Saturday, 25 November 2017 09:14

ገቢዎችና ጉምሩክ ግብር በአግባቡ ለመሠብሠብ ተቸገርኩ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

      የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የ4 ወር የግብር አሠባሠብ አፈፃፀሙን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ለህግ ተገዢነት ባለመጎልበቱ ምክንያት ግብር በአግባቡ ለመሰብሠብ መቸገሩን አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ በመግለጫቸው እንደ ጠቀሱት መስሪያ ቤቱ በ2010 ዓ.ም በአጠቃላይ 230 ቢሊዮን ብር
ለመሠብሠብ ያቀደ ሲሆን ባለፉት አራት ወራት 63 ቢሊዮን ብር መሠብሰቡን ጠቁሞ ይህም ከእቅዱ አንፃር አነስተኛ አፈፃፀም መሆኑን
አስታውቀዋል፡፡ባለፉት አራት ወራት ውስጥ የንግድ ትረፋቸውን ለባለለስልጣኑ ካሳወቁ 16 ሺህ ግብር ከፋዮች መካከል በትክክል ትርፋቸውን ያሣወቁት 63 በመቶ ሲሆኑ 28 በመቶዎች የኪሣራ ሪፖርት ማቅረባቸውን ተናግረዋል-ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋዮች ከሆኑ ነጋዴዎች መካከል በአግባቡ ግብራቸውን ያሣወቁት 30 በመቶ ብቻ መሆናቸውንና 45 በመቶ የሚሆኑት ተመላሽ መጠየቃቸውን እንዲሁም 25 በመቶ ያህሉ “ምንም ስራ አልሠራንም፤ ትርፍ አላተረፍንም” ማለታቸውን አቶ ሞገስ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ይህ የግብር ከፋዮች መረጃ በተጨባጭ በኢኮኖሚው እንቅስቃሴው ውስጥ ካለው ነባራዊ ሃቅ ጋር ይቃረናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የአመለካከት ችግርና ለህግ ተገዢ ያለመሆን ጉዳይ በእጅጉ አሣሣቢ ሆኗል ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የግብር አሠባሠቡን ዘመናዊ ለማድረግም በዚህ አመት ሁሉም ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ እንዲጠቀሙ ይደረጋል ተብሏል፡፡

Read 2849 times