Saturday, 18 November 2017 13:29

መሐመድ አሊ የምንግዜም ምርጥ ቦክሰኛ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 ይህ የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ በየጊዜው የሚቀርበው፤ ‹ታላላቅ ስፖርተኞችን አስደናቂ ብቃታቸውንና የህይወት ዘመን ታሪካቸውን ባስታወስን ቁጥር ለዛሬም ለወደፊትም የመንፈስ ብርታት ይሆነናል› በሚል ነው

              
   ቦክሰኛ የሆነበት አጋጣሚ የተፈጠረው በ12 ዓመቱ ነበር፡፡ በ1954 እኤአ ብስክሌቱን ሰረቁበት። በሊውስቪል ኬንታኪ ለሚገኝ ጆ ማርቲን ለተባለ ፖሊስ ስርቆቱን አመለከተ፡፡ ፖሊሱ የቦክስ አሰልጣኝ ስለነበር እንዴት መደባደብ እንደምትችል በመጀመርያ ተማር ብሎ መከረው፡፡ ከ6 ሳምንታት በኋላ በሰፈሩ በአንድ አማተር የቦክስ ግጥሚያ ላይ ለመሳተፍ ችሎ አሸነፈ፡፡
የዓለም ሻምፒዮን ብቻ አልነበረም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና በመላው ዓለም  በስፖርት እና በታላቅ ስብዕና እንደተምሳሌት ለመታየት የበቃ ነበር፡፡ የቦክስ ስፖርትን ጥበባዊ ገፅታ በማላበስ ባለውለተኛ ፤በታሪክ የምንግዜም ምርጥ ቦክሰኛ የተባለ እና ሊረሱ በማይችሉ ታላላቅ ግጥሚያዎች የተሳተፈ ነበር፡፡
የትውልድ ስሙ ካሴስ ክሌይ ነበር፡፡ በ19ኛው ክፍለዘመን ባሮችን ነፃ ለማውጣት በታገሉ ታላቅ ሰው መታሰቢያነት ያገኘው ስም ነበር፡፡ ይሁንና ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮን በሆነ በማግስቱ የነፃነት ታጋዩን ማልኮለም ኤክስ ከጎኑ አድርጎ በሰጠው መግለጫ ዘ ኔሽን ኦፍ ኢስላም አባል እንደሆነ አስታውቆ የባርያ ስም ይለው የነበረውን ካሴስ ክሌይ በመቀየር ካሰስ ኤክስ ብላችሁ ጥሩኝ ብሎ አወጀ፡፡ ያኔ ኔሽን ኦፍ ኢስላም የሚመራው ኤልጅያህ መሃመድ በ1964 እኤአ ላይ መሐመድ አሊ የሚለውን ስም ሰጥቶ አፀድቆታል እስከ ህይወት ዘመኑ መጨረሻ በዚያው ተጠርቷል፡፡
በ1970ዎቹ መጀመርያ አሜሪካ በቬትናም ያደረገችውን ጦርነት በመቃወሙ ለ3 ዓመታት ክፐሮፌሽናል ቦክስ ታግዶ የነበረ ሲሆን በዚህ ወቅት ከ10 በላይ የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮና የቦክስ ግጥሚያዎች አምልጠውታል፡፡
ለ3 ጊዜያት የዓለም ከባድ ሚዛን  ሻምፒዮን ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው በ22 ዓመቱ በ1964 እኤአ ሲሆን  2ኛውን  በ1974 እኤአ ላይ እንዲሁም ሶስተኛውን   የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮና ክብር የተጎናፀፈው ደግሞ በ1978 እኤአ ነበር፡፡
በ61 ዓለም አቀፍ ፕሮፌሽናል  ግጥሚያዎች ተሳትፎ 56 ገዜ ያሸነፈ ሲሆን 37 ድል ያደረገው በዝረራ ነው፡፡  በ31 ተከታታይ የቦክስ ግጥሚያዎች ሲያሸንፍ ቆይቶ ለመጀመርያ ጊዜ የተሸነፈው  የክፍለዘመኑ ምርጥ ፍልሚያ በተባለ ግጥሚያ በጆ ፍሬዘር ነበር፡፡ በፕሮፌሽናል ቦክሰኛነት ለ5 ጊዜያት ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ የመጨረሻውንና 61ኛውን ፕሮፌሽናል የቦክስ ፍልሚያ በ1981 እኤአ ላይ ከትሬቨር ቤሪቢክ ጋር በማድረግ ጓንቲውን ሰቅሏል። በፕሮፌሽናል ቦክሰኛነት ለ21 ዓመታት ተሳትፏል፡፡
ጓንቲዎቹን ከሰቀለ ከ3 ዓመታት በኋላ ከስፖርቱ ልምድ ጋር በተያያዘ ፓርኪንሰንስ በተባለ በሽታ ተይዞ ለ32 ዓመታት ህመሙን ሲታገል ቆይቶ በ74 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
በህይወት ዘመኑ ከአራት ሚስቶች ጋር በትዳር ህይወት ያሳለፈ ሲሆን ከእነዚህ ትዳሮቹ 7 ልጆችን አፍርቷል፡፡ ያለው የሃብት መጠን እስከ 82 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ የስሙን ብራንድ እና ምስሉን በመጠቀም የሚሰሩ ከ40 በላይ ኩባንያዎች ናቸው።
ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ ሽልማት ያገኘው በ1959 እኤአ ሲሆን በቀላል ሚዛን የአሜሪካ ሻምፒዮን ሆኖ የወርቅ ጓንቲዎች የተቀበለበት ነው። በቦክስ ግጥሚያ ትልቁን ክፍያ ያገኘው እኤአ በ1980 በላስቬጋስ ሲሆን በቴክኒካል የበቃኝ ውጤት ቢሸነፍም የተከፈለው 8 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በ1960 እኤአ ላይ በሮም ኦሎምፒክ በቀላል ሚዛን የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፅፎ ነበር፡፡ ይሁንና ይህን የወርቅ ሜዳልያውን በሊውስ ቪል ግዛት በሚገኘው የኦሃዮ ወንዝ እንደጨመረና ምክንያቱም ሜዳልያውን ለአሜሪካ እና ለትውልድ ከተማው ሊውስ ቪል ቢቀዳጅም በርገር የመግዛት መብት ባለመኖሩ ተቃውሞውን ለመግለፅ ነበር፡፡ በ1996 እኤአ የአሜሪካዋ ከተማ አትላንታ ባዘጋጀችው ኦሎምፒክ ችቦውን ከመለኮሱ ባሻገር በ1960 እኤአ ወንዝ የጨመረው የወርቅ ሜዳልያ ምትክ ተበርክቶለታል፡፡
