Sunday, 19 November 2017 00:00

“ኢትዮጵያን የሚያከብር ሁሉ ይክብራል፤ ኢትዮጵያን ያኮሰሰ ሁሉ ይኮስሳል”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ግልጽ ደብዳቤ ይድረስ  ለአቶ  ለማ  መገርሳ፤  የኦሮሚያ  ክልል  ፕሬዚደንት ይድረስ  ለአቶ  ገዱ አንዳርጋቸው፤
 የአማራ  ክልል  ፕሬዚደንት
     የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ

   ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ በቋንቋ ላይ ከተገነባ ጎሰኝነት ይልቅ በደም፣ በተዋልዶና አብሮ በመኖር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነትን ክህዝባችሁ ጋር ሆናችሁ አብስራችሁና አውጃችሁ፣ በባህርዳር ከተማ፣ ከኦሮሞና ከአማራ ዘመዶቻችሁ ጋር በቅርቡ ያደረጋችሁት ውይይት ልቤን ነክቶታል። በእዚህ ጉዳይ ዛሬ እኔ ክማንም በላይ ሃሴት አደርጋለሁ። ቅድስት ኢትዮጵያ እንድትከበርና የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያንሰራራ ላለፉት 28 ዐመታት አቅሜ የሚችለውን ሁሉ አድርጌአለሁና።  ኢትዮጵያዊነት እንደ እርኩስነት በተቆጠረበት በቀውጢዎቹ  28 ዐመታት ውስጥ፣ በትንሿ አቅሜ፣ ኢትዮጵያዊነት ቅድስና እና ልእልና መሆኑን ለማንፀባረቅ ሞክሬአለሁ።  ይህን በማድረጌ የዘለፋና የስድብ ውርጅብኝ ደርሶብኝ ስለነበር፣ አሁን እናንተ በፍቅር ተገናኝታችሁ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ ስታደርጉ ሳይ፣ ይህ ክስተት በህልሜ ነው በውኔ፣ ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ። የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያዛምደውና የሚያስተሳስረው፣ እንዲሁም  አብሮ ለመኖር የሚያስችለው ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።  በእርግጥም እንደ ተራራ ለተቆለለው የኢትዮጵያ ችግር መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ስለሆነ፣ እናንተ በትክክለኛው ጥርጊያ መንገድ ላይ መጓዝ ጀምራችኋል። የጉዟችሁን መጨረሻ እግዚአብሄር ያሳምረው። ጅማሮአችሁ እንዳይጠለፍ ወይም እንዳይደመሰስ  ይጠብቀው። እናንተም ነቅታችሁ ጠብቁት።
ጉራጌ፣ አማራ፣ ተጋሩ፣ አፋር፣ ኦሮሞ፣  ከምባታ፣ ሀዲያ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ እና ሌሎቻችንን በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ሀገር የምንኖረውን ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያዛምደን ኢትዮጵያን በስሙ ያስጠራት የንጉሦች ንጉሥ፣ የካህኖች ካህን የነበረው አባታችን ኢትዮጵ ነው። ኢትዮጵ የኖረው በጣና ደሴቶች ላይ ሲሆን ዘመኑም ከ4000 ዐመታት በፊት ነው። እሱም 10 ወንድ ልጆች ወልዶ ነበር። እነዚህ 10 ወንድ ልጆች 10 ነገዶች ሆነው፣ ለ4000 ዐመታት በመባዛት እኛን የዛሬዎቹን ኢትዮጵያውያንን አስገኝተዋል። የኢትዮጵ አስሩ ወንድ ልጆች ስሞችም፡- አቲባ፣ ቢዖር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክዚብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ፣ እና አዜብ ነበሩ። የዛሬ 4000 ዐመት ከወጡት ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ ወለጋ ውስጥ ይኖር የነበረው የኦሮሞው አጎቴ ስም ቶላ ነበር። ኢትዮጵ ከኦሮሞዎች ጋር ዝምድና ስለአለው ነው፣ የዛሬ 4000 ዐመት ለልጁ የሰየመው ስም ዛሬ የኦሮሞው የኔ አጎትና የሌሎችም ኦሮሞዋች  ስም ሊሆን የቻለው። ከአባታችን ከኢትዮጵ በኋላ የተክተሉት ነገሥታት ልጆቹ፣ የኢትዮጵያን ስልጣኔ በመላው አፍሪካ አሰራጭተው፣ ዛሬ አፍሪካ የሚባለው ሰፊ ምድር እስከ ዛሬ ሁለት መቶ ዐመታት ድረስ ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ ነበር። LOWER እና UPPER ETHIOPIA ብለው ከፍለውት ነበር።  ከእዚህም በላይ የህንድ ውቅያኖስና ከምእራብ አፍሪካ ብብት ስር ያሉት ውቅያኖሶች ሁሉ የኢትዮጵያ ውቅያኖሶች ነበር የሚባሉት፡፡ ለማመሳከርያ ከዚህ ፅሁፍ እግርጌ የሰፈሩትን ሁለት ጥንታዊ የአፍሪካ ካርታዎች ተመልከቱ።
አሁንም ቢሆን አፍሪካ፣ አፍሪካ የተባለችው በእኛው በአፋሮች ስለሆነ ደስ ይለናል እንጂ አንቆጭም። እስያም እስያ የተባለችው ንግሥተ ሳባ ዙፋኑን በተካችው በዐፄ እስያኤል ስለሆነ በእዚህም እንታበያለን። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ “የተቃጠለ ፊት” ሳይሆን “ቢጫ ወርቅ” ስጦታ ለእግዚእብሄር ነው። ቅዱስ ስሟን ለመፋቅ ወይም ለመቀየር የተመኙ ሁሉ የኢትዮጵያ ስም ከእግዚአብሄር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ምኞታቸው ከሽፎ ቀርቷል። ኢትዮጵያን ሊያገንን የተነሳ ሁሉ ይገንናል። ኢትዮጵያን የሚያከብር ሁሉ ይክብራል። ኢትዮጵያን ያኮሰሰ ሁሉ ይኮስሳል።  ኢትዮጵያን ያንቋሸሸ ሁሉ ይንቋሸሻል።  
