Sunday, 26 November 2017 00:00

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ተስፋና ስጋት??

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

እዚህ ኢትዮጵያ “ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” የተባለ በኢንተርቴይመንት ቢዝነስ ላይ የተሰማራ ድርጅት፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ሰላምና አንድነት የማጠናከር ራዕይ ሰንቆ፣ “የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦ” በሚል መርህ፣ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ከ800 በላይ የሁለቱም አገራት ምሁራን፣ስደተኛ ኤርትራውያንና የስነ-ህዝብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ በተጨማሪም የኤርትራና የኢትዮጵያ ዕውቅ ድምፃዊያን የሚሳተፉበት የሙዚቃ ኮንሰርትም እንደሚዘጋጅ ታውቋል፡፡
ባለፈው ህዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም በሀርመኒ ሆቴል በተካሄደው የግማሽ ቀን የትውውቅና የግንዛቤ ማስጨበጪያ መድረክ ላይ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ተመራማሪ፣ ፕሮፌሰር መድሀኔ ታደሰንና ዓለም ዓቀፉን የህግ ባለሙያ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምን ጨምሮ የሚዲያ ባለቤቶች፣ የታሪክ ምሁራንና ጋዜጠኞች እንዲሁም ስደተኛ ኤርትራውያን  ጋዜጠኛና መምህራን የነበሩ ኤርትራዊያን፣ የኢትዮጵያ የሚዲያ ባለቤቶችና የታሪክ ምሁራን የተሳተፉበት የግማሽ ቀን ውይይት በሀርመኒ ሆቴል ተካሂዶ ነበር፡፡ በሁለቱ አገራት ተስፋና ስጋት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናታዊ ፅሁፍ በፕሮፌሰር መድሀኔ ታደሰ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የሁለቱን አገራት ህዝቦች ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ታልሞ በተካሄደው የመጀመሪያ የውይይት መድረክ ላይ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ስደተኛ ኤርትራውያን መካከል አንዳንዶቹን አነጋግራ ሃሳባቸውን እንዲህ አጠናቅረዋለች፡፡

ባለፈው ረቡዕ ውይይቱ ያተኮረው በሁለቱ አገራት ህዝቦች ላይ ሰላም በማስፈን ዙሪያ ነው፡፡ ከሰላም በዘለለ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ወደ በለጠ ትብብር እንዴት ያምሩ በሚለውም ላይ ተነጋግረናል፡፡ ስብሰባውን በጣም ነው የወደድኩት፡፡ በተለይ በኤርትራውያን ወንድሞቻችን በኩል የተንጸባረቀው  ሀሳብ፤ የሁለቱን አገራት ህዝቦች ተስፋ የሚያሳይ ነው፡፡ ታዋቂ ምሁራን፣ በርካታ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ በጠቅላላው ሲንሸራሸር የነበረው ሀሳብ ለሁለቱ አገራት ጥቅም ያለመ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የአቅማችንን እንደምንሰራ እተማመናለሁ። እኔ እንደሚመስለኝ፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች ራዕይ ማጣት፣ የመለስና የኢሳያስ ከአፍንጫ አርቆ አለማሰብ እንጂ ኢትዮጵያና ኤርትራ መለያየት አልነበረባቸውም። ዛሬ ሁለቱ አገራት አንድ ላይ ቢሆኑ ኖሮ፣ ሁለት ዓለም አቀፍ ወደቦች፣ ከመቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የኤርትራውያን ትጋት ተዳምሮ፣ ለቀጠናው ልዕለ ኃያል ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች ነበሩ፡፡ መሪዎቹ ግን ይህንን ራዕይ ማየት ባለመቻላቸው በአጭር ቀጩት፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ተለያይቶ የሚለያይ ህዝብ አይደለም፡፡ በሁሉም ነገር ተመሳሳይነት ያለው፣ በጣም ተቀራርቦ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ በአንዳንዶቻችን ልጆች ውስጥ አሁንም የኤርትራዊያን ደም አለ፡፡ በኤርትራዊያንም ውስጥ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ደም አለ። ሁለቱም ህዝቦች ተለያይተው የሚኖሩበት ሁኔታ ላይ አይደለም ያሉት፡፡ እኔ በግሌ ምስራቅ አፍሪካም ምዕራብ አፍሪካም በሥራ ኖሬ አይቸዋለሁ፡፡ ሆኖም የኤርትራንና የኢትዮጵያን ህዝብ ዓይነት ተመሳሳይነት ያለው ህዝብ የትም አላየሁም፡፡ ስለዚህ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ለጦርነት መፈላለግ፣ የራስን እህትና ወንድም ለመግደል እንደመፈለግ ነው፡፡ የዚህን ህዝብ አንድነትና ሰላም ለመመለስ እንቅስቃሴ መጀመር የተቀደሰ ሀሳብ ነው፡፡ እናም የሁለቱም አገራት ህዝቦች በደንብ ሊሳተፉበትና ሊደግፉት የሚገባ ጅምር ነው፡፡
በመንግስታቱ በኩል ስናየው፤ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ በኩል ወደ ሰላም የሚያመጣም ሆነ ወደ ትብብር የሚጋብዝ ምንም ዓይነት ተስፋ የለም፤ጨለማ ነው፡፡ እኔ ተስፋ የማደርገው በወጣቱ ነው፡፡ አሁን ወጣቱ እኮ በየቦታው ውይይት ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ “ኤርትራን ሶሊዳሪቲ ግሩፕ” የሚባል አንድ ቡድን አለ፡፡ ኢትዮጵያዊያኑና ኤርትራዊያኑ አሜሪካ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌሎች ተቋማት ውስጥ ሲገናኙ፣ እንደ አንድ አገር ህዝቦችና ወንድማማቾች ይቀራረባሉ፡፡ ታዲያ የእነዚህ ወጣቶች ቅርርብ፣ ለሁለቱ አገራት ሰላምና ትብብር፣ የሚጭርብኝ ተስፋ አለ፡፡ በሁለቱ መንግስታት በኩል ግን የምሰንቀው ተስፋ የለም፡፡ ሆኖም አገር የ10 እና የ20 ዓመት ጉዳይ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው፤ ስለዚህ ዘላለማዊ ወዳጅነትም ዘላለማዊ ጠላትነትም አይኖርም፡፡ ሁለቱ አገራት ዘላለማዊ ቢሆኑም አሁን የሚመሯቸው መንግስታት ግን  ያልፋሉ፡፡ ያን ጊዜ የሁለቱም አገራት ህዝቦች ሁኔታ የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። በሁለቱም አገራት ፍትህና ዴሞክራሲ ያብባል ብዬ አምናለሁ። ዲሞክራሲና ፍትህ  የሰፈነባቸው አገራት ደግሞ በጦርነት አይፈላለጉም፡፡ ተስፋ የማደርገውም በመጪው ትውልድ ይመሰረታል ብዬ በማስበው ዲሞክራሲያዊ ሥርአት ነው፡፡ በውይይቱም መሳተፍ የፈለግሁት ይህን ተስፋ ሰንቄ ነው፡፡
የሁለቱም አገር ህዝብ እውነተኛ ታሪኩን ቢያውቀውም በኤርትራ በኩል ወጣቱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን እንደ ጠላት እንዲያይ ተኮትኩቶ ነው ያደገው፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ባለበት አይቀጥልም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጎ ፈቃድና ወንድምነት ካሳዩ ነገሮች ይለወጣሉ፡፡ ታሪኮችን ሲያነቡና የሰላምና የአንድነትን ጥቅም ሲረዱ፣ ሁኔታዎች ቀስ በቀስ ይለወጣሉ፡፡  በፖለቲካ ውስጥ ጥላቻ ብዙ አይዘልቅም፡፡ ሁሉም በጥሞና ሲያስብና ሲያሰላስል ከጉዳቱ ጥቅሙን አስበልጦ ይቀጥላል፡፡
አሁንም ቢሆን ብዙ ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፤ እንደ አገራቸው ተደስተው እየኖሩ ነው። ባለፈው የሀርመኒ ሆቴል ስብሰባ ጥሩ መተሳሰብና መፈቃቀር እንዳለ አመላካች ነገር አይተናል፡፡ በኤርትራዊያንም ሆነ በኢትዮጵያዊያን በኩል የተንሸራሸሩት ሀሳቦች ያሳዩን ያንኑ ነው፡፡ በኤርትራ መንግስት የተሰራው የጥላቻ ስራ የትም የሚደርስ አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያኖችም በኩል እንዲህ አይነት ፍራቻ የለም። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት፣ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ኤርትራዊያንን በሚያባርርበት ወቅት ኢትዮጵያዊያን እያለቀሱና ስንቅ እያስያዙ ነው የሸኟቸው፡፡ እንደውም የቻሉት እንዳይሄዱ ሁሉ ደብቀዋቸዋል፤ ይሄ ሀቅና የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እናም የተዘራው ጥላቻ ላይ ሁሉም ከተረባረበበት በአጭር ጊዜ ሊሽር ይችላል፡፡
ሁለቱ መንግስታት እስካሉ ድረስ እንቅፋት መፈጠሩ አይቀርም፤ በተለይ በኤርትራ መንግስት በኩል እንቅፋት እንደሚጋረጥ ግልፅ ነው፡፡ ግን መታገል ያስፈልጋል፤ የተጀመረው እንቅስቃሴና ግብ በጎ ሀሳብ ያለውና ለሁለቱ አገራት የሚጠቅም ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ ከሰላም መፍጠር ባሻገር እስከ ወደብ መቀራረብ ሊደርስም የሚችል ነው፡፡ በመሀላቸው ሰላም በማስፈን ብቻ ሳይወሰን ከዚያም ያለፈ ነገር ይፈጥራሉ ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡ ማለም ክልከል አይደለም፡፡ እንደውም ወደ ፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽንም ሊያድግ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ የብዙ ኢትዮጵያዊንም ስሜት ይሄው ነው፡፡ በዚህ ሂደት እንቅፋት ይገጥማል ወይ? አዎ በደንብ ይገጥማል፤ይሄንን በትግል ማለፍ ያስፈልጋል። ምንግዜም ደግሞ ህዝብ ያሸንፋል፡፡ ህዝብ እስካለ ድረስ መንግስታት ይሸነፋሉ፤ እጅ ይሰጣሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

