Sunday, 26 November 2017 00:00

የሰው ልጅ ---- እየነቃና እየደነቆረ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

    ከአንዱ ወዳጅ ጋር ሳወራ … ወይም ከራሴ ጋር ሳወራ (እንደራሴ የሚቀርበኝ ወዳጅ መቼም የለኝምና) አንድ ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ብዙ የሀሳብ መወላገድ የሚከተለው ከስሜታዊ ድምዳሜ (premise) ወይንም መነሻ ነው፡፡ “premise” የሀሳብ ቀብድ ወይንም የክርክር መነሻ መሆኑ አልጠፋኝም። ግን፤ በሚያሳዝን ሁኔታ … እና በዚህ መነሻውን አጥብቆ በመመርመር፣ ከመነሻው በተቃራኒ የቆመ ድምዳሜ የሚያዋልዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
ብዙዎቻችን ከመነሻው ጨርሰን ነው ለመመርመር የምነሳው … የምንደርሰውም እዛው ወዳልተነሳንበት ይሆናል፡፡ ስለዚህም እኔ … ምናልባት የሰው ሁሉ የሀሳብ ተመሳሳይነት … ወይንም መንጋዊነት … አልያም በሁሉም አንፃር የሚነሱ የክርክር አቅጣጫዎች ሳይጥሙኝ ቢቀሩ … “የሰው ልጅ ..ለ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደነቆረ በመሄድ ላይ ነው” ብዬ ደመደምኩኝ፡፡ ወይንም ለመደምደም ተነሳሁኝ፡፡
እንግዲህ የድምዳሜዬ ዓረፍተ ነገር በራሱ “ከዚህ ቀደም የሰው ልጅ ደንቆሮ” እንዳልነበረ---- በገበሩ ውስጥም ቢሆን ይጠቁማል፡፡ ከሁሉ የገረመኝ ደግሞ ከዘመኑ የሰው ልጆች መሀል አንዱ እንደመሆኔ … ደንቆሮ ሆኜ ነው፣ በሰው ልጅ መደንቆር ላይ የደረስኩበት ማለት ነው፡፡ ድምዳሜዬ በራሱ ውስጥ እነዚህን ትልልቅ ተቃርኖዎች ይዟል። የሰጠሁት ድምዳሜ ራሱ ቢመረመር ደግሞ ብዙ ከሞፈር የሚበላልጡ ስህተቶች እየተገነደሱ እንደሚወጡ መጠርጠር ይቻላል፡፡ ጥርጣሬም “premise” ነው፡፡ የተጠረጠረ ነገር ይመረመራል እንጂ በአንዴ ተፈርዶ የስህተት ዘብጥያ ውስጥ አይወረወርም፡፡
ትውልዱ በኒውዝላንድ የሆነ የፖለቲካ ተመራማሪ፣ በ1980 ባደረገው ጥናት የደረሰበት መረጃ ግን ከእኔ ድምዳሜ ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ተመራማሪው፣ ጄምስ ፍሊን ተብሎ ይጠራል፡፡ በ1980 ያወጣው ጥናቱ፤ የሰው ልጅ “IQ” በዓለም ዙሪያ እየጨመረ እንደመጣ የሚያሳይ ነው፡፡ በአማካይ በየሰላሳ ዓመቱ፣ IQ የቁጥር መለኪያ ላይ ሶስት እርከን ከፍ እያለ መምጣቱን ነው የሚያሳየው፡፡ ምናልባት ከዚህ ጋር ግንኙነት ባይኖረውም የሰው ልጆች ቁመትም ከበፊቱ እየጨመረ ስለመምጣቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። IQ መጠንም ሆነ የቁመቱ፣ በተወሰነ የዓለም ክፍል ላይ ለሚኖሩት ብቻ ሳይሆን ቦነስ የተሰጣቸው ለሰው ልጅ ባጠቃላይ ነው፡፡
ይህ ጭማሪ የመጣው ትምህርት ቤት በሚሰጠው እውቀት ምክንያት አይደለም። የትምህርት ጥራትም ሆነ ሽፋን በዓለም አቀፍ ደረጃ እኩል አለመሆኑ ግልፅ ነው። ከትምህርት ቤት ውጭ ያለውን ዓለም በውስብስብ መንገድ ለመረዳት ካሳዩት ብቃት አንፃር ነው፣ የIQ መጠናቸው ጎልቶ የተገኘው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ተብሎ ሲጠየቅ የሚቀርቡ ብዙ መላምቶች አሉ። እንደ ማስታወቂያ፣ ፊልምና ኢንተርኔት በመሰሉ የቴክኖሎጂ መስፋፋት ምክኒያት ነው፣ንቃተ ህሊና የጨመረው የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሌላ መላምቶች ያቀርባሉ። መላምቶች ድምዳሜ እስካልሆኑ ድረስ መሰንዘራቸው በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
