Saturday, 18 November 2017 13:09

የበላይ በቀለ ወያ አዳዲስ ግጥሞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)

    ሁለት የግጥም መጻህፍትን ለንባብ ያበቃው ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ፣ አሁንም ሌላ የግጥም መጽሐፍ አበርክቷል - “ከሴትኛ አዳሪ የተኮረጀ ሳቅ“ በሚል ርዕስ። ምንም እንኳን የግጥም መጽሐፍ ርዕስ ዝርው መሆኑ ለምን እንደተመረጠ ባላውቅም ሃሳቡን እስክናገኝ ገጾች ገልጦ፤ ምስሉን ማየት ምናቡን መለካት፤ ሙዚቃውን በልቦና ማላመጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በላይ ከዚህ ቀደም ባሳተማቸው መጻህፍት በጥልቅ አተያዩ ድንቅ የሚባል ተሰጥኦ ያለው በመሆኑ እንዴት አሰበው? የሚለውን ነገር፣ መቸም አናጣውም ብለን ብንወራረድ አያሳፍረንም።
በጭብጥም ደረጃ ሀገር፣ ፍቅር፣ እምነትና ሌሎችም ጉዳዮች በራቸው ሳይንኳኳ አይቀርም። ሽሙጦቹ ቆንጣጭ ናቸው። የየዕለት ኑሯችንን፤ ስንገባ  ስንወጣ የሚገላምጡንንና የምንገላምጣቸውን ነገሮች፤ በየጓዳችን አፍነን ትንፋሽ ያሳጣናቸውን  ነጻነቶች ፈልፍሎ  የማውጣት አቅምም አለው። በተስፋ ትኩሳታችንን፣ ህመማችንን፣ መተንፈሻ ያጣንላቸውን የሚሊዮኖች ሃሳብ ባንድ ሳንባው ይተነፍስልናል። ለምሳሌ የፖለቲካ ድምጻችንን ለዘብ ባለ ሁኔታ በተዋዛ ጥበብ እንዲህ ይተነፍሰዋል፡-
   “ለመንግሥት የተጻፈ ደብዳቤ”
እንደምነህ መንግሥት እኔ አለሁ በደህና
ባመቻቸህልኝ የልማት ጎዳና።  
ታክሲ ለመጠበቅ ሰልፍ ተሰልፌ፤
ለወንበር ስጋፋ ኪሴን ተዘርፌ፤
ለማይሰራ መብራት ቀብድ እየከፈልኩኝ፤
ለማይሰራ ኔት ወርክ ካርድ እየገበርኩኝ፤
በሰጠኸኝ ዕድል ቆንጆ ሴት አፍቅሬ፤
የማይወጣ ውሃ የማይመጣ መብራት፤
የማትመጣ ሴት አንድ ላይ ቀጥሬ…
የተወሰኑ ስንኞች እንኳ ብዙ ይናገራሉ፡፡ የሃገር ሰው በልቡ ምን አለ? የእምባና ሳቁ ግራፍ የትና የት ነው? …በላይ በቀለ በስላቅና በገደምዳሜ እየነገረው ነው። ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፤ንፋስ እንደ መጎሰም ነው የሚል አንድምታ አለው። መንግሥት ተመቻችቷል ይላል፤ ህዝብ ታክሲ አጣን መብራት አጣን፤ ሌባ ፈጀን እያለ ነው። ቴሌና መብራት ሃይል የሞቱ ያህል ተቆጥሮ ነጠላ ቢሸረጥላቸው ይገባል የሚል ስሜት ፈጥሯል (ምናልባት ቴሌ አሁን ነጻ እየወጣ ይመስላል።)
ይህኛው ግጥም ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የገጣሚው ብዙ ሥራዎች አይሰለቹም። ዘና አድራጊ ናቸው። በፈረጠሙ የቃላት ጡንቻዎች ልብን አይደልቅም። ልስስ ባለ ፍሰት ስሜት ይኮረኩራሉ። ምሁራን እንደሚሉት፤ ማዕከላዊ ሃሳቡን ለማወቅ አያምታታም፣ ወደ ግቡ ይፈስሳል፣ ዓላማውን ለማሳካት የፈሰሰበት ሃዲድ ባግባቡ ተሳክቷል ወይ? ያነሳውስ ጭብጥ ያን ያህል አስፈላጊ ነው የሚለውን ያሳካ ግጥም ነው።
የገጣሚው አንድ ልዩነት፣ ግጥሞቹ ቁጣ ያዘሉ ቢሆኑ እንኳ በሳቅ መጠቃለላቸው፣ በዋዛ መተረካቸው ነው። በንዴት ሳይንተገተጉ አንባቢ ልብ ውስጥ ገብተው ጮኸው የሚረብሹ፣ ኮርኩረው የሚያስቁ ሃሳቦች አሉት፤ ሲፈላሰፍም ከፍታ ላይ ወጥቶ ጢሙን እየሸረበ እንደሚያወራ ሰው አይደለም። ገበያ መሃል ረጋ ብሎ እንደሚጓዝ ሰው እንጂ!
