Sunday, 19 November 2017 00:00

ከጨንቻ እስከ ዳላስ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

  የአሰፋ ጫቦ ነገር እንደ አንቲገንና የክሪየን ያለ የሞራልና የፖለቲካ ውዝግብ ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ መሳሳትና ትክክል መሆን ከማይጠየቅበት ሆኜ አየሁት፡፡ በብቻ አደባባይ ሳለሁ፤ አሰፋ ጫቦን ሳየው በሐሳቦቼ ከተማ አንድ ሥፍራ ይዞ ተቀምጧል፡፡ ይህ ከ10 ዓመት በላይ በእስር የቆየው፤ ከ20 ዓመታት በላይ በስደት የኖረው፤ ከልደቱ ጨንቻ ተነስቶ፤ 67 ዓመታትን ተራምዶ፣ በዳላስ ያረፈው የብዕር ሰው፤ ህይወቱ እንደ ‹‹ፎረስት ጋም›› (Forest Gump) ያለ ዘይቤ አለው፡፡ አሰፋ ከጨንቻ እስከ ዳላስ በሩጫ ተጉዟል፡፡ ህይወት ‹‹Run Asefa Run›› ትለዋለች፡፡ አሰፋ ይሮጣል፡፡ ጺሙን አጎፍሮ ይሮጣል፡፡ ከኩተት እስከ ሽበት ይሮጣል፡፡ በፊደል ቴሌቪዥን የሚያዩት ሁሉ ይከተሉታል፡፡ እርሱም በየፌርማታው ለሚያገኛቸው አረፍ እያለ ህይወትን ያወራል፡፡ እርሱ ዝም ብሎ ያወራል፡፡ ትውልዶች እየተፈራረቁ ያዳምጡታል፡፡ ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ምልከታው፣ ስለ ገጠመኙ፣ ስለ ጉዞው፣ ስለ ጨንቻ ስለ ኢትዮጵያ ወዘተ-- ያወራል፡፡
አሰፋ አነጋጋሪ ሰው ነው፡፡ ባቡርና አውቶቡስ የሚጠብቅ የህይወት መንገደኛ ሲገጥመው ጠጋ ብሎ ያወራል፡፡ አሰፋ little talk ይችልበታል። አሰፋ ወሬ ያውቅበታል፡፡ ታላቅ ‹‹ወሬኛ›› ነበር። ከፌርማታ አግዳሚ ወንበር ተቀምጦ ባቡር የሚጠብቅ ሰው ሲያገኝ ጨዋታ መለኮስ ይችላል። የሚያመጣውን ጨዋታ የውሃ መንገድ ማስያዝ ይችልበታል፡፡ ከአሰፋ ጋር ከተገጣጠማችሁ፤ ለአፍታም ቢሆን የጊዜን ጫና ቀለል ለማድረግ ዕድል አታጡም፡፡ ሽፍንፍኑን ገላልጦ ለማየትና ተዝናንቶ ለመቆየት የሚረዳ ጨዋታ አታጡም። ከአሰፋ ጋር የተገጣጠመ ሰው፤ ‹‹እስኪ ጨዋታ አምጣ›› አይለውም፡፡ አሰፋ ጨዋታ ነው፡፡ እርሱ ካለ ጨዋታ ይኖራል፡፡ ጨዋታ ሲያቀባብል ግሩም ነው፡፡ አመጣጡ እንደ ሽምቅ ተዋጊ ባልታሰበ መንገድ ነው፡፡ አሰፋ ሲያወራ መንገደኛን ከመንገዱ ያስተጓጉላል፡፡ ያዘናጋል፡፡ አሰፋ ሲያወራ ቀልብ አስከፍቶ ነው፡፡ ለዚህ ብዙ መላ አለው፡፡ በአጻጻፍ ብልሓቱ ከአንባቢ ጋር ልዩ ቅርበት መፍጠር ይችላል፡፡
ሆዱ ባዶ እስኪሆን ምስጢሩን የሚያወጋን ይመስላል፡፡ ይህም አንባቢን የቅርብ ሰው ወይም ጓደኛ የማድረግ በር ይከፍታል፡፡ በእንዲህ ያለ ወሬ ህይወትን ዘበት ያደርጋታል፡፡ ወሬ መወጠን፤ መቋጨት እንደ ከብት ወደ በፈለገው መስክ የማሰማራትና መልሶ ከፈለገው በረት የማሳደር ልዩ ጥበብ ያለው የወሬ እረኛ ነው፡፡ የተለያዩ የወሬ ክራር ክሮችን በፈለገው ስልት ቃኝቶ የሚፈልገውን ዜማ ማምጣት ይችላል፡፡ አካሄዱን ያልታሰበበት፤ ድንገቴና ቅጽበት ዘራሽ ሲያደርግ ያውቅበታል፡፡ የወሬ ሐይማኖት ማስቀየር ይችላል፡፡ ‹‹አላስቀምጥ የሚልን ሐሳብ ገለል የሚያደርግልኝ ወዳጄ፤ ወሬ ነው›› ይላል ኮልርጅ፡፡
አሰፋን በደንብ ሊገልጸው የሚችል አሰፋ ብቻ ነው፡፡ አሰፋ ታሪክ ነው፡፡ ሥነ ጽሑፍ ነው። ፖለቲከኛም ነው፡፡ የ1960ዎቹን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመረዳት ወይም ለመጻፍ የሚሞክር ሰው፤ አሰፋን ማማከር ያስፈልገዋል በሚያሰኝ መጠን ያውቀዋል፡፡ በዚህ ዘመን ላይ ያተኮረ የታሪክ ሥራ አሰፋን ሳይጠቅስ ሊሟላ አይችልም። አሰፋ የታሰረና የተሰደደ አጨቃጫቂ የብዕር ሰው ነው፡፡ ብዕሩን ቸል ለማለት አይቻልም፡፡ ‹‹ምን ታደርጊዋለሽ›› አስብሎ እና በዋልድባ አስዘፍኖ የሚገዛ ጸሐፊ ነው፡፡ የአሰፋን የብዕር ውበትና ብቃት ሳይመሰክሩ ትክክል ከመሆን፤ ይህን በማድረግ መሳሳት ይሻላል የሚያስብል ጸሐፊ ነው፡፡
አሰፋ በአንድ የኪነ ጥበብ ሥራ ከሚገኝ ሥነ ጽሑፋዊ ለዛ የበለጠ ውበት ባለው አኳኋን መጻፍ የሚችል ነው፡፡ ዘይቤዎቹ አንጀት አርስ ናቸው። ምልከታዎቹ እንደ ግጥም ጣዕም አላቸው፡፡ አጻጻፉ የፖለቲካ ሰውነቱን ሁለተኛ ደረጃ ለማድረግ የሚያስገድድ ነው፡፡  ማንኛውም የሥነ ጽሑፍ ሥራ ፖለቲካዊ ሊሆን የሚችለውን ያህል፤ የአሰፋ የፖለቲካ ጽሑፎች ሥነ ጽሁፋዊ ናቸው፡፡ አሰፋ በአንድ ጊዜ ዘመድና ባዕድ ነው፡፡ አጨቃጫቂ ሆኖ እንደኖረ፣ አጨቃጫቂ ሆኖ አረፈ፡፡ በህይወቱ ሞትን ታቅፎ ኖረ፤ እስኪ በሞቱ ህይወትን ያግኝ፡፡

Read 1056 times