Saturday, 25 November 2017 09:58

“አጀንዳ ከማስቀየስ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

51 የቀድሞ “አንድነት” ፓርቲ አባላትና አመራሮች ከሰሞኑ “ሰማያዊ” ፓርቲን ተቀላቅለዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ፓርቲው ከመኢአድ ጋር የሚያደርገው ውህደት ከዚህ ዓመት እንደማያልፍ ጠቁሟል፡፡ በአመራሩ መካከል በተፈጠረ ውዝግብ ከፓርቲው ተገልለው የቆዩት በኢ/ር ይልቃል ጌትነት የሚመሩት “የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ሸንጎ” አባላትም፣ በቅርቡ በሽምግልና ወደ ፓርቲው ሊመለሱ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡በፓርቲው እንቅስቃሴዎችና በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤
ከ”ሰማያዊ” ፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

ፓርቲያችሁን በቅርቡ የተቀላቀሉት የቀድሞ “አንድነት” ፓርቲ አባላት እነማን ናቸው?
ወደ ‘እኛ ፓርቲ የመጡት “አንድነት”  በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለሌላ ሰው ሲሰጥ፣ ከፓርቲው የወጡ ዋና ዋና አመራሮችና አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት አዲስ ፓርቲ ለመመስረትም እንቅስቃሴ ላይ ነበሩ። ባደረግነው ውይይትም አዲስ ፓርቲ መመስረቱን ትተው፣ ባለፈው ወር ጥቅምት 21፣ መኢአድ ቢሮ ተሰብስበው ውሳኔ በማሳለፍ ነው፣ ሰ”ማያዊ”ን  የተቀላቀሉት፡፡
ምን ያህል ናቸው? በቀድሞ ፓርቲያቸው የነበራቸው የሃላፊነት ደረጃስ?
51 ናቸው፡፡ ፓርቲው ለሌላ ሰው ሲሰጥ በሊቀመንበርነት ላይ ከነበሩት አቶ በላይ ፍቃዱና ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በስተቀር  ሁሉም የሥራ አስፈፃሚዎች አሉበት፡፡ አብዛኞቹም በ”ቅንጅት” ውስጥ ጠንካራ ሚና የነበራቸው ናቸው፡፡
እነዚህ የቀድሞ “አንድነት”  አመራርና አባላት፣ “ሰማያዊ”ን  መቀላቀል  ፋይዳው ምንድን ነው?
አንደኛ ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ያላቸው የትግል ልምድ፣ ቁርጠኝነትና እውቀት ለፓርቲያችን ትልቅ ግብአት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሌላ ፓርቲ መምራትም የሚሉችና ሲመሩም የቆዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ አቅማችንን የበለጠ ያዳብሩልናል። ሌላው እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይደግፉ የነበሩ ኢትዮጵውያንም፣የኛ ደጋፊ የመሆን እድላቸው ይሰፋል፡፡ በአጠቃላይ ለፓርቲያችን ትልቅ ግብአት ነው፤ የበለጠ መጠናከር ይፈጥርልናል፡፡
ከፓርቲዎች ጋር ህብረት ፈጥሮ በመስራት በኩል “ሰማያዊ” ፓርቲ መርሁ ምንድን ነው?
በፓርቲ ውስጥ ትልቁ ቁም ነገር በውስጡ ያለው የሰው ኃይል  ቁርጠኝነት፣ ልምድና እውቀት ነው። ይሄን እውቀት መንዝሮ ለሀገሪቱ አመራር ለማፍራት እስከተቻለ ድረስ ለአባላት የምንሰጠው ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ፓርቲው መሪዎችን ለሀገሪቱ ያበቃል። ፓርቲው የመሪዎች መፈልፈያ ቦታ ይሆናል ብለን እናምለን፡፡ “ሰማያዊ” የሚያራምደው ለዘብተኛ ሊብራል አስተሳሰብን ነው፡፡ ለዘብተኛ የሚያደርገን በኢኮኖሚና ማህበራዊ አስተሳሰቦች ላይ ከግለሰቦች ባለፈ የቡድን መብት አለ ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ መንግስትም ሜጋ ፕሮጀክቶችን መስራት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡
ፓርቲያችሁ ከተመሰረተ 6 ዓመት ሆኖታል፤ እስካሁን ሰላማዊ ሰልፍ ከማዘጋጀት ባለፈ ምን ተጨባጭ ውጤት አምጥቻለሁ ብሎ ያምናል?