ግጥሞቹ ለአንዳንዱ ትዝታ፤ ለሌላው የዛሬ ህይወት፤ ለሌሎችም ተስፋ ያዘለ ነው። ሳቅን ቆስቋሾች፤ ልዝብ ሽሙጦች፤ የዕለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኞች ናቸው። ያልገባኝ ያልገባት፤ ፍቅር የያዘው ሃብታም የጻፈው ግጥም፤ የአፍቃሪ ዕድልና ሌሎችም ፍቅርን በማሽሞንሞን፣ መዓዛውን ወደ ነፍስ በማስጠጋት፣ እሣት በማውለብለብ ያርገበግቡታል፡፡
     እስቲ  “ከናፍቆትና ከእንቅልፍ”
…ትናንት ናፍቀሽኛል “ተኝታለች” አሉኝ
ስልክሽን ያነሱት እናትሽ መሰሉኝ፤
“መሰሉኝ” አለ አይደል
እንዲህ ነው እንግዲህ
እርግጥ መሆን ሲፋቅ የሚያውቁት ሲነደል።
ዛሬ አንቺ ደወልሽ “ናፍቀኸኛል” አልሺኝ
ልጠይቅ ከልቤ ልጠርጥር ከሆዴ
መናፈቅን የሚያውቅ
እንቅልፍ ይሉት መንገድ ይወስደዋል እንዴ?
ልጠርጥርሽ ደግሞ
ልጠይቅሽ ደግሞ ሙሽራዬ ውዴ።
እንቅልፍ ከናፍቆት በላይ፣ ከፍቅር ነበልባል እኩል አይደለም። ምናልባትም ፍቅር ይህ የዕውን ዓለም ስለሚጠብበው፣ ወደ ህልም ዓለም ጎራ እያለ፣ የሰውን ልጅ የኑሮ ወሰን ያሰፋዋል። ስለዚህ  በርካታ ከያንያን ዜማ የተነከሩ ግጥሞችን አቀንቅነዋል።  ችቦ ለኩሰው ሞቀዋል። እየጠዘጠዛቸው አቃስተዋል። “እያመመ የሚጣፍጥ!” ብለው አያዎነቱን መስክረዋል። የልቦለድ ደራስያንም በትርክታቸው ቃላት፣ በመቸታቸው ዓለም፣ በገጸ ባህሪዎቻቸው አንደበት፣ ፍቅርን ገላጭ ህይወት ልጠው አሳይተውናል። በላይ በቀለም ያሳየንና የሚያሳየን ይህንኑ ነው።
ስልክ መደዋወል የጦፈ ፍቅር ግርግር ነው። በእናት እጅ መውደቅ፣ የስልክ በሌላ ሰው መነሳት--- ስብራት የሚያክም ዕውነት ነው።… “የፍቅር ግርግር ቀልቡን የነሳው ሰው፣ ስልኩን ያነሳው ማን እንደሆነ እስኪጠፋው ዞሮበታል!”  እያልን ነው። ለምንም ነገር እርግጠኛ መሆን ያቅታል። መባተት ይበዛል። ንፋስ ይኮናል፤ነፍስ ወዲያ ወዲህ ትነፍሳለች እንደማለት ነው። ቅጥ አምባሩ ይጠፋል፤ በትዝታው ክራር ይገዘግዛታል።
ተራዋን እርስዋም “ናፍቀኸኛል” ብላዋለች እናም የናፈቀ ሰው እንቅልፍ ይወስደዋል ወይ እያለ፣ ስለ ፍቅር ሰሞን ስንኞች ያዋድዳል። አንዳች ሃሳብ አንዳች ገጽታ--- የሆነ ግርግር ይታየናል። እናትዋ ነጠላቸውን አጣፍተው ስልኩን ብድግ አድርገው… ብቻ ብቻ የሆነ የፍቅር ትርምስ!… የጎረምሳ ግሳት፤ የወጣት ድልብ ልብ!… የፍቅር ሰቀቀናዊ ዜማ፣ ሳቃዊ ትርክት… የእንባ ሳቅ!