…ወይም ደግሞ የእኔን የቀደመ መላምት በጭንቅላቱ በመዘቅዘቅ ሌላ መላምት ወይም ድምዳሜ ላይ መድረስም ይቻላል፡፡ እኔ “የሰው ልጅ እየደነቆረ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥቷል” ብዬ የተነሳሁበት መላምት፤ በጭንቅላት ሲዘቀዘቅ፣ “ሰው ከድንቁርናው እየተላቀቀ መጥቷል…” የሚል ድምዳሜ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት በአጭሩ የድሮው ሰው ነበር፣ ደንቆሮ ማለት ነው፡፡
ድሮ የነበረውን አሁን ካልሆነ ወይም አሁን የሆነውን ድሮ ካልነበረ አንዳች ለውጥ ተከስቷል ማለት ነው። ተጨባጩ ነገር ለውጡ ነው፡፡ ለውጡን “መልካም” ወይንም “እኩይ” ብሎ መደምደም ግን ከግል የመላምት አንፃራዊነት የሚወሰን ነው፡፡
በመሰረቱ “IQ” ወይም “Intellegence questions” የሚለው የንቃተ ህሊና ደረጃ መለኪያው አውታር ራሱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? ብለን ብንጠይቅ፣አስገራሚ መልሶችንና ጥርጣሬዎችን ወደሚያራባ መስመር ሳንፈልግ እንድንገባ ያደርገናል፡፡ ለምሳሌ በ1920 እ.ኤ.አ ገደማ የሚሰሩ የIQ ጥያቄዎች፤ የተጠያቂውን የዘር ሀረግ፣ ግንዛቤ ውስጥ የማያስገቡ ነበሩ፡፡ ስለ ዘረመል መወራረስም ሆነ ከውልደት በኋላ ተፈታኙ ያደገበት ሁኔታ (environments) መሰረታዊ ዋጋ አይሰጣቸውም ነበር፡፡
IQ የሚባለው ፈተና ራሱ ልክ እንደ ሰው ልጅ የራሱን ዝግመተ ለውጥ እያከናወነ፣ ከብዙ የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ቀስ በቀስ እየጠራ የመጣ መመዘኛ ነው፡፡ ማርክ ፒሎት የሚባል ሰው፤ በዚሁ በመመዘኛው ፈተና ላይ ያሉ የስህተት ዝግመተ ለውጦችን “The fog of imperfect tests” ብሎ ይጠራቸዋል፡፡
እርሳስ ምን እንደሆነ የማያውቅን ሰው፤ በእርሳስ የሚፃፍ ጥያቄን በመስጠት የንቃት ደረጃውን መለካት፣ የፈታኙ ወይንም የፈተናውን ስህተት ብቻ ነው እንደ ውጤት አስቀምጦ ሊያሳየን የሚችለው። የፈተናው ጥያቄዎች፤ የፈታኞቹን ርዕዮተ ዓለም ወይንም ስነልቦና የማንፀባረቅ አቅማቸው ከፍ ያለ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሁለተኛ አለም ጦርነት በፊት ያለው አስተሳሰብ በዘረኝነት የሚያምን ስለነበር፤ ከፈተናዎቹ የሚገኘው ውጤት የአንዱን ዘር አቅም በጥቅሉ ከፍ ስለማለቱ እና የሌላውን ደግሞ በንፅፅር ማነስ የሚጠቁም ነበር። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ከዘር የሚገኝ ውርስ ንቃተ ህሊናን በአንደኛ መንገድ እንደሚለውጥ የሚያሳዩ የIQ ፈተና ውጤቶች ታዩ፡፡ እነዚህን ውጤቶች ያመጡት የፈተናው አይነቶች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ከዛ በመከተል ዘር በሰው ልጅ ንቃተ ህሊና ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ በሰው Intelligent ላይ የሚመጣ ለውጥ ካለ፣ በተማረው ትምህርትና በአስተዳደጉ ስነ ልቦና ምክንያት ብቻ ነው … የሚሉ አስተሳሰቦች ተራመዱ፡፡ ከ1960 እ.ኤ.አ በኋላ ደግሞ “አስተዳደግ እና environment” ናቸው ዋናው ተባለ፡፡ … እነዚህ ድምዳሜዎች ከፈተናው ውጤት የመነጩ ይሁኑ ወይንም የፈተናው ውጤት ከድምዳሜዎቹ ግልፅ አይደለም፡፡ አንዱ ሌላውን ለማረጋገጫነት ግን እርስ በራሳቸውን ተገልግለዋል።
“ዘንድሮ ደግሞ፤ የዘረ መል ጥናት ዘመን፤ የሰው ልጅ ንቃተ ህሊናን እድገት የሚወስነው ዘረ - መልና አስተዳደግ በመተባበር የሚፈጥሩት መስተጋብር ነው” የሚል አዝማሚያ ይዘው በመከራከር ላይ ናቸው፡፡
…ስለዚህ የ IQ የንቃተ ህሊና መጠንን ደረጃ መለኪያው ፈተና ምናልባት የተቀረፀው፣ ይሄንን ድምዳሜ ከግንዛቤ ውስጥ ከቶ መሆኑ ይጠበቃል። ምናልባት ከዚህ እይታ አንፃር ከተቀረፁ ፈተናዎች። ሊሆን ይችላል ኒውዚላንዳዊው የፖለቲካ ተመራማሪ፤ የሰው ልጅን የጥቅል ንቃተ ህሊና በዲጂት እድገት ያበሰረን! …
… ስለዚህ ትምህርት … አስተዳደግ … እና ዘረ - መልን በግንዛቤ ውስጥ የከተተ ድምዳሜ፤ መማርን የንቃተ ህሊና መለኪያ አያደርