Print this page
Saturday, 18 November 2017 13:44

በ360 ሚ. ብር የተገነቡት “ኮከብ” እብነበረድና ቀለም ፋብሪካዎች” ነገ በባህርዳር ይመረቃሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በኮንስትራክሽን፣ በግብርናና በአስመጪና ላኪነት ተሰማርቶ ሲሰራ የቆየው ቢአይካ ጀነራል ቢዝነስ፤ በ360 ሚ. ብር ወጪ ያስገነባቸው “ኮከብ እብነበረድና ቀለም ፋብሪካ” ነገ በባህርዳር ከተማ ይመረቃሉ፡፡ ሁለቱ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ስራ ሲጀምሩ ለ500 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ የቢአይካ ጀነራል ቢዝነስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ምስጋናው አየሁ ገልፀዋል፡፡
“ኮከብ እብነበረድ” በሁለት መልኩ እብነበረድ እያመረተ ለውጭ ገበያ የሚልክ ሲሆን ኮከብ ቀለም ፋብሪካ ደግሞ የእብነበረዱን ተረፈ-ምርት በጥሬ እቃነት እየተጠቀመ፣ ቀለም በማምረት እየተስፋፋ የመጣውን የግንባታ ኢንዱስትሪ በመቀላቀል የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡
የእብነበረዱ ማዕድን የሚወጣው ቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ማንኩሻ ከተባለ ቦታ ሲሆን በዚሁ ቦታ ላይ “ዳይመንድ ዋየር” የተባለ ፋብሪካ በማቋቋም እብነበረዱ እየተቆረጠና እየተስተካከለ ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ሁለተኛው በእብነበረዱ ላይ እሴት ጨምሮና ያለቀለት ሆኖ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት “ኮከብ” እብነበረድና ቀለም ፋብሪካው 200 ያህል ሰራተኞችን በስሩ እንደሚያስተዳድር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቢአይካ ጀነራል ቢዝነስ፤ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በኮንስትራክሽን፣ በአስመጪና ላኪነት እንዲሁም በቴፒ ጎደሬ ወረዳ በ2700 ሄክታር መሬት ላይ በቡና ልማት ላይ ተሰማርቶ “ስፔሻሊቲ ቡና” ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ሲሆን ከእብነበረድና ከቀለም ፋብሪካው በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ በ50 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈና 200 ሚ. ብር በጀት የተያዘለት የዘይት ፋብሪካም ገንብቷል። የኑግ፣ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር፣ የተልባና የሱፍ ጤንነቱ የተጠበቀ ዘይት ለአገር ውስጥ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሬን ከማዳኑም በተጨማሪ ለ200 ሰራተኞች የስራ እድል እንደሚፈጥር ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። ፋብሪካው ከአንድ ወር በኋላም ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ ካሣሁን በቀጣይም የተለያዩ 5 አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እቅድ መያዙን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ቢአይካ ጀነራል ቢዝነስ እስካሁን በስሩ 5 ሺህ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራ ሲሆን አጠቃላይ ካፒታሉም ወደ 5 ቢ. ብር ማደጉን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
ነገ ከሰዓት በኋላ በሚመረቁት “ኮከብ” እብነበረድና ቀለም ፋብሪካዎች ሥነ- ስርዓት ላይ የክልሉ ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

Read 3729 times