================

“ኤርትራውያን ይጠሉናል የሚባለው በጥናት አልተረጋገጠም”

ሁለት አገር ላይ የሰፈርን አንድ ህዝብ ነን
ፕሮፌሰር መድሀኔ ታደሠ
አሁን በተጀመረው “የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች” በተሰኘው እንቅስቃሴ ውስጥ የእርቅ ሂደቱ የምሁራን ፓነል ሊቀመንበር ሆነው እየሰሩ ነው። ሁለቱን ህዝቦች ማስታረቅ ሲባል ምን ማለት ነው? ምክንያቱም የሁለቱ አገራት መንግስታት እንጂ ህዝቡ አልተጣላም የሚሉ ወገኖች አሉ…
ሁለት የፖለቲካ ሥርዓቶችና ሁለት አገራት አሉ። እነዚህ ሥርዓቶችና አገራት ሰላም ላይ አይደሉም። በአደጋ የሚፈላለጉ ናቸው፡፡ አደጋና ግጭት ላይ ናቸው፡፡  ይሄ ግጭት ሁለቱን ህዝቦች ከማቀራረብ ይልቅ እያራራቀ፣ አቅማቸውንና እድላቸውን በትክክል እንዳይጠቀሙበት እያደረገ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ሥርዓቶችና አገራት የራሳቸውን ጽንፍ ይዘው፣ የራሳቸውን ህዝብ አሰልፈው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት፣ ሥርዓቶቹና መንግስታቱ ብቻ ናቸው የተጣሉት ማለት አይቻልም፡፡
ሁለቱም ሥርዓቶች የሚያሰልፏቸውና የሚቆጣጠሯቸው ዜጎች አሉ፡፡ ድጋፋቸው ይነስም ይብዛ ዋናው ነገር በሁለቱም አገራት መካከል የሚፈለገውን ያህል ግንኙነት የለም፡፡ ሁለቱ አገራት እንደ ጎረቤት ብቻ ሳይሆን አንድ ታሪክ እንዳላቸው፣ አንድ የወደፊት እጣ ፈንታቸው የተወሰነ እንደሆኑ ህዝቦች አይደለም እየተገናኙ ያሉት፤ ስለዚህ ግጭቱና የሰላም እጦቱ ሁለቱንም ህዝቦች ነው እየጎዳ ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር አሰላለፉን መቀየር ያስፈልጋል፡፡ አሰላለፉን ለመቀየር ህዝቦች ራሳቸው አቅም አግኝተው፣ “ይሄ አካሄድ አይጠቅመንም፤ ለእኛና ለመጪው ትውልድ የሚያስፈልገን ሰላም ነው” ብለው የየራሳቸውን እንቅስቃሴ ካላደረጉ በስተቀር በዚህ መልኩ መቀጠሉ ሁለቱንም ህዝብ እየጎዳ ነው፡፡
መንግስታቱ በማይታረቅ ግጭት ውስጥ እያሉ ህዝቡ አቅም አግኝቶ በራሱ የሚንቀሳቀሰው እንዴት ነው? ለህዝቡስ አቅም የሚሰጠው ማን ነው? ህዝቡ በራሱ መንቀሳቀሱ ብቻ የሚያመጣው ለውጥ አለ?
ለውጥ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ይህ እንቅስቃሴ የሚካሄደው ከመንግስታት ጋር ሳይሆን ከትውልዶች ጋር የሚደረግ ነው፡፡ መንግስታቱ የሚያሰልፉት ሀይል አንዳንዱ በእውቀት ሌላው ባለማወቅ ነው። አንዳንዱ በስሜት፣ አንዳንዱ ደግሞ በአቅም ማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ከስሜት ውጭ ሆኖ ይሄ ነገር ጠቃሚ ሳይሆን ጎጂና አውዳሚ እንደሆነ እየተገነዘበ በሄደ ቁጥር የራሱን አደረጃጀትና አቋም እየያዘ ስለሚመጣ፣ መንግስታት መጨረሻ ላይ መቀበላችው አይቀርም።  የዚህ እንቅስቃሴ ጉዳይ የሁለቱ መንግስታት በስልጣን ላይ መቆየት አለመቆየት አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግስታቱ የመሰላቸት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ነው የምንገነዘበው፡፡ ቢሰለቹም ባይሰለቹም እነሱን ለመቀየር የሚያስችለው ተፅዕኖ መምጣት ያለበት ከተፅዕኖ ፈጣሪዎችና ከህዝቡ ነው፡፡ ቅድም የህዝቡ አቅም ምንድነው? አቅሙን የሚሰጠው ማን ነው? ብለሻል። ጥሩ! ህዝቡ የሚያስፈልገው አቅም እውቀት ነው፡፡ እውቀቱን ደግሞ የሁለቱም አገራት ምሁራን ለህዝቡ መመገብ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥናት የሰሩ፣ የሁለቱን አገራት ጉዳዮች በጥልቀት የሚከታተሉ… የሁለቱም አገራት ምሁራን፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች… አንድ ላይ ተሰብስበው፣ “ይሄ ነገር ይዞን እየጠፋ ነው፤ እኛን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ትውልድ እጣ ፋንታ የሚያጨልም ነው፤ ሥለዚህ ከዚህ ወጥተን ጥቅማችን ላይ ማተኮር አለብን፤ ጥቅማችን የሚመሰረተው በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ እውቀት ስንጨብጥ ነው፡፡ ይህ እውቀት ሲኖረን አንድም መንግስታቱን ትተን፤ እርስ በእርሳችን መገናኘት እንጀምራለን ወይም መንግስታቱን መለወጥ እንችላለን” ነው ዋናው ነገር፡፡ ይህ ደግሞ የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ ከመንግስታትና ከትውልዶች ባሻገር የሚሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም አገርና ህዝብ ቀጣይ ነውና፡፡
እነዚህን ሥራዎች ለመስራት በሁለቱም አገራትና ህዝቦች ምሁራን በኩል የሚፈለገውን ያህል ተነሳሽነት አለ?
መጀመሪያውኑም በግጭቱ ላይ የህዝቡ እጅ አልነበረም፤ ጠብና ግጭቱ የመጣው ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ ነው፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ሁለት አገር ሆነው ሲቆሙ፣ በተለይ ኤርትራ አዲስ አገር ሆኖ ስትፈጠር፣ ለግጭት ሊዳርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለይቶ ካለማውጣትና ካለመፍታት የመነጨ የመንግስታት ችግር ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ ህዝቦች በዚህ መሀል ወደውም ይሁን ተገድደው ወደ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ህዝቦቹ ለስላም ያላቸው ፍላጎት፣ ለግጭት ካላቸው ፍላጎት ያየለ ነው፡፡ ህዝቡ ከመንግስታት ውጭ በተለያየ መድረክ ሲገናኝና ሲወያይ ይታያል፡፡ ግንኙነቱና ውይይቱ ግን በእውቀት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ አሁን ምሁራን ይህን ድጋፍ ለህዝቡ መስጠት አለባቸው፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ምንድን ነው፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምስ ምንድን ነው? የሁለቱ ጥቅም ለአካባቢው የሚሰጠው ፋይዳ ምንድን ነው? በዓለም አቀፍ ደረጃስ የነዚህ አገሮች ተፅዕኖ ምን ያህል ነው? ጠንካራና ደካማ ጎናቸውስ ምንድን ነው? ይሄን ማስተማር ከቻልን፣ የተማረው ክፍል የራሱን አቋም እየያዝ ህዝቡን ሊያደራጅ ይችላል፡፡ መንግስታት ደግሞ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የህዝባቸውን ተፅዕኖ መቀበላቸው አይቀርም፡፡ ዓለምም እየመራን ያለው ወደዚሁ መንገድ ነው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ደግሞ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት መንግስታትን መጠበቅ የለባቸውም… የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፡፡
