Sunday, 26 November 2017 00:00

ዶ/ር አለማየሁ አረዳ በወቅታዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የቀድሞ የቅንጅት አባል የነበረው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ሊግ (ኢዲሊ) መስራችና ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አለማየሁ አረዳ፤ከዚህ ቀደም “የሰጎን ፖለቲካ” የተሰኘ ምሁራኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚኖራቸውን ሚና የሚተነነትን መፅሐፍ ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል፡፡ በቅርቡም በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ እንደሚያወጡ የገለጹት ዶ/ር አለማየሁ፤በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች፣በምሁራን ሚና፣እንዲሁም በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡


· የኢትዮጵያ ፖለቲካ የባላንጣነት ነው፤የተቃውሞ ፖለቲካ አልተጀመረም
· ምሁራን ለእውነት መቆም፣ለዕውቀታቸው ታማኝ መሆን አለባቸው
· አሁን አንጋፋዎቹ ኢህአዴጎች ያሉት መውጫ በሩ ላይ ነው
· ዲሞክራሲ በሌለበት መልካም አስተዳደር አይታሰብም
· የቡድን መብት በዜግነት መብት ኪሣራ አይገነባም

በአገሪቱ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብ ምን አዲስ ነገር አለ? እስካሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታስ እንዴት ይገመግሙታል?
ያን ያህል ጎልቶ የታየ፣ አዲስ ነገር የለም፡፡ መልካም የሆነ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ ኢህአዴግ በመዋቅሩ ውስጥ አለመረጋጋት ይታይበታል። ያ አለመረጋጋት ደግሞ ያለ ምክንያት የመጣ አይደለም፡፡ በኢህአዴግ ነባር (መስራች) ታጋዮችና በአዲሶቹ መካከል ባለው አለመጣጣም የተፈጠረ ነው፡፡ አንጋፋዎቹ አሁን መውጫ በሩ ላይ ነው ያሉት፡፡ በሩ ላይ ቆመው በቅጡ የገፋቸውም የለም፤ ወደ ውስጥም በደንብ የሳባቸው የለም፡፡ በመውጫ በሩ ላይ ትግል ይታያል፡፡ አዲሶቹ የኢህአዴግ ሰዎች ደግሞ አንጋፋዎቹን ገፍትረው ቦታውን ለመያዝ ቁመናው የላቸውም፡፡ በተለይ ኢህአዴግን የመሰረተው ንድፈ ሀሳብ ዕውቀቱ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ አቶ መለስ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ በብዙ የፖለቲካ አመለካከቶች ልንለያይ እንችላለን፤ ግን አቶ መለስ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው ቁመና ልዩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
አሁን ይህ ኢህአዴግን ተሸክሞ ይዞ የነበረው ንድፈ ሀሳብ በአግባቡ የተሸጋገረ አይመስለኝም። እነዚህ ነባር የሚባሉት ለአዲሶቹ ይሄን ቁመና ማስተላለፍ የቻሉ አይመስለኝም፡፡ አዲሶቹ ደግሞ መርከቧ ላይ በትክክል የተሳፈሩ አይመስለኝም። በዚህ የተነሳ መንገጫገጭ ይታያል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይሄንን በተሳሳተ መንገድ ይተረጉሙታል፡፡ የኢህአዴግ መድከም ይመስላቸዋል። አልደከመም። ይሄ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ ሌላው ኢህአዴግ ውስጥ የምናስተውለው፣ ድርጅቶቹ ራሳቸው የተጣመሩበት መንገድ ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑን ነው። ህወሓት የደፈጣ ውጊያውን የመራ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም ያለምንም ጥርጥር በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ የትግል ልምዳቸውም ከፍተኛ ነው፤ አመራሩንም በስፋት የያዙት እነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ አብረው የተጣመሩ ድርጅቶች አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃና ሶስተኛ ደረጃ ተብለው የተጣመሩ ነው የሚመስለኝ፡፡ እናም ያ በሙሉ ቁመናው አመራሩን የያዘው አካል ገለል ሲል የስልጣን ክፍፍሉ ላይ ሚዛናዊነትን የመፈለግ አዝማሚያ፣ በእነዚህ በደረጃ በተጣመሩት ድርጅቶች በኩል የመጣ ይመስለኛል። ለዚህ ነው ዛሬ በኦህዴድ ውስጥ የሚታየው እንቅስቃሴ በግልጽ የሚዛን ጥያቄ እንቅስቃሴ የሆነው፡፡
ብአዴን ውስጥ የሚታየውም ተመሳሳይ የሚዛን ጥያቄ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ በመነሳቱ በትንሽ በትንሹ የሚሰሙ የተወሰኑ ንግግሮች አሉ፡፡ እነዚያ ንግግሮች ደግሞ እጅግ እርስ በእርስ የተቃረኑ፣ የማይቀራረቡ ናቸው። ኢህአዴግ አሁን እንደ መንግስት አልደከመም፡፡ ፖለቲካዊ ምህዳሩን ዲሞክራሲያዊ በማድረግ ረገድ ችግር አለበት ልንል እንችላለን እንጂ ደከመ ማለት አንችልም፡፡ እዚህ ባልተረጋጋው የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ውስጥ የተረጋጋች ሀገር በመፍጠር ረገድ የኢህአዴግ መንግስት ሚና የለውም የሚል ሰው ካለ፣ ሁኔታውን ቁጭ ብሎ ቢያጠና ይሻለዋል፡፡ ኢህአዴግ ራሱን የሰየመው ልማታዊና ዲሞክራሲዊ መንግስት ብሎ ነው፡፡ ልማታዊ ነው አይደለም? ዲሞክራሲያዊ ነው አይደለም? የሚለውን ልንከራከርበት እንችላለን፡፡ መከራከሪያችን ይሄ ነው መሆን ያለበት እንጂ ከአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ተጠቃሽ የሆነች ሀገር እየመራ ያለ መንግስትን፣ደክሟል ወይም መግዛት አቅቶታል የምንል ከሆነ ተሳስተናል!
እርስዎ እንደገለጹት የኢህአዴግ ድርጅቶች ንቅናቄ እያሳዩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፣ ፖለቲካዊ ቁመናው ምን ይመስላል?
በኢህአዴግ ውስጥ የፖለቲካ ትውልድ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ አቶ መለስ ነበር ለድርጅቱ ብዙ እየተለመለት የሚሄደው፡፡ እሱ ከመሃል ዞር ሲል ብዥታ ውስጥ የገቡት ቀሪዎቹ ኮምፓሱ ነው የጠፋባቸው፡፡ አቶ መለስ በፊት “ቦናፓርቲዝም አሳስቷችኋል” ወይም “ኒዮሊበራሊዝም አሳስቷችኋል” እያለ ነበር በራሱ መንገድ የሚመራቸው፡፡ አሁን ያንን ማድረግ የሚችል የለም። በህወሓት ውስጥ የሚታየው ችግርም ነባሮቹና አዲሶቹ የፈጠሩት መገፈታተር ነው፡፡ አንድ ችግር ሲመጣ ወይ በሃይል ያሳልፈዋል፤ አሊያም አድፍጦ እንደ ሰጎን አንገቱን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ ነፋሱን ያሳልፈዋል። ድንገት ደግሞ ዋና የሚባለው የኢህአዴግ ሰውዬ ብድግ ይልና “ችግሩ የአመራሩ መበስበስ ነው” ብሎ ሁላችንንም ያስደነግጠናል፡፡ ይሄ ሰውዬ፤እሱ በሰራው ፍኖተ ካርታ ሰዎች ገደል መግባታቸውን ለማወቅ አይፈልግም፡፡ በአጭሩ አሁን ኢህአዴግ ፍኖተ ካርታው ተበላሽቶበታል፣ ኮምፓሱን አጥቷል፡፡ ግን በታሪኩ እንደሚታወቀው ሁሌም የሚያገግም ድርጅት ነው፡፡ ሞተ ሲባል በዛም በዚህም ብሎ አገግሞ ይነሳል፤ አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡
አሁንም ሀገሪቱ ከፖለቲካዊ ቀውሶች አልወጣችም፡፡  ችግሩ ምንድን ነው ይላሉ?