የእግዚአብሄር ዐይኖች ኢትዮጵያ ላይ ተተክለዋል። በቅዱስ መፅሐፉ ውስጥ እግዚእብሄር ኢትዮጵያን ደጋግሞ የሚጠራት ያለ ምክንያት አይደለም። ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ስለሚወዳት ነው። በነቢዩ አሞፅ አፍ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- “እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፤ እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያውያን ልጆቼ አይደላችሁምን?”  (አሞፅ 9: 7) ከዚህ ጥቅስ የምንማረው እኛን ኢትዮጵያውያንን እግዚአብሄር ክእስራኤላውያን ይበልጥ ወይም እኩል እንደሚወደን እና ልቡ ውስጥ እንዳለን ነው። ስለዚህ እሱ ጥሎ አይጥለንም።  
የሁለቱ ትልልቅ ህዝቦች፣ ማለትም የኦሮሞና የአማራ በሰላምና በፍቅር መኖር ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋስትና ነው። ኦሮሞና አማራ እየተጫረሱ እኔ ተገልዬና ተዘልዬ ግንብ አጥሬ፣ ለዘላለም በሰላምና በብልፅግና ለብቻዬ እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ ጅል ብቻ ነው። የሁለቱ ጠብ ዳፋ ለሁሉም መዳረሱ አይቀርም፡፡ ደሞም ሁለት ዝሆኖች ሲራገጡ ሳሩ መጎዳቱ አይቀርም፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ትጎናፅፍ ዘንድ ኦሮሞና አማራ በፍቅርና ሰላም አብረው እንዲኖሩ ግድ ይላል። የአማራና ኦሮሞን ቤቶች የሚያነደው እሳት ካልጠፋ፣ ወደ ሌሎቹም ቤቶች መዛመቱ አይቀሬ ነው።
የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት በእርግጥም በኢትዮጵያውያን ልቦች ሁሉ ሰርጎ የገባ ፍቅር ነው። ይህ ባለፉት 4000 ዐመት በቅሎ ስር የሰደደ ፍቅር፣ በ30 ዐመታት ውስጥ ሊተን አይችልም። ከእዚህ ጋር በተያያዘ የአቶ መለስ ዜናዊን ስህተት ያስታውሷል። አቶ መለስ ዜናዊ፤ “የአክሱም ሃውልቶችና የጎንደር ቤተ መንግሥቶችን የተጋሩ የጎንደር አማራዎች እንጂ ለኦሮሞና ለጉራጌው፣ እንዲሁም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ምኑም አይደሉም፣” ብለው ለሟቹ ለፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ቃለመጠይቅ ሰጥተው ነበር። እኔም ለዚህ ስህተት እጸፋውን በዛው ሰሞን በኢትዮጵያን ሪቪው መፅሄት ላይ በእንግሊዝኛ መልሼለት ነበር። እንዲህ ስል፤ “አቶ መለስ ተሳስትሃል። በኋላ በጉራጌነት የተጠሩ ህዝቦች በትግራዩ ተወላጅ በአዝማች ግርማይ መሪነት በዛን ጊዜ የትግራይ ክፍል ከነበረው ከጉራእ ተነስተው ሸዋ ላይ ሰፍረው ነበር። ስለዚህ አክሱም የጉራጌዎችም ነው። ኦሮሞም በጎንደር ቤተ መንግሥት ውስጥ ከመጀመሪያው  አንስቶ አፄ ቴዎድሮስ  እነ ትንሹን ራስ አሊን ከእቴጌዋ እናታቸው ጋር አስወጥተው እስከ አባረሯቸው ጊዜ ድረስ ይፈነጭበት ነበር። ስለዚህ አቶ መለስ ሆይ፤ ስህተትህ አጥፍ ድርብ ነው።”
አቶ መለስ ለዶናልድ ሌቪን ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት፤ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት የላቸውም የሚል ነበር። እንደ እሱ አባባል፤ ትግራይ የተጋሩ ብቻ ስለሆነች ትግራይ ስትወረር ተጋሩ ያልሆኑት ኢትዮጵያውያን ለትግራይ ደማቸውን ማፍሰስ አልነበረባቸውም። እኛን ምን አገባን? ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ማየት ነበረባቸው። ሀቁ ግን የድሉ ተጠቃሚዎች ሌሎች ቢሆኑም በሃገር ፍቅር ተቃጥለው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደማቸውን ለትግራይ  ነፃነት ገብረዋል።  ያኔ ኢትዮጵያውያን ለትግራይ ባይሞቱ ኖሮ፣ ምናልባት ዛሬ ነፃይቷ ትግራይ ባልኖረች ነበር።     
አቶ መለስ ብሄራዊ ስሜት የለውም ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ በእርግጥም ኤርትራ ትግራይን በወጋች ጊዜ ህገሬ በጠላት ተወረረች ብሎ የብሄራዊ ስሜት ሲቃ ይዞት፣ ግር ብሎ እየተመመ ከድፍን ኢትዮጵያ ተነስቶ ትግራይ ላይ ተሰባስቦ፣ ለሃገሩ ሉአላዊነት ደሙን አፈሰሰ። በዚያን ጊዜ ለአቶ መለስ ዜናዊ በእንግሊዝኛ  ግልፅ ደብዳቤ ፅፌ ተበቀልኩት፡---”አየህ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ሞትን ከመጤፍ የማያስቆጥረው እሳታዊ የእናት ሃገሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስሜት አለው፣” ብዬ። አሁንም ቢሆን ይህ የኢትዮጵያዊነት እሳት በጎሰኝነት አመድ ቢዳፈንም አመዱ ሲበን ተገልጦ ዳግም እየተንቀለቀለ ይነዳል። ሰሞኑንም መንደድ ጀምሯል።
ፕሬዚደንቶች ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ሆይ!                 
