪ የሚያንፀባርቅ ይሆን ነበር፡፡
ደራሲውበጥንታዊት ኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ፈጠራ ከመለኮት ኃይል ጋር መገናኘቱን በተደጋጋሚ አጥብቆ ሲኮንን እናስተውላለን፡፡ ይህ ሂስ ግን ውሃ የሚያነሳ አይደለም፡፡ እንኳን በዚያ ሀይማኖት ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት ዘመን ይቅርና አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለዘመን እንኳን የፈጠራን ምንጭ በስነ-አመክንዮ ማብራራት እንደማይቻል ሊኅቃን ያስረዳሉ፡፡ የምሥራቁ አስተምህሮት ፈጠራን በዚህ መልኩ ነው የሚገልጸው፡- The real creater know it perefectly well, that they are not the creaters-they were just instrumental, they were mediums. something happened through them, true, but they are not the doers of it. የጥንቱ ማኅበረሰብ የቅዱስ ያሬድ ዜማን፣ የአኩስምና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ትንግርታዊ ፈጠራከመለኮታዊ ኃይል ጋር ማስተሳሰሩ ምንም ሊደንቀን አይገባም፡፡ የደራሲው ህጸጽ የመነጨው ታሪክን ለመርመር ከሄደበት የተሳሰተ ስልት ነው፡፡ታሪኩን የገመገመበት መንገድ ታሪኩ በተፈጸመበት አውድ ላይ ቆሞ ሳይሆን በዛሬ ነባራዊ ሁኔታ መሆኑ ድምዳሜው ከአመክንዮ የተራቆተ ሊሆን ችሏል፡፡
ሌላው የደራሲው ጥድፊያ የተሞላበት ድምዳሜ በግልጽ የሚስተዋለው ስለ ዶ/ር ዳኛቸው በሰጠው ብይን ላይ ነው፡፡ የሀገራችንን ኋላቀርነት በተመለከተ በፍልስፍናዊ ዕይታ ለመተንተን የሞከሩ ብቸኛ ምሁር እንደሆኑ በገጽ 179 ላይ ያትታል፡፡
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ከአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ እስከ አሁን ዘመን ድረስ ያሳለፈውን የእሴት ሽግግር፣እንዲሁም አሁን ላለንበት ኋላ ቀር የማኅበረሰብ ሁኔታ ወደ ኋላ ሄደው መነሻ ምክንያቶቹን በታሪክ ውስጥ በርብረው ያሳዩን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው፡፡ ከእሳቸው በፊት ይሄንን ያደረገ ኢትዮጵያዊ ምሁር አልሰማሁም፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው ከሸገር ኤፍኤም ራዲዮ 102.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ከማቲው አሮንልድ ሄሌኒዝምና ሄብራይዝም ምልከታን በመዋስ ስለ አኩስማዊነትና ላሊበላዊነት መነሻ ሐሳብን ከማስተዋወቅ በዘለለ በጉዳዩ ላይ በጥልቅ ሄደውበት በድርሳን መልክ ያዘጋጁት ጥናት የለም፡፡ ደራሲው እዚህ ጋ ጠቀም ያለ ምርምር ሳያደርግ ችኩል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ እንደውም በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ፕሮፌሰር መሳይ በእጅጉ የተጠበበ ልሂቅ የለም፡፡Survival and Modernization, Ethiopia’s Enigmatic Present: A Philosophical Discourse በሚለው መፅሓፋቸው፤ ኢትዮጵያ ለዘመናዊነት የሚያስፈልገውን ሁሉም ነገር ልክ እንደ ጃፓንና ብሪታኒያ አሟልታ ለምን መዘመን ተሳናት? የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ግሩም በሆነ ፍልስፍናዊ ቅኝት ባህላችንን፣ታሪካችንንና ስነልቦናችንን እየበረበሩ ጥልቅ እሳቤያቸውን ያጋሩናል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፍልስፍና መጽሐፍ  ጥለን የመጣነውን ታሪካዊ ዳራ በቅጡ ለመፈተሽ የሙግት በር መክፍቻ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። እንዲህ ያሉ የጥበብ ሥራዎች የበለጠ የሚጠናከሩበትን የውይይት መድረክ መክፍቱ ፋይዳው የጎላ ይሆናል፡፡

Read 2429 times