እንግዲህ በቀጠናው ሰላም ግጭቶች ላይ እንደመስራትዎ… እንዲሁም ኢትዮ ኤርትራ ላይ በደንብ እንደማጥናትዎ፣ አማካዩ ህዝብ ከሚያወራው የተለየ መልስ እንዲሰጡኝ የምፈልገው፣ “የኤርትራ ህዝብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር የለውም” የሚባለውን በተመለከተ ነው…?
ይሄ እንግዲህ የአንድ በኩል ጉዳይ ሳይሆን በሁለቱም በኩል ያለ ይመስለኛል፡፡ የሚነገር ተረት አለ፡፡ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡ የፖለቲካ ትዝታም አለ፡፡ በየአገሩ ያለውን የፖለቲካ ትዝታ የሚቀርፀው ማን ነው? ይሄ ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ እነዚህ መንግስታት፤ ሌሎች ተቋሞችና መድረኮች በሌሉበት ሁኔታ የራሳቸውን ተረት፣ የራሳቸውን የፖለቲካ ትዝታና የራሳቸውን የፖለቲካ ታሪክ ሲያሰርፁ ነው የኖሩት፡፡ ጉዳዩን በዝምታ መመልከት ለዚህ አብቅቶናል፡፡ አሁን ያለው የኤርትራ ወጣት፣ መንግስቱ ጥላቻን ሲያሰርፅበት፣ የራሱን ትዝታና የፖለቲካ ታሪክ ሲነግረው፣ “አይ ይሄኛው ትክክለኛ ታሪክ አይደለም” ብሎ አማራጭ ያስቀመጠለት አካል ወይም መድረክ አልነበረም፡፡ ይሄ ደግሞ እንኳን በሁለት አገራት ቀርቶ በአንድ አገር ህዝቦች መካከል የህዝቦችን አንድነት፣ ሰላምና መከባበርን ለመፍጠር ትክክለኛ ታሪካቸውን መንገር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ራሱ በመድረክ የሚነገረው፣ ህዝቡ የሚያውቀውና በጥናት የሚረጋገጠው ፍፁም የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ ኤርትራ ውስጥ ከነፃነት ጀምሮ እየተነገረ ያለውን ተረትና የፖለቲካ ትዝታ፣ በእውቀት የሚገዳደር አማራጭ ባልቀረበበት ሁኔታ ጥላቻ ቢያሳድሩ አይገርምም። ኢትዮጵያም ውስጥ ተመሳሳይ ነው፡፡ “ኤርትራዊያን በጅምላ ይጠሉናል” የሚባለው በጥናት አልተረጋገጠም። አንዳንድ ጊዜ “ደጋው አካባቢ ያለው ኤርትራዊ ነው ከኢትዮጵያ ጋር መገናኘት የሚፈልገው፤ ሙስሊሙ አይፈልግም” ይባላል፤ ይሄም በጥናት አልተረጋገጠም፡፡
ምፅዋ ላይ ያለው ሙስሊም ሁሉ ከኃይለስላሴ ቤተሰቦችና ከኢትዮጵያ ጋር ቁርኝነት እንደነበረው ምሁራን ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ስለዚህ “ይሄ ይጠላናል፣ ይሄ ይወደናል” የሚለው በጥናት መረጋገጥ አለበት፡፡ ሁለተኛ ለምንድን ነው የሚጠላን? ለምንስ ነው የሚወደን? የሚለው በትክክል ታይቶ፣ የችግሩ ምንጭ ተለይቶና ተጠንቶ፣ አማራጭ ሀሳቦች መቅረብ አለባቸው፡፡ እስካሁን ይሄ አልተደረገም፤ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው ስንጓዝ የነበረው፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱም በኩል የእውቀትና የግንዛቤ ችግር አለ፤ በዚህ ላይ አልተሰራም፡፡ ከዚያ ይልቅ አንድ አቅጣጫ ነበር የሁሉም ነገር ፍሰት የነበረው፡፡ ስለዚህ የሁለቱ አገራት ታሪክ በደንብ ተጠንቶ፣ ህዝቡ እንዲወያይና እንዲነጋገር፣ ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ቢተጉ፣ አሁን የሚባለው ሁሉ አይኖርም፡፡ የዚህም እንቅስቃሴ ዋና አላማ፣ እነዚህን በጥናትና በታሪክ ላይ የተመሰረቱ እውቀቶችና ግንዛቤዎች ለመፍጠር ነው፡፡
በሌላው አለም አገርና ህዝብ ግንባታ ላይ ሲሰራ፣ በትክክል ታሪኩ ይጠናና ለአገር ግንባታ የሚሆነው መልካም መልካም ነገሩ ተመርጦ፣ ለትውልዱ ይቀርባል። በመጥፎ በመጥፎ ታሪኩ ተምሮበት እየተረሳ ይሄዳል፡፡ እኛ አገር ይሄ የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ልዩነት ላይ እናተኩራለን፤ የሚያጋጨን ላይ እንበረታለን፤ መጥፎ መጥፎ ነገሮችን እናጎላለን፡፡ ዋናው ችግር ይሄ ነው፡፡
ታዲያ ለዚህ ተጠያቂው ማነው?
አመራሩና ልሂቃኑ ናቸው፡፡ አመራሩም ለራሱ በሚመቸው መልኩ አጀንዳውን ያራምዳል፡፡ ትውልዱ ትክክለኛ ታሪክ እንዲያውቅ አይደረግም፡፡ ልሂቃንም ይሄ ሲደረግ ለማረቅና ትክክለኛውን ነገር ለመንገርናም ሆነ ለማስተማር አይታትሩም፡፡ ስለዚህ ተጠያቂዎቹ እነዚህ አካላት ናቸው፡፡ ሁለት አገራት ቀርቶ በአንድ አገር ውስጥ ትክክለኛ ታሪክ ቢነገር፣ ሁሉም ያግባባናል ልዩነት የለንም ማለት አይደለም፤ አንድ በሚያደርጉን ላይ አብረን እንሰራለን በልዩነቶቻችን ላይ ላለመስማማት እንስማማለን እንከባበራለን፡፡ ይሄኛው ለራስ የሚመች ያልተፈጠረ ታሪክን ለትውልድ እየነገሩ፣ የተጣመመ ታሪክ ከመስራት በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ የመለያያ ነጥቦቹም ለምን እንደሚለያዩን በግልፅና በጥናት፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለትውልድ ስንነግር፣ ከጭፍንነት ወጥቶ ወደ ማመዛዘንና በልዩነቶች ላይ ወደ መከባበር ይመጣል፡፡ አንድ የሚያደርጉን ላይ በደንብ እንሰራለን፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገራት አንድ ባለመሆን፣ እርስ በእርስ በመናከስ፣ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ እንዲገቡ እድል በመስጠት መጫወቻ ሆነዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ደግሞ ከዚህ በላይ በልዩነትና እርስ በእርስ በመናከስ መራመድ አይችሉም፤ ተፈጥሮም ሁኔታዎችም አይፈቅዱላቸውም፡፡ ስለዚህ ሁለት አገራት በሚያስማማቸው ላይ አብረው እየሰሩ በልዩነታቸው ላይ ተስማምተው፣ ከዚያም ልዩነታቸውን እያጠበቡ፣ አገራቸውን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ አለባቸው፡፡
ሁለቱን መንግስታት ለማስታረቅ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፈው አልተሳካም፡፡ እርስዎ በጥናት ደርሰውበት ከሆነ፣ የሁለቱ አገራት መንግስታት ወደ እርቅ እንዳይመጡ ያደረጋቸው ዋነኛ ችግር ምንድን ነው ይላሉ?
