Saturday, 18 November 2017 13:05

ህዳሴና እምነት፣ ቀንና ሌሊት

Written by  ዘርይሁን አሰፋ (ከብራሰልስ፣ ቤልጅየም)
Rate this item
(3 votes)


   “የባህልና የትውፊት ተቋምን ያገለለው የህዳሴ ፕሮጀክት” በሚል ርዕስ፣ በአቶ ብሩህ ዓለምነህ መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም የተፃፈውን መጣጥፍ፣ በጋዜጣችሁ ድረገፅ ላይ አነበብኩትና እምነቱ ወይም ህዳሴው (ወይም ሁለቱም) የሚመለከተው ሰው፣ አስተያየቱን እንዲሰነዝር የሚጋብዝ ሆኖ ስላገኘሁት፣ የግሌን ኃሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ መቼም ከሚያሳዝኑ ሀገራት በደረጃ አንደኛ ሳትሆን አትቀርም። የፖለቲከኞቻችንና የልሂቃኖቻችን ሥነ-ምግባር በአጠቃላይም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የዕድገት ደረጃ ለሚታዘብ ተመልካች፣ መንግሥትነታቸውን በብዙ ሺህ ዓመታት ከሚያስቆጥሩ ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆንዋን የሚያመላክት አንድም ነገር አይታየውም ማለት ይቻላል። ይህን ጉዳይ የተገነዘቡ አንዳንድ ምሁራን፣ የዚህ አዙሪት ጠንሳሽና አቀንቃኝ የተማረው የህብረተሰቡ ክፍል መሆኑን ይጠቁሙና መነሻው ደግሞ የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት እንደሆነ ያስረዳሉ። የትምህርት ስርዓቱ ዋና ችግር የሆነበትን ምክንያትም ሲያብራሩ፣ ዘመናዊው ትምህርት የሀገሪቱን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጋር የማይመሳሰልና የማይጣጣም፣ ከምዕራባዊያን ተቀድቶ የተለጠፈ፣ የባዕድ ባህል አራማጅ በመሆኑ ነው ይላሉ። በዚህ አመለካከት መሠረት፣ ባለፉት መቶ ዓመታት፣ የሀገሪቱ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ያፈራቸው ትውልዶች በአጠቃላይ ለህብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጡ የማይችሉ የሀገር ዕዳዎች መሆናቸው ነው። በተጨማሪም ይህ ማንነቱን የማያውቅ ትውልድ፣ ሀገሪቱን ላለችበት ምስቅልቅል ያበቃት ስለሆነ መፍትሔ ሊያመጣ የማይችል ከመሆኑም በላይ ከአሁን በፊት ያደረጋቸው ሙከራዎች ሁሉ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዘነ መሆኑን እያየን ነው በማለት ሊያስረዱ ይሞክራሉ። ይህ መላምት ምንም እውነትነት የለውም ባይባልም ለሀገራችን ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ለመሆኑ ግን አጠራጣሪ ነው።
ፅሑፌን በአከራካሪ ጉዳይ የጀመርኩት አቶ ብሩህ ያቀረቡት ሐሳብ፣ ለመግለጽ ከሞከርኩት መላምት የመነጨ ስለመሰለኝ ነው። እንደ ፀሐፊው አባባል፤ “የኢትዮጵያን ህዳሴ ማምጣት የምትችለውና የፕሮጀክቱም ባለቤት መሆን ያለባት በዋነኛነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ነች፡፡” በሐሳባቸው እንስማማ እንኳ ቢባል ህዳሴው በምኞት የሚቀር መሆኑን ከማስረዳቴ በፊት ፅሑፉ ከያዛቸው ስህተቶች አንዳንዶቹን መጠቆም አለብኝ (ሃሳቡ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ይሄዳል ወይ የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው)።