አሁን እናንተ ኦሮሞዎችና አማሮች ወንድማማቾች፣ በባህርዳር ተገናኝታችሁ ያረጋገጣችሁት ዝምድና  እና ትስስር፣ ሁለታችሁም ባነበባችሁት  “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በተሰኘው መፅሀፌ  በግልፅ ተንፀባርቋል። ከመፅሀፌ እንደተገነዘባችሁት፣ በእውነትም አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት እንጂ በቋንቋ ላይ የተገነባ ጎሰኝነት አይደለም። ጎሳ ማለት ቋንቋ ማለት ነው፡፡ እሱም “ጎሰአ” ማለትም  ተናገረ  ከሚለው የግዕዝ ቃል የፈለቀ ነው። ስለዚህ ቋንቋ ማለት ጎሳ ነው። ጎሳ ማለትም ቋንቋ ነው።  በሌላ አነጋገር፣ ጎሳ የቋንቋ ክፍል እንጂ የደም ወይም የዘር ዘርፍ አይደለም። አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በሞላ በዛ ቋንቋ አፍ ከፈቱ፣  የዚያ ቋንቋ ወይም ጎሳ አባላት ይሆናሉ። ይህን በምሳሌ ላሳይ፡- እኔ በፈረንሳይ፣ በጀርመንና አንግሊዝ ሃገሮች ኖሬ፣ ሶስት ልጆች ብወልድና እነሱ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና እንግሊዝኛ ቢናገሩ፣ የእኔ አፍ መፍቻ ደግሞ ኦሮምኛ ቢሆን ልጆቼ ሶስት የተለያዩ ቋንቋዎች በመናገራቸው ጎሳቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ቢሆንም የርስበርስ ዝምድናቸው አይፋቅም። እኔም ኦሮምኛ ስለተናገርኩ ጎሳዬ ኦሮሞ ቢሆንም አባትነቴ አይሰረዝም። እኛን የሚያዛምደን  ደም ወይም ዘር እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለምና።  ስለዚህ ሰዎችን በስጋ የሚያዛምድ ደም ወይም ዘር ነው እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለም። ደሞ ቋንቋ ሊረሳም ሊለዋወጥም ስለሚችል አስተማማኝ የማንነት መለያ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ቋንቋዎች እንዳሉ ይነገራል። ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ስለሆነ በዚህ ቁጥር መሰረት 82 ጎሳዎች አሉ ማለት ነው። በልጆቼ ምሳሌ እንደምናየው፣ ደም አንጂ ቋንቋ አያዛምድም።  እነዚህ ሁሉ የቋንቋ ተናጋሪዎች በደም ወይም በዘር የሚዛመዱት ሁሉም ከኢትዮጵ ወይም ከእሱ 10 ልጆች አብራክ ስለፈለቁ ብቻ ነው። በተጨማሪ ደግሞ በጋብቻ ደም ስለተደበላለቁና በኢትዮጵያ ግዛት ለሺዎች ዐመታት አብረው ኖረው በባህል፣ በልቦና እና እምነት ስለተሳሳቡ እንዲሁም ስለተወሳሰቡና የጋራ የማንነት እሴቶችን ስለአካበቱ  ነው።  እንግዲህ እናንተም የኢትዮጵያን ህዝቦች የሚያዛምዳቸውና አንድ የሚያደርጋቸው፣ ክዛም አልፎ የሚያኗኑራቸው ኢትዮጵያዊነት አንጂ ጎሰኝነት ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል አለመሆኑን ተረድታችሁ፣ሁለታችሁም ከኢትዮጵ ዘር ከወረደው አባታችሁ ከፈላስፋውና ከነብዩ ደሸት፣ የዛሬ 3600 ዐመት አካባቢ በተፈጠራችሁበት በጎጃም ተገኝታችሁ፣ ኢትዮጵያዊነትን መዘመራችሁ ያስመሰግናችኋል። ይህ ሊሆን የቻለው የእግዚእብሄር መንፈስም ዘንቦባችሁ እንደሆነ አኔ አልጠራጠርም። የደም ወተቷን እያጠባች ያሳደገቻቸው ልጆቿ፣ ኢትዮጵያ አመድ-አፋሽ ሆና፣  ጡት ነካሽ ሆነውባታል።  ምንም እንኳን እሷ ብታወፍራቸውና ብታፋፋቸውም፣እንዲሁም ብታቶጅራቸውም፣ ርእሰ ብሄሮቿ እንኳ ሳይቀሩ ለ28 ዐመታት ኢትዮጵያ ብለው ስሟን ለመጥራት ሳይደፍሩ፣ “ሃገሪቱ፣ ይች ሃገር” ይሏት የነበረችውን እናታችንን ኢትዮጵያን፤ እናንተ ከፍ ከፍ አድርጋችኋታል። ነገር ግን ተግባራችሁ በእዚህ ብቻ እንዲገታ አይገባም። አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ አለባችሁ።
ግን ምን ዐይነት እርምጃ? ከዝምድናችሁ በተጨማሪ፣ በቁጥር ብዛታችሁና ክዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ህልውና አብራችሁ የተሰለፋችሁትን መለስ ብላችሁ በማጤን፣ የአመራር ሚና እየተጫወታችሁ ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም፣ ማለትም ብዙሃኑን የአፋርን፣ የተጋሩን፣ የሲዳማን፣ የጉራጌን፣ የሃዲያን፣ የከምባታን፣ የሱማሌን፣ የከፋንና ሌሎቹን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋብዛችሁ ተመካክራችሁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ርትእ፣ የሰብአዊና የሃብት እኩልነትን አስከብሩ። የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ በድፍን ኢትዮጵያ የመንቀሳቅስና የመኖር መብትን አስተግብሩ። በጎሰኝነት ጦስ በከንቱ የሚፈሰውን ደም አስቁሙ። የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ በአስቸኳይ አስፈቱ። ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትን  የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰባዊ ማህበራትን ሳትንቁ በማሰባሰብ፣ ከእናንተ ጋራ ሆነው፣ እነሱም የሃገራቸውን እጣ ፈንታ እንዲወስኑ እድል ስጡአቸው። የእንቅስቃሴአችሁንም አርማ እስከ መጨረሻው ኢትዮጵያዊነትን አድርጉ። አሁን በሃረር የሶማልያ ክልል፣ በእብሪተኞች መሰሪነት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ኦሮሞዎችና ከነሱ ጋር በሰላም ለዘመናት የኖሩት ሶማሌዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ ጣሩ። የጎንደር ህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ የተቻላችሁን ፈፅሙ።  ይህን ሁሉ ብትፈፅሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር፡ አንድነት፣ እኩልነት፣ የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሰብአዊ መብት፣  ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ይሰፍናሉ። ኢትዮጵያም በነፃነቷ ለዘላለም ትኖራለች።  
ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በልብና ደም ስር ውስጥ መገኘቱንና እንደሚያሰክር ልዩ ዕፅ መሆኑን ለመግለፅ  ሞክረው ነበር። እኔ ከዚህ ቀደም ስለ ኢትዮጵያዊነት በጥልቅ አስቤበት የደረስኩበትን መደምደሚያ ከዚህ በታች አያይዤዋለሁ። የኢትዮጵያዊነት ማኒፌስቶ ወይም መግለጫ ብዬዋለሁ። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለምን በኢትዮጵያዊነታችን  መኩራት እንደሚገባንም ዘርዝሬአለሁ። በኢትዮጵያዊነት ጉዞአችሁ ይህ መግለጫ ፋና ይሆናችሁ ዘንድ አበርክቼላችኋለሁ። ከእሱ በተጨማሪ፣ እናንተ ከዚህ ቀደም ባነበባችሁት “የኦሮሞ እና የእማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በተሰኘው መፅህፌ፣ እና አሁን ሰሞኑን ባሳተምኩት ሥራዬ  ውስጥ፣ ማለትም “የተሰወረውና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ” በሚለው መፅሀፌ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ፍንትው ብሎ ስለሚታይ በእነሱም ልትመረኮዙ ትችላላችሁ።  በዚሁ በአይሁዳውያንና አትዮጵያውያን የታሪክ መፅሃፍ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ምንነት ዝርዝር፣ በተቀፅላ በቋሚነት ስለተቀመጠ መፅሃፉን እንደ አሻችሁ እየገለጣችሁ፣ እሱን ለመመልከት የሚያግዳችሁ ነገር የለም።     
የኢትዮጵያዊነት ምንነት መግለጫ እና ለምን በኢትዮጵያዊነታችን መኩራት እንደሚገባን
MANIFESTO OF ETHIOPIANISM
 ክፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ የጽፈት ጠረጴዛ
ኢትዮጵያዊ መሆን እጅግ የሚያኮራ ነገር መሆኑን ባለመገንዘባችንና “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል ትክክለኛ ፍቺ ባለማወቃችን፣ አንዳንዶቻችን በኢትዮጵያዊነታችን እናፍራለን።  
“ኢትዮጵያዊነት” ምን ማለት እንደሆነ  ለማብራራት የቃሉን ትርጉም  ምንጭ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ “ኢትዮጵያ” ማለት ቢጫ ወርቅ ስጦታ (ለእግዚአብሄር ማለት) ነው፡፡ ይህ ስም የተሰጠው ለኢትዮጵያ መስራችና የኢትዮጵያውያን አባት ለሆነው ለኢትዮጵ ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ወርዶ፣ ወርዶ  ወደ እኛ የደረሰው ከሱ ስም ነው ማለት ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊ” ማለት በግሪክ ቋንቋ የተቃጠለ ፊት ነው  የተባለው ነጭ ውሸት ነው። በግሪክ መዝገበ ቃላት ውስጥ እንደዚህ የሚል ቃል የለም። ደሞም የኛ ፊት የተዋበ እንጂ የተቃጠለ አይደለም።     
ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው፣ ከፍ ሲል ኢትዮጵያን በስሙ ካስጠራው ከካህኑና ከንጉሠ ነገሥቱ ከኢትዮጵ፣ ዝቅ ሲል የሱ ዘር ከሆነው ከነቢዩና ከፈላስፋው ከደሸት መውረዳቸው ነው፡፡ ኢትዮጵ የዛሬ 4000 ሺ ዐመት አካባቢ ዐስር ወንድ ልጆች ወልዶ ነበር። ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፡፡--
አቲባ፣ ቢኦር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክሲብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ እና አዜብ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አሻን፣ በሪሳ፣ ቶላ እና አዜብ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። የኢትዮጵ ዘር፣ የነቢዩ ደሸት ልጆች ደግሞ መደባይ፣ መንዲ፣ ጂማ እና ማጂ ይባሉ ነበር፡፡ ማጂ ማራ (አማራ) ን እና ጀማን ወለደ። ሰዎቹ የተሰየሙት የዛሬ 3600 ዐመት ቢሆንም፣ እነዚህ ስሞች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡
የኢትዮጵ 10 እና የደሸት 4 ልጆች ተባዝተው ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉት ሰዎች በሞላ ሆነዋል። በኢትዮጵያና በመላው ዐለም ባሉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የደም ስሮች ውስጥ የኢትዮጵ እና የደሸት ደም ይዘዋወራል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በሞላ ምንጫቸው አንድ እና አንድ ነው፡፡ ስለዚህም ቋንቋቸው  ቢለያይም ደምና ዘራቸው አንድ ነው። ቋንቋ ደግሞ የመግባቢያ መሳሪያ እንጂ ዘርን አመላካች ወይም የዘር ክፍል አይደለም፡፡ ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ነው፡፡  
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ጎስአ (ጎሳ)  ልብየ ሰናይ ይላል፡፡ ልቤ መልካም ተናገረ፣ ማለት ነው። አገሳ ወይም ከውስጥ አወጣ፣ የተሰኘውም ቃል ከዚህ የመነጨ ነው። ጎሳ ማለት አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ነው። ዘር ማለት አይደለም።  ለምሳሌ አንድ አባትና እናት ወደ ፈረንሳይ ሃገር ሄደው ልጅ ቢወልዱና ፈረንሳይኛ ቢናገር፣ ከዛም ወደ አሜሪካን አገር ተጉዘው፣ ሌላ ልጅ ወልደው እንግሊዝኛ ቢናገር፣ ልጆቻቸው ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ስለተናገሩ ወንድማማችነታቸው አይፋቅም፡፡ ወላጆቹም አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም አፋርኛ በመናገራቸው ወላጅነታቸው አይደመሰስም፡፡ ደምና ዘራቸው አንድ ነውና። ስለዚህ ወሳኙ ቋንቋ ሳይሆን ደምና ዘር ነው፡፡ ቋንቋ ወይም ጎሳ ወሳኝ አይደለም። መግባቢያ ነው እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚናገሩ ጎሳዎች አሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ጎሳዎች በቋንቋ ቢለያዩም በደማቸው አንድ የኢትዮጵ ልጆች ናቸው፡፡ የሚያገናኛቸውም ኢትዮጵያን በስሙ ያስጠራው ኢትዮጵ አባታቸው ነው፡፡
ከ200  ዐመታት በፊት መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ይባል ነበር። የዚህ ምክንያቱ የኢትዮጵ ተወላጆች በመላው አፍሪካ ተሰራጭተው፣ አፍሪካን አሰልጥነው ስለኖሩበት ነው። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በቅኝ መግዛት ከጀመሩ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ቀርቶ አህጉሩ አፍሪስካውያን በተባሉት አፋሮች አፍሪካ መባል ጀመረ። አሁንም ድረስ ስሙ ክእኛው ስለ አልወጣ ቅር አንሰኝም።
አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ወይም ትውልደ-ኢትዮጵያዊ ሰው በሁለት ምክንያቶች ኢትዮጵያዊ ይሆናል። አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዱ። ሁለተኛ፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ በመሆኑ። ሁለቱንም የሚያገናኛቸው በደምና በዘራችው ክኢትዮጵ መውረዳቸው ነው።  ኢትዮጵያዊነት ማለት በዐለም ልዩ የሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ  የሚገኝ፣ ዮጵ የተባለ ቢጫና ብርቅዬ ወርቅነት ማለት ነው። ክዚህም በላይ፣ ለዐለሙ ፈጣሪ ለእግዚአብሄር ብቻ የሚቀርብ ልዩ ገጸ-በረከት ማለት ነው።
