Sunday, 26 November 2017 00:00

ጀምበር በእበት አይመረግም “ቤያት ይባራ ኤያረ” (የጉራጊኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከጥንታውያን ፋርሶች ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖር እጅግ ሞገደኛና አስቸጋሪ ወጣት ነበር፡፡ ይህ ወጣት ልጃገረዶችን እየደበደበ ያስቸግራል፡፡ ንብረታቸውን ይቀማል፡፡ ወደ ቤታቸው በጊዜ እንዳይገቡ አግቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡ አባቱ አንቱ የተባለና የሚፈራ በመሆኑ፣ ደፍሮ የሚናገረውና ተው የሚለው ቤተሰብ የለም፡፡
ይኼ ወጣት፣ ከልጃገረዶችም አልፎ ወጣት ወንዶችን ያስፈራራል፡፡ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ያደርጋል፡፡ እያስፈራራ ፍራንክ ይቀበላል፡፡ ደብተር ይነጥቃል፡፡ ለሞገደኛ ተግባሩ ተባባሪ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል፡፡
ይኼ ወጣት በወጣት ሴቶችና ወንዶች ላይ የሚፈፅመው ጥፋት አልበቃ ብሎት፤ አረጋውያንና አሮጊት ሴቶች እያስፈራራ፣ ቁልቁል ይሄዱ የነበሩትን ሽቅብ፤ ሽቅብ ይሄዱ የነበሩትን ቁልቁል፣ ያስኬዳቸው ነበር። ይህ ሞገደኛ የሰፈር ወጣት፣ ለወላጆቹ ጥፋቱ ተነገረ፡፡ ተው ተባለ፡፡ አሻፈረኝ አለ። ለትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ  እንዳይነገር ትምህርቱን ጥሎ ከወጣ ቆይቷል፡፡ እንዲህ በሞገደኝነት እየተቀናጣ ብዙ ጊዜ ሲያስቸግር ከረመ፡፡
አንድ ቀን የሰፈር ልጆች ተሰበሰቡና፤
“እስከመቼ ይሄ ሞገደኛ ሲጫወትብን ይኖራል? አንድ ነገር ማድረግ ይገባናል” ማለት ጀመሩ፡፡
የሞገደኛውን ወጣት የዱሮ ዝና ያስታወሱ አፈገፈጉ፡፡
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ያሉትም አያመልጥም፤ በጋራ እናሳየዋለን፤ አሉ፡፡
ሁለተኞቹ ወገኖች፤ ሰፈሩን ዙሪያውን ከበን እንያዘው ተባባሉ፡፡ የሞገደኛውን ቤት ከበቡ፡፡ እንደተከበበ ያወቀው ወጣት እቤቱ አጠገብ ካለ ትልቅ ባህር ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ጫፉ ላይ ተቀመጠ፡፡
ተከትሎት ዛፉ ላይ የሚወጣ ጀግና ጠፋ፡፡ ስለዚህ መላ መምታት ተያዘ፡-
አንዳንዶች - እዛው እንዳለ በድንጋይ እንውገረው - አሉ፡፡
አንዳንዶች - የለም ዝም ብለን ብንጠብቀው ሲርበው ይወርዳል-አሉ፡፡
ሌሎች - ቀላሉ መንገድ ለፖሊስ ነግረን እንዲያስወርደው ማድረግ ነው አሉ፡፡
ተቃራኒዎቹ፤ ፖሊስ እጅ ከፍንጅ ሲያጠፋ አልያዝኩትም፤ ዛፍ ላይ መውጣት ወንጀል አይደለም፤ ማስረጃ ሰብስቡ ነው የሚለን አሉ፡፡
ደግሞ ሌሎቹ - ዛፉን ብንቆርጥበት ይወድቃልኮ! አሉ፡፡
የሰፈሩ ወጣቶች ይሄን ይሄንን ሲመክሩ፤ ሞገደኛው ወጣት ድንገት መውረድ ጀመረ፡፡ አካባቢው ሁሉ ፀጥ አለ፡፡ ወጣቶቹ ሲወርድ ምን እንዲያደርጉ ግራ ተጋቡ፡፡ ግማሾቹ ገለል ማለት ጀመሩ፡፡ ግማሾቹ ዱላ አዘጋጁ፡፡ ከፊሎቹ ድንጋይ ያዙ!