“ፍቅር የያዘው ሃብታም የጻፈው ግጥም” የሚለው ትንሽ ወደ ማፈገጉ ያዘነብላል። የደሃውን ገጣሚ ግጥም ለማኮሰስ መሃል ያለችውን ተፈቃሪ ለመጠየቅ ፍልሚያ ነው። ርዕሱ ያን ያህል ባይረዝም መቼም ደግ ነበር። ርዕስ ቅልብጭ ሲል ይጥማልና!
እንዲህ ነው ግጥሙ፡-
“እመጣለሁ ብለሽ” ከቀጠርሽኝ ቦታ
ዕድሜ እንደ “ቅጽበት” ዘመን እንደ “አፍታ”
ቆሜ ስጠብቅሽ፤ ሳላገኝሽ ያልፋል
ስትቀሪ ጊዜ
ዘላለሜ ባክኖ፤ ናፍቆትሽ ይገዝፋል።”
ምናምን እያለ
በቃል አሳምሮ፤ የሚጽፍ ብሶቱን
ደሃ ገጣሚ ነው፤ ልንገርሽ እውነቱን
ይህ አንጓ ደሃውን ገጣሚ እየተቸ ሀብታሙ የጻፈው ነው። እርሱ ቢሆን ግን እንዴት እንደሚያደርግ እንደዚህ ደርድሮታል።
እናልሽ የኔ ውብ በፍቅርሽ ተቃጥላ፤ ነፍሴ ብትቀልጥም
ቆሜ ስጠብቅሽ
ዕድሜዬ አያልፍም፤ ዘመኔ አያመልጥም
ባለሽበት ቦታ “ ሳልቀጥርሽ ላግኝሽ”፤ ሚል ነው የኔ ግጥም።
ዋይ ዋይ የሚለውና ጉዳዩን እያካበደ ቋጥኝ በራሱ የሚጭነው ደሃው ገጣሚ ነው። ዕድሜ ገባሪ፤ አልቃሽ ሆደ ባሻ፣ ዘመኑን በርካሽ የሚሸጥ እርሱ ነው። እኔ ግን እንኳን ቀጥሬሽ ሳልቀጥርሽ አገኝሻለሁ።” ብዬ ነው ግጥሙን የጻፍኩት ነው የሚለው። ለዛ ባለው ቃል በሽሙጥ የልቡን ይናገራል። ወደ ዘመናችን ብብት ሥር ገብቶ የምንደነቅበት ሃሳብ አለው። የሚጎነትለው ስንፍናም አለ። የሚሳለቅበትን ዕውነት አከማችቷል። በዜማ እየወለወለ የጎሪጥ እያየ፣ ግጥሙ ብዙ ጉድፎችን ያሳያል። የተፈጥሮንም የሰውንም ልብ ይሰልላል። የተጋነኑ ኩሸቶችንም በቃላት ይነርታል። ሁለቱን ገጣሚያን በትይዩ አቁሞ፣ በዚያች ተፈቃሪ እንስት ላይ ያለውን እሰጥ እገባ እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋባል።
ይህ ገጣሚ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ለሥርዓተ ነጥቦች ዋጋ ይሰጣል። ሥርዓተ ነጥቦች ሃሳብ ያፋልሳሉ፤ ትርጉም ያስታሉ፤ ዜማ በመስበር አንካሳ ያደርጋሉ። ድምጸት ያባክናሉ፤ ስለዚህ ከግባቸው አይደርሱም። አንባቢውም ባይተዋር ይሆናል። ይህንን በላይ አጥብቆ የተረዳ ይመስላል- ይበል ያሰኛል።
ሌላው በንቡር ጠቃሽ ዘይቤ የጻፈው “ኢትያጵያዊው ዘኬዎስ!” የሚል ግጥሙ የዛሬ ዳሰሳዬ አካል ነው።  የመጽሃፍ ቅዱሱ ዘኬዎስ፣ በዘመኑ ቀራጭ የነበረ ቱጃር ሲሆን ቁመቱ አጭር ስለሆነ በወቅቱ የአገልግሎትና አስተምህሮት ዝናው የናኘውን ኢየሱስን ማየት ፈልጎ፣ በህዝብ ግርግር ምኞቱ ስላልተሳካለት ዛፍ ላይ ወጥቶ ኢየሱስን የተመለከተውና ኢየሱስ ክርስቶስም ዓይን ውስጥ የገባ ሰው ነው። ሰውዬው ከዚያም ባለፈ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ “እቤትህ ገብቼ ራት እበላለሁ!” ብሎ ያስደነቀው ሰው ነው። ያንን ሰው በላይ በቀለ ወዲህ አምጥቶ እንዲህ ጽፎለታል።
እኔ እንደ ዘኬዎስ ቢያጥርብኝ ቁመቴ
ጌታ አንተን ለማየት፤ ዛፍ ላይ ከመውጣቴ
“ና ውረድ ከዛፉ
እራት ካንተ ጋር ነኝ እንዳትለኝ አምላክ!
