Print this page
Sunday, 26 November 2017 00:00

ፍሬን የበጠሱ እግሮች!!

Written by  ሳምሶን ጌታቸው ተ/ሥላሴ
Rate this item
(4 votes)

   የቀሉ ዓይኖቹን አፍጥጦ፣ ሥሩ የተገታተረና በላብ የወረዛ ግንባሩን አኮሳትሮ፣ ቀጫጭን ጅማታም እግሮቹን እያምዘገዘገ ሲሮጥ ሲያዩት፤ አትሌቱ ሩጫ እየተወዳደረ ሳይሆን፣ በእልህ የተጣላውን ሰው አባሮ ይዞ በካልቾ የሚማታ ይመስላል። ሰውየው እንደተኮሳተረ በጀመረበት ፍጥነት ታላቁ ሩጫ ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ብቃት በአንደኝነት ጨረሰ። ግን የሚገርመው ነገር ሩጫውን ጨርሶም መቆም አልቻለም፡፡ በዚያው ፍጥነት ሩጫውን ወደመጣበት ቀጠለ፡፡ የድካም ስሜት አይታይበትም። ፍጥነቱንም አልቀነሰም። ግራ የተጋቡት የሩጫው አዘጋጆች፣ በድምፅ ማጉያ “አትሌት ቁጥር 0038፤ እባክህን ሩጫህን በአንደኝነት ስለጨረስክ በቃ ይበቃል ተመለስ ---- እባክህ አትሌት 0038፤ ሩጫህን ጨርሰሃል፡፡ ጎሽ ጎሽ ጎሽ--- ወደዚህ ና--” ምንም መልስ የለም፡፡ አትሌቱ በቃ ገሰገሰ፡፡
ሁሉም ሰው ግራ ተጋባ፡፡ ወዲያውኑ የተወሰኑ ጋዜጠኞች አትሌቱን በመኪና ለመከተል ተነሱ። ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ሳር ቤት መታጠፊያው ላይ ደረሱበት፡፡ ጋዜጠኞቹ ካሜራ ጠምደዋል፡፡ ማይክራፎን ወደ አትሌቱ አፍ እያስጠጉ፤ “አትሌት 0038 --- በቃ ውድድሩ እኮ 10 ኪሜ ነው፤ እሱንም ጨርሰሃል፡፡ ለምን አትቆምም?” መልስ የለም፡፡ ብቻ አፉን ከፈት አድርጎ “ህሃ... ህሃ... ህሃ...” እያለከለከ ሮጠ፡፡ ጉዳዩ መስቀል አደባባይ ባለው ትልቁ ስክሪን ላይ መዘገቡን ተከትሎ በሬዲዮም በቴሌቭዥንም ቀጥታ ሽፋን ማግኘት ጀመረ።
አትሌቱ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለተኛውን ዙር ጨርሶ፣ ብዙ ሯጮችን ደራርቦ፣ ወደ መስቀል አደባባይ ተቃረበ፡፡ ከባድ ጭብጨባ እና የአድናቆት ድምፆች አካባቢውን አደባለቀው። አሁንም ግን ዙሩን ጨረሰና ፊቱን ወደ ሜክሲኮ አዙሮ እንደገና ሩጫውን ለ3ተኛ ዙር በዚያው ፍጥነት አስነካው። ከአዘጋጆቹ አንዱ ሰውዬ ተቆጣ። “አይ እንግዲህ!! አትሌት 0038 ይበቃሃል። አትሌት 0038 ይሰማል? ተመለስ እኮ ነው የምንልህ፡፡ እኛ ሥራ አለብን፡፡” አሁን ብዙ የሀገር ውስጥም የውጭ ጋዜጠኞችም በመኪና፣ በሞተር እየተከታተሉ፣ የጥያቄ ዓይነት ያቀርቡለት ያዙ። ፍጥነቱ ደግሞ የማራቶንን ርቀት ከ2 ሰዓት በታች መግባት የሚያስችለው በመሆኑ፣ የአብዛኞቹን የስፖርት ጋዜጠኞች ቀልብ ስቧል፡፡