አንደኛ ጉዳዩ “አሊቲስት” ነው፤ ከላይ ዝም ብሎ የተጫነው እንጂ ህዝቡን ያሳተፈ አይደለም፡፡ ሁለተኛ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አሰራርም አልነበረም። የተባበሩት መንግስታት፣ የአካባቢው መንግስታት ብዙ ጊዜ የሚያውቁት፣ የመንግስታትን አማራጭ እንጂ የህዝቡን አማራጭ አያውቁም፤ ያን ያህል አይገባቸውም ማለቴ ነው፡፡ እነሱ በአብዛኛው የሚሄዱበት የግጭት አፈታት መንገድ ችግር አለበት፡፡ ሶማሊያም ሂጂ ሱዳንም ችግር አለበት፤ ምክንያቱም ከላይ የተጫነ (Top down) ነው… አሊቲስት ነው:: ጣልቃ ገብነት አለ፤ በገንዘብና በተፅዕኖ ነው:: የተወሰኑ ሰዎችም የሚቆጣጠሩት ነው። ከዚህ ወጥቶ “የህዝብ ለህዝብ” የሚል አጀንዳ ይዞ፣ እንቅስቃሴ ለመጀመር፣ የሁለቱም ህዝብ ታሪክና የደረሰበትን ሁኔታ አይቶ አጣርቶ፣ለመድረክ አቅርቦ፣ አወያይቶ፣ መፍትሄ የፈለገ እስካሁን የለም፡፡ ለዚህ ነው ግጭቱ እስካሁን ያልተፈታው፡፡ ሁለቱ መንግስታትም ሊታረቁ ያልቻሉት፡፡ ለዚህ ነው የከሸፉት፡፡
 ሶማሊያ ውስጥ ያለው እርቅ እስካሁን ያልተሳካው እኮ ሶማሊያ ሶማሊያ ስለማይሸት ነው፡፡ የደቡብ ሱዳንም ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ የተወሰኑ ልሂቃኖች ተሰብስበው የሚያመጡት መፍትሄ ወይ አይሰራም፤ ቢሰራም ጊዜያዊ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁለቱ አገራት በታሪክ የነበረውን ችግር ከስር ከስር ሳይፈቱ፤ እሱ ተጠራቅሞ ትልቅ ሆነ፤ ወደ ጦርነት ገቡ፡፡ ሁለቱም ህዝብ አሰልፈው ውጊያ ገጠሙ፡፡ ህዝቡ ይዋጋ የነበረው ብዙም በማያውቀውና በማይረዳው ሁኔታ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ችግሩን ለመፍታት የሁለቱ አገራት ምሁራን በደንብ ይስሩ፡፡ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ላይ ይሳተፍ፡፡ ታሪክ በደንብ መነገር፣ በትክክል መታወቅ አለበት፡፡ አብዛኛውን ቅኝ ገዢ ሲዋጋ የነበረው እነ ቱርክን… እነ ጣሊያንን ሲያባርር የነበረው የኤርትራ ህዝብ አይደለም!? ይሄ ለምን አይነገርም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሰራዊት ጣሊያንን ሲያሸንፍ፣ የኤርትራስ አሰላለፍ ምን ይመስል ነበር? አገራችን ብለው አልነበረም እንዴ ሲዋጉ የነበሩት? ስለዚህ እንደነዚህ አይነት ታሪኮች በትክክል መታወቅና መነገር አለባቸው። ይሄ እኮ የሚያሳየው አንድነታችንን ነው፡፡ “Genetic body” ላይም አንድ ነን እኮ፡፡ እርግጥ ነው ይሄ ሁለት አገር መሆናችንን አይከለክልም፤ ግን አንድነታችንን አውቀን፣ አንድ ህዝብ ሁለት አገር ላይ እንደሰፈርን አስበን፣ በአካባቢው ያለንን ተሰሚነት የምናጠናክርበት፣ ችግሮቻችንን ተቀራርበን ተነጋግረን የምንፈታበት፣ አቅማችንን አስባስበን የምንወጣበት መንገድ መፈለግ አለብን፡፡ ይህንን ግን የምንጀምረው ከታሪክ ነው፡፡ እኔ አሁን በእንቅስቃሴው ውስጥ የምመራው አካዳሚክ ፓነሉ፣ ወደ ኋላም ወደ ፊትም የሚሄድ ነው፡፡
እስኪ ያብራሩልኝ …በምን መልኩ ወደ ኋላና ወደ ፊት እንደሚሄድ?
እነዚህን መንግስታት ትቶ ወደ ኋላ፣ ወደ መጣንበት ታሪካችን ይሄድና… በጥልቀት ታሪክ ይመረምራል። ለምን እዚህ ችግር ውስጥ ገባን? ብሎ ይፈትሽና፣ ከዚያ ከነዚህ መንግስታት ባሻገር ወደፊት ይሄዳል፡፡ ለዚህ ነው ለየት የሚያደርገን፡፡ ወደፊት ረዥም ትልም ላይ ስለሚያተኩር፣ አሁን ባሉት ሥርዓቶችና የፖለቲካ ልዩነቶች ላይ አይዳክርም ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሁለቱም አገሮች ላይ የውስጥ ችግር አለ፡፡ ኢትዮጵያም  በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህ የውስጥ ችግር ሳይፈታ ወደ ውጭ ችግር ማተኮር አግባብ ነው ይላሉ?
የሁለቱም አገራትና ህዝቦች ችግር ተወራራሽ ነው። አሁን ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ ኤርትራ ውስጥ ያለው የእርስ በርስ ችግር፣ የሁለቱ መንግስታት ችግር ነፀብራቅ ነው፡፡ ችግሩ ከሁለቱ አገሮች ጠብ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
እንዴት?
ምክንያቱን ላስረዳሽ፡- ሁለታችንም አቅማችንን እርስ በእርስ መጠፋፋት ላይ ስናውለው፣ የውስጥ ሀይላችን ይሟሽሻል፡፡ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ላይ በፍጥነትና በብቃት እንድንሰራ ከሚያደርገን ጉዳይ፣ አንዱና ዋነኛው፣ የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ነው፡፡ ትልቁ ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ፡- የኢትዮጵያ ጉዳይ ለኤርትራ መንግስት የውስጥ ጉዳዩ እንጂ የውጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሁልጊዜ አጀንዳው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ አስመራ ውስጥ የሚነሳው ልክ እንደ አገር ውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የድንበር ልዩነት ይኑር እንጂ ጉዳዮቻቸው አንድ ናቸው። ሁለቱ እርስ በእርስ በመጣላታቸው ምክንያት ሁለቱ ህዝቦች እርስ በእርስ ተራርቀዋል፡፡ ተዳክመዋል። አቅም አጥተዋል… ይሄ እርስ በእርስ መጠፋፋት ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል።
የግጭት ሲስተሙ የተሳሰረ ስለሆነ መንግስታትና ህዝቦች ይዳከማሉ፡፡ ሶማሊያና ሱዳን ላይ ያለው ግጭት ኢትዮጵያን ይጎዳል እያልን፣ አንድ የነበረ ህዝብ ሲጋጭ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ማሰብ አያዳግትም፡፡ ግጭትም የፖለቲካ ችግርም ከሁለቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው።  በሁለቱም መካከል ለአስራ ምናምን አመታት ሲደረግ የነበረው የእርስ በእርስ መጠፋፋት፣ የውድመት ችግር፣ አሁን ላለው የውስጥ ችግር እርሾ ነው፡፡ የግጭት ሲስተሙ አንድ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ እንኳን የሁለቱ አገራት ይቅርና ከዳርፉር እስከ ሱማሌ ያለው የግጭት ሲስተም አንድ ነው፡፡ የወንጀሉ የድንበር ጥሰቱ፣ ግጭቱ፣ ህገወጥ ንግዱ፣ የመንግስት መዳከም፣ የህዝቦች የግጭት አፈታት አለመሰልጠኑ… ሁሉም ጋር ተወራራሽ ነው፡፡

