Saturday, 18 November 2017 13:45

የቢራ ኢንዱስትሪውና የገብስ ምርት አለመጣጣም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • ሄኒከን ከ20ሺ በላይ አርሶ አደሮች ጋር በአጋርነት ይሰራል
          • 60 በመቶ የቢራ ገብስ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ ነው
                          
    በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው የኢትዮጵያ የቢራ ኢንዱስትሪ፣ የቢራ ገብስ ፍጆታው በከፍተኛ መጠን ማደጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 63 ሺህ ቶን የገብስ ብቅል ይጠቀም የነበረው የቢራ ኢንዱስትሪው፤ አሁን ከ120 ሺህ ቶን በላይ ይጠቀማል፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ 200 ሺህ ቶን ገብስ ያስፈልገዋል ተብሎ ይገመታል።
ይህን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላትም ሀገሪቱ ገብስ ከውጭ ሀገራት ለማስገባት በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች ይላል- በገብስ ምርት ጉዳይ ላይ የሚሰራው ሚስታራ ባዮተች ኩባንያ፡፡ የሀገሪቱን የቢራ ገብስ ፍላጎት በእጅጉ እንዲጨምር ካደረጉት የቢራ ኩባንያዎች ውስጥ በዓለም አቀፍ የቢራ ኢንዱስትሪ ከ145 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው፣ በ192 የዓለም ሀገራት፣ ከ25 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራው ሄኒከን አንዱ ነው፡፡
በዋሊያ፣ በሶፊ ማልት፣ በሐረር፣ በበደሌ፣ በክለር እና በሄኒከን ቢራ ምርቶቹ በአገር ውስጥ በስፋት የሚታወቀው ሄኒከን ኩባንያ፤ በአሁን ወቅት 28 በመቶ የገብስ ፍላጎቱን ከሀገር ውስጥ እያሟላ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ የ9.2 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት  ያለው ሄኒከን፤ የገብስ ፍላጎቱን ከሀገር ውስጥ ለማሟላት የተከተለው ስልት ደግሞ ራሱ መሬት ወስዶ፣ የገብስ እርሻ ከማስፋፋት ይልቅ ለቢራ ገብስ ማብቀል ተስማሚ የሆኑ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት፣ አርሶ አደሮች የተሻሻለ ዝርያ አምርተው እንዲያስረክቡት አጋር በማድረግ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በተጀመረው በዚህ የእርሻ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የማህበረሰብ ገቢን ማሳደግ ፕሮጀክቱ፤ በቀጥታ ከ20ሺ 894 ገበሬዎች ጋር አብሮ እየሰራ ሲሆን በተጨማሪም 30ሺ ያህል ገበሬዎችን የተሻሻሉ የገብስ ዝርያዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ይገልፃል፡፡
ቀድሞ አርሶ አደሮች የሚጠቀሟቸው የገብስ ዝርያዎች በሄክታር ከ15-18 ኩንታል ብቻ ምርት የሚሰጡ እንደነበር የጠቆመው ኩባንያው፤ አሁን ከጀርመንና ከፈረንሳይ ያስገባቸው Traveler እና Grace የተባሉ የገብስ ዝርያዎች የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት አንዲያገኙ እያስቻላቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ኩባንያው ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርግባቸው ከመረጣቸው የሃገሪቱ ገብስ አብቃይ አካባቢዎች መካከል ደግሞ ምዕራብ አርሲ ዞን፣ አርሲ ዞን እና ባሌ ዞን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአርሲ ዞን በቆጂ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችም በዚህ ፕሮጀክት ከታቀፉ በኋላ ምርታማና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማግኘታቸው ዓመታዊ ምርታቸውና ገቢያቸው ከፍተኛ ጭማሪ ማሣየቱን ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የ6 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤት የሆኑት አርሶ አደር ፋዬ ተሠማ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ፋዬ እንደሚሉት፤ ቀድሞ እስከ 18 ኩንታል በአንድ ሄክታር የሚያገኙት ምርት፣ አሁን በተሻሻሉ ዝርያዎች ከ60 ኩንታል በላይ ማግኘት እየቻሉ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል። በየአመቱም በሚሊዮን ብር የሚገመት የገብስ ግብይት ከሂኒከን ኩባንያ ጋር እየፈፀሙ እንደሆነ የሚጠቅሱት አርሶ አደሩ፤በቀጣይም ምርታቸውን አሣድገው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡  
ሄኒከን አንዱን ኩንታል በአንድ ሺህ ሃያ ብር እንደሚረከባቸውና ይህም በገበያ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ድጋፍም እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው በበኩሉ፤ በቀጣይም ከእነዚህ 20 ሺህ አርሶ አደሮች በተጨማሪ በጎንደር፣ በጎጃምና በደቡብ አካባቢ ካሉ አርሶ አደሮች ጋር ተመሳሳይ ፕሮጀክት ዘርግቶ ለመስራት እቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡  
በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በ1.1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ገብስ እያመረቱ ቢሆንም ከዝርያዎች አለመሻሻል ጋር ተያይዞ የሃገሪቱን የገብስ ምርት ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው ቢራ ፋብሪካዎች፣ 60 ከመቶ የሚሆነውን የቢራ ገብስ ከውጭ ሃገራት ነው የሚያስገቡት - በውጭ ምንዛሪ፡፡ በኢትዮጵያ በቢራ ኢንዱስትሪው ከተሰማሩት መካከል ቢጂአይ፣ ዲያጆ፣ ዳሸን፣ ሄኒከን፣ ሐበሻ፣ ዘቢደር እና ራያ ቢራ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

Read 3322 times