1. “የከሸፉት 4ቱ የነገስታቱ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች” የተባሉትና 4 ነገሥታት ብቻ ናቸው የሞከሩት የተባለው ህዳሴ በኢትዮዽያ የተጀመረው በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ አድርገው አቅርበዋል። ይህ መነሻ ሐሳብ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በፊት በነበሩት ሥርዓቶች እና ከዚያ ወዲህ ደግሞ ከተጠቀሱት 4ቱ ገዥዎች በስተቀር በሌሎቹ ህዳሴ አልተሞከረም ወደሚል አደገኛ መደምደሚያ የሚወስድ ከባድ ስህተት ነው። በኔ ግምት ኢትዮጵያ ውስጥ ህዳሴ በዋናነት የተጀመረው የክርስትናን ሃይማኖት ስንቀበል ነበር ቢባል ይመረጣል።
2. ፈረንጆች ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የእነሱ ህዳሴ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ስላወደመባቸው ነው ብለዋል። ለዚህ በቂ ማስረጃ ቢቀርብለት በተለይም ደግሞ ከፈረንጆቹ ሀገር በህዳሴ ምክንያት የጠፋና ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ባህላዊ እሴት ቢጠቀስ ይመረጣል። እንዲሁም ምንም ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ኢትዮጵያን በዓለም ቁጥር አንድ የቱሪስት መስህብ የሚያስመስል እንደዚህ አይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ ትክክል አይደለም።
3. እንደ ምሳሌና ማነፃፀርያ የቀረቡት የአረብና የደቡብ ኤስያ ሀገሮች አንፃራዊ የእድገት ፍጥነት የማይመሳሰሉ ሞዴሎች ናቸው። ባጭሩ ሲታይ አድገዋል የተባሉት የአረብ ሀገሮች ህዝቦች ከጥቂት ዓሥርተ ዓመታት በፊት በብዛት አርብቶ አደር የነበሩ ሲሆን አሁን አብረቅርቀው የሚታዩት ረጃጅም ህንፃዎችና ሰፋፊ መንገዶች ባጋጣሚ በተገኘ የነዳጅ ክምችት የተነሳ በገንዘብ የተገዛ (ባለ)ሙያና መጤ ቴክኖሎጂ ቅንብር ውጤት እንጂ ምንም አይነት የአካባቢው ሥልጣኔ ባህርይ የለውም። የደቡብ ኤስያ ሀገሮች አመርቂ የእድገት ጉዞ ሁኔታ ከዚህ የተለየ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም በአካባቢው ባሉ በጣም የተለያዩ (ቀደምት) ሃይማኖቶች ለመመራቱ ግን ምንም ማስረጃ የለም። ወደ አቶ ብሩህ ሐሳብ እንመለስና፣ ጥያቄው እውነትም የሃይማኖት ተቋማት ባጠቃላይ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ (ኢኦተቤ) ህዳሴውን በባለቤትነትና መሪነት ሊያገለግሉ ይችላሉ ወይ ነው። ይህ ደግሞ በለፀጉ በተባሉት ሀገራት ህዳሴና የእድገት ጉዞ ውስጥ የዕምነት ተቋማት