Sunday, 19 November 2017 00:00

ድሃውን ከገበያ ናዳ ማን ይታደገው?!

Written by  ገለታ ገ/ወልድ
Rate this item
(0 votes)

     በሀገሪቱ ቢያንስ ባለፉት አስር ዓመታት ገደማ  የተጀመረው አበረታች  ኢኮኖሚያዊ  ዕድገት መሰረታዊ ለውጦችን እያሳየ እንደነበር ሊካድ አይችልም፡፡ በአንድ በኩል ትራንስፎርሜሽናል የኢኮኖሚ ሽግግር ባለመደረጉ፣ በሌላ መልኩ ምልዐተ ህዝብ አሳታፊ ዲሞክራሲ መሳ ለመሳ ባለመጎልበቱ እድገቱ በታሰበው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነም ይታወቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ገና እንደ ለጋ  ኢኮኖሚ  ወቅታዊ  የገበያ ፈተናዎች፣ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የሚፈጥሩት ማህበረሰባዊ ጫናም ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኗቸዉ ቀላል አልሆነም፡፡
በእርግጥ በዜጋው ላይ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ መለስ ቀለስ የሚለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ መንግስት ሀገር በማረጋጋትና እምቢተኝነትን በማስቆም ላይ ማገዶ መጨረሱ፣ ባለፈው አመት ተከስቶ የነበረው ድርቅና መሰል ወቅታዊ ፈተናዎች የራሳቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም፡፡ ከቅርብ ጊዜ አኳያም መንግስት የወጭ ንግድን ለማበረታታ በሚል የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ጭማሪ ማድረጉ (የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሙ) ለህገ ወጡም ሆነ ምክንያታዊ ለሆነው የገበያ  የዋጋ መናር በር ከፍቶለታል፡፡
አሁንም የገበያ መረጋጋቱ  ጉዳይ  በወሳኝነት ትኩረት እንደሚሻ አልሞ መንቀሳቀስ ግን ከመንግስት፣ ከራሱ ከንግዱ ማህበረሰብና ማህበራቱ እንዲሁም ከተለያዩ አደረጃጀቶች የሚጠበቅ  ያፈጠጠ ተግባር ሆኗል፡፡ ትልቁ ፈተና ደግሞ በሀገሪቱ የወጡ  የንግድና የገበያ ህግጋትን አጥብቆ መተግበርና ማስተግበር አለመቻል እንደመሆኑ፣ ይህን ለመሻገር ወሳኝ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም እንደ ኮንትሮባንድና አየር ባየር አይነት ህገ ወጥ ንግዶችን በሚፈለገው ደረጃ  ለማድከም፣ መንግስት ልዩ ትኩረትና እርምጃ ሊወስድ  የሚገባው ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል፡፡
በአንዳንዱ የንግድ ማህበረሰብ አባላት  በኩል  ያለው ኢ-ሞራላዊ ስግብግብነትና ህዝብን የማማረር ድርጊትም ከህግና ስርዓት ማስተግበርም በላይ የሞራል ግንባታና አስተምሮት ሊደረግበት የሚገባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሀይማኖት አባቶችና ተቋማቱ እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የየበኩላቸዉን ድርሻ መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንና የሚመለከታቸዉ የሲቪክ ማህበራትም እንዲሁ።  ለዚህ ግን አሁን በሀገራችን የንግድና ገበያ ስነ ምህዳር ውስጥ ተደጋግሞ እየታየ ያለውን ብልሽት መፈተሽና ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ለስርነቀል ለውጥ መነሳትም ግድ ይለናል፡፡
የአንዳንድ ነጋዴዎች አልጠግብ ባይነት!