ካደረጋቸው ታላላቅ የቦክስ ግጥሚያዎች መካከል በ1974 እኤአ ላይ በ32 ዓመቱ ተሸንፎ ከማያውቀው የ25 ዓመቱ ጆርጅ ፎርማን ጋር ‹‹ራምብል ኢን ዘ ጃንግል› ተብሎ በተጠራ የዓለም ከባድ ሚዛን ቦክስ ፍልሚያ በኮንጎ ኪንሻሳ የተቧቀሰበት ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ የኮንጎ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሞቡቱ ሴሴሶኮ ለሁለቱ ቦክሰኞች በኪንሻሳ ከተማ እንዲጫወቱ በነፍስ ወከፍ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏቸው ነበር፡፡ ከስምንት ዙር በኋላ ጆ ፍሬርን በዝረራ በማሸነፍ 3ኛውን የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ክብር አግኝቷል፡፡
የመጀመርያውን የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ክብሩን ሊስተንን ከሰባት ዙር ፍልሚያ በኋላ በበቃኝ አሸንፎ ሲጎናፀፍ 630ሺ ዶላር የተሸለመ ሲሆን የተቧቀሰባቸው  ጓንቲዎቹ ከ50 ዓመታት በኋላ በጨረታ የተሸጡት በ836ሺ ዶላር ነበር፡፡
የመጀመርያ ልዩ የክብር ሽልማቱን ያገኘው በ1970 እኤአ ላይ የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት ነው፡፡ ባንድ አጋጣሚ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ተብሎ የተወደሰ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖ ከ1998 እሰከ 2008 እኤአ ለ10 ዓመታት በታዳጊ አገራት በመዘዋወር ግልጋሎት አበርክቷል፡፡ በ2005 እኤአ የአሜሪካ ከፍተኛውን የሲቪል ክብር ሽልማት‹‹ ፕሬዝዳንሺያል ሜዳል ኦፍ ፍሪደም››፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የህይወት ዘመን ስኬት የክብር ሽልማት እንዲሁም በ2005 እኤአ በተባበሩት መንግስታት የሰላም መልዕከተኛነት እና በአሜሪካ የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴ ላደረገው አስተዋፅኦ በጀርመን መንግስት ‹‹ የኦታ ሃን› የሰላም ሜዳልያን ተቀብሏል፡፡ በቦክስ ስፖርት ለነበሩት አስተዋፅኦዎችም በርካታ ሽልማቶችን የሰበሰበ ሲሂን ስፖርት ኢልስትሬትድ በተባለው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የስፖርት መፅሄት የክፍለዘመኑ ምርጥ የስፖርት ሰው፤ እንዲሁም በቢሲ የክፍለዘመኑ ምርጥ የስፖርት ስብዕና እንዲሁም ጂኪው በተባለ ታዋቂ መፅሄት የክፍለዘመኑ ምርጥ አትሌት ተብሎ ልዩ የክብር ሽልማቶችን ተጎናፅፏል፡፡
በስተርጅናውም በበርካታ የበጎፍቃድ ዘመቻዎች ተሳታፊ ነበር፡፡ በአፍጋኒስታንና በሰሜን ኮርያ በበጎፍቃድ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል። በኩባ የህክምና መሳርያዎች ድጋፍ አቅርቧል። በመጀመርያው የገልፍ ጦርነት  ወደ ኢራቅ ተጉዞም 15 የአሜሪካ ታጋቾችን ባስለቀቀ ዘመቻ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ታላቁን የደቡብ አፍሪካ ነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እንደተፈቱ በአካል ተገኝቶ ደስታውን ተቋድሷል፡፡ በአካል ካገኛቸው ታላላቅ መሪዎች የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤት፤ የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ጆን ፖል፤ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ እንዲሁም የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ይገኙበታል፡፡
The Soul of a Butterfly, The Greatest: My Own Story,I am the Greatest!, Healing, Black Crusoe, White Friday: Memoirs of “Paddy-Ali” የተባሉ መፅሃፍት በህይወቱ ዙርያ ተዘጋጅተው በዓለም ዙርያ ተሰራጭተዋል፡፡
በህይወቱ ዙርያ በሚያተኩሩ ጥናታዊ እና የሙሉ ጊዜ ፊልሞች የሰራ ሲሆን በተለይ ለመጀመርያ ጊዜ በተዘጋጀው እና ዘ ግሬተስት በተባለ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡ የህይወት ታሪኩ ላይ በማተኮር ከተሰሩ ፊልሞች የኦስካር ሽልማት በጥናታዊ ፊልም ዘርፍ ያገኘው ‹‹ዌን ዊ ዌር ኪንግስ›› እና ዊል ስሚዝ በመቲ ተዋናይነት የተጫወተው ‹‹አሊ›› የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡

Read 3092 times