ሚና ምን ነበር ወደሚለው ይወስደናል። ባጠቃላይ ሃይማኖቶችም ሆኑ የሃይማኖት ተቋማት በየትኛውም አገር፣ በየትኛውም ዘመን የህዳሴ (የለውጥ) ምንጭ፣ ፋና ወጊ ወይም መሪ ሆነው አያውቁም። ሊሆኑ የማይችሉበትም ምክንያት ደግሞ ቀላል ነው፤ የሃይማኖት ተቋማት በመሠረቱ ወግ አጥባቂ ናቸው፤ መሆንም ይጠበቅባቸዋል። የአንዳንዶቹ ህግጋት እኮ ከመጀመርያው በዓለት ላይ የተቀረጹት በቀላሉ እንዳይቀየሩ ሳይሆንም አይቀርም።
ከዚህ በታች የማቀርባቸው ቅንጥብጣቢ ታሪካዊ ማስረጃዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ቢበዛ የህዳሴ ሐሳብ አፍላቂ ግለሰቦችን ማፍራት እንጂ እንደ ተቋም የህዳሴ ባለቤትና መሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ያሳያሉ የሚል ግምት አለኝ። (ይህ በሀገራችን በስፋት ከሚታወቁት ውስጥ ሦስቱ ሃይማኖቶች - ካቶሊክ ፥ እስልምና እና የኢኦተ - በተለያዩ ዘመናት በህዳሴ ላይ የነበራቸውን ተፅዕኖ ለመጠቆም ያህል እንጂ ዝርዝር መረጃ አይደለም።)
1. ፀሐፊው ሃሳባቸውን በሚፃረር መልኩ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የፈረንጆችን፣ የኢኦተቤ ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስን የህዳሴ ጅማሮ በብርቱ እንደተቃወሙት በትክክል ገልፀውታል። (የኢኦተቤ ለአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ አሳዛኝ አፈፃፀም የነበራትን ሚና ሁላችንም እናውቃለን።) ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምሁራን ማፍለቂያ የመሆንዋን ያህል (ትምህርት በስፋት ያለው ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለነበረ) ለምርምር ውጤታቸው ታማኝ በመሆናቸው ብቻ ከግትር መለኮታዊ ትምህርቷ ያፈነገጡ የመሰላትን ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎችን ለቁም እስረኝነት፣ ለግዞት እንዲሁም ለአሰቃቂ ሞት ቅጣት መዳረጓ በሰፊው የሚታወቅ ነው። አንዳንዶቹ የምርምር ውጤቶች እውነትም የዕምነት ምሰሶዎቿን የሚቦረቡሩ በመሆናቸው ቤተክርስቲያኒቱ አደጋውን ለመቋቋም የነበሯት አማራጮች አንድም አብሮ መቀየር ወይም ደግሞ ግኝቶቹን ማውገዝና ማፈን ካስፈለገም ተመራማሪዎቹን ማስወገድ ናቸው። ምርጫዋ ሁለተኛው መሆኑን በፍጥነት የተገነዘቡት የህዳሴው መሪዎች ቤተክርስቲያኒቱን ከማግለልና ከሷም ከመራቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ዛሬ በምዕራቡ ዓለም የሚታየው ሥልጣኔ የዚያ ጊዜ ትግልና መስዋዕትነት ውጤት ነው። ለዚህም ነው ምዕራባውያን እነዚያን ስደትንና ሞትን የተጋፈጡትን የለውጥ ሐዋርያት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያወድሷቸው የሚኖሩት።
2. የእስልምና ሃይማኖት በመጀመርያዎቹ 600 ዓመታት ቆይታው፣ በማህበረሰቡ የዕለት ኑሮ ላይ አሁን በሚታወቀው ደረጃ ወሳኝ ሚናና ተፅዕኖ አልነበረውም ማለት ይቻላል። ይህ በስፋት የሚታወቀው ለሌሎች ዕምነቶችና ለሳይንሳዊ ምርምር በነበረው ታጋሽነትና ድጋፍ ነው። ከዚህም የተነሳ አረባውያንና የፋርስ ተመራማሪዎች (አንዳንዶቹ ሙስሊም ባይሆኑም) ከሌላው ዓለም ሁሉ ቀድመው በሒሳብ፣ በሥነ-ሕይወት፣ በሕክምናና በሥነ-ምህዋር በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች በጣም የረቀቁ ነበሩ። ከዝነኛው የቁጥር ሥርዓት አንስቶ እስከ ጠፈር ምርምር ድረስ ብዙው የዓለም ሥልጣኔ ከሙስሊሞችና በእስልምና ሃይማኖት ሥር ይተዳደሩ ከነበሩት ሌሎች ሕዝቦች የተወረሰ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ አለ። ጥያቄው ሥልጣኔው ለምን ተገታ፤ እንዴትስ ሊገፉበት ሳይችሉ ቀርተው ተቀሙ ሲሆን መልሱም ባጭሩ ሃይማኖት ጣልቃ ስለገባበትና የመሪነቱን ሚና ስለያዘ ነው። (ዝርዝሩ ለሌላ ጊዜ ይቆየን።)
3. የኢኦተቤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከገዥው ንጉሣዊ ቤተሰብ ስለጀመረች ሳይሆን አይቀርም የሀገራችንን እና የህዝቦቿን ዕጣ ፋንታ የመወሰን ዕድል ነበራት። ይህን ዕድልም በበጎ እንዲሁም በአሉታዊ መልኩ በሰፊው ተጠቅማበታለች ማለት ይቻላል። ባለፉት 1600 በላይ ዓመታት በብዙ ፈርጅ የሀገሪቱና የህዝቦቿ የዕድገት ፍጥነትና አቅጣጫ ላይ ወሳኝ ተፅዕኖ ነበራት። በተጨማሪም አጠቃላይ ስነልቦናችንና የተለያዩ ባህላዊ እሴቶቻችን የተቀረጹት በቤተክርስቲያን ትምህርት ነው። ኢትዮጵያዊ በመሆናችን ብቻ የምንጋራቸው ወጎችና ልማዶች፣ ምግብና አለባበስን ጨምሮ ብዙዎቹ እሴቶቻችን የቤተክርስቲያን (በጎ) ተፅዕኖ ይንፀባረቅባቸዋል። በጣም የሚያሳዝነው ግን በነበራት ፈላጭ ቆራጭነት ሚናዋና ያላትን ተፅዕኖ አሳዳሪነቷን ተጠቅማ ያፈለቀችው ወይንም ኮትኩታ ለፍሬ ያበቃችው የሀገር ህዳሴ እንቅስቃሴ አለ ቢባል እንኳ ለብዙዎቻችን ግልፅ አይደለም። በአንፃሩ ደግሞ ከውስጧ ወይንም ከአካባቢዋ በተለያዩ ዘመናት የተነሱ አዳዲስ ሃሳቦችን የነበራትን አቅም በሙሉ ተጠቅማ ከግብ እንዲደርሱ ከማድረግ ይልቅ ባጭሩ እንዲቀሩ (ሲብስ ደግሞ እንዲታፈኑም) አድርጋለች። ከላይ እንደተጠቀሰው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን “ቢሆንስ ኖሮ” የሚያሰኝ የኢትዮጵያ ባለ ብዙ ፈርጅ የተሃድሶ ሙከራ ግንባር ቀደም ተቃዋሚ የኢኦተቤ ነበረች። ይህ ሚናዋ ተድበስብሰው ከቀሩት የታሪካችን ክፍሎች አንዱ ሲሆን ለዚህ ፅሑፍ መልዕክት ከግምት ውስጥ እንዲገባልኝ እንጂ ወደ ዝርዝሩ የመግባት ዓላማ የለኝም። ቤተክርስቲያኒቷ ለህዳሴ ወይንም ለበጎ ለውጥ ሰፊ ዕድልና ብቃት እያላት ዝግጁነት ግን የሌላት መሆንዋን ለመረዳት፣ ትንሽ ወደ ኋላ በታሪካችን ተመልሰን ግለሰቦች በውስጧ የጀመሩትንና ያገኟቸውን ዕጣ በሦስት ምሳሌዎች እንመልከት።