3ተኛውን ዙር ጀምሮ ወደ ለገሃር አካባቢ ሲደርስ፣ በስቃይ ውስጥ በሆነ ሰው ድምፅ፣ አንድ ነገር ተናገረ፤ “በገብርኤል አስቁሙኝ! ህሃ ህሃ ህሃ” አለ እያለከለከ። “ምን?!” አሉ የሰሙት ጋዜጠኞች። “እባካችሁ እግሮቼ ሃህ ሃህ ሃህ አልቆም ብለውኝ እኮ ነው፣ ያዙኝ፡፡ ሃህ ሃህ ሃህ መቆም አልቻልኩም፣ እግሮቼ ፍሬን በጥሰዋል፡፡” ደገመ፡፡ ጋዜጠኞቹ ዓይናቸውን አፈጠጡ፡፡ ፈረንጆቹ “what did he say?” አሉ፡፡ ተነገራቸው፡፡ አንዳንዱ ቢገረምም፣ በጣም የሚስቁም አልጠፉም፡፡ “ምን ማለቱ ነው? መቆም አልቻልኩም? አስቁሙኝ? እግሬ ፍሬን በጠሰ?”
እንደገና ተጠግተው ጠየቁት፤ “አትሌት 0038 እውነት እግሮችህ ከቁጥጥርህ ውጭ ሆኑብህ?” አንድ ጋዜጠኛ ጠየቀው፡፡ “አዎ ሃ-- ህሃ --- ህሃ አስቁሙኝ እባካችሁ፡፡ ህሃ-- ህሃ ----ህሃ ወድጄ አይደለም እኮ የምሮጠው፤ በጣም ደክሞኛል...” በቃ አሁን ወደ መፍትሔ እንሂድ ተባለና፤ ጉዳዩን ወደ አዘጋጆቹ ደውለው መወያየት ጀመሩ፡፡ “ወይ ጉ...ድ ምን ይሻላል?” ተባለ፡፡ ጉዳዩ በአንዴ ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ተዳረሰ። በኢትዮጵያ በመካኼድ ላይ ባለው ታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ አንድ ተወዳዳሪ ባልተለመደ ሁኔታ “እግሩ ፍሬን በጠሰ” 10 ኪሜ የሚፈጀውን ውድድር ቢጨርስም አሁንም ገና እየሮጠ 23 ኪሜ በላይ አገባዷል፡፡” ተባለ፡፡ አባባሉ ለብዙ ሰዎች ግልፅ ሊሆን አልቻለም፡፡ “እግር ደግሞ እንዴት ፍሬን ይበጥሳል?” ጉድ!! ተባለ፡፡
አትሌቱን ለመርዳት የተለያዩ ሃሣቦች ቀረቡ። የስፖርቱ ጠበብቶች፣ ሀኪሞች፣ ጋዜጠኞች መወያየት ያዙ፡፡
“ለምን ተባብረን አንይዘውም?” አለ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ፡፡
“የመሮጫ ጉልበቱ በቀላሉ ይዞ ለማስቆም ያዳግታል፣ በራሱም ላይ ሆነ ለመያዝ በሚሞክሩት ላይ አደጋ ያደርሳል፡፡ እግሮቹ እኮ ናቸው ከቁጥጥር ውጭ የሆኑበት!” አሉ አንድ የአትሌቶች ዶ/ር፡፡
“ታዲያ ለምን ከምትበር ሄሊኮፕተር ላይ ሆነን፣ ገመድ ወደ ታች ጥለን አንጠልፈውምና፣ አየር ላይ አናንሳፍፈውም?” አለ አንድ ወጌሻ፡፡
“ከዚያስ?”