 ኢትዮጵያዊነት ማለት የህይወት ምንጭነት፣ የሰብእና  መገኛ ስፍራ ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የስነመለኮት ከፍታ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ፣ የሰው ዘር አርአያ፣ የስነምግባር ልእልና ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የህርነት፣ የጀግንነትና የፍትሀዊነት ተምሳሌነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የእኩልነትና የሰው ልጅ ክቡርነት አርማ ነው።
እትዮጵያዊነት ማለት የታማኝነትና የተአማኒነት እንዲሁም የመለኮት ማህደርነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የፅናት፣ የብርታትና የትእግስትና የዘላቂነት ምልክት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የሀቀኝነትና የእውነተኛነት ምሳሌ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የርህራሄና የቸርነት ናሙናነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ይሉኝተኝነትና አዙሮ ተመልካችነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት የጥበበኝነት ቁንጮ፣ የብልህነት እራስ ማለት  ነው።
ኢትዮጵያዊነትማለት የቅድስና እና የብጹእነት ጫፍ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት፣ የመተዛዘን ማማነት ነው።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሞላ በሚከተሉት ምክንያቶች በኢትዮጵያዊነታቸው ሊኮሩ ይገባል። የኩራቶቹን ሁሉ ምክንያቶች ለመዘርዘር ጊዜም ቦታም ስለሚፈጅ ጥቂቶቹ ብቻ ይቀርባሉ።  
1.  ኢትዮጵያ በሳይንስም ሆነ በመፅሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ፣
2.  ከ4500 ዐመታት በፊት በንጉሥ ስብታህ አማካኝነት የጋዜጣንና የፖሊስን ሥራ ከዐለም ቀድማ ኢትዮጵያ በማቋቋሟ፣
3.  በዐለም ላይ የሌለ ከኖህ ጀምሮ ስሞቻቸውና የነገሡበት አዝማናት የተመዘገበ ነገሥታት በመኖራቸው፣
4. አባታችን ኢትዮጵ እና ሚስቱ እናታችን ሲና እንቁዮጵግዮን፣ መሲሁ እየሱስ ሲወለድ፣ ልጆቻቸው ወደ እስራኤል ተጉዘው ገዳ  እንዲያበረክቱለት በእግዚአብሄር ትዕዛዝ ከኢየሩሳሌም  ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውና ጣና ጎጃም ላይ በተልእኮ በመስፈራቸው፣
5. የኢትዮጵና የእንቁዮጳግዮን  ልጆች ታላላቅ ነገሥታት ሆነው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና እስያ በመንሰራፋታቸው፣ ስልጣኔአቸውን በማሰራጨታቸውና መላውን አፍሪካ ኢትዮጵያ በማሰኘታቸው፣
6.  አጼ እስያኤል እስያን አሰልጥኖ በስሙ አህጉሩን እስያ በማሰኘቱ፣ እጽዋትንና እንስሳትን አዳቅሎ አዲስ ውጤት ያስገኘው በዐለም የመጀመሪያው ጄኔቲክ ኢንጂኔር በመሆኑ፣ ክ3000 ዐመታት በፊት ይኽው ትልቅ ሰው ምናልባት በዐለም የመጀመሪያ የሆነውን ሰንደቅ አላማችንን በመፈልሰፉ፣
7. በንግሥተ ሳባ ትልቅነት--- ኢትያኤል የተባለች የሳባ ንግሥት በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰች፣ የዐለሙ ፈጣሪ እየሱስ ክርስቶስ ስሟን ጠርቶ፣ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበበኝነት ለመፈተን ኢየሩሳሌምን መጎብኝቷን የመሰከረላት ትልቅ ሰው በመሆኗ፣
8.  በአፋሮች ትልቅነት---አፍሪካ በአፋሮች አፍሪካ ስለተባለች። ከ3000 ዘመናት በፊት አፋሮች ታላቅ መርከብ ገንቢዎችና መርከበኞች እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና በእስራኤል ስመጥር የኦፊር ወርቅ ነጋዴዎች ከመሆናቸውም በላይ ተጽእኖ አሳዳሪዎች በመሆናቸው፣
9.  የኢትዮጵ ዝርያዎች 12 ጠበብት ነገሥታት ሆነው እስራኤሎቹ የሚጠብቁት መሲህ መወለዱን ሳያውቁ የእኛዎቹ ከሩቅ ሆነው የመሲሁን መወለድ ተረድተው፣ ከኢትዮጵያ ተነስተው በኮከብ እየተመሩ፣ ቤተልሄም ደርሰው ለመሲሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ገዳ በማቅረባቸው፣
10.   በዐለም ላይ ከአሉት ነገሮች ሁሉ በጣም ውድ እና ብርቅ የሆነው  የታቦቱ ማረፊያና መኖርያ አድርጎ እግዚአብሄር ከእስራኤል ይልቅ ኢትዮጵያን በመምረጡ፣
11.  ኢትዮጵያ በዳዊት መዝሙርና በሌሎችም መጽሃፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ በእግዚአብሄር በመጠራትዋ፣
12. ከእግዚአብሄር በታች ኢትዮጵያ አይሁዳውያንን በእግራቸው ስለማቆማቸው፣ ከነብዩ ከሙሴ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ አይሁዳውያንን ወደ ግዛትዋ እያስገባች ጥገኝነት፣ መሬት እና ንግሥና ሳይቀር እየሰጠች አስተናግዳለች። በሌላ ሃገራት ግን እስራኤላውያንን ያሳድድዋቸው፣ እንዲሁም ይገድሏቸው ነበር። በእኛ በጎ አድራጊነት እንኮራለን።  ክዚህ በተጨማሪ፣ እስራኤላውያን በባርነት በባቢሎን 70 ዐመት ሲሰቃዩ ቆይተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተመቅደሳቸውን ካደሱ በሁዋላ መጻህፍት አጡ። መጽሃፍ ቅዱስን እና ሌሎች ብርቅዬ መጻህፍትን ኢትዮጵያ ስለላክችላቸው እንታበያለን።  
13.  ትልቅ ለሚባለው ለሙሴ ጥገኝነት እና ሚስት ኢትዮጵያ ሰጥታ፣ የፍትህንና የሕግ አስተዳደርን እንዲሁም ነገረ መለኮትን ስለአስተማረችው፣
14.  ከባለፉት 3800 ዐመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ በርካታ  የሴት ነገሥታትን በኢትዮጵያና በግዛቶቿ ላይ ሾማ የሴቶችን መብት በማስከበር በዐለም ግንባር ቀደም በመሆኗ፣
15. ኢትዮጵያ ክጣና ሃይቅ ተነስታ ወደ ኑብያና ግብጽ ወርዳ፣ የግብጽንና ኑብያን ስልጣኔ በመፍጠርዋ፣ ሕልቆ መሳፍርት ወንዶች ፈርኦኖችንና ህንድኬ በሚል ማእረግ 19 የሴት ነገሥታትን በግብጽ፣ በሊቢያና ኑብያ ላይ በመሾሟ፣   
16.  አጼ አክሱማይ የዐለም አባት፣ የነገሥታት እራስ ተብሎ ከባቢሎን ሳይቀር በንጉሦች የተበደሉ ዜጎቹ ለአቤቱታ ወደ እሱ ሲመጡ እምባቸውን ስለአበሰላቸው፣   
17.  ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ በኢትዮጵያ ግዛት፣ በግብጽና በኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት አግኝተው በመኖራቸው፣
18.  ኢየሱስ ራሱን ለዐይሁዳውያን ሳይገልጽ በ22  ዓመት ዕድሜው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ ለኛ ቅድሚያ ሰጥቶ ራሱን ለኛ ገልጾ፣ እስከ 25 ዓመት ዕድሜው ድረስ ሲያስተምርና ሲፈውስ ሃገራችን ውስጥ በመኖሩ፣
19. ኢየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ሲል ግብጽ ሳለ ጥገኝነት የሰጠውን ንጉሥ አማናቱ ተትናይን እግረመንገዱን  ጎብኝቶ፣ ለአንድ ሳምንት እሱ እልፍኝ ውስጥ ሰንብቶ ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንደተሻገረ እልፍኙን ንጉሥ አማናቱ ተትናይ ቤተክርስትያን አደረገው:። ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወቱ እያለ እኛ በዐለም የመጀመሪያውን  ቤተ ክርስቲያን በመመስረታችን፣
20. የንግሥት ሕንደኬ ዣን በጅሮንድ በቅዱስ ፊሊፖስ መጠመቁና እሱ ከአውሮፓውያን ክርስትያንነት ቀድሞ ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባቱ፣
21.   አውሮፓውያን ወደ ክርስትና የተሽጋገሩት ከአረማዊነት ሲሆን ኢትዮጵያውያን ግን ከኦሪት ሃይማኖት ነው። ይህ በመሆኑም የክርስትና እውቀታችንን ከአውሮፓውያን ለማጥለቅና ለማበልጸግ አስችሎናል። በእዚህም እንኮራለን።
22. ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ኢትዮጵያውያን ውስጣቸው የኖርኩ ዘመዶቼ ናቸው፣ በእኔ ያምናሉ፣ እናንተ እነሱን  ለማሳመን ሳትደክሙ አጥምቃችሁ አቁርቡአቸው፣” ብሎ ደቀመዛሙርቱን በርጠለሚዎስን፣ ማቴዎስን፣ ቶማስን ናትናኤልን፣ እንድርያስን እና ማርቆስን ወደ ኢትዮጵያ ልኳቸው፣ ክሃዋርያቱ ግማሾቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለአስተማሩ፣ በእግዚአብሄር እንደተከበርን ስለሚሰማን፣
23. ኢትዮጵያውያን ክርስትያናት እና አይሁዳውያን ያለ ደም መፋሰስ ተስማምተው የኦሪትንና የክርስትናን አምልኮ ስርዐቶች የሚተዉትን ትተው፣ የተረፉትን ወደ ክርስትና በማሸጋገራቸው፣
24. ክኢትዮጵ እስከ አጼ እስያኤል ድረስ የኢትዮጵያ ነገሥታት ክእግዚአብሄር ጋራ በቀጥታ የሚነጋገሩ ሊቀካህናት መሆናቸውና በፈሪሃ እግዚአብሄር ህዝባቸውን በፍትህና ርትህ በማስተዳደራቸው፣ይህም ክስተት በዐለም ላይ የሌለ በመሆኑ፣