==================

“የሁለቱ አገር ህዝቦች ጠብና ጥላቻ የላቸውም”

በረከት አብርሃም (ኤርትራዊ ጋዜጠኛ)

ተወልጄ ያደግኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በእናቴም በአባቴም ኤርትራዊ ነኝ፡፡ በ1990 በነበረው የሁለቱ አገራት ግጭት፣ ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ኤርትራ ሄጄ፣ ለ18 ዓመታት እዛው ቆየሁ፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እዚሁ ተምሬ፣ ኤርትራ ደግሞ በጋዜጠኝነት ዲፕሎማ ካገኘሁ በኋላ ለ10 ዓመታት በጋዜጠኝነት አገልግያለሁ፡፡
ኤርትራ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የተራዘመ የውትድርና ሂደት በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በእጅጉ መብትን ስለሚጋፉና በነፃነት ለመኖር ስለሚያስቸግሩ ይሄው ተሰደን፣ ቀድሞ ተወልደን ወዳደግንበት አገር መጥተናል፡፡ እኔም ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ሆኖኛል፡፡ ስደተኛ ብሆንም “LRS” የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሚያዘጋጀው መፅሄት ላይ በአዘጋጅነት እየተሳተፍኩ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሰላም የሁሉም ነገር ቁልፍ ነው፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት በብዙ ኤርትራዊያን ወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለው መከራና ግፍ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በሁለቱ መንግስታት አለመስማማት፤ ባለፉት 20 ዓመታት፣ የሁለቱ አገራት ወንድማማች ህዝቦች፣ ብዙ ሰብአዊና ቁሳዊ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል፡፡ በተለይ በሁለቱ አገራት ድንበሮች ላይ ያሉት ሁለቱም ህዝቦች “No Peace No war” በሚለው ጉዳይ ምን ያህል እንደተጎዱ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ እኔ እዚህ ብሆንም እህት ወንድሞቼና ሌሎች ኤርትራዊያን እዛው በችግር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ አገራት ቢስማሙ ኤርትራም ወደ እድገትና ልማት፣ ህዝቡም ወደ ሰላም ይመጣ ነበር፡፡ ይሄ “No Peace No war” የሚለው የጦርነት ድባብ፤ ሁለቱን አገራት አፋጥጦ፣ በተለይ በኤርትራ በኩል ለእድገትና ለልማት እንቅፋት ሆኗል፡፡ ሰርቶ መለወጥና ማደግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ስለ ሰላም ዋጋ ከምንም በላይ እረዳለሁ፡፡
የሁለቱ አገር ህዝቦች ጠብና ጥላቻ የላቸውም፤ ኖሯቸውም አያውቅም፤ ወደፊትም አይኖራቸውም። ይሄ የሰላም ሂደት እስካሁን ለሁለቱ መንግስታት ብቻ የተተወ ነበር፡፡ ግን ስህተት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ነው መጨረሻው እየጠፋና መፍትሄው እየራቀ የሄደው፡፡ አሁን የችግሩ ሰለባም የጉዳዩ ባለቤትም ህዝብ በመሆኑ፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጀምሮ መፍትሄ መምጣት አለበት፡፡ ህዝብ ሀይል አለው፤ መንግስታት ከህዝብ ውጭ አይደሉም፡፡ የጉዳዩ ባለቤት ተቀራርቦ ከመከረ መፍትሄ ይመጣል፡፡ አሁን በምሁራን፤ በተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ በአርቲስቶናች በ“ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” አስተባባሪነት የተጀመረው እንቅስቃሴ እየጎለበተና ነፍስ እየዘራ ትልቅ ተስፋ ፈጥሯል፡፡ ወደፊት በጥቂት ግለሰቦች የተጀመረው እንቅስቃሴ እያደገና እየሰፋ… የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሲቪክ ሶሳይቲ፣ ዓለም አቀፍ ምሁራንና የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተሳትፈውበት፣ በሁለቱ አገራት ላይ ሰላም እንዲወረድ ተፅዕኖ የማሳደር እቅድ አለ፡፡ ይህ አቅም ያለው ራዕይና ተስፋ፣ በህዝብ ርብርብ እውን እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡
በእርግጥ በሁለቱ መንግስታት መካከል ቀደም ሲል በህግ የተወሰኑ ውሳኔዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት “ድርድር እናድርግ” ሲል፣ የኤርትራ መንግስት “የለም በህግ የተወሰነው ፀንቶ መቀጠል አለበት” ሲል ቆይቷል። አሁን የኢትዮጵያ መንግስት ራዕዩንና ሀሳቡን በሙሉ ደግፎትና ፈቅዶልን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ለህዝቦች ሰላምና አንድነት ይሄ ቡድን ጠንክሮ ከተንቀሳቀሰ፣ በሁለቱ መንግስታት ላይ ጫና የማይፈጥርበት ምክንያት የለም፡፡ በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ስለሆነ እኛ ከበረታን ይሳካል፡፡