ኢህአዴግ በልማቱ በኩል ጥሩ ሆኖ ሳለ ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን በመዘርጋት ረገድ ከፍተኛ ክፍተት አለበት፤ ለምሳሌ ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ “ችግሬ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ነው” ይላል። አንድ ልብስ በአጃክስ ሳሙና አጥበኸው ጭቃው የማይለቅ ከሆነ፣ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ሳይሆን የመልካም አስተዳደር አለመኖር ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ደግሞ በዲሞክራሲ ውስጥ ብቻ ነው ሊኖር የሚችለው፡፡ ዲሞክራሲ በሌለበት መልካም አስተዳደር አይታሰብም። ለምሳሌ በደርግ ጊዜ አስተዳደር ነበረ፤ ግን መልካም አስተዳደር አልነበረም፡፡ በኃይለ ሥላሴ ጊዜም አስተዳደር ነበር፣ በሮማውያን ጊዜም እንዲሁ አስተዳደር ነበር፤ ነገር ግን መልካም አስተዳደር ተብሎ አያውቅም፡፡ መልካም አስተዳደር የዲሞክራሲ ልዩ የመዋቅር ይዘት ነው፤ ብቻውን ተነጥሎ የሚተገበር አይደለም፡፡ ለዲሞክራሲ ደግሞ ማህበራዊ ስምምነት ያስፈልጋል፤ የህግ የበላይነት ያስፈልጋል፤ በሁሉም ዘርፎች ለእኩልነት የሚደረግ ውድድር ያስፈልጋል፤ መልካም አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን አራት ነገሮች ሳያሟሉ ወይም ለማሟላት ጥረት ሳያደርጉ ዲሞክራሲያዊ ነው አይባልም፡፡ ነኝ ማለት ይቻል ይሆናል፤ግን መሆን አይቻልም፡፡
የኢህአዴግ አንዱ ክፍተት እዚህ ላይ ነው። ለምን ይሄ ክፍተት መጣ ካልን፣ መልሱ ቀላል ነው። ምክንያቱም ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት አይደለም፡፡  ኢህአዴግ ከአመሰራረቱም የነጻ አውጪ ድርጅቶች፣ የብሔረሰብ ነጻ አውጪ ንቅናቄዎች፣ የቡድን መብት ጠያቂዎች የተሰባሰቡበት ነው እንጂ የዜጎች መብት መጠየቂያ መድረክ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በአንፃሩ ስለ ዜጎች መብት ነው የሚያወራው፡፡ ስለ ዜግነታችን ነው የሚያወራው፡፡ የቡድን መብት ለማክበር ልዩ ሳይንስ አይጠይቅም። የቡድን መብት መከበር እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት የ1992 ስምምነት አፅድቆታል፡፡ ግን የቡድን መብት በዜግነት መብት ኪሳራ አይገነባም፡፡     
ህገ መንግስቱ ራሱ ሉአላዊነትን ለብሄር ብሄረሰቦች ነው የሚሰጠው፤ ለዜጎች አይደለም። ዲሞክራሲ ደግሞ የሚናገረው ስለ ሉአላዊነት ነው፤ ስለ እኩልነት ነው፡፡ የማን ሉአላዊነት? ሲባል - መልሱ የዜግነት ነው፡፡ ስለዚህ ዲሞክራሲ ላይ የታየው ክፍተት ከመነሻው የጀመረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ህዝብ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ለመወያየት እድሉን አላገኘም፡፡ ህዝብ ችግሩን ለመናገር እድል አልተሰጠውም፡፡  
ግን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ህዝብ አደባባይ እየወጣ ተቃውሞና ብሶቱን እያሰማ ነው ---
ጥቂት ምሁራን ወይም ዳያስፖራዎች ስለተናገሩ ህዝብ ተናገረ ማለት አይደለም፡፡ ህዝብ መች እድሉን አገኘ? መቼ እና የት ተናገረ?
