Sunday, 26 November 2017 00:00

የይቅርታ መንገድ ጠራጊ !!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

“ኢትዮጵያዊነት፤ ከፍ ብሎ ወደ ሰማይ መብረር ነው”

  አብርሃም ሊንከን በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ስሙ እንደ ሃመልማል ለምልሞ፣ ቅርንጫፉ በፍሬ የሞላው ለምንድነው? ብለን ስናስብ፣ በዘመኑ ያሳለፋቸው ጠንካራ ዱካዎች፤ በክፉና ደግ ቀን የወሰናቸው ጠንካራ ውሳኔዎች ውጤት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ስለ ሊንከን በርካታ መጻህፍት ተፅፈዋል - እንደየደራሲዎቹ አቅምና ልክ፣ አተያይና ፍልስፍና፡፡ እኔ ግን ከሁሉም ይልቅ ስቴፈን ሎረንት ስለ ፍቅር፣ ዴል ካርኔ፣ ስለሚስቱና ጥልቅ ህይወቱ … የፃፉትን በእጅጉ አደንቃለሁ፡፡
ሊንከን በአሜሪካ ታሪክ ስመ-ጥር ይሁን እንጂ አሜሪካንን አልፈጠራትም፡፡ በዋናነት ቶማስ ጀፈርሰን፣ ጆርጅ ዋሽንግተን፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ አሌክሳንደር ሀሚልተንና ሌሎች ናቸው ከእንግሊዝ እጅ መንጭቀው የወለዷት፡፡ ግና ሊንከን …በእርስበርስ ጦርነቱ በፈራረሰች ጊዜ፣ ቀንና ሌት ደክሞ፣ ግራንትና ሸርማን … የመሳሰሉትን ይዞ፣ ዳግም ሀገር አደረጋት፡፡
ትልቁ ጀግና ሮበርት ኢ.ሊ. በስሜታዊ ፍቅር ተጠልፎ፣ በክልል ጠባብነት ተለክፎ፣ “እወዳታለሁ” ያላትን አሜሪካ፤ በካደ ጊዜ፣ ሊንከን በቤትና በአደባባይ የገጠመውን ሰልፍና ውጊያ ታግሎ፣ በቀና መንፈስ ሀገሩን ከፍ ያደረገ፣ የሰንደቅዋን ክብር ያፀናና ያፀደቀ ጎበዝ ነው! ያ ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ውስጤን ኮርኩሮ፣ የቀለሜን አንጀት የናጠው፣ ከልቤ አድማስና አድማስ እየተጋፋ፣ ዕረፍት የነሳኝ የይቅርታ ልቡ ነው፡፡ ጦርነቱ አብቅቶ፣ ጄነራል ሊ. ተማርኮ፣ ሊንከን ለመጨረሻ ጊዜ በተገኘበት የካቢኔ ጉባኤ ላይ የተናገረው የሰለጠነ ሀሳብ ሁሌም ይደንቀኛል፣ ሁሌም ያረካኛል፣ ሁሌም ያስቀናኛል፡፡
ብዙ ጊዜ እኛ ሀገር የሙሴን ህግ ይመስል፤ “የገደለን ግደል!” የሚል ልብ ይበዛል፡፡ ዐይን ያጠፋ ይጥፋ! … እንደማለት፡፡ ግን የሊንከን ልብ እንደዚያ አልነበረም። አዲስ ኪዳናዊ ፀጋ የሞላው ነበር፡፡ ይቅርታ ማድረግ ይችላል፤ ይወዳልም፡፡ ይህንን ያንፀባረቀው ደግሞ ቀደም ብዬ በጠቀስኩት የመጨረሻው የካቢኔ ጉባኤ ላይ ነበር፡፡ “ሀገሪቱን አምሰዋል፣ ለመገንጠል አሲረዋል፣ ጦር ሰብቀዋል፣ ለብዙዎች ህይወት መጥፋት መንስዔ ሆነዋል …የተባሉ “አሸባሪዎች” ቅጣት ምንድነው?” ተብሎ ሲጠየቅ፡-  “እስከ ዛሬ ድረስ የፈሰሰው ደም በቂ ነው፣ ከእንግዲህ በኋላ ሊንከን የማንም ደም እንዲፈስ አይፈቅድም” ነበር ያለው፡፡ ታዲያ ይህ የይቅርታ ቃል በአሜሪካ የፈጠረው ስሜት ቀላል አልነበረም፡፡ በቁስል ላይ ቁስል፣ በቂም ላይ ቂም ከመፍጠር ይልቅ፣ በይቅርታ ዘይት ቁስልን ማድረቅ መርጧል፡፡  
አማፂውን ጀነራል ሮበርት ኢ ሊን፣ ከእስር ቤት ይልቅ ወደ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዚዳንትነት ያመጣው የሊንከን ቀና ልብ ነው፡፡ ጆን ኤፍ ዌስትዌል ጥላቻና ይቅርታን በተመለከተ በከተቡት መጽሐፍ እንዲህ ይላሉ፤ “Darkness can not drive out darkness; only light can do that; hate can not drive out hate; only love can do that; hate multiply hate, violence multiply violence.”
