Saturday, 25 November 2017 10:32

“ምትክ” እና “ሎሌ” የተሰኙ አዲስ ዓይነት የኢንሹራንስ አገልግሎቶች ተጀመሩ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

ከአሁን ቀደብ በአገራችን ያልነበሩ “ምትክ” እና “ሎሌ” የተሰኙ አዲስ ዓይነት የኢንሹራንስ አገልግሎቶች መጀመሩን ዘ አልትሜትስ ኢንሹራንስ ብሮከር አስታወቀ፡፡
የአልትሜስ ኢንሹራንስ ብሮከር ዋና ሥራ አስፈጻሚና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ምግባር ከትናንት በስቲያ ጽ/ቤታቸው በሚገኝበት ሬዊና ሕንፃ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያሉ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚሰጡት አገልግሎት የሕይወትና ሕይወት ነክ ያልሆኑ መድን ሽፋን እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በ2009 በጀት ዓመት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው 17ቱም መድን ሰጪ ኩባንያዎች 7.5 ቢሊዮን ብር አረቢን መሰብሰባቸውን፣ ከዚህ ውስጥ 7.1 ቢሊዮን ብር አረቦን የተሰበሰበው ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከዚህ አረቦን ውስጥ ከ56 በመቶ በላይ ለተሸከርካሪ ከተሰጠ የመድን ሽፋን ተሰበሰበ መሆኑን፣ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ኢንሹራንስ ኬባንያዎች ለካሳ ክፍያ ካዋሉት 3.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የተከፈለው በተሽከርካሪዎች ላይ ለደረሰ አደጋ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የተሽከርካሪ ዋስትናና የጉዳት ካሳ ክፍያ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ብዙ ጊዜና ጉልበት እንደሚወስድ በመገንዘብ ድርጅታቸው ዘ አልትሜትስ ኢንሹራንስ ብሮከር ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት አድርጎ “ምትክ” እና “ሎሌ” የተባሉ ሁለት ዓይነት የኢንሹራንስ አገልግሎቶች እንደመፍትሄ ማቅረቡን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች ተገቢ ካሳ ለማግኘት፣ የተጎዳውን ተሽከርካሪ አስጠግኖ መልሶ ለመጠቀም በወራት የሚቆጥ ጊዜ ስለሚወስድ ኢንሹራንስ የገቡ ደንበኞች መኪና በማጣት የቀን ተቀን ስራቸውን፣ የቤተሰብና የማኅበራዊ ጉዳያቸውን ለማከናወን ችግር ይፈጠርባቸዋል ወይም መኪና በመከራየት ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ለዚህ ችግር መፍትሔ እንዲሆን “ምትክ” የተሰኘ አዲስ ዓይነት አገልግሎት ይዘን ቀርበናል ብለዋል፡፡
የ”ምትክ” አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ደንበኛው የኢንሹራንስ ውሉን በድርጅታችን በኩል መግዛት ይኖርበታል ያሉት ዋና ሥራ አሰፈጻሚ፣ “ምትክ” አገልግሎት፣ የደንበኞች መኪና አደጋ ሲደርስበትና ለጥገና ጋራዥ በሚገባበት ወቅት መኪናቸው ተጠግኖ እስኪወጣ ድረስ መንቀሳቀሻ እንዳይቸገሩና ምቾታቸው እንዳይጓደል ምትክ ተሸከርካሪ ለማቅረብ የሚያስችል በአገራችን የመጀመሪያና በዓይነቱ ልዩ የሆነ አገልግሎት ነው ብለዋል፡፡ ለቤት አውቶሞቢሎች አገልግሎቱን አሁን እንደሚጀምሩና ሌሎችንም ለማጠቃለል እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“ሌሎ” የተሰኘው አገልግሎት ደግሞ በብዙ ሞያዊ (ቴክኒካል) ቃላት የተሞላ ስለሆነ ደንበኞች በከሣ ጥያቄ ወቅት ያላቸውን መብትና ግዴታ ለመረዳት ሲቸገሩ ይስተዋላል ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ከኢንሹራንስ አገልግሎት ጋር በተያዘ ደንኞች የሚገባቸውን የኢንሹራንስ ካሣ ክፍያ ማግኘት እንዲችሉ፣ ጥያቄዎችን ለማቅረብ፣ ለመከታተል፣ ለመደራደርና ለማስፈጸም የተጀመረ አዲስ አገልግሎት እንዲሆን ገልጸዋል፡፡
ይህን በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የካሣ ክፍያ የማስፈጸም አገልግሎት የጀመርነው፤ የካሣ ክፍያ ጥያቄ ሂደት የቅብርብ ክትትልና ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ፣ ደንበኞች፣ ይህንን የክትትል ሂደት በእኛ ላይ ጥለው በዋና ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ፣ ደንበኞች ሙሉና ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ ለማስቻልና የካሣ ክፍያ ሂደት ሰፊ ድርድር የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ፣ ደንበኞቻችንን “ጌታ” አድርገን እኛ “ሌሎ” ሆነን ለማገልገል ነው ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተስፋዬ ምግባር፡፡

Read 2761 times