“ከዚያማ አየር ላይ ሆኖ አልቆም ብለው የሚሮጡ እግሮቹን እያንፈራገጠ ለማስቆም እንጥራለን፡፡ ልቡ ሳትፈነዳ በቶሎ የሆነ ነገር ማድረግ አለብን፡፡”
አይ! አይ! ሄሊኮፕተሯ ለስንት ደቂቃ ተንሳፋ አንድ ቦታ ትቆማለች? በዚህ ላይ እሷም እየበረረች፣ እሱም እየሮጠ የሰውዬውን ወገብ በገመድ መጥለፍ በጣም ይከብዳል፡፡ እንደገናም ተከራይተን እስክናመጣትም ጊዜ የለንም፡፡ በአካባቢው የነበረ አንድ ወታደር በእጁ የያዘውን ዱላ እያጠባበቀ፤ “ስሙ እናንተ! የምን ልምምጥ ነው፤ እኔና ጓደኞቼ በአንዴ እናስቆመዋለን! ይኼ ሽብርተኛ፡፡ ፍቀዱልን!” አለ፡፡
“በል በል በል አንበሳችን አንተ ተው! እኛ እናስብበታለን፡፡ አትጨነቅ ጎሽ! ከአቅም በላይ ከሆነ እንነግርሃለን፡፡”
አንድ ሌላ ኃሣብ፣ በታዋቂ አትሌት ቀረበ፡፡
“ከአስፋልቱ ማዶ ካለው ጂም ቤት፣ በፍጥነት የመሮጫ ማሽን እናምጣና ከፊቱ ቀድመነው እናስቀምጥ፡፡ ከዚያም ማሽኑን አትሌቱ አሁን እየሮጠ በሚገኝበት በሰዓት 21.4 ኪሜ ፍጥነት ላይ እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያም አትሌቱ ማሽኑ ላይ በመጣበት ፍጥነት እንዲወጣ እናድርገው፡፡”
በዚህኛው ኃሣብ ሁሉም ተስማሙ፡፡ አዘጋጆቹ ተወያይተው እስኪጨርሱ እና የመሮጫ ማሽን እስኪዘጋጅ ድረስ አትሌቱ በጋዜጠኞችና በሕዝብ እንደታጀበ፣ በዚያው ፍጥነት 3ተኛውን ዙር ጨርሶ 4ተኛውን ጀመረ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ሯጩ 4ተኛ ዙሩን እያጋመሰ፣ መሿለኪያ አካባቢ ደረሰ፡፡ የሩጫው ማሽንም ተገኝቶ፣ መስቀል አደባባይ ላይ ተጠመደ፡፡
በርካታ የሚዲያ ተቋማት መኪኖች፣ ሁለት የእሳት አደጋ መኪኖች፣ 4 አምቡላንሶች፣ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ መኪኖች ሰውዬውን አጅበውታል። 6 የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ሞተሮች መንገዱን እያስከፈቱለት ነው፡፡
“ፍሬን የበጠሰ አትሌት” የሚለው ዜና በአንዴ በመዳረሱ፣ በመሮጥ ላይ ከነበሩት ሰዎች በተጨማሪ ከየቤቱ ሰዉ ወጥቶ መንገዱ ተጥለቀለቀ፡፡ አሁን ሯጩ ወደ መስቀል አደባባይ ደረሰ፡፡ “ህኻ ህኻ ህኻ... ኧረ ያዙኝ በእናታችሁ፣ አስቁሙኝ ህኻ ህኻ ህኻ...” አለ በተቆራረጠ ድምፅ እንደምንም፡፡ “አይዞህ አትሌት 0038! ልክ መስቀል አደባባይ ስትደርስ፣ የተዘጋጀ የመሮጫ ማሽን አለ፤ እዚያ ላይ ትወጣለህ፡፡ በአንተ ፍጥነት ልክ ተዘጋጅቶ እየጠበቀህ ነው። አይዞህ በርታ!” በአካባቢው ያለው ሕዝብ ሁሉ አፈጠጠ። ሚዲያዎች ካሜራዎቻቸውንና ደምፅ መቅረጫዎቻቸውን ጠመዱ፣ አብዛኛው ሰው የሞባይል ስልኩን ካሜራ አነጣጥሮ መጠባበቅ ያዘ። አትሌቱ ደረሰ፣ ወደ ማሽኑ ተጠጋ፣ ተጠጋ፣ ተጠጋ ... የስ!! ትንሽ ተደነቃቅፎ መሮጫው ማሽን ላይ ወጥቶ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ አካባቢው በጭብጨባ፣ በፉጨትና በእልልታ ተደበላለቀ፡፡ “ዬዬዬዬዬዬዬ... ፊው ፊው ፊው ጨብ ጨብ ጨብ ጨብ ጨብ--- በስማም ሰዉ ጭንቅ በጭንቅ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን በመሮጫ ማሽኑ ላይ ሆኖ ባለበት እየሮጠ ነው፡፡ የህክምና ሰዎች በማሽኑ አማካይነት የልብ ምቱን ለመለካት ሞከሩ፡፡ ለክፉ አይሰጥም፡፡ የላቡ አወራረድ ግን የሚቀልጥ ሻማ አስመስሎታል፡፡
አትሌቱ፤ “ኧረ ደከመኝ፣ አስቁሙኛ” አለ በልምምጥ ስሜት፡፡
ሀኪሙ ውሃ ሊሰጡት ሞከሩ፤ አትሌቱ አልቻለም። ስለዚህ እየሮጠ ግሉኮስ ይሰካለት ተብሎ ተወሰነ፡፡ ችግሩ ያልተሰማ እንቆቅልሽ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡
የተለያዩ መላ ምቶች ተሰነዘሩ፡፡ “እግሮቹን የሚቆጣጠረው የአእምሮው ክፍል በሆነ ምክንያት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ይሆናል፡፡”
“ከመጠን በላይ አበረታች መድኃኒት ወስዶ ሊሆን ይችላል፡፡”
አሁን መሬት ላይ ከሮጠው 40 ኪ.ሜትሮች ሌላ  ማሽኑ ላይ ወደ 2 ኪሜ ጨምሮ፣ ወደ 42 ኪሜ ሮጠ፡፡ በብዙ ሀገራት የቀጥታ የዜና ሽፋን አገኘ፡፡ ሀኪሞቹ በውሃ ሰውነቱን እያቀዘቀዙ፣ የልብ ምቱን እየተቆጣጠሩ፣ የተለያዩ መላ ምቶችን እየሰነዘሩ የሰውየውን ሩጫ ለማስቆም ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ አሯሯጡ በጣም ያስገርማል፡፡
42 ኪሜ በ1፡58 በሆነ ፍጥነት ጨረሰ። ምን እናድርግ በሚለው ክርክር መሀል አንድ የረዥም ዓመት አሰልጣኝ፤ የማሽኑን ፍጥነት ቀስ ብለው ለመቀነስ ደፈሩ፡፡ እውነትም ሯጩ ፍጥነቱን አብሮ ቀነሰ፡፡ አሁንም አሰልጣኙ ማሽኑን ቀስ በቀስ አቀዘቀዙት፤ አትሌቱ አብሮ ፍጥነቱ ወረደ። በመጨረሻም የእርምጃ ፍጥነት ላይ ሲደርስ አትሌቱ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ እግሮቹ ግን አሁንም በተኛበት በቀስታ እየተራመዱ ነው፡፡ ልክ ጀግናው አበበ ቢቂላ ከድል በኋላ በጀርባው ተኝቶ እግሮቹን እንዳፍታታው ዓይነት፡፡ ታላቁ ሩጫ የግሪኩን የኦሎምፒክ አጀማመር ታሪክ የሚሻማ ገድል ተፈፀመበት፡፡ አትሌቱ በውጤትም፣ በጤና ሁኔታውም፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም አትሌቲክስ ማኅበራትና ለሕክምናው ሳይንስ ብዙ የቤት ሥራ ሰጥቶ አለፈ፡፡ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ሌላ ታሪክ ተጻፈ።

Read 2127 times