ከመውረዴ በፊት
እራት እንድትበላ፤
በቤቴ ያለውን ባዶ ሌማቴን ባርክ።
ልዩነቱ ምጣኔ ሃብታዊ ነው። የዚያኛው ቤት ሙሉ፣ የዚህኛው ጎደሎ ነው። ያኛው ቤት ለገባ እንግዳ የሚያቀርበውን ነገር አያጣም። ይኼኛው ግን ሌማቱ ባዶ ነው። ስለዚህ የመጀመሪያ ጸሎቱ እንጀራ ነው። ድህነት ነው። “ፍቅርህን ለመግለጽ ቤቴ ስትመጣ ስቄ እንድቀበልህና እንዳልሳቀቅ እንጀራዬን አስቀድም!” የሚል ነው። በደንብ ስንበረብረው ትንሽ ህመም ያለው፣ የፈጣሪን ፍቅር ለማጣጣም እንኳ የማያስችል የዳቦ ዱላ አለብን እያለ ነው። የጸሎታችን ሀ እና ፐ እንጀራ ወይም ዳቦ ነው። አባታችን ሆይ ብለን ከልብ የምንጸልይበት ቦታ የዕለት እንጀራችንን ስጠን የሚለው ነው ብለን፣ ሃሳቡን ልንለጥጠው እንችላለን።
ግጥሙ ግሩም ሃሳብ ያለው፣ ማሰብ የሚያስችልና የሚያመራምር ነው። ትንሽ ድክመቱ አሰኛኘቱ ላይ ነው። ምክንያቱም ሦስተኛውና አራተኛው ሃሳብ፣ ተዋረዳዊ ግጥምጥሞሽ እንዲኖራቸው ባንድ ማለቅ ነበረባቸው። ከዚያ ውጭ መነጣጠሉ ከማፍረስ ውጭ የትርጉምም ሆነ የውበት ለውጥ አላመጣም። ሃሳቡ ግን ጥልቅና ንጽጽሩም በሩቅ ዘመን ህይወት ያለውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥያቄ ትኩረት የሚጠቁም ነው። ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላም የኛ ጥያቄ ከዳቦ አላለፈም።
“ከሴትኛ አዳሪ የተኮረጀ ሣቅ” በሚል ርዕስ የታተመው የበላይ በቀለ ወያ መጽሐፍ ጠቅለል አድርገን ስናየው፣ ከቀደሙት ሥራዎቹ ይልቅ ከፍ ያሉ ሃሳቦች የተዳሰሱበትና ርዕሰ ጉዳዮቹም በሰፋና በጠለቀ መልኩ የታዩበት ነው። የዜማቸው ስልትም ጥሩ ነው። እንደ አብዛኛዎቹ የዘመናችን ግጥሞች፣ ዜማ እየሰበሩ አያነክሱም። ምናልባትም ረሃባቸው የላቀ ቋንቋ፣ ከፍ ያለ ዘይቤ ነው።…. ያንን ደግሞ በተለያየ መንገድ ማካካስ ይቻላል!... ይሁንና የአብዛኛዎቹ ግጥሞች ቅርጽ ተመሳሳይ መሆኑ አሰልቺ ያደርገዋል የሚል ፍርሃት አለኝ። ከዚህ በፊት እንደምናውቃቸው የአገራችን ገጣሚያን፣ በተለያዩ ቅርጾች መጻፉ ተወዳጅነቱንና ጣዕሙን ይለውጠዋል። ገብረ ክርስቶስ፤ ጋሽ ጸጋዬ፤ ነቢይ መኮንን፤ ወንድዬ አሊና ሌሎችም ለዚህ ማሳያ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ቢሆንም በላይ በቀለ በንባብ ወደ ፊት ከቀጠለ፣ ላቅ ያለ ምናብ ያለው፣ ንስር ዓይኖችን ያበቀለ ባለ ተስፋ ገጣሚ ነው።

Read 2385 times