 “ሰማያዊ” እንደ ፓርቲ 6 ዓመት ይሁነው እንጂ የተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ አመራር የነበሩ ግለሰቦች የመሰረቱት ነው። ሰላማዊ ሰልፍ የምናደርገው ህዝቡ ዘንድ ያሉ ብሶቶችና ቅሬታዎች ወደ አደባባይ እንዲወጡ ለማገዝ ነው፡፡ መብትን መጠየቅ በተመለከተ ያለውን አመለካከት ለመለወጥ ነው እንቅስቃሴ ስናደርግ የነበረው፡፡ የመጀመሪያ ሰልፋችንን ያደረግነውን ባለፈው ሰሞን በጣሊያን ፍ/ቤት እንዲፈርስ የተወሰነውን የግራዚያኒን ሀውልት በመቃወም ነበር፡፡ አንድ የፖለቲካ ኃይል፣ ያለውን ችግር በአደባባይ አውጥቶ ማሳየት አንዱ ኃላፊነቱ ነው፡፡ ይሄን በተለያዩ አግባቦች ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ስናዘጋጅ ሂደቱንም በዚያው እየፈተሽን ነበር፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ጉዳይን ፈትሸን ለአደባባይ አብቅተናል፡፡ ሰልፎቹም ህዝቡን ያነቃቁና አሁን ላለው ህዝባዊ የመብት ጥያቄ፣ በር የከፈቱ መነሻዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ከቀድሞ የ”ሰማያዊ” አመራሮች ጋር ቅራኔ ውስጥ ከርማችሁ አሁን ሽምግልና ተቀምጣችኋል፡፡ ሽምግልናው ምን ላይ ደረሰ?
እዚህ ላይ ብዙ መናገር አልችልም፡፡ ግን እነዚህ ጓዶች፣ ወዳጆቻችን ናቸው፤ በትግል ብዙ ያሳለፍን ነን። አሁንም ቢሆን ያስፈልጉናል፡፡ ግን ስህተቶች ነበሩ። ትግሉን ወደፊት ማራመድ ሲገባን በወቅቱ የተሰሩ ስህተቶች ነበሩ፡፡ አሁን ይሄን ስህተት ተራርመን፣ ወደፊት ለመቀጠል፣ ሽማግሌዎች እያግባቡን ነው፡፡ በኛ በኩል ሙሉ ፍቃደኛነታችንን ገልፀናል፡፡ በእነሱ በኩል ያለውን በዝርዝር ባላውቅም፣ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ የሽምግልናው የመጨረሻ ውጤት ይታወቃል  የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከመኢአድ ጋር የጀመራችሁት ውህደትስ መቼ ይጠናቀቃል?
አሁን አብረን እየሰራን ነው፡፡ የሁለቱም ፓርቲ መሪዎች በአሜሪካ ለዚሁ አላማ የሚሆን ተግባር እያከናወኑ ነው። እነሱ ሲመለሱ ሶስት ጉባኤዎች ይደረጋሉ፡፡ ጉባኤዎቹ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። በቂ አቅም ከተፈጠረ በኋላ ውህደቱ ይጠናቀቃል፡፡ ውህደቱ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል፡፡ ከዚህ ዓመት የሚያልፍ አይሆንም፡፡
“ሰማያዊ” ፓርቲ  አገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዴት ያየዋል? መፍትሄውስ ምንድን ነው?
ችግሩን የፈጠረው ለዘመናት የተከመረ የህዝብ ብሶት ጫፍ ላይ መድረሱና መፍሰስ መጀመሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ለማስተካከል እድል የነበረው ቢሆንም የተሰጡትን ምክሮች ተቀብሎ አለማስተካከሉ  ዋጋ እያስከፈለው ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ስርአቱ ችግሮችን ቀርፎ፣ ቆሞ ለመሄድ አቅም አለው የሚል ግንዛቤ የለንም፡፡
በቅርቡ የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ምን ፋይዳ አላቸው?
ችግሩ ህዝቡ ጋ ቢሆን ኖሮ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ መፍትሄ ያመጣ ነበር፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የስልጣን ባለቤት አልሆንኩም፣ የኢኮኖሚ ችግር አለብኝ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አለኝ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ አለኝ ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ የዲሞክራሲ ጥያቄን ላነሳ ህዝብ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዴት መልስ ሊሆን ይችላል?! ከህዝቡ ጥያቄ አንፃር ውጤት የሚኖረው አይመስለኝም፤ ነገር ግን ህዝብን በማቀራረብ ረገድ ድርሻ ሊኖረው ይችላል፡፡ የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ግን ጥያቄው ይቀጥላል፡፡ ኢህአዴግ አጀንዳ ከማስቀየስ ይልቅ የህዝቡን ጥያቄ በትክክል መገምገም ይሻለዋል፡፡  
ለ1 ዓመት ይተገበራል በተባለው “የፀጥታ እቅድ” ላይ አስተያየታችሁ ምንድን ነው?
ይሄም ለህዝብ ጥያቄ መልስ አይሆንም፡፡ እቅዱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ይሻላል በሚል የመጣ የጭንቅ መፍትሄ ነው፡፡ ይሄ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር ተጋግዘን እንዳንፈታው የሚያደርግ ነው። ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ የሚገኘው “ፀረ-ሰላም ኃይል” ከሚሉት ጋር ሳይቀር ቁጭ ብለው ለመነጋገር ፈቃደኛ ሲሆኑ ነው፡፡  

Read 1333 times