በተለይ በኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎችና አድማዎች ተደርገዋል----”ነፃነት እንፈልጋለን” የሚሉ ጥያቄዎች ሳይቀሩ ተደምጠዋል ----
በእርግጥ በኦሮሚያ የነበረው የህዝብ ጥያቄ ነው ማለት አልችልም፡፡ ኦህዴድ የህዝብ ጥያቄ ነው ብሎታል። ነገር ግን ጥያቄው እንደሚባለው “የነፃነት ነው ወይንስ የፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ነው?” የሚለውን መፈተሽ  ያስፈልጋል፡፡
እርስዎ ጥያቄው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ጥያቄው  “ከማህበረ ኢኮኖሚው ተገልለናል፤ የበይ ተመልካች ሆነናል” ነው፡፡ በአብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ማን ነው ኢንቨስት እያደረገ ያለው? ይሄ ጥያቄ ነው በህዝቡ መሃል  ያለው፡፡ በገዛ መሬታችን ተገልለናል ነው ጥያቄው። “ህዝቡ ከሃብትና ከስልጣን መድረክ ላይ እየተገለለ ነው” የሚል የተወሰነ የልሂቃን ቡድንም አለ፡፡ ወጣቶቹ በተቃውሞ ላይ ፋብሪካዎች ሲያቃጥሉ እንኳን እየመረጡ ነበር፡፡ የሚወዱትና የሚጠሉት ኢንቨስትር አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በሃብት ክፍፍል ውስጥ የመገለል ስሜት የፈጠረው መቋሰል እንዳለ ነው የሚያሣየው፡፡
ሌላው ለምሳሌ፣ የኦሮሚያ ም/ቤት አዲስ አበባ ላይ ያለው የጥቅም ጥያቄ ለምን መጣ ካልን፣ ይሄም የሃብት ጥያቄ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በማንኛውም መንገድ ቢመጣ፣ የህዝብ ጥያቄ ትንሽ ነው ትልቅ ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ጥያቄው የሃብት ድርሻ ተጠቃሚነትና ከማህበራዊ-ኢኮኖሚ የመገለል ጉዳይ ነው፡፡
መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች በትክክል ተረድቷል ማለት ይቻላል? መልስ ወይም መፍትሄ በመስጠት ረገድስ?
ለአንድ ችግር መፍትሄ ለመስጠት የተለያየ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ግን ይሄ ሲደረግ አላየንም። ከመፍትሄ መንገዶች አንዱ ትንሽ ፋታ ለማግኘት በመጠኑ አፈር ማልበስ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው መንገድ፣ “ለምን ይሄ ችግር ተንፀባረቀ?” የሚል ጥያቄ አስቀምጦ መፍትሄ ማፈላለግ ነው። ለዚህ ደግሞ ነፃ ህዝባዊ ውይይቶችን በየቦታው ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ያንን መድረክ መምራት ያለበት ደግሞ መንግስት አይደለም። ገለልተኛ የሆኑ አካላት ናቸው ሊመሩት የሚገባው። ለምሳሌ የሠራተኛ ማህበራት፣ የመምህራን ማህበራት፣ ሌሎች ማህበራት ---- በነፃነት ስለ ሃገራቸው ጉዳይ እንዲወያዩ መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡
እስካሁን ይሄ ሲደረግ አላየንም፡፡ ኢህአዴግ በዘረጋው መንገድ ውስጥ ብቻ ነው አሁንም እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ ጥያቄው ደግሞ “ኢህአዴግ የዘረጋው መንገድ አልተመቸንም” የሚል ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ባለ ሁኔታ ነው መነጋገር የሚቻለው? ምሁራኑ ለሀገራቸው የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሀሳብ አጥተው አይደለም ግን ሰሚ ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚ ነን የሚሉት ፓርቲዎች፣ ራሳቸው በህዝብ መድረክ ላይ በሚያቀርቡት አማራጭ እንዲፈተኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ እስካሁን ተደርጓል? አልተደረገም። ተቃዋሚዎች አማራጭ እንዳያቀርቡ መደረጉ ወደ መፍትሄው የሚወስደውን መንገድ እንዳልጀመርነው ያመለክታል፡፡ እውነተኛ ተቃዋሚም የሚበቅለው እንዲህ ያለው መድረክ ሲፈጠር ነው፡፡ አለበለዚያ ተቃዋሚ ፓርቲ ሳይሆን እስካሁን እንደነበረው ባላንጣ ነው እየተፈጠረ የሚሄደው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁንም ድረስ የባላንጣነት ፖለቲካ ነው። የተቃውሞ ፖለቲካ ገና አልመጣም፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት፤ “መንግስቴን የምመሰርተው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው” ብሎ ነው የሚነሳው፡፡ ይሄ የመጠፋፋት ፖለቲካ ነው የሚባለው፡፡
የሀገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
የሰሞኑን የዚምባቡዌ ሁኔታ እንኳን ብንመለከት፣ ሮበርት ሙጋቤ በሃገር ውስጥም በውጪም  እየተጠላ ነው የኖረው፡፡ ግን እየተገፋፋም ቢሆን ይሄን ያህል ዘመን ሊቆይ ችሏል፡፡ ግን መጨረሻው እንደምናየው ነው የሆነው፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነገርም፣ በጣም ያስጨንቀኛል፡፡ የሚያስጨንቀኝ ደግሞ መፍትሄው ከግንዛቤያችንና ከእውቀታችን በላይ እንዳልሆነ እያየን፣ በመነጋገር ብቻ ብዙ ነገር ልንሰራ እንደምንችል እያወቅን ሳናደርግ ማለፋችን ነው፡፡ ከዛ በተረፈ መንግስት ትልቅ አካል ነው፡፡ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ ብዙ ጥያቄ ይዞ ውስጥ ለውስጥ ሊብከነከን ይችላል፡፡ ይሄ መብከንከን ግን መጨረሻው ምሬት ነው የሚሆነው፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እንዳሰበ ለማወቅ ያስቸግራል። መከላከያው ምንድን ነው የሚያስበው? ደህንነቱስ? የሚለውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን ደግሞ ፓርቲ ሲዳከም ወታደሩ ምን እንደሚያደርግ ለኛ ባዳ አይደለም፤ የምናውቀው የቅርብ ታሪክ ነው፡፡ እኔ ግን የሚታየኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ የሚመጣ ከሆነ፣ የኢህአዴግንም መዋቅር ያካተተ መሆን አለበት። አለበለዚያ በህዝባዊ እንቅስቃሴ ለውጥ ይመጣል ብለን የምናስብ ከሆነ፣ አንደኛ ህዝባዊ እንቅስቃሴውን የሚፈቅድ ሁኔታ መኖር አለበት። ሰልፍ በተወጣ ቁጥር ጠመንጃ ይዞ የማይመጣ ቡድን ያስፈልጋል፡፡ በደርግ ዘመን የነበሩ ምሁራን ችግር እኮ የአደረጃጀት ነው፡፡ በአደረጃጀት ችግር ትግሉን አጋልጠው ስኬት ማግኘት አቃታቸው። አሁንም በህዝባዊ እንቅስቃሴ ብቻ ዝም ብሎ ሥርዓቱ ይፈርሳል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡
ወዴት አቅጣጫ እየተጓዝን እንደሆነ አናውቀውም ማለት ነው?