ዛሬ ዛሬ በሀገራችን የሸማቾች የህብረት ስራ ቢቋቋምም፣ የሸማቾች መብት ጥበቃ ኮሚሽን ቢመሰረትም ከነፃ ገበያው መርህ አኳያ ብዙሃኑ  ሽማች ለንግዱ ማህበረሰብ ብዝበዛ በቀላሉ የተጋለጠ  ሆኗል። አሁን ባለዉ ሁኔታ ድንገት የሚፈጠር የዋጋ ጭማሪና ምርት መደበቅ ብቻ ሳይሆን በሞኖፖል የተያዘ በተለይ የውጭ ምርትን  ከሚገባው በላይ አትርፎ የመሸጥ ችግር ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ ተፈፅሞ ህዝብን ሲያማርር ታይቷል፡፡ ሌላው ይቅር የሰሞኑ የስኳር፣ የዘይትና መሰል ሸቀጦች መጥፋት ያጤኗል፡፡
እታች ያለው ቸርቻሪና አገልገሎት ሰጭ ነጋዴ የሚፈፅመው ህገወጥ ተግባር ደግሞ ለህዝቡ ምሬትና መንገፍገፍ በር በመክፈት ላይ ነው። ገና ለገና የዶላር ምንዛሬ ተመን ጨመረ (የብር የመግዛት አቅም 15 በመቶ ቀነሰ) በሚል እዚሁ ሀገር ውስጥ በየጓሮው  በሚመረተው በቆሎና ስንዴ ላይ ሳይቀር ወይም በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በሚውለው ጤፍ ላይ ዋጋ መቆለል ከስግብግብነት ውጭ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በብረትና መሰል የግንባታ ዕቃም ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ቀድሞ ተገዝቶ በመጋዘን የከረመን  ምርት እንኳን  በዋጋው ከመሸጥ  ይልቅ በህዝቡ ላይ ያልተገባ ትርፍ ጭኖ እስከ መበዝበዝ የሚገፋ ነዉ፡፡  
ከዋጋ መናር ባሻገር አንዳንዱ ምንም እንኳን ንግድ ፈቃድ አውጥቶ ህጋዊ ቢመስልም ሰው እየመረጠ የሚሸጥ አድሎኛ ቸርቻሪ ሆኗል። ሲፈልግ ይሸጣል፤ ካልተመቸውም ተደራድሮ ያየኸውን ሸቀጥ እንኳን እያለ ‹‹የለም›› ይልሃል። ድርጊቱ በሁለቱም የሀገራችን ታላላቅ እምነቶች (ክርስትናና እስልምና) እንዲሁም በሀገሪቱ የንግድ ህግ የተከለከለና የሚያስቀጣ መሆኑን እያወቀ ሚዛን ይቀሽባል፡፡ ስጋ፣ ቅቤ፣ ማርና ዋጋው እያሻቀበ የመጣውን የአትክልት ዘር ይቅርና ከቅመማ ቅመምና  ከዳቦ ግራም ላይም  ሚዛን ይቀንሳል፤ እምነቱን ያጎድላል፡፡ ወገኑን በድሎ የማይሞላውን ሆዱን እያሰበ  ሲያዛጋ ይውላል፡፡
በአንዳንድ  መደብሮችና መቸርቸሪያ ሱቆችማ  ስለ ዕቃው ጥራት መጠየቅ አይቻልም። ዋጋ መከራከር አይታሰብም፡፡ አማርጦ መግዛት የሚሆን አይደለም። አንዳንድ ነጋዴ ተብዬዎች ህግ ቢያስገድዳቸውም የንግድ ፍቃዳቸውንና የሸቀጦቹን ዋጋ በግልጽ በሚታይ ስፍራ አይለጥፍም፡፡ የተበላሸና ጊዜው ያለፈበትን  ዕቃ በድፍረት ለመሸጥ ወደ ኋላ አይልም፡፡  ከሸጠ በኋላም ተነቅቶበት  መልስ ሲባል ፣ አይመልስም። ይህ የተረገመ ድርጊት በሰፊው ባህር መርካቶ ላይ  የባሰ ሲሆን በብዙዎቹ ቦታዎችም ቀስ በቀስ እንደወረርሽኝ እየታየ ነው፡፡
አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ የገበያውን ብልሽት ያረጋጋሉ የተባሉት የሸማች ማህበራት ሱቆች (የደርጉ የህብረት ሱቆች) እንኳን  ድሃውን ሊታደጉ ራሳቸውንም በስርዓት አላወቀሩም፡፡ አንዳንዶቹ የጥቂት ጥገኞች  መፈንጫ ሲሆኑ በተለይ ተከራዩን ህዝብ በኩፖንና በመታወቂያ መለየት  ስም ያገለሉ ናቸው። ጤፍና ጥራጥሬን የመሰሉ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ከአምራች የህብረት ስራ ገዝተው   በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያከፋፍሉ ብዙ የተነገረላቸው  ጉደኞቹ የሸማች ማብራትም  የሰብል  ምርት ሊያቀርቡ ይቅርና  በደርግ ጊዜ የተቋቋሙ ወፍጮ ቤቶችንም ከሥራ ውጭ እያደረጉ ተቀምጠዋል፡፡
እነዚህ ማህበራት  የፖሊሲም  ሆነ የመመሪያ ችግር  ባይኖርባቸውም በመልካም አስተዳደር እጦትና በሙስና እንዲሁም ከፋይናንስና የማስፈጸም አቅም ውስንነት አንፃር ብዙዎቹ የተሽመደመዱ ናቸው፡፡ ለነገሩ ገበያ በማረጋጋት በኩል በሸማች ማህበራት የተቋቋሙት ይቅርና መንግስት ሰፊ ፕሮፓጋንዳ የሰራባቸው እነ “ጅንአድ” እና “አለ በጅምላ”ም የህዝብን የገበያ ተጠቃሚነት ከማረጋጋጥ አንፃር ዉጤታቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት ችግሩ ያለው እዚያው በየሱቁ ውስጥ ነው፡፡ ሸማቾች ሱቅ ውስጥ ብዙ ነገር አይገኝም፡፡ በተለይ አሁን ላይ እንደ ስኳርና ዘይት ያሉ መሰረታዊ ሸቀጦችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ መሆኑ አንድ ማሳያ  ነው፡፡ አብዛኛው የገበያ ዕቃ ከውጭ የሚገባ እንደመሆኑም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ሊያንቀሳቅሳቸው እንዳልቻለ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ሱቆቹ ዕቃ አስገብተዋል እንኳን ሲባል  የሚያቀርቡት ምርት ያንኑ መከረኛ ስኳርና ዘይት ሲሆን  ዛሬ ገባ የተባለን ስኳር ነገ ‹‹የለም››  ለማለት ቅንጣት ያህል አይሳቀቁም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በስውርና በጅምላ ለጥቅም ተጋሪያቸው ህገ ወጥ ነጋዴ አሳልፎ በመሸጥ ህዝብን ለችግር የሚዳርጉ እየሆኑ  ነው፡፡  ላለፉት በርካታ ዓመታት “አድገናል” እያልን በምንለፍፍበት  ሀገር ውስጥ ዘይትና ዱቄት  በሰልፍ እየሸጡ መኖርን የሥራቸው አልፋና ኦሜጋ አድርገው ተቀምጠዋል፡፡ በቀን  ሦስት ጊዜ ወደ መብላት መሸጋገራችን በቀይ ሪቫን በደመቁ በዓላት እየተበሰረ፣ የዕለት ማጣፈጫዎች ከገነት እንደሚመጡ መለኮታዊ መናዎች ርቀውብናል፡፡  
በሀገሪቱ የሸማቾች ህግ ቢወጣም፤ በየሜዳው ድብልቅልቅ ልብስ የለበሱ (የፌደራል፣ የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የመከላከያ ወይም የደንብ ማስከበርና የአድማ በታኝ) ፖሊሶች ቢኖሩም የሸማችነት መብታችንን እምብዛም የሚያስከብረው አልተገኘም። ራሱ የፀጥታ ሃይሉም በዝቅተኛ ደመወዝ ውስጥ እየታሸ እንኳን ለጋራ መብቱ አይቆምም፡፡ ቅሸባው፣ ኮንትሮባንዱ፣ የምግብ እህልንና ቅመማቅመምን ከባዕድ ነገር (አንዳንዱ ከፍተኛ የጤና እክል የሚያመጣ) ጋር በመቀላቀል ሲሸጥ ይታያል፡፡ ድርጊቱን ለማስቆም የአንድ ሰሞን ሆሆታ ቢጀመርም የትም ሲደርስ አይታይም። በየሜዳው አነስተኛውን ህገ-ወጥ ቸርቻሪ በቆመጥ መድረሻ የሚያሳጣ የደንብ ሰራተኛ፣ እንዴት ድሃውን የሚያግዝ የገበያ ብልሽትን ለማስተካከል የድርሻውን መወጣት ተሳነው? የሚለው ጥያቄ የበረታ መልስን የሚሻ ነው፡፡
አሁን ላይ ምንም እንኳን መንግስት ልማታዊ መስመር የሚከተል ቢሆንም መነሻው ነፃ ገበያ እንደመሆኑ ‹‹ገበያው በመንግስት አይመራም››  ይባላል፡፡ ይህ ማለት ግን  ምን ማለት  ነው? በማን እየተመራ ነው? ብሎ መፈተሽን የግድ ይላል። ማንም ይምራው ማን በተጨባጩ ሁኔታ ግን ገበያው  በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ህግ በመመራት ስም፣ ድሃውንና አብዛኛውን ሸማች በምጣኔ ሀብት ናዳ እየጨፈለቀ የሚሄድ ከሆነ፣ አስቸጋሪ ነገር መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡  
ከዚህ አንፃር በሀገራችን ሊኖር የሚገባው ገበያ፣ መንግስት ተያያዥም ሆነ ተያያዥ ያልሆነ አዲስ እርምጃ በወሰደ ቁጥር የሚረበሽና ሸማቹን የሚያደቅ መሆን የለበትም፡፡ ለዚህም  የነጋዴውም ሆነ የሸማቹ ግንዛቤ እንዲቀየር ከመትጋት ጎን ለጎን የወጡት ህጎችን በመተግበር ገበያው ተገቢው ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ጠበቅ ያለ ርምጃ የሚወሰድበት፣ እሽሩሩ የማይባልበት ሆኖ፣ በተቀናጀና በተሳለጠ አግባብ  መመራት ይኖርበታል፡፡ የነጋዴም ሆነ (ካለ) የሸማች ማህበራትና ራሱ ህዝቡም የገበያ ማስተካከል ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ጉዳዩ የጋራና የራስ ነውና!!