25. ነብዩ መሃመድ በችግር ላይ ሳለ ዘመዶቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ኢትዮጵያ ጥገኝነት ስለሰጠቻቸው፣ መሃመድ ራሱ ሙስሊም ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ በመካና በመዲና ውስጥ የራስዋ ቤተክርስትያን ስለነበራትና እሱ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ተጠቃሚና የሊቀካህናቱ ወዳጅ በመሆኑ፣ እንዲሁም በመጀመሪያ አላሁ አክበር ብሎ የጮኸው ድምጸ-መረዋው ኢትዮጵያዊ ቢላል ሃበሽ በመሆኑ፣ ነብዩም “ካልነኳችሁ ኢትዮጵያውያን ላይ ጂሃድ አታኪያሂዱ” በማለቱ፣
26.  በዐለም ላይ በሌለ አኳኋን  ኢትዮጵያ ውስጥ  ሙስሊሞችና ክርስትያኖች በሃይማኖት ልዩነቶች ካለመጋጨታቸውም በላይ ተፋቅረውና ተባብረው፣ ቤተክርስትያኖችና መስጊዶች አንዱ ለሌላው በመገንባታቸው፣ አብረው በመጸለያቸውና ከተዋደዱ ያለ ብዙ ችግር መጋባት በመቻላቸው፣
27.  ቀዳማዊ አባቶቻችን  በዐለም ላይ የሌሉ ብርቅዬ የሱባ እና የሳባ ፊደላትን ፈጥረው ስለአቆዩልን፣
28.  እንደ አክሱምና ላሊበላ ዐይነት ያልተለመዱ ቤተክርስትያናት መኖራቸው፣ ክነሱ የተገኘው ቅዱስ ያሬድ ልዩ ማህሌትን በመድረሱና ክአውሮፓውያን 700 ዐመታት አስቀድሞ የዜማ ምልክቶችን በመፈልፈሰፉ፣ እንዲሁም  የማንንም የማይመስል ቅዳሴና ስርዐተ ዐምልኮ ስለአለን፣
29. በቀለማችንና በተክለ-ሰውነታችን የተቅለመለምን አበቦች ከመሆናችንም በላይ የተለያዩ አልባሳት፣ ዳንኪራዎችና ባህላዊ እሴቶች ስለአሉን፣
30. ከተለያዩ የምግብ አሠራር ሙያዎች በተጨማሪ ለዐለም ምግቦች ያበረከትናቸው እንደ ቡና እና ጤፍ የመሳስሉ አዝእርት ስለአሉን፣
31. ኢትዮጵያ፣ ባለፉት 4000 ዐመታት ጠላቶችዋን ሮማውያንን፣ ግብጾችን፣ አረቦችንና ሌሎችንም በጦርነቶች ድባቅ እየመታች፣ ነጻነታችንንና ክብራችንን በማስጠበቋና ለዐለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነትና የድል አድራጊነት ዐርማ እና ተምሳሌት በመሆንዋ እንኮራለን። አባቶቻችን በኮሪያ ዘምተው፣ በተሰማሩበት የጦር ሜዳ ሁሉ ድል-አድራጊዎች ክመሆናቸውም በላይ አንዳቸውም ባለመማረካቸውና ጠላት ሬሳቸውን አንኳን ለመያዝ ባለማቻሉ ደጋግመን እንኮራለን።     
32. ቀጥሎም፣ ደረታችንን የሚያስነፋን በኢየሱስ ክርስቶስ የደም ስር ውስጥ የእኛ የኢትዮጵያውያን ደም መፍሰሱ ነው። እንዴት ቢሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ዳዊት ዘር በመሆኑና የእሱም እናት አይሁዳውያን አዶልያ ወይም አዴል የሚሏት፣ እኛ ደግሞ ሀብሌ የምንላት የኢትዮጵ የቀጥታ ተወላጅ ኢትዮጵያዊት በመሆኗ።
33. በመጨረሻም በቀዳማዊ ወላጆቻችን ክህነታዊ ማእረግና ክብር እንኮራለን። እግዚአብሄር ሁለት ዐይነት የክህነት ማእረግ ሰጥቶአል። አንደኛው ዝቅተኛውና ለዐይሁዳውያን ብቻ የሰጠው የአሮን ክህነት ሲሆን ሁለተኛው እጅግ ከፍተኛው ለኢትዮጵ አባት ለሳሌሙ ንጉሥ ለመልከጸዲቅ ያቀደው ነው። የአሮን ሹመት ካህንነት ብቻ ሲሆን የመልከጸዲቅ ግን የንጉሥ ንጉሥነት እና የካህን ካህንነት ነው።
መለኮታዊ እና ዐለማዊ ማእረግ ነው። ራዕየ ዮሃንስ አንድሚተነብይልን፤ የዐለሙ ፈጣሪ ኢየሱስ ከርስቶስ ወደፊት በመልከጸዲቅ ስርዐት የካህን ካህን፣ የንጉሥ ንጉሥ ሆኖ በኢየሩሳሌም ላይ የራሱን ምድራዊ መንግሥት መስርቶ ይነግሣል። በዛም ጊዜ አባታችን ሆይ መንግሥትህ ይምጣ፣ ብለን የጸለይነው ይፈጸማል። የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና ንግሥና በአባቶቻችን በመልክጸዲቅ፣ በኢትዮጵ እና በልጆቹ ስርአት ስለሆነ እጅግ እንኮራለን።
የሚያኮሩንን ሁሉ ነገሮች በእርግጥ ዘርዝረን አንጨርሳቸውም። ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የሰፈሩት ናቸው። እነሱን መስፈንጠሪያ ኢድርገን፣ ደረታችንን ነፍተን፣ በኢትዮጵያዊነታችን ታብየን፣ እርስ በርሳችን ተከባብረን፣ ተፋቅረንና ተቃቅፈን በእኩልነት ወደፊት እመር! እንላለን። እንግዲህ ጥንታዊ አባቶቻችንና እናቶቻችን ትልቅ ከነበሩ፣ እኛም የእነሱን አርአያና ፈለግ ተከትለን በመነሳሳት፣ ወደፊት ትልቅ የማንሆንበት ምክንያት የለም።
መላው አፍሪካ ድሮ ኢትዮጵያ ይባል እንደነበር የሚመሰክር ጥንታዊ ካርታ ከዚህ በታች ሰፍሮአል። ያኔ አፍሪካ የታችኛውና የላይኛው አፍሪካ ተብሎ ነበር የተከፈለው። ዝቅ ብለው እሱን ከማየት አይዘናጉ።

Read 8327 times