Saturday, 18 November 2017 13:37

የሙጋቤ ማምሻ…

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በስተመጨረሻም…
ሙጋቤ ወደ ራሳቸው ተኮሱ!
ዚምባቡዌን ላለፉት 37 ዓመታት ያስተዳደሩት፣ ከመንበረ ስልጣናቸው የሚያነሳቸው ሞት ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ የኖሩት፣ ወንበራቸውን ለሚስታቸው ሲያደላድሉ የከረሙት፣ የ93 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ተቀናቃኛቸውን መትተው ለመጣል ወስነው የመዘዙትን ጠመንጃ ምላጭ ሳቡት፡፡
ሙጋቤ ተሳስተዋል፤ የጠመንጃው አፈ ሙዝ ወደ ራሳቸው ግንባር መዞሩን ልብ ሳይሉ ነበር ምላጩን የሳቡት!
ኖቬምበር 6 ቀን…
ቀጣዩዋ የአገሪቱ መሪ ሊያደርጓት ያሰቧት የባለቤታቸው የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑትንና ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ኤመርሰን ማናጋግዋን ከስልጣናቸው ማባረራቸውን በይፋ አስታወቁ፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላም፣ “አዞው” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁትና ቀጣዩ  የአገሪቱ  መሪ  ለመሆን ከቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ጋር የሚፎካከሩት ተባራሪው ምክትል ፕሬዚዳንት፤ ”ሙጋቤ ነፍሰ ገዳዮችን አሰማርቶብኛል፣ ለደህንነቴ ስል አገር ጥዬ ተሰድጃለሁ” ሲሉ አስታወቁ፡፡
ሙጋቤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ በተጎዳበትና የፖለቲካ ውጥረቱ በተባባሰበት ወሳኝ ወቅት፣ ሚስታቸውን ለስልጣን ለማብቃት በመጓጓት የ75 ዓመቱን የፓርቲ ጓዳቸውን ኤመርሰን ማናጋግዋን ከስልጣንና ከአገር ማባረራቸው በፓርቲያቸው ዛኑፒኤፍ ውስጥ አስደንጋጭ የመሰንጠቅ አደጋን አስከተለ፡፡
የሙጋቤ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ወይስ ተባራሪው ምክትል ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ፣ ማንኛቸው ስልጣኑን ይረከቡ? የሚለው ጉዳይ፣ ዛኑፒኤፍ ፓርቲን ሲያወዛግብ ነበር የከረመው፡፡
የሙጋቤን እርምጃ ተከትሎ የዚምባቡዌ የቀድሞ የጦር መኮንኖች ማህበር ባወጣው መግለጫ፣ የምክትል ፕሬዚዳንቱን መባረር አውግዞ፣ በሚስታቸው በኩል ስልጣናቸውን ለማስቀጠል የጓጉትን ሙጋቤን ከእነሚስታቸው ከፓርቲው አባልነት ማባረሩን በይፋ አስታወቀ፡፡
በዚምባቡዌ ውጥረቱ እየተባባሰ መቀጠሉን ያጤነው የአገሪቱ መከላከያ ሃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ባለፈው ሰኞ ለሙጋቤ በላኩት መልዕክት፣ “ተቀናቃኞችን በማባረር ወንበርዎን ለሚስትዎ የማስረከቡን አካሄድ የሚገፉበት ከሆነ፣ ወታደሩ በጉዳዩ ጣልቃ እንደሚገባ ይወቁ” በማለት አስጠነቀቁ፡፡
ሙጋቤ ሰምተው ዝም አሉ፤ ወታደሩ ረቡዕ ማለዳ ያለውን አደረገ፡፡
እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን ያሳፈሩ የጦር መኪኖች በዚምባቡዌ ርዕሰ መዲና ሃራሬ ጎዳናዎች ላይ ሲመላለሱ ታዩ፡፡ የጦር መኪኖቹ ፓርላማውን ጨምሮ ቁልፍ በተባሉ ህንጻዎች ዙሪያ ሰፈሩ፡፡ ሃራሬ ጸጥ ረጭ፣ ጭው ጭር አለች፡፡ ጥይት እና ወታደር ብቻ ሳይሆን ፍርሃት እና ስጋት የጫኑ ታንኮች ከተማዋን ተመላለሱባት፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር፣ አንድ ወሳኝ ነገር እየተከናወነ ነበር፡፡
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ…
የዚምባቡዌ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ሰዓቱን ጠብቆ ይተላለፍ የነበረውን የወትሮውን መደበኛ ፕሮግራም ስርጭት ድንገት አቋረጠና፣ ያልተገመተ ሰበር ጉድ ማሰማቱን ቀጠለ፡፡