1. ቅዱስ ያሬድ ድምፅን በምልክት በመተካት ዜማዎች እንዴት ሊለያዩ እንደሚችሉ ያበሰረው ግኝት ቢያንስ በአህጉራችን በሙዚቃ ዘርፍ ታይቶ የማይታወቅ ድንቅ እመርታ ነበር። ዳሩ ግን ይህ ሥራ፣ የሰው ልጅ የድካም ውጤት ሳይሆን አንዴ በነፋስ ከሚወዛወዝ ዛፍ ወይም ከወፍ ጫጫታ በመላዕክት እርዳታ የተቀዳ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለቤ/ክ አገልግሎት ብቻ የሚውል ፍፁም መለኮታዊ ስጦታ በማስመሰል ሳይሻሻልና ሳይስፋፋ ከሞላ ጎደል እንደነበረ በቁጥጥሯ ሥር በጅምር እንዲቀር አድርጋለች።
2. በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘርዓያዕቆብና ተከታዮቹ የጀመሩት የፍልስፍና ጥንስስ ሥራ በተለያዩ ሰበቦች (ሥነ- መለኮትንና አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ይፈታተናል የሚሉ አሉ) ታፍኖ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሰፊው ሳይታወቅ ቆይቷል። ከዚህም የተነሳ አፍሪካ ውስጥ ፍልስፍና የለም፣ ጥቁር ህዝቦች ፍልስፍና አያውቁም እስከ ማለትም ተደርሶ ነበር።
3. አባ እስጢፋኖስ በ15ኛው መቶ ክፍለዘመን የጀመሩት መንፈሳዊና ሀገራዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ምንም ውጤት ሳያሳይ ተደምስሶ ተከታዮቻቸው (ደቂቀ-እስጢፋኖስ) ለስደትና ለዘግናኝ ጭፍጨፋ የተዳረጉት በአፄ ዘርዓያዕቆብና በቤተክርስቲያን ትብብር ነው። ይህ “ቤተክርስቲያንን ያመለጠ ዕድል” የተባለለት የተሃድሶ እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ባልሆነ መልኩ እንኳ (የቴክኖሎጂ ሙከራዎቻቸውን መጥቀስ ይቻላል) በህብረተሰቡ ውስጥ ወደፊት እንዳይራመድ ስለተደረገ፣ ኢትዮጵያን ያመለጣት ብርቅዬ ዕድል ነበር ማለት ይቻላል።
እነዚህና ሌሎችም በረጅም ጊዜዋ ለህዳሴ የነበራት አመለካከቶች ሲገመገሙ፣ ቤተክርስቲያናችን እንደ ተቋም ለለውጥ ዝግጁ አለመሆኗን በግልፅ ያሳያሉ። በሌላ አባባል፣ በአሁን ጊዜ አለ የተባለውን ህዳሴ በሃላፊነት ለመምራትም ሆነ ሌላ አማራጭ ሐሳብ ለማፍለቅ የሚያስችላት ተዓማኒነትና አስተማማኝ ቀዳሚ ታሪክ ይጎድላታል። እንዲያውም በፖለቲከኞችና በሌሎችም ለሚሞከረው የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ በሙሉ ልብ አጋር ትሆናለች ለማለትም አያስደፍርም ባይ ነኝ። የለውጥ ተከላካይነት ደግሞ የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መለያ ባህርይ ስለሆነ ሊያስወቅስ አይገባም፤ ሃይማኖት እንደ ፅንሰ-ኃሳብ ሲወርድ ሲዋረድ ይኖራል እንጂ ትውልድ በተቀየረ ቁጥር አይከለስም።
በመጨረሻም “ስዩመ-እግዚአብሔር” የሚባሉ ወንዶች ብቻ ለዕድሜ ልክ የሚመሩት ማንኛውም ተቋም፣ ምናልባት ለራሱ ህልውናና መልካም አስተዳደር ህዳሴ ያስፈልገው እንደሆን እንጂ የሀገር ህዳሴ ጀማሪም ሆነ መሪ ሊሆን አይችልም፤ አይገባምም። የካሁን በፊቱን ተፅዕኖንም መላቀቅ ከባድ ፈተና ሆኗል፤ የአስተዳደር፣ የትምህርት፣የአገልግሎት ወዘተ ተቋሞቻችን ትልቁ ችግር፣ ከሃይማኖት ተቋማት በተወረሰ፣ ምላሽ ሰጪነት በሌለው ግትር የሥልጣን ተዋረድ ሞዴል ስለተቀረፁ ይመስለኛል።

Read 1854 times