Sunday, 19 November 2017 00:00

የአባይን ውሃ ያንቋሸሸችው ዝነኛ ድምጻዊት ከሙዚቃ ታገደች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ከወቅቱ የግብጽ ዝነኛ እንስት ድምጻውያን አንዷ የሆነቺው ሼሪን አብደል ዋሃብ ባለፈው አመት በተካሄደ አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ አባይን ውሃ የሚያንቋሽሽ ንግግር በማድረጓ በአገረ ግብጽ የሙዚቃ ሥራዋን በመድረክ ላይ እንዳታቀርብ መታገዷ ተዘግቧል፡፡
ይህቺው ዝነኛ ግብጻዊት አቀንቃኝ የሙዚቃ ስራዎቿን በምታቀርብበት ኮንሰርት ላይ “የአባይን ውሃ አልጠጣሽም” የሚል ርዕስ ያለውን ዘፈን እንድትጫወት ከአድናቂዎቿ ጥያቄ በቀረበላት ወቅት፣ “ምን ማለታችሁ ነው… የአባይን ውሃ ከጠጣሁ እኮ፣ በጥገኛ ትላትሎች በሚከሰተው ሺስቶሞሲያሲስ የተባለ በሽታ እያዛለሁ” ብላ መመለሷንና አድናቂዎቿንም የአባይን ውሃ እንዳይጠጡ መምከሯን የዘገበው ቢቢሲ፤ይህን ተከትሎ በአገሪቱ የሙዚቃ ማህበር ከኮንሰርት ስራ መታገዷን አመልክቷል፡፡
የ37 አመቷ ዝነኛ ድምጻዊት “የህልውናችን መሰረት በሆነው በታላቁ ወንዛችን አባይ ላይ ያልተገባ ንቀት አሳይታለች፣ ስለሆነም በዚህ ህገ ወጥ ተግባሯ የተነሳ ለተወሰነ ጊዜ በየትኛውም የግብጽ የሙዚቃ መድረክ ላይ ስራዎቿን እንዳታቀርብ አግደናታል” ሲል ማህበሩ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ ድምጻዊቷ በዱባይ ባቀረበቺው ኮንሰርት ላይ በአባይ ወንዝ ላይ ያልተገባ የንቀት ንግግር ማድረጓን በማመን፣ “ያልሆነ ነገር ዘባርቄ ስላስቀየምኳችሁ ተወዳጇን አገሬን ግብጽንና ግብጻውያን ወገኖቼን በሙሉ ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ስትል በይፋ መጸጸቷን አስታውቃለች፡፡

Read 4926 times