=================

“መንግስታት ያልፋሉ፤ህዝብ ይቀጥላል”

አቶ ሀብቶም ገ/ሊባኖስ
(“የሰለብሪቲ ኤቨንትስ” መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

ስለ ራስህና ስለ ድርጅትህ አስተዋውቀኝ?
ሀብቶም ገ/ሊባኖስ እባላለሁ፤ ተወልጄ ያደግኩት ኤርትራ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ እንደተባረሩ ሁሉ፣ እኔም ከኤርትራ ወደዚህ ከተባረሩ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነኝ። ትምህርቴን እዚህ ከመጣሁ በኋላ ነው የጨረስኩት-በማኔጅመንት ዲግሪ አለኝ፡፡ የትግራይ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ሆኜ ለ3 ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት ማህበራት ጥምረት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆንም ለ5 ዓመት አገልግያለሁ፡፡ የወጣቶች ማህበራት ላይ ብዙ ጊዜ ስለቆየሁ፣ ሃላፊነቴን ለሌሎች አስረክቤ፣ በቀጥታ ወደ ግል ቢዝነስ ነው የገባሁት፡፡
ምን አይነት የቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ ገባህ?
ወደ መዝናኛው ኢንዱስትሪ ነው የገባሁት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት የመዝናኛ ክለቦች ከፈትኩ - “ሰለብሪቲ ባርና ሬስቶራንት”፡፡ “ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” ከዚህ ድርጅት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሰለብሪቲ ባርና ሬስቶራንት በአብዛኛው ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች አብረው የሚዝናኑበት ነው፡፡
“የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች” በሚል መርህ፣የሁለቱን አገራት ህዝቦች ወደ ሰላምና አንድነት ለማምጣት እንቅስቃሴ የጀመርከው ከወራት በፊት ነው፡፡  ሀሳቡ እንዴ መጣልህ?
ከዚህ በፊት ሺመልባ የሚባለው የኤርትራ ስደተኞች ካምፕ ሄደን ነበር፡፡ የተለያዩ ስራዎችን ሰርተናል። ይሄኛው የዚያ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ እዚያ ሄደን ሁኔታዎችን ስንመለከት፣ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ሰላም ወሳኝ ነገር ነው፤ ህዝቡ ሰላም ይፈልጋል፡፡ ሁለቱ ህዝቦች፤ “ሰላም ለሁለቱ አገራት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ማለትም ለምስራቅ አፍሪካ ወሳኝ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ይሄ የሰላም መንገድ ለምን በወጣቶች አይጀመርም፡፡ ወጣቶች የያዙት ነገር ዳር ይደርሳል በሚል “ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” ተነሳሽነቱን ወስዶ፣ ኤርትራዊያን በሚገኙበት ካምፕ ላይ ብዙ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ እንግዲህ በአምስቱ ካምፕ፣ ከ180 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች አሉ፡፡ እኛም እዚያ ለ3 ወራት ቆይተን ዳሰሳ አድርገን፣ ከነሱ ጋር ተወያይተን ስንጨርስ፣ የጉዳዩ አስፈላጊነት አንገብጋቢ በመሆኑ፣ ይህንን መንገድ ጀመርን፡፡ የኤርትራ ስደተኞችን አነጋግረን ስንጨርስ፣ እዚህ የሚኖሩ ኤርትራዊያንን አነጋገርን፡፡ እነሱም ለሁለቱ አገራት ህዝቦች፣ሰላም ወሳኝ መሆኑ ላይ ጥብቅ አቋም አላቸው፡፡ እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያዊያን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የዞርነው፡፡ ምሁራንን፣ አርቲስቶችንና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ሰዎችን… ይዘን ምክክር ያዝን፡፡ ከዚያ ዝቅ እያልን በክ/ከተማ ደረጃ ውይይት ጀመርን፡፡ በኋላም ጉዳዩ በሁሉም ዘንድ ድጋፍ አግኝቶ፣ ከምሁራንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ለትውውቅና በቀጣይ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር፣ ሰሞኑን በሀርመኒ ሆቴል የተደረገው ስብሰባ ላይ ደርሰናል፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ የአንተ ተስፋ በዋናነት ማን ላይ ነው?
የኔ ተስፋ ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ከታረቀ መንግስታትም የማይታረቁበት ምክንያት የለም፡፡ ህዝብ ከታረቀ መንግስታት ባይታረቁም እንኳን ችግር የለውም፡፡ መንግስታት ያልፋሉ፤ ህዝብ ይቀጥላል፡፡ አሁን ጉዳዩ ተቀጣጥሏል፡፡ አውሮፓ የሚገኘው የኢትዮ-ኤርትራ ኮሚዩኒቲ እንቅስቃሴውን ተቀላቅሎታል። መቐሌ ላይ በቅርቡ ትልቅ ጉባኤ ይካሄዳል፡፡ አዲስ አበባም ላይ ከ800 በላይ የሁለቱም አገራት ምሁራን፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የስነ-ህዝብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ይካሄዳል፡፡ ከዚያ በኋላ የመጨረሻ ግባችን የሰላምና የፀጥታ ካውንስል ማቋቋምና ካውንስሉ፤ ለኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱን አገራት ህዝቦች ሰላምና አንድነት ይፈልግ እንደሆነ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ በተመሳሳይ ለኤርትራ መንግስትም ጥያቄው ቀርቦ ምላሽ ሲያገኝ፣ አዲስ አበባ ውስጥ በ800 ሰዎች የሚካሄደው አይነት ጉባኤ አስመራም ላይ ይካሄዳል፡፡
ይህንን እንቅስቃሴ ስትጀምሩ ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅናና ይሁንታ ማግኘት የግድ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄውን ስታቀርቡ ፈተና አልገጠማችሁም? ጉባኤውን አስመራ ለማድረግ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ቀና ምላሽ እናገኛለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