ዛፉ ወገብ ላይ ሲደርስ፤
“ለፖሊስ እጄን ልሰጥ ነው፡፡ እንደማትነኩኝ ቃል ግቡልኝ” አላቸው፡፡
“ውረድ ማንም አይነካህም” አሉት፡፡ ፖሊስ ተጠርቶ መጣ፡፡ ወጣቱ ወርዶ እጁን ሰጠ፡፡
“ለዚህ ለዚህ ለምን በፊት እንደዚህ አላደረግህም?” አሉት፡፡
“እንዳስቸገርኳችሁ ጀምሬ እንዳስቸገርኳችሁ ለመጨረስ ስለፈለግሁ ነው!” አላቸው፡፡
*      *     *
መሪዎች አሻፈረኝ ሲሉ ህዝቦች ልክ ያገቧቸው ዘንድ የዲያሌክቲክ ህግ ግድ ይላል፡፡ አምባ - ገነን መሪነት ከአፍ እስከ ገደፏ የሆነችው አፍሪካ፤ በጉልበት ወደ ሥልጣን የሚመጡ፣ በጉልበት ሥልጣን ላይ የሚቆዩና ያለ ጉልበት ከስልጣን አንወርድም የሚሉ መሪዎች ተለይተዋት አያውቁም፡፡ በእርግጥ ከስልሳዎቹ እስከ ዛሬ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆኑ የላቲን አሜሪካም መሪዎች አምባገነናዊ ባህሪያቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም እያወሩ ህዝብን ረግጠው ይገዛሉ፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም እያወሩ የህዝብን ሀብት ይመዘብራሉ፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም፣ ስለ መልካም አገዛዝ፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ብሄራዊ ብልፅግና፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮ መኖር… ወዘተ ያወራሉ፡፡ ድርጊታቸው ግን ተፃራሪ ነው! ከአፍሪካ ካውንዳ፣ ኢዲ አሚን፣ ሞቡቱ፣ ኦማዱ፣ ቦካሳ፣ አራፕሞይ፣ ሳሙኤል ዶ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ አሚን፣ ኬንያታ፣ ንጉማ፣ ቦንጎ፣ ሲያድ ባሬ፣ አልባሺር፣ ሴኩ ቲሬ፣ ሀሰን ጉሌድ፣ ካሙዚ ገንዳ፣ ሙጋቤ፣ የሚጠሩት ስሞች ሁሉ ቦታ ቢለዋወጡ ስለ አንድ ሰው የምናወራ ያህል አንድ ናቸው፡፡ የካምቦዲያው ፓል ፖት፣ የቺሊው ፒኖሼ፣ የፓራጉዋዩ ስትሮስነር፣ የፖላንዱ ጃሬ ሴልስኪ፣ የአርጀንቲና ዱዋርቴ፣ የስፔኑ ፍራንኮ ወዘተ… ሁሉም ያው ናቸው! አምባገነን አምባገነን ነው! ምንም ቦቃ አይወጣለትም - በጉልበት ይወጣል፣ በጉልበት ይኖራል፤ በመጨረሻ በጉልበት ይወርዳል!
ሐማ ቱማ የተባለው ኢትዮጵያዊ ፀሀፊ ስለ አካፋና ኢትዮጵያውያን (of spades and Ethiopians) በተባለው የግጥም መድበሉ What is in a name (ከስሙ ምን አለህ? እንደማለት ነው) እንዲህ ይለናል፡-
“… ሌሮይ ጆንስ አልከው ኢማሙ ባራካ
ጆሴፍ ዴ ሲሬ ሴሴኮ ዋዛባንጋ፤
ሊዎፖልድ ሆነ አማዱ
ኬራኩ ሆነ መንግሥቱ፤
አሚን ቦካሣ ቦንጎ
ሐቢብ ሞይ አሊያም ሳሚዶ፤
ስሙ ይቀያየር እንጂ
ሎሌማ ያው ሎሌ’ኮ ነው
ገዳይ ምንጊዜም ገዳይ ነው!
ስማቸውን ብትለዋውጥ
ወይ ቢቀያየር መልካቸው
ሎሌ ሁሌም ሎሌ ነው
ነብሰ - ገዳይ ያው ገዳይ ነው!!
ሁሉን የሚያስረው ሰንሰለት፣
ጫፉ ሌላ ቦታ ነው
አንተ ከሰሙ ምናለህ
ጠማማውን ጭንቅላት እየው እንጂ አዟዙረህ!
እየው ቦታውን ለዋውጠህ!”
ይለናል፡፡ የአምባገነን ስሙና መልኩ እንጂ ሥራውና ሤራው አንድ ነው፡፡
“አምባገነኖች መውረድ ከማይችሉበት የነብር ጀርባ ላይ ሆነው ወደፊትና ወደኋላ ይጋልባሉ፡፡ ነብሮቹ ግን ከቀን ቀን እየራባቸው ይሄዳሉ” ይላሉ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፀሐፊ፤ ዊንስተን ቸርችል። ሁሉም አምባገነኖች እናታቸው አንድ ናት! አንዳቸውም ከአንዳቸው አወዳደቅ አይማሩም! የታላላቅ ሰዎችን ማንነት፣ ማክበርና ማስከበር ከብዙ ደካማ አገዛዝና ውድቀት ያድናል፡፡ ትልቅን ለማክበር ዝግጁ መሆን፣ ወደ ትልቅነት መንገድ መጀመር ነው፡፡ ተገፍትረው እስኪወድቁ የሚጠብቁ ያልታደሉ መሪዎች ናቸው፡፡ ታላላቅ ሰዎቻቸውን የሚያዋርዱና የሚንቁ መጨረሻቸው አያምርም! ትልቅን ለመሸፈንና እንዳይታይ ለመጋረድ መሞከር የጅል ጥረት ነው! “ጀምበር በእበት አይመረግም” የሚለው የጉራጊኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ዕውነት ነው!

Read 4507 times