የአገሪቱ የመከላከያ ሃይል፣ ዚምባቡዌን ላለፉት 37 ዓመታት ከነበረችበት የሮበርት ሙጋቤ መዳፍ ፈልቅቆ ማውጣቱን፣ አገሪቱን የመምራት ስልጣኑን በመረከብ ሙጋቤንና ክብርት እመቤት ግሬስን በመኖሪያ ቤታቸው ማሰሩን ይፋ አደረገ፡፡
ሮበርት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ፤ ጠባቂ ተመድቦላቸው በመኖሪያ ቤታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት ጄኔራሎቹ፤ ”የወታደሩ አላማ መፈንቅለ መንግስት አካሂዶ ስልጣን መንጠቅ አይደለም፤በሰውዬው ዙሪያ ተጠልለው የአገሪቱንና የህዝቧን ደም ሲመጥጡ የኖሩ ስግብግብ ወንጀለኞችን አነፍንፎ መያዝና ለፍርድ ማቅረብ እንጂ፤ ስለዚህ ተረጋጉ!” ሲሉም የጦር ሃይሉ መኮንኖች ለህዝቡ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ዚምባቡዌ ይህን ሰበር ጉድ ስትሰማ፣ ብዙ ለየቅል የሆነ ነገር ሆነች - በድንጋጤ ክው አለች፤ በደስታ ፈነጠዘች፣ በጭንቀት ተወጠረች፣ በእፎይታ ተነፈሰች…
ቢቢሲ ረቡዕ ማለዳ በሃራሬ የሆነውን ነገር ሲዘግብ፤ ”የተቀላቀለ ስሜት የታየበት” ነበር ያለው። “የወታደሩ ያልተጠበቀ እርምጃ አገሪቱን ለ37 ዓመታት ያህል ከማቀቀችበት የአንድ ሰው አገዛዝና የኢኮኖሚ ድቀት ነጻ የሚያወጣ የትንሳኤ ዘመን ጅማሬ ነው” ያሉ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል፣ ወታደር የገባበት ነገር እንደዋዛ እይቋጭም ብለው የሰጉ ብዙዎች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
ወታደሩ በሃይል ስልጣን መያዙን ተከትሎ “ጄኔሬሽን 40” የተባለውና የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ቀንደኛ ደጋፊ እንደሆነ የሚነገርለትን የገዢው ፓርቲ አካል የሆነ ቡድን ተሰሚነት ያላቸው አባላት ማሰር መጀመሩ እየተነገረ ሲሆን፣ አንዳንዶችም የሙጋቤ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ግን፣ ረቡዕ ዕለት ከሙጋቤ ጋር በስልክ ተገናኝተው ማውራታቸውንና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንደገለጹላቸው አስታውቀዋል፡፡ ሲኤንኤን በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባው፣ ሙጋቤ ከጦር ሃይል አዛዡ ጋር ድርድር ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ ደጋፊያቸው እንደሆነ በሚነገርለት ሄራልድ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ላይ ታትሞ መውጣቱን አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ “በዚምባቡዌ እየሆነ ያለው ነገር መፈንቅለ መንግስት ይመስላል፤ ጦሩ አገሪቱን ወደ ቀውስ ከሚያመራ ነገር መቆጠብና ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲመለስ ጥረት ማድረግ ይገባዋል” ብሏል፡፡
የእንግሊዟ ጠ/ ሚ ቴሬሳ ሜይ፤ በዚምባቡዌ እየሆነ ያለው ነገር ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ በግርግር መሃል ግን ሌላ ጨቋኝ ሃይል ስልጣን እንዳይይዝ ያሰጋል ሲሉ ጭንቀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የዚምባቡዌ ጉዳይ ከተቀረው የአፍሪካ አገራት በተለየ መልኩ ደቡብ አፍሪካን አስጨንቋታል። የዚምባቡዌ ኢኮኖሚ በ2008 ክፉኛ በቀውስ መመታቱን ተከትሎ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሰደድ አሁንም ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ወቅታዊው የዚምባቡዌ ቀውስ ከተባባሰ፣ ደቡብ አፍሪካ ከአቅሟ በላይ የሆነ ስደተኛ ለመቀበልና በጎረቤቷ ጦስ የባሰ ቀውስን ለማስተናገድ ትገደዳለች፤ ይህ እንዳይሆንም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች ሰላም ለማውረድ እየሰራች ነው ተብሏል፡፡
የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ አባል አገራት ተወካዮችና የደቡብ አፍሪካ ሚኒስትሮች ልኡካን ቡድን መሪዎች፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚደረግበትና አገሪቱን ከባሰ ቀውስ መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር ከትናንት በስቲያ ወደ ሃራሬ አቅንተዋል፡፡
በወታደሩ እጅ ላይ የወደቀቺው የዚምባቡዌ ቀጣይ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች የተለያየ ግምት እየሰጡ ሲሆን ከብዙዎች ዘንድ የሚደመጠው ግን በሙጋቤ ተባርረው አገር ጥለው የተሰደዱት ምክትል ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ ወደ አገራቸው ተመልሰው ስልጣን የመያዝ ዕድል ይኖራቸዋል የሚለው ግምት ነው፡፡
ወታደሩ ከሙጋቤና ከስደተኛው ማንጋግዋ ጋር ድርድር እያደረገ እንደሚገኝና ድርድሩም ማንጋግዋ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ፣ ሙጋቤ መልሰው እንዲሾሟቸውና ስልጣን እንዲለቅቁ ለማድረግ፣ በስተመጨረሻም ፓርቲው መሪውንና ፕሬዚዳንቱን እንዲመርጥ ለማድረግ ሳይሆን እንደማይቀር ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በውጭ አገር የካንሰር ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ታዋቂው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ሻንጋራይ፣ ወደ አገራቸው ተመልሰው፣ተቃዋሚዎችን ያቀፈ ንቅናቄ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን የሰጡም አልታጡም፡፡ ዚምባቡዌ ባለፉት 10 ዓመታት በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ መዝለቋን የዘገበው ቢቢሲ፤ የገንዘብ እጥረት መባባሱን፣ የመገበያያ ገንዘቧ የመግዛት አቅም እጅግ በጣም መዳከሙንና የስራ አጥነቱ በዚህ ዓመት 90 በመቶ መድረሱን አመልክቷል፡፡
አምና ብቻ የ18 አገራት ምርጫ፣ በኢንተርኔት አማካይነት ተዛብቷል
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በ18 የተለያዩ የአለማችን አገራት በተካሄዱ ምርጫዎች በኢንተርኔት አማካይነት በተደረጉ ጣልቃ ገብነቶች የመራጮች ድምጽ አሰጣጥ መዛባቱ ተነግሯል፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው ዓለማቀፍ ተቋም ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፤ በ2016 ምርጫ በተካሄደባቸው 18 አገራት ውስጥ መንግስታት፣ ቡድኖች፣ ተቃዋሚዎችና የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት በሚያሰራጯቸው መረጃዎች አማካይነት በመራጮች ድምጽ አሰጣጥና በምርጫ ውጤቶች ላይ መዛባት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡
በ65 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባወጠው ሪፖርት፤ በአመቱ የ30 የአለማችን አገራት መንግስታት ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተቃውሞዎችን የሚያፍኑ መልዕክቶችን በስፋት በማሰራጨት ተግባር ላይ ተጠምደው ሲሰሩ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡
በአመቱ የተጠናከረ የኢንተርኔት ጣልቃ-ገብነትና አፈና ከተካሄደባቸው አገራት መካከል ቻይናና ሩስያ እንደሚገኙበት የጠቆመው ተቋሙ፤ ቱርክ፣ ፊሊፒንስ፣ ሶርያና ኢትዮጵያም በዝርዝሩ ውስጥ መካተታቸውን ጠቅሷል፡፡

Read 3555 times