Sunday, 26 November 2017 00:00

አቶ በቀለ ገርባ ለዋስትና እግዳቸው ምላሽ ሰጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

   የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የሰጠው ብይን በአቃቤ ህግ አቤቱታ የታገደባቸው የኦፌኮ
ተ/ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፤ ጉዳዩን ለሚመለከተው የሰበር ሰሚ ችሎት በዋስትና እግዱ ላይ አስተያየትና ምላሻቸውን በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በ30 ሺህ ብር ዋስትና ጉዳያቸውን ከእስር ውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ወስኖላቸው እንደነበር በአቤቱታቸው የጠቀሱት አቶ በቀለ፤  ወዲያው የተጠየቀው የዋስትና ገንዘብ ተከፍሎ፣ ትዕዛዙም ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቢደርስም ማረሚያ ቤቱ “የሚጣራ ነገር አለ” በሚል በእለቱ ሳይፈታቸው እንደቀሩ ጠቁመዋል፡፡በማግስቱ ጥቅምት 21 አቃቤ ህግ ለሰበር ሰሚ ችሎት በዋስትና ጉዳይ አቤቱታ ማቅረቡን መረዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ተከሳሹ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ በፅሁፍ ባቀረቡት በዚህ ምላሽ ላይ የዋስትናው መከልከል ጉዳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን እረዳለሁ ብለዋል፡፡ ለአቃቤ ህግ የዋስትና ይታገድልኝ አቤቱታ ምላሽ የሰጡት ፍትሃዊ ውሳኔ ይሰጠኛል ብዬ ሳይሆን የክስ መዝገቡ ከታች እስከ ላይ ድረስ በምን ሂደት ውስጥ እንዳለፈ ወደፊት በዳኝነት ነፃነት ጉዳይ ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች ማስረጃ እንዲሆንና ለሀገሬ ተቋም ተገቢውን ክብር ላለመንፈግ ብቻ ነው ብለዋል… በፅሁፍ ምላሻቸው፡፡ የአቶ በቀለ ገርባን የፅሁፍ ምላሽ የተቀበለው ሰበር ሰሚ ችሎቱም የአቃቤ ህግን መልስ ለመቀበል ለታህሳስ 2 ቀን 2010 ቀጠሮ ይዟል፡፡

Read 2982 times