አልተሳሳቱም፡፡ ብርሃን እንጂ ጨለማ፣ ጨለማን አያስወግድም፤ ፍቅር እንጂ ጥላቻ፣ ጥላቻን አያሸንፈውም፡፡ ይልቅስ ያከርረዋል እንጂ፡፡ ጥላቻ ከቃል ይጀምራል፡፡ ከንግግር! አንደበት እሳት ነው እንዲል መጽሐፉ፡፡ ሁሌ ንግግር በሰው ልብ ውስጥ ሀሳብ ይጠነሰሳል፤ ያ ሀሳብም በገቢር ይገለጣል፡፡
ሀሳብ በፅሁፍ ወይም በአንደበት ይንፀባረቃል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአገራችን የሆነውም ይሄ ነው፡፡ ልጓም ያልተበጀለት የጎሳ ፖለቲካ ክፉ መርዝ በቃልና ዲስኩር ተጀምሮ ዛሬ የት እንዳደረሰን እናውቀዋለን፡፡ መጪውን በተስፋ እንድንጠብቅ ሳይሆን በትካዜና በቁርሾ እንድንቆዝም፣ አንዳችን በሌላችን ላይ ሾተል እንድንመዝ አድርጎናል፡፡
ስለ ቃልና ሀሳብ ሳስብ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት አምባገነን መሪ ጆሴፍ ስታሊን ትዝ ይለኛል፡፡ ስታሊን የደሀ ገበሬ ልጅ ነበር፡፡ እናቱ ለእግዚአብሔር ዕድል ፈንታ አድርጋ የሰጠችው፣ እንደ ሃና ልጅ ነቢዩ ሳሙኤል፣ ዘመኑን ለፈጣሪው እንዲያስረክብ የተሳለችለት ነበር፡፡ እናቱ ፀሎቴ ተሰማ ብላ በሩሲያ ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ ሆኖ፣ ቅዱስ ቃሉን እንዲያጠና ያስረከበችው ቢሆንም፣ የካርል ማርክስ ርዕዮተ ዓለም መንፈሳዊ ህልሙን ነጥቆታል፡፡ ማርክስ፣ ለርሱ በተግባር ያሳየው ነገር የለም፤ ግን በቃሉ አሳመነው፡፡ ቀጣዩን ዓለም ሳለለት፡፡
በኢትዮጵያም በዘር የተዘነጣጠለና በጥላቻ የተገነጣጠለ ፖለቲካ መነሻው ይሁነኝ ተብሎ የተዘራው ሃሳብ ነው፡፡ ካድሬዎች ሁሉ የተሞሉትን ክፉ ሃሳብ፣ “ትምክህተኛ …ነፍጠኛ…” ጠባብ ወዘተ--- እያሉ የህዝቡን ልብ መረዙት፡፡ የጥላቻ መርዙም ተዛመተ፡፡ እናም ዛሬ ያለንበትን ነውጥ ፈጠረ፡፡ የማያዋጣው የዘር  ፖለቲካ ያሰጋቸው ወገኖች ብዙ ቢጮሁም፤ከመንግስት ያገኙት ምላሽ ግን “… ፀረ ሰላም! ፀረ ዲሞክራሲ! … ትምክህተኛ! … ወዘተ” ብቻ ሆነ፡፡
የስነ አመራር ምሁሩ ጆን ሲ ማክሲዌል እንደሚሉት፤ መንግስት ለጥያቄ የሚሰጠው መልስ አንድ አስቸጋሪ ባል ቴሌቪዥን እያየ፣ ለሚስቱ እንደሚሰጠው አይነት ነበር፡፡
ሚስት፡- “ውዴ፤ ዛሬ ቧንቧ ሰሪው ከውሃ ማሞቂያው ጀርባ የሚፈስሰውን ውሃ ለማቆም አልመጣም፡፡”
ባል፡- “ተይው”
ሚስት፡- “ዛሬ የውሃው ቧንቧ ፈንድቶ፣ ምድር ቤቱን አጥለቅልቆታል፡፡”