የመጀመሪያ ስጋታችን እሱ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሀሳቡ አዲስና ድፍረት የሚጠይቅ ስለሆነ፣ መጀመሪያ የ10 ሺህ ኤርትራዊያንን ፊርማ አሰባስበን ሄድን፡፡ የሚገርምሽ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ስንነግራቸው በጣም ነው ደስ ያላቸው፡፡ “እኛ እንደውም ግማሽ መንገድ ሄደን እንደራደራለን፤ ቀድመንም ያስቀመጥነው ጉዳይ ነው፡፡ ከህዝብ ከመጣ መልካም ነው፡፡ እናንተ ስብሰባ ስታደርጉ፣ የህዝብ ለህዝብ ስራ ስትሰሩ፣ የፀጥታ ችግር እንዳይገጥማችሁ፣ አዳራሽ ስታስፈቅዱ እንዳትቸገሩ ድጋፍ እናደርጋለን፤ ነገር ግን ጉዳዩ የህዝብ ለህዝብ ስለሆነ መንግስት ጣልቃ አይገባም” ብለው አበረታቱን፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሞራልና አቅማችን የጎለበተው፡፡
በኤርትራ በኩል ቀና ምላሽ ይገኛል ወይ? አዎ ተስፋ አለን፡፡ አሁን በቅርቡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ያደረጉት ንግግር ለዚህ የሚጋብዝ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት ከአፋቸው እንደዚህ አይነት ንግግር ወጥቶ አያውቅም። ምን አሉ? “እስከ ዛሬ ከጎረቤት አገሮች ጋር የነበረን የግንኙነት መንገድ የተሳሳተ ነበረ፣ አሁን ግን ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላም መፍጠር አለብን፤ መንገድን ጨምሮ በሁሉም ነገር መተሳሰር አለብን፤ ይህንን ደግሞ ከኢትዮጵያ መጀመር አለብን” ብለዋል፡፡ ይህንን ቃለ ምልልስ የኤርትራ ህዝብም አስምሮበታል፡፡ ይሄ ደግሞ አዲስና ያልተለመደ ስለሆነ፣ በዚያም በኩል በጎ ምላሽ ይኖራል የሚል ተስፋ አለን፡፡ አሁን ኦፊሴላዊ ደብዳቤ ከኢትዮጵያ መንግስትና አንድ ከውጭ በተመረጠ አደራዳሪ በኩል፣ ለኤርትራ መንግስት ይላካል፡፡ ዞሮ ዞሮ ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ ትልቅ የሰላምና የፀጥታ ካውንስል ይቋቋምና የካውንስሉ መሪ ፕሮፌሰር መዳኔ ታደሰ ይሆናል፡፡ ወጣቶቹ ከስር ያስኬዱታል ማለት ነው፡፡
በአምስቱም የኤርትራ ስደተኞች ካምፕ ተዘዋውራችሁ የህዝቡን ፍላጎት አጢናችኋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እዛው ኤርትራ ውስጥ ያሉ ኤርትራዊያን፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይፈልጋሉ አይፈልጉም የሚለውንስ አጥንታችኋል?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፡፡ በነገራችን ላይ እኛ ይሄንን ነገር ባንይዝ፣ እንቅስቃሴውን ባልጀመርን ነበር፡፡ እኛ በአሁኑ ጊዜ ሽሬ በሚባለው አካባቢ የስደተኞች ካምፕ ቢሮ ከፍተናል፡፡ ከኤርትራ ስደተኞች ሲመጡ የእኛን ቢሮ ያገኛሉ፡፡ በኤርትራ ያለውን የህዝብ ፍላጎትም ይነግሩናል፡፡ እዛ ያለው ህዝብ፣ በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ሰላምና አንድነት መፍጠር እንደሚፈልግ በደንብ እናውቃለን፡፡ ሲሰደዱ መጠለያ እያደረጉ ያሉት ኢትዮጵያን ነው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ይፈለጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ልነግርሽ የምፈልገው፣ በአሁኑ ወቅት የተጀመረ “አጋዚያን” የተባለ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ፣ከእኛ እንቅስቃሴ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ የእኛ እንቅስቃሴ የሉአላዊት ኢትዮጵያና የሉአላዊት ኤርትራ ህዝቦችን አንድነትና ሰላም ለማምጣት ሲሆን “አጋዚያን” የሚባለው የትግርኛ ተናጋሪዎችን ብቻ አቅፎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በጣም እንለያያለን፡፡ የእኛ በቋንቋ የተከፋፈለ አይደለም፤ በሁለቱም አገራት የትኛውንም ቋንቋ የሚናገር ህዝብ ላይ ነው የምንሰራው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ልብ እንዲባሉልን እንፈልጋለን፡፡
“ኤርትራዊያን ኢትዮጵያዊያንን አይወዷቸውም ” የሚሉ መረጃዎች ይደመጣሉ፤ ያንተ አስተያየት ምንድን ነው?
ምን መሰለሽ… አሁን ያለው ወጣት በደርግ ጊዜ የነበረ ወጣት አይደለም፡፡ ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ የህዝቡ ጭንቅላት ላይ እንዲህ አይነት ስራ ተሰርቷል። ሆኖም ግን ወጣት፤ ወጣት ሆኖ አይቀርም፣ ሁሉም የተሳሳተ ነገር እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ አሁን አንድ ኤርትራዊት እናት፣  ልጇን ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ “ወገኖችህ ናቸው፤ ሰላም ነው” ብላ ነው፡፡ ይሄ ባይሆን አትልክም ወይም ራሷም አትመጣም፡፡ እናትየዋ የቀደመውንም ነገር ታውቃለች፡፡ ልጇ ይህ የጥላቻ አስተሳሰብ ቢኖርበት እንኳን እናቱ “ኢትዮጵያ ይሻላል” ብላ ስትልከው፤ለምን? ይላል፤ ይረዳል፡፡ አሁን እኮ የኤርትራ ልጆች በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል --- በሌሎችም ክልሎች ከወገናቸው ጋር እየኖሩ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ጥላቻ ይከስማል፡፡ በየዩኒቨርሲቲው ገብተው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቀብሏቸው እየተማሩ ነው፡፡ ጥላቻ ቢዘራባቸውም እውነቱን ኖረው እያዩት ነው፡፡ በቀጣይ የሌሎች ኤርትራዊያንንም አስተሳሰብ፣ እነዚህ እውነቱን የሚያውቁ ሰዎች ይለውጣሉ፡፡ ጥላቻ መኖሩ አይካድም ግን በቀላሉ የሚቀረፍ ነው፡፡ የሁለቱ አገራት ልጆች በጋራ መነገድ ሁሉ ጀምረዋል፡፡ የሚያስጨንቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ጥላቻ አይኖርም፤ ህዝቡ ይዋደዳል፤ አንድ ነው፡፡  