አዎ! ምንድን ነው የምንፈልገው? ለዲሞክራሲ ነው የምንሄደው? ለዲሞክራሲ የምንሄድ ከሆነ ደግሞ አሁን ኢህአዴግ የገነባው “ኢትኖ-ናሽናሊዝም ፌደራሊዝም” ቦታው ምን ጋ እንደሆነ ተንትኖ ማየት ያስፈልጋል። ይሄ ጉዳይ ከምሁራኑም ከፖለቲከኞቹም በአግባቡ ሲቀርብ አናይም። በቀጣይ ሊሆኑ የሚችሉ ግምቶችን (ሴናርዮ) ለማስቀመጥ ያስቸግራል፤ ግን እኔ አሁን እንደማየው ኢህአዴግ በራሱ ውስጥ በነጠላም በጋራም እየተወያየ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ክልሎች እየተቀናጁ እየተወያዩ ነው። ይሄ አሁን ኢህአዴግ  አስቦ ያደረገው ይሁን አይሁን አላውቅም፤ ግን ገና ድሮ መደረግ የነበረበት ነው። ለህዝብ ይጠቅማል ወይ? ዲሞክራሲን ያመጣል ወይ? የሚለውን ለወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ግን ምን ያህል የዜግነት መብትን ለማስከበር ይረዳል? የሚለው አሁንም ጥያቄ ነው፡፡ ለኔ የሚታየኝ አሁንም ኢህአዴግ እነዚህንም “ማሣጅ” አድርጎ ያበራርድና ችግሩ ይቀጥላል፡፡ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፤እኔ የሚታየኝ በዚህ መልኩ ነው፡፡
ሌላው የጥላቻ ፖለቲካ የመበርከቱ ጉዳይ ነው። ፖለቲከኞች ነገሮችን ተንትኖ ለማየት አይሞክሩም። በቃ አንድን ነገር ከጠላህ ተቃዋሚ ለመሆን በቂ ነው። ከዚያ እነሱ ከሚጠሉት ሰው ጋር ቡና የጠጣም ይጠላል። በመጥላት ስርአት አይለወጥም፣ ስርአት የሚለወጠው በእውቀት ነው፡፡ ለስርአት ለውጥ ቁልፉ፣  ጥላቻ ሳይሆን እውቀት ነው፡፡
ዛሬ የቸገረው እኪ የነገደ - ብሄርተኝነት (ethno-nationalism) አቀንቃኝ የሆነው ምሁሩ ራሱ ነው፡፡ ህዝብ ርዕዮተ አለም አያውቅም፡፡ ድህነት አስጨንቆታል። ስለ ርዕዮት ሲመራመር አይውልም። ርዕዮት የሚያቀርብለት ልሂቁ ነው። ልሂቁ ርዕዮት ለማቅረብ ደግሞ ምህዳሩ መከፈት አለበት፡፡ ሌላውም “እንዲህ ለህዝብ ስታገል ነበር” እያለ ተረት ሲያወራ ከሚውል፣ ለህዝብ ስልጣኑን ለቀቅ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይ እንደ እኔ እድሜያቸው ከፍ ያሉት፣ ምህዳሩን ለወጣቱ ቢለቁለት ጥሩ ነው፡፡
አሁን ያለው የተምታታ ነገር ነው፡፡ በአንድ ጎን ስለ ባንዲራ ቀን ያወራሉ፣ በሌላ በኩል ስለ ጠባብነት ያወራሉ፡፡ በአንድ በኩል “ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች” እንላለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ይሄ ህዝብ ያኛውን ጨቁኖታል” እያልን እናወራለን። ሁኔታው የተምታታ ነው፡፡ ልክ እንደ ባቢሎን ግንብ ገንቢዎች፣ ጠጠር ሲባል ውሃ፣ ውሃ ሲባል አሸዋ እንደሚያቀብሉት ነው የሆነው። ይሄ ሥነ ምህዳር መቀየር አለበት፡፡ የወደፊት የለውጥ ፍኖተ ካርታችንን ሳንሰራ፣ ዝም ብሎ በግርግርና በጩኸት ለውጥ ሊመጣ አይችልም።
በዚህ ሁሉ መሃል የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴና  ሚና  እንዴት ያዩታል?
ከበፊት ጀምሮ በዚህች ሀገር ማምጣት ያልተቻለው፣ በሳል የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲን ነው። የመጀመሪያው ችግር ዲሞክራሲን እንደ አጀንዳ ይዞ የተንቀሳቀሰ አካል ያለመኖሩ ነው። በተማሪዎች እንቅስቃሴ “መሬት ለአራሹ” በምንልበት ጊዜ ሀገራዊ አጀንዳ ነበረን። ያ ሀገራዊ አጀንዳ ግን ብዙ እድሜ አላገኘም፡፡ በማርክሲዝም ርዕዮተ አለም ተጠለፈ፡፡ በ1983 ደግሞ አጀንዳውን በሙሉ ነገዳዊ ብሄርተኝነት ጠለፈው። ነገዳዊ ብሄርተኝነት በወቅቱ ዲሞክራሲን ከጨዋታ ውጪ ነው ያደረገው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ነገዳዊ ብሄርተኝነትን ነው ዲሞክራሲ የሚሉን። ዲሞክራሲ ግን ፅንሰ ሀሳቡ ይሄ አይደለም። ተቃዋሚዎች የሚባሉትም ስለ ዲሞክራሲ ምንም ያህል አያውቁም። እኔም በቅንጅት ውስጥ ነበርኩ። ግን በመጯጯህና በግርግር ስለማላምን፣ መታገል ያለብን በእውቀት ነው እያልኩ ነበር የምጮኸው። “ዳር ተቀምጦ ገብቶ ማስተካከል” በሚል እሳቤ ነበር ወደ ቅንጅት የገባሁት፡፡ ይሄን ሳደርግ ለፓርላማ አልተወዳደርኩም ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ትልቅ ስህተት ነው የሰራነው፡፡ ቅንጅት በወቅቱ ያገኘውን ወንበር ይዞ ፓርላማ መግባት ነበረበት፡፡ ይሄን በማድረግ ቢያንስ ቅንጅት የሚለውን መንፈስ ማቆየት ይቻል ነበር። ዛሬ ያሉትን በውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ ስንመዝናቸው፣ የረባ ነገር የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም እምነቱን አልጣለባቸውም፡፡
እኔ “ለኢትዮጵያ ብንታገል መልካም ነገር እናመጣለን” ብለው የሚያምኑ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን፣ ስብስቦችን፣ ፓርቲዎችን አከብራለሁ። ግን ትልቁ ጥያቄዬ፤ እነሱ ራሳቸው ዲሞክራሲያዊ ናቸውን? የኢትዮጵያን ችግር እንዴት ለመፍታት ነው የተዘጋጁት? የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ጥያቄ ለመሸሽ ደግሞ አሁን ትልቅ ማሳበቢያ አግኝተዋል። እሱም የምህዳሩ መጥበብ ነው። አንድ የኢህአዴግ ጎምቱ ሰው ሲናገሩ የሰማሁት አንድ ነገር አለ፡፡ “ለኢትዮጵያ ችግር የተቃዋሚዎች ደካማ መሆንም መታየት አለበት” ነው ያሉት፡፡ ይሄ ይገርማል። ተቃዋሚዎች የድክመታቸውን ክፍተት ለመሙላት ነፃነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይም የጠራ አቅጣጫ አልተያዘም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መመስረትና መምራት የጀብድ ሥራ አይደለም፡፡ ሀገሪቱ ላይ ያለው የጣሊያን መንግስት አይደለም’ኮ! ጎራዴ ይዘን ጦር የምንገጥምበት የጀብድ ጉዳይ አይደለም! የፈሪና የጀግና ጉዳይ አይደለም፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ማለት፣ የሰለጠነ ህዝብ በሀሳብ የሚያደርገው ፍጭት ነው፡፡ እስክሪብቶ ይዞ፣ ታንክ ከያዘ መንግስት ጋር መላተም የምን ጀብድ ነው? ይሄ ነው  ከሁለቱም ወገን መታረም ያለበት፡፡
በዚህ  ሁኔታ ውስጥ የምሁራኑ ድርሻስ ምን ጋ ነው ያለው?
ምሁራኑ አሁን አድፍጠዋል፡፡ ምሁራኑ አንደኛ በነገዳዊ ርዕዮት አመለካከት በሁለት ፈርጅ ተከፋፍለዋል። ይሄን በቅርብ በሚወጣው መፅሐፌ በዝርዝር አስፍሬዋለሁ፡፡ ሌሎቹ ከመንግስት ሥርአት ጋር ወግነው፣ ለሱ የቆሙ እና ከሂደቱ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ከተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉም አሉ፡፡ ምናልባት ለውጥ ቢመጣ ብለው፡፡  አብዛኛው ግን አድፍጧል፡፡ አድፍጦ ዝምታ ውስጥ ነው ያለው፡፡
ግን ከምሁራኑ የሚጠበቀው ምንድን ነው?
አንደኛ ከእውነት መወገን ነው ያለባቸው፡፡ ምሁራን ለእውነት መቆም አለባቸው፡፡ ለእውቀቱ ታማኝ መሆን አለበት፤ ምሁሩ፡፡ አተርፋለሁ ብሎ ራሱን ለጥቅም መሸጥ የለበትም፡፡ ምሁር እውነቱን ባይናገር እንኳ አይዋሽ፤ ዝም ይበል፡፡
“እውነት ካልተናገርን ዝም ብንል ይሻላል” በሚል አድፍጠው ይሆን እንዴ?