ባል፡- “ይህ ሶስተኛው ዙር ነው፣ የቀረው ጎል ማግባት ነው፡፡
ህዝቡ ሌላ ነገር ሲጠይቅ፣ መንግስት ሌላ እየመለሰ ባለመግባባት ብዙ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሁሉም ለአገሩ አሳቢ፣ ይበጃል የሚለውን ተናገረ፡፡ ግን ሰሚ አልተገኘም፡፡ መንግስት እንደ ክፉው ባል፤ የራሱን ህልም በቴሌቪዥን እያየ፣ “ዕድገት ነው፣ ሰላም ነው፣ ጥጋብ ነው” ማለቱን ትቶ እውነታውን ካልተጋፈጠ መፍትሄ አይገኝም፡፡ “የማይመስል ነገር፣ ለሚስትህ አትንገር” እንዲሉ!
ባለፉት ወራት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተደረጉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ የብዙዎች ኑሮ ፈርሷል፡፡ ከመንግስት ግን ተስፋ የሚሰጥ እርምጃ አልታየም- ህዝብ አንጀት ጠብ የሚል! “በተለይ ለወደፊት ምን መፍትሄ ማበጀት ይሻላል?!›› የሚል ለትውልድ ተስፋ የሚሆን  ሃሳብ አልቀረበም፡፡ መንግስት ልክ እንደ ማንኛውም ተራ ተርታ ሰው፣ ‹‹የመጣው ይምጣ!..›› አይነት የምንግዴ ምላሽ ሲሰጥ ያሳፍራል፡፡ ሃገር የሚመሩ ሰዎች የዛሬን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ስለ ነገ አርቀው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ለዚህ የሰሞኑ የዚምባብዌ ወታደራዊ መኮንኖች ተግባር አይነተኛ አስተማሪ ነው፡፡ አገራቸውን ለባዕድ አሳልፈው ሳይሰጡ፣ነገሩን ሁሉ በጥበብና በመግባባት በይቅርታ ጨረሱት፡፡ ደም አልፈሰሰም፤ ጠላቶቻቸው እጃቸውን አላስገቡም፤ ሙጋቤም የጠላት መሳቂያ አልሆኑም፡፡ ተደራደሩ፤ ይቅርታ ተደረገላቸው፡፡   
እኛ አገር በመጠኑምቢሆን  የይቅርታና የፍቅር ተስፋ  የሰማነው ከአቶ ለማ መገርሳ ነው፡፡ ያለፈውን እየረሳን የፊቱን ለመያዝ እንዘርጋ፣ እንዲል መጽሃፉ፡፡ ቂምና በቀል ቀርቶ ሁላችንም ተያይዘን ለጋራ ብልጽግና እንስራ ብለዋል፡፡ ይህ ቃል ነው፤ ሃሳብ ነው፡፡ መሬት ወርዶ ፍሬ የሚያፈራውም ይህ ነው፡፡ በእሳቸው የአንድነትና የፍቅር ቃል የተኛው ሁሉ ከእንቅልፉ ይንቃ፡፡ የተከዘው ይፍካ! በጥላቻ የሰከረው በምህረት ልቡ ይባባ፡፡ “ለማ መገርሳ” የምድረ በዳው ድምፅ፣ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የይቅርታና ምህረት መንገድ ጠራጊ ይመስላሉ፡፡ ያዝልቅላቸው!!
