Saturday, 18 November 2017 13:45

የወር አበባ መቋረጥ በዘር ሊወረስ ይችላል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(11 votes)

     የወር አበባ ተቋረጥ ሲባል ምን ማለት ነው? ደረጃውስ ምንድነው? ምክንያቱስ? መቼ ነው የሚቋረጠው? ከወር አበባ መቋረጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የስነልቡናና የጤና ችግሮች ምንድናቸው? የሚለውን ባለሙያው ዶ/ር ማለደ ቢራራ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ለዚህ እትም ጋብዘናል፡፡ ዶ/ር ማለደ ቢራራ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡
ዶ/ር ማለደ እንዳሉት የሴቶች የወር አበባ በሴቶች ሕይወት ውስጥ አንድ ትልቅ ክስተት ነው፡፡ በሴቶች ልጆች እድገት ውስጥ የሚከሰተው በአማካይ በ14/ አመት እድሜ ነው፡፡ ከዚያ በሁዋላ እርግዝና እስካልተከሰተ ድረስ በየወሩ መፍሰሱን ይቀጥላል። ከዚያም በአማካይ በ50/አመት እድሜ መጀመሪያ ወይንም 51/አመት አካባቢ ይቋረጣል፡፡ የወር አበባ መቋረጥ (Menopause) ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋናነት ግን የሴቶች የዘር ፍሬ ማለትም ኦቫሪ የሚባለው የወር አበባን በወር በወር እንዲመጣ የሚያደርገው የሰውነት ክፍል ስራውን ሲያቆምና ለዚህ ተፈጥሮአዊ ሂደት የሚያገለግሉ ሆርሞኖችን ማምረት በማቆሙ ምክንያት የወር አበባ ይቋረጣል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሂደት ተፈጥሮአዊውና ትክክለኛው መንገድ ሲሆን ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ ግን አልፎ አልፎ ሴቶቹ በ40/ዎቹ አመታት ውስጥ እያሉ የወር አበባ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ይህ በእንግሊዝኛው Premature Menopause ይባላል፡፡ ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌም የማህጸን ኦፕራሲዮን የተሰራላቸው እና የዘር ፍሬያቸው የወጣ ሴቶች ወይንም ከባድ እና ጭንቀት የተሞላው ሕመም ማለትም እንደካንሰር የመሳሰሉትን  ሕመሞች የታመሙ ሴቶች፣ የወር አበባቸው ከመቋረጫው እድሜ አስቀድሞ ሊቋረጥባቸው ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዘር የሚተላለፍበት ሁኔታም ስለአለ የዘር ፍሬአቸው ስራውን አስቀድሞ የሚያቆምበት ሁኔታ ይከሰታል ዶ/ር ማለደ እንዳሉት፡፡
የወር አበባ አስቀድሞ ወይንም አለጊዜው ሲቋረጥ በሚደረግ የህክምና እርዳታ ተመልሶ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የመምጣት እድሉ እንደተቋረጠበት ምክንያት ይወሰናል፡፡
ለምሳሌም
በከባድ ሕመም እንደ ሳንባ በሽታ ወይንም የስኩዋር ሕመም፣
(ሕመሞቹን ለማስታገስ የሚሰጡት መድሀኒቶች የወር አበባው እንደገና እንዲመጣ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡)
ክብደታቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑ ሴቶች ክብደታቸው ሲስተካከል፣
(በዝቅተኛ የክብደት መጠን የወር አበባው እንዲመጣ የሚያስፈልገው ቅመም መጠን ከማነሱ የተነሳ የወር አበባ ከቆመ ክብደታቸው ሲስተካከል እንደገና ሊታይ ይችላል፡፡)
የወር አበባ አለጊዜው ተቋረጠ የሚባልበት ምክንያት ከላይ እንደተገለጹት ባሉ ምክንያቶች ከሆነ መፍትሄ የሚኖረው ሲሆን  በተወሰኑ ምክንያቶች ግን መፍትሔውን ማምጣት አይቻልም፡፡ ለምሳሌም፡-
በኦፕራሲዮን ምክንያት ኦቫሪ ወይንም የዘር ፍሬ የወጣ ከሆነ፣
የወር አበባ መቋረጥ በዘር ሊወረስ ይችላል፡፡ በዘር ምክንያት የወር አበባ ካለጊዜው ከተቋረጠ እንደገና እንዲታያ ማድረግ አይቻልም፡፡
ነገር ግን አርተፊሻል ወይንም ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ የዘር ፍሬው ሊያመርት የሚችለውን ሆርሞን በመድሀኒት መልክ በመስጠት የወር አበባቸውን እንዲያዩ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ሂደት ግን የተሰጣቸውን መድሀኒት በየጊዜው መውሰድ ግዴታ ነው፡፡ መድሀኒቱ ከተቋረጠ ግን የወር አበባውም መልሶ ይቋረጣል፡፡
Menopause ማለት የመጨረሻው የወር አበባ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም እድሜያቸው 51/አመት ሞልቶም ይሁን ከዚያ በፊት የሚቋረጥ የወር አበባ ስያሜውን ይጋራል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሴት ልጆች የወር አበባ ሊያዩ በሚገባቸው እድሜ ማለትም  ከ14- እስከ 16/ አመት ድረስ ማየት ካልቻሉ ስያሜው Menopause ሳይሆን Amenorrhea  ነው፡፡ አሜኖሪያ ማለት የወር አበባ የሌላቸው ወይንም የማያዩ ማለት ነው፡፡ ሴቶች ሁለት አይነት የወር አበባ ያለማየት አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ከመጀመሪያውም የማያዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ማየት ከጀመሩ በሁዋላ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቋረጥባቸው አሉ፡፡ ስለዚህም ይህ አይነቱ የወር አበባ አለማየት ተመልሶ ሊመጣ ስለሚችል ሜኖፖዝ አይባልም፡፡
ሴት ልጆች ተወልደው ከ14-16 አመት እድሜያቸው የወር አበባ የማያዩ ከሆነ Primary Amenorrhea ይባላል፡፡ ይሄ ሜኖፖዝ ሳይሆን ከመጀመሪያውም የወር አበባ አላዩም የሚባለው ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡
የአፈጣጠር ችግር፡-
ጭንቅላት ውስጥ Hypothalamus  ማለትም የሰውነት ሙቀትን የሆርሞን ማመንጨትን የሚተገብረው የአእምሮ ክፍል በትክክል አለመስራት፡-
የpituitary gland ችግር (ይህ የአእምሮ ክፍል ሆርሞንን የሚያመርት ሲሆን የወሲብ ብቃትንም ለማግኘት የሚረዳ የአእምሮ ክፍል ነው፡፡)
የOvary ወይንም የዘር ፍሬ ችግር፣
ከማህጸን ውስጥ ካለ ችግርም ሊከሰት ይችላል፡፡
የድንግልና አፈጣጠር ዝግ ወይንም ድፍን መሆንም ሌላው ችግር ነው፡፡
Primary Amenorrhea የገጠማቸው ሴት ልጆች በአብዛኛው መታከም የሚችሉ ሲሆን አንዳንዶች ግን ለሕክምናውም ችግር የሚገጥማቸው ይኖራሉ። አንዳንዶች በቀላል ሕክምና ሊስተካከልላቸው ሲችል አንዳንዶቹ ደግሞ ሕይወታቸውን ሙሉ ሆርሞን እንዲሰጣቸው የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ …ሴት ልጆች የገጠማቸው የድንግልናው አፈጣጠር ድፍን መሆን ከሆነ የወር አበባው በጊዜው እየመጣ ነገር ግን ወደ ውጭ ሳይፈስ በሆድ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ  ስለሚጠራቀም በድንገተኛ ሕመም ወደሆስፒታል የሚመጡበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በዚህ ጊዜ በቀላል ኦፕራሲዮን ድንግልናውን በመክፈት በሆድ ውስጥ የተጠራቀመው ደም እንዲፈስ ይደረጋል፡፡ ለማንኛውም ወላጆች ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞውኑ ልጃቸው የወር አበባ በጊዜው ማየት አለማየቷን ተከታትለው ሁኔታውን ለሐኪም ቢያሳውቁ በቀላሉ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል፡፡
ሴቶች የወር አበባ ማየት ከጀመሩ በሁዋላ በ25/ ወይንም በ26/ አመታቸው ለስድስት ወር ያህል ወይንም ከዚያ በላይ የወር አበባቸው ሲቋረጥ Secondary Amenorrhea ይባላል፡፡ ነገር ግን Secondary Amenorrhea የሚባለው የወር አበባ መቋረጥ የሚገጥመው በእርግዝና ወይንም የጡት ወተት በሚመረትበት ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ሌሎች ምክንያቶችም ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌም ከበድ ያለ ሕመም፣ ክብደት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፣ ጭንቀት ለመሳሰሉት ሕመሞች የሚሰጡት መድሀኒቶች የወር አበባ መምጣቱን ሊያውኩ ይችላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የተለያዩ ስሜቶች ሴትየዋን ሊገጥሙዋት ይችላሉ። ለምሳሌም፡- የጡት ጫፍ ፈሳሽ እንዲኖረው ሊደርግ ይችላል፣ የፀጉር መሳሳት፣ እራስ ምታት፣ የእይታ መቀነስ፣ ፊት ላይ ብዙ ፀጉር መውጣት፣ የጀርባ ሕመም የመሳሰሉት ሴትየዋን ሊያስቸግሩዋት ይችላሉ፡፡ ለሁሉም ነገር መፍትሔው ወደሕክምና ተቋም በመሄድ ሐኪምን ማማከር ነው ብለዋል ዶ/ር ማለደ ቢራራ፡፡
ባጠቃላይም የወር አበባ ሊቋረጥ በሚያስብበት የሽግግር ወቅት ምናልባትም ለአንድ አመት ያህል የሚከሰቱ የስነልቡና እና የጤና ችግሮች ትኩረት የሚሹ ናቸው፡፡ በዋናነት የሚታዩትም የመነጫነጭ፣ እንቅልፍ የማጣት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ሙቀት መሰማት፣ በእግር እጅ እንዲሁም ጭንቅላት አካባቢ ሊገለጽ የማይችል ሙቀት ያለው ላብ ማላብ ይከሰታል፡፡
እየቆየ ሲሄድና ወደ ሜኖፖዝ ከተገባ በሁዋላ ደግሞ የግብረስጋ ግንኙነት ፍላጎት መቀነስ፣ የአጥንት መሳሳት ችግር የመሳሰሉት የጤና ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያቱ የሴቶች የወር አበባ እንዲመረት የሚያስችሉት የኢስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን መመረት መቀነሱ ነው፡፡
ይቀጥላል

Read 13160 times