የኛ ሀገር ምሁራን ሁኔታ እንደዚያ አይደለም። እርግጥ በኛ ሀገር ምሁራን ላይ ወቀሳ በስፋት ይሰነዘራል። ይሄን ስመለከት ለምን የዓለም ምሁራንን ሁኔታ አላጠናም ብዬ በርካታ መፅሃፍት ለማገላበጥ ሞከርኩ፡፡ ግን ሁሉም የዓለም ምሁራን አፈግፍገዋል፤ አድፍጠዋል የሚል ወቀሳ ነው የሚሰነዘርባቸው። በኛ  ሀገር እስከ 1983 አንድ አይነት አጀንዳ ነበር በሀገር ጉዳይ የሚወራው። በ1984 ላይ ከተመሰረቱ 60 ያህል የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አብዛኞቹ የብሄር ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ምሁሩም በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ነው የተገጠገጠው። የፖለቲካ ስርአቱ ምሁሩን በነገዳዊ ብሄርተኝነትና በሀገራዊ ብሄርተኝነት ነው የከፋፈለው። አሁን ሀገራዊ ብሄርተኝነትን የሚያቀነቅነው በስደት ላይ ነው ያለው። ግን እዚህ እዝ አለው፡፡ እዙን የሚያስፈፅመው ደግሞ የእውቀት ክፍተት አለበት። ስለዚህ የኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ነው ያሉት፤ ይሄ በትክክል መጠናት ያለበት ነገር ነው፡፡
በዚህ ሀገር ላይ እርስዎ በሚሉት ልክ የዲሞክራሲ ሥርአት ላለመፈጠሩ ዋና ተጠያቂው ማን ነው?
የመጀመሪያው ተጠያቂ የሚሆነው ባህላችን ራሱ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ የሊበራል አስተሳሰብ አልሰፈነም፡፡ አሁን እኛ ያገኘነው መንግስት የሚገባንን ነው፡፡ የኛ ባህል ነው የፈጠረው፡፡ ባህላችን፣ ድህነታችን አጎብድደን እንድንኖር ነው የሚያስገድደን፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ምሁራንን አሸሽቶ ጥግ የሚያስይዛቸው የኑሮ አቅማቸው ነው። የመጠለያ ቤት ችግር አለባቸው። የኢትዮጵያ ምሁራን ድሆች ናቸው፡፡ የሌሎች አገራት ምሁራን እኮ ሀብቱም እውቀቱም እኩል አላቸው፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት አለመገንባት አጠቃላይ ሶሺዮ- ኢኮኖሚያዊ ስርአቱ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማቋቋም እኮ ተአምር አያስፈልግም፡፡ አንዱና ዋነኛው ከህገ መንግስት በታች የሆነ መንግስት መኖር ነው፡፡ ሌላው እኛ ሀገር  ገንዘብ ያለው መካከለኛ መደብ እንጂ እውቀት ያለው መካከለኛ መደብ ህብረተሰብ አልተገነባም፡፡ ይሄም የራሱ አስተዋፅኦ አለው፡፡
በአጠቃላይ ለሚታዩት ፖለቲካዊ ችግሮች እርስዎ የሚጠቀሙት መፍትሄ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመመስረት በጎ ፍቃድ ያለው አካል ያስፈልጋል። በቃል የሚባለውን መተው አለብን፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ እውቀት ይፈልጋል። እውቀት ደግሞ ከውይይት ይመነጫል፡፡ ስለዚህ ህዝቡን ለማወቅ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ የጎደፉ ሀሳቦች የሚሸነፉት በሀሳብ እንጂ በጠመንጃ መሆን የለበትም። በጠመንጃ የሚሸነፍ ሀሳብ የለም፡፡ የምንማማርበት መድረክ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ለመማማር የሀሳብ ነፃነትን መፍቀድ አለበት። ጠመንጃውን ከፖለቲካ አውዱ ላይ ገለል ማድረግ አለበት፡፡ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ንግግር ውስጥ እንዲገቡ የመጀመሪያ እድሉን መፍጠር የመንግስት ድርሻ ነው፡፡ ኢህአዴግ አንድ አካሄድ አለው፤ ችግር ሲመጣበት መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ አንገቱን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ፣ ነፋሱን ያሳልፋል። ነፋሱ ካለፈ በኋላ ደግሞ “ችግሩ እኔው ጋ ነው ያለው” ይለንና ያስደነግጠናል። ይሄ ይገርመኛል። ለምን ቀድሞ ማስተካከል አይቻልም? ይሄን ማድረግ ለምን አይደፍርም?


Read 3645 times