ሰውየው አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ … በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን አንድ ናቸው እያሉ ነው፡፡ አያቶቻችን የራሳቸውን ታሪክ ሰርተው አልፈዋል፤ ባለፈ ታሪክ መናቆር አይጠቅመንም፤ ይልቅስ የራሳችን ታሪክ ሰርተን የህዝባችንን ኑሮ እንለውጥ---በማለት ሃቁን ደጋግመው እየነገሩን ነው፡፡ ይሄንንም ዕውን ለማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማደስ አማራጭ የሌለው የመፍትሄ አካል ነው፡፡ ኦሮሞና አማራው የጀመሩት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከዳር እስከ ዳር ማጥለቅለቅ አለበት፡፡ ምንም ፖለቲካዊ ሰበብ ሳያስፈልገው፣በግልጽና በጀርባ ያሉ ቅሬታዎች ሁሉ በራሱ በህዝቡ መፈታት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ይቅርታ በመጠየቅና በመቀበል አርአያ መሆን መቻል አለበት፡፡ ይህንን ደግሞ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታትና በመደራደር በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡
የኢትዮጵያዊያን ችግራችን፣ እልኸኝነታችን ይመስለኛል፡፡ ህዝብ እልኸኛ፣ መንግስትም የባሰበት እልኸኛ ነው፡፡ ገጣሚ በለው ገበየሁ እንዲህ እንደሚል፡…
 ሃሰት ተኮላሽቶ፤..ሃቅ እንዲፈረጥም
  የመለወጥ ማጡ …ድጡ እንዳያሰጥም
ሁላችን ተቃጥለን…በወሬ ውሃ ጥም፣
በ‹ኛ›ነት አንቀልባ፣
ታዝለን ዙሪያ ጥምጥም…
እንናገራለን አንደማመጥም!
ችግራችን ይህ ነው፤ በውይይት አናምንም፤ ጠመንጃ የያዝን ተረኞች ሁሉ በጠመንጃ አገር የምንገዛ ይመስለናል፡፡ ያ ጠመንጃ ደግሞ ሌላ ጠመንጃ ይወልዳል፤ የበቀል ደም አይደርቅም፡፡ ትውልድ በእንባ ኖሮ በእንባ ያልፋል፡፡ ይህ ስልጣኔ አይደለም፤ ኋላቀርነት ነው፡፡ ክብር አይደለም፣ ውርደት ነው፡፡ እኛ ግን ዛሬም የምንኮራው በዚህ ነው፡፡ ነጻ እናወጣችኋለን!›› ያሉ ሁሉ ክደውናል፡፡ ተስፋ ያደረግናቸው ፊታቸውን አዙረዋል፡፡  
ይሁን እንጂ ከዚህ አዙሪት ልንወጣ የምንችልበት መንገድ አለ፡፡ ይህ ለዘመናት በክፉና በደግ ተባብሮና ተከባብሮ፣ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ ህዝብ መለያየትና መቀያየም የለበትም፡፡ ቴዎድሮስ የሞተው ለኢትዮጵያ ነው፡፡
ዮሃንስም እንደዚሁ፡፡ ምኒሊክና ገበየሁ፣ አብዲሳና ባልቻ የተጋደሉት ለዚችው አገር ነው፡፡ ለአገር ነጻነትና አንድነት፡፡ ህዝቡ አንድ ነው፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚኖረው አንድ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም ወደ አንድነታችን ለመመለስ እርቅና ይቅርታ ያስፈልጋል። ፖለቲከኞች ዘላለም አይኖሩም፤ ፖለቲካም እንደየዘመኑ ይቀያየራል፤ ህዝብ ግን ዘላለማዊ  ነው፡፡
ስለዚህ አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ስለ አንድነት የሚያመጣውን በጎ ሃሳብ ተቀብሎ፣ ለከፋፋዮች ድምጽ ጆሮ መንሳት ጊዜው የሚጠይቀው ስልት ሊሆን ይገባል፡፡ ረባሽ ቁራዎችን መሸሽ ግድ ይላል፡፡ ንስር አሞራ በቁራዎች በሚጠቃበት ጊዜ፤ ጩኸታቸው ጆሮውን ሲጠዘጥዘው፣ ድል የሚነሳው የበረራ ከፍታውን አልቆ ወደ ላይ በመብረር ነው! ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅመን ወደ ላይ መብረር ነው፡፡ በፍቅርና በይቅርታ ልቀን መብረር! አክራሪ ጎሰኝነት፣ ጭፍን ዘረኝነት፣ የመንደር ጠባብነት … ወዘተ ሁሉ እንጦሮጦስ መውረድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ደሞ ከፍ ብሎ ወደ ሰማይ መብረር ነው--- መክነፍ!

Read 1342 times