======================

“በሁለቱ መንግስታት
ችግር ሰለባው ህዝብ ነው”

አቶ ይስሀቅ ዮሴፍ (ኤርትራዊ ስደተኛ)

የምኖረው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ድግሪዬን በሶስዮሎጂና በሶሻል አድሚኒስትሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው ያገኘሁት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ13 ዓመታት በመብራት ሀይል ማሰልጠኛ ተቋም መምህር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ አሁን ምንም የምሰራው ስራ የለኝም፤ ስደተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን በተጀመረው “የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች” እንቅስቃሴ ላይ በፈቃደኝነት እየሰራሁ አገኛለሁ፡፡ ወደ ኤርትራ የሄድኩት ሁለቱ አገራት ሲለያዩ እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም ነበር፡፡ በስደት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ አንድ ዓመት ከአራት ወር ሆኖኛል፡፡
እኔ ተስፋ ያለኝ በህዝቡ ላይ ነው፡፡ እንዳስተዋልኩት ህዝቡ ተስፋ ፈላጊ ነው፡፡ የሰላምን እጦት ችግር በደንብ የሚገነዘብ ህዝብ ነው፡፡ በጦርነት ውስጥ መከራ ሲገፋ ረጅም ጊዜ ያሳለፍ ህዝብ ነው፡፡ ከጦርነቱም አልፎ በጦርነት ድባብ ውስጥ ብዙ ያለፈና አሁንም በዚያው ድባብ ውስጥ ያለ ህዝብ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተስፋ የተደረጉ ነገሮች አልተሳኩም፡፡ ሁለቱም መንግስታት ያሰቡት ነገር አልተሳካላቸውም፡፡ የዓለም መንግስታት ብዙ ተፅዕኖ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ አሁን እንግዲህ ህዝቡ የድርሻውን ይወጣ በሚል ነው እንቅስቃሴው የተጀመረው፡፡ ህዝቡ ግን ከተባበረ ችግሩን መፍታት ይችላል፡፡ በመንግስታቱም ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ይቻላል የሚል እምነት ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እስካሁን ጉዳዩ ለሁለቱ መንግስታት ተትቶ ነበር የቆየው፡፡ አሁን ግን ህዝቡ መነሳት አለበት፤ ምክንያቱም የችግሩ ተጎጂ ህዝቡ ነው፡፡ ተስፋችንም በህዝብ የበላይነት ላይ የተመረኮዘና ህዝብ አሸናፊ ነው የሚል ነው፡፡ መንግስታትም በህዝብ ስር ሆነው ህዝብን የሚያገለግሉ እንጂ በህዝብ የሚገለገሉ አይደሉም፡፡
እውነት እንነጋገር ከተባለ ሁለቱ ህዘቦች አሁን ሰላም አይደሉም፤ ጦርነት ቢገጥሙም የሚዋጋው ህዝቡ እንጂ መንግስታቱ አይደሉም፡፡ በዚህ ሁሉ ተጎጂው ህዝብ ነው፡፡ ህዝቡ ሰላም ባለማግኘቱ በሚፈለገው መጠን ግንኙነት እየፈጠረም አይደለም፡፡ ህዝቦቹ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በመካከላቸው የለም። እንደውም በጦርነት ስጋት ላይ ነው ያሉት፤ ጦርነቱ መቼ እንደሚነሳ አይታወቅም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የውጭ ሀይሎችም ጣልቃ እየገቡ፣የራሳቸውን አጀንዳ የሚያራምዱበት ሁኔታ እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ የቀጠናው ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቡ ማድረግ ያለበት በሁለቱም መንግስታት አለመግባባት በተለኮሰው ጦርነት ምክንያት በሁለቱ አገራት ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር የሚፈታበትንና የሚቋጭበትን መንገድ መፈለግ ነው። እስካሁን ጉዳዩ እንቆቅልሽ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ችግሩ ለምን እንዳልተፈተና እንዳልተቋጨ፣ እንዲሁም እንቅፋቱ ምን እንደሆነ መጠናት አለበት፡፡
ሁለቱም መንግስታት ችግሩን ለመፍታት ተራራ የሆነባቸው ነገር ምንድ ነው? ለማይታረቅ ችግር እንዴት ተጋለጡ? የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነት ነው ወይስ የራሳቸው ችግር? የሚለው መጠናት አለበት፡፡ ግጭት የትኛውም ዓለም ላይ አለ፤ አዲስ ነገርም አይደለም፡፡ ነገር ግን ረጅም ጊዜ ወስዶ መቀጠል የለበትም፡፡ የሁለቱ አገር ህዝብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ባህልም አለው። ብቻ የትኛውንም አይነት ዘዴ ተጠቅሞ መጀመሪያ  ችግሩ ከተፈታ በኋላ ወደ ግንኙነት ይሄዳል፡፡ የሰላምና የትብብር ግንኙነት ደግሞ አንዴ ተደርጎ የሚቆም ሳይሆን ሂደት ነው፤ ይጀመርና እደገ የሚሄድ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሁለቱ አገራት ህዝብ ግንዛቤ ምን ያህል ነው? ግንዛቤያቸውስ አንድ አይነት ነው አይደለም? የሚለው ደረጃ በደረጃ ይታያል፡፡ ዋናው ጅማሬው ነው፤ አሁን ጅማሬው ላይ ነን፡፡
እንቅስቃሴው በትክክል ውጤት ያመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዋናው ባለቤቱ ነው፡፡ የዓለም ማህበረሰብም ይሁን ሌሎች የራሳቸውን ፍላጎትና አጀንዳ ነው የሚያራምዱት፡፡ የሁለቱ አገራት መንግስታትም ቢሆኑ  ቅድሚያ የሚሰጡት ለራሳቸው ህልውና ነው፡፡ ይሄ ግን የህዝብ ጉዳይ ነው፤ ህዝብ ደግሞ የራሱን ችግር የመፍታት አቅም አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእስከዛሬው ጥረት ያልተሳካው የጉዳዩ ባለቤት ስላልተሳተፈበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የኤርትራ ህዝብ ለኢትዮጵያውያን ጥላቻ አለው የሚለው ጉዳይ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ መመለስ አልችልም፡፡ እኔ ግን በግሌ ኢትዮጵያን እንደ አገሬ ነው የማየው፤ ህዝቡም የራሴ ወገን ነው። በዝምድና፣ በአምቻም በጋብቻም እየተሳሰሩ ኖረዋል። ግጭት እንግዲህ የትም ያጋጥማል ብያለሁ፡፡ ሁለት የአንድ እናትና አባት ልጆች፣ ወንድማማቾችም ይጋጫሉ። የኤርትራ ህዝብን ስንመለከት ሰፊ ህዝብ ነው፤ እርስ በራሱም የሚተዋወቅ አይደለም፡፡ ኤርትራ የምትባለው አገር እራሷ በህዝቦቿ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተች ወይም /Nation building Process/ የሚባለው ገና አልተጀመረም፡፡  
ኤርትራዊያን ኢትዮጵያዊያንን ይጠሏቸዋል የተባለውን ነገር በተመለከተ፣በችግር ጊዜ ተሰደን የመጣነው እንግዲህ ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ሲከፋሽ ወደምትጠይው ህዝብ አትመጪም፤ አሁን እዚህ አገር ላይ በስደት የሚኖረው የኤርትራ ህዝብ ቁጥር እስከ 300 ሺህ ይደርሳል ሲባል እሰማለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ኤርትራዊ ወደሚጠላው ህዝብ ከመጣ መቼም ይገርመኛል፡፡
እንግዲህ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል በነበረው የታሪክ ግንኙነት የተከሰተ ብዙ መጥፎ ነገር ነበር፡፡ በኃይለ ስላሴ ጊዜ እንደምታውቂው፤ የበላይነቱ የክርስቲያን ኃይማኖት ስለነበር በሙስሊሞች አካባቢና በቆላማ አካባቢ ብዙ ችግር ይደርስ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ችግር የደረሰበት ሰውና ያልደረሰበት እኩል ስሜት አይኖረውም፡፡ እንደኔ አይነቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ተምሮና ሰርቶ ኑሮ ያጣጣመ ሰው ጥላቻውን ከየት ያመጣዋል? ዞሮ ዞሮ በነበሩ ችግሮች ላይ አተኩሮ የማስታረቅ ስራ አልተሰራም፡፡ የተቀየመውም መቀየም ስላለበት ነው፤የተጎዳው የሚካስበትና የተቀየመው ቂሙን የሚሽርበት የእርቅ ስራ አልተሰራም፡፡ ከዚያ ይልቅ ቂሙን ወደማጎልበቱና ወደ መከፋፈሉ ነው ትኩረት የተደረገው፡፡ ስለዚህ ያነሳሽው ችግር የለም አይባልም፡፡
የእርቅ ሥራ ስላልተሰራ አኩራፊ መኖሩ አይቀርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በትክክል ስለማላውቅ ብዙ ባልናገርም በጃንሆይም ሆነ በደርግ ዘመን በኤርትራ ህዝብ ላይ የደረሰው ግፍና መከራ ቀላል አይደለም፡፡ ጥላቻ አለ ከተባለ ምክንያቱ የእርቁ ስራ ስላልተሰራ ነው እላለሁ። ይሄ ደግሞ የታሪክ አጋጣሚ ነው፡፡ አውሮፓውያንን ብንወስድ፣ እንደነ እንግሊዝና ፈረንሳይ እስከ መቶ ዓመት ተዋግተው አሳልፈው አሁን የሰላም ቀጠና መስርተው እየኖሩ ነው፡፡ እንኳንስ ሁለቱ አንድ ሆነው የኖሩት ህዝቦች ቀርቶ መላው አፍሪካ አንድ የሚሆንበት ነገር አያሳስብም ነበር፡፡ ይሄ የአፍሪካ ቀንድ የሚባለው ቀጠናው ራሱ አብሮ የመስራት ነው ያለው ትልም፡፡

Read 1184 times