በእርግጥ መንግስት የሀገር ደህንነትና ሰላምን ከመጠበቅና ከማስተዳደር ባሻገር በኢኮኖሚው መስክም በኢንቨስትመንት ይሳተፋል፣ አቅጣጫ ያስቀምጣል፤ እቅድ ያወጣል፡፡ ይህን ከማድረግ ውጭ የነፃ ገበያው ኢኮኖሚ ውስጥ እንደፈለገው ጣልቃ እየገባ  ማነቆ  ሊሆን አይገባም፡፡ መንግስት ብዛት ያላቸው የግል ባለሀብቶችንና ካፒታሊስቶችን ማፍራት እንደሚፈልግም ይታወቃል፡፡ እስከዚህ ድረስ ችግር የለብንም፡፡ ችግሩ ያለው በማን ወጭ? በማን ኪሳራ? የሚለው ላይ ነው፡፡
በዚያ ላይ የነፃ ገበያውን የፖሊሲ አቅጣጫ አንዳንዱ ነጋዴ ጠልፎ ለራሱ ጥቅም እያዋለው መሆኑ ሲታይ ጉዳዩ የበረታ ትኩረትን ይሻል፡፡ የንግድ አሠራራችን በመንግስትም ሆነ በገበያው በራሱ እየተመራ ካለመሆኑ በላይ እንደፈለገ የሚያሽከረክረውና የሚያጦዘው ነጋዴው  መሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡  በመሰረቱ ይበልጡኑ አሁን አሁን እንደሚታየው፣ የሸቀጦች ዋጋ የሚጨምረው ‹‹አቅርቦትና ፍላጐት›› በሚባሉት የገበያ መለኪያዎች መሆኑ ቀርቷል፡፡ በገበያ ውስጥ በአንዱም አይነት ምርት ወይም አገልግሎት ላይ የሚታይ ተወዳዳሪነት (ለምሳሌ እንደ አሸን እየፈሉ ያሉት ቢራ ፋብሪካዎች እንኳን በአድማ መልክ ተመሳሳይ ዋጋ እያወጡ የሚሸጡ እንጂ በውድድር ተጠቃሚውን የሚያረካ የዋጋ ቅናሽ ሲያሳዩ አይታይም) ቀንሷል፡፡
በአጠቃላይ  መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ለንግድ አሰራርና ለሸማቾች ጥበቃ ጉዳይ ትኩረት   እንደሰጠ መግለፁን በበጎ ማንሳት ይቻል ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መንግስት የንግድ ሥራ አገሪቱ በምትከተለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሰረት እንዲካሄድና ተገቢውን የገበያ መር ስርዓት ተከትሎ እንዲከናወን ለማድረግ  የሰራውን ያህል የሸማቹን የገበያ ተጠቃሚነት በማረጋገጥና በየጊዜው የሚያገረሸውን የኑሮ ውድነት በማርገብ በኩል የሚበዛው የአፈጻጸም ክፍተቱ ነው። በተጨባጭ እንደተረጋገጠውም ገና የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ በተደረገ ማግስት፣ ገበያው ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መቀየሩና ሸማቹም በድንገተኛ የገበያ ናዳ ሲመታ፣ ማንም ሊያስታግሰው አለመቻሉ አንዱ ማረጋጋጫ ነው፡፡  
ለቀጣይም  ሸማቹን ህዝብ ለመታደግና ከዕለት ገቢው ጋር ከማይጣጣም ጫና ለማዳን  እንዲቻል የንግድ ስርዓቱንና  ግብይቱን ፈር ከማስያዝ ጀምሮ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ህጎችን ማስፈፀምና መቆጣጠር  ለነገ የሚባል ስራ መሆን የለበትም። ህዝቡም ቢሆን ህገ-ወጥ የንግድ ተግባራትን ለፖሊስና ለሚመለከታቸው አካላት በመጠቆም ትብብሩን በተግባር ማሳየት ራሱን እንደማዳን የሚቆጠር ነው፡፡ ሁላችንም የመፍሄው አካል በመሆን መስራት ቢጠበቅብንም የገበያው ችግር ግን የመንግስትን ያልተቋረጠ ክትትልና ልዩ ትኩረት ይጠይቃል  በማለት ብንቋጨው ሳይሻል አይቀርም።

Read 1416 times