Saturday, 25 November 2017 09:17

ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ግማሽ ሚሊዮን ደርሰዋል
   ባለፉት 10 ወራት ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት የእርዳታና ሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ፤ በሀገሪቱ ከሚገኙት 9 መቶ ሺህ ያህል ስደተኞች ግማሽ ያህሉ ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው ብሏል፡፡
በስደተኞች ጉዳይ ላይ ወቅታዊ ሪፖርቱን ከትናንት በስቲያ ያወጣው ተቋሙ፤ ከጥር 2009 እስከ ጥቅምት 2010 ድረስ 73 ሺህ 857
ደቡብ ሱዳናውያን፣ 20 ሺህ 700 ኤርትራዊያንና 6 ሺህ 600 ሶማሊያውያን በድምሩ 103 ሺህ 263 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ
መግባታቸውን አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር 9 መቶ ሺህ መድረሳቸውን የገለፀው ሪፖርቱ፤ ግማሽ ሚሊዮን ያህሉም ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው ብሏል፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን የእርስ በእርስ ግጭትን በመሸሽ፣ ኤርትራውያን ደግሞ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላና የሰብአዊ መብት ጥሰትን እንዲሁም ሶማሊያውያን የተለያዩ ግጭቶችንና ድርቅን በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ተቋሙ አስታውቋል፡፡ ስደተኞቹ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌና በትግራይ ክልል የመጠለያ ካምፖች መጠለላቸው የታወቀ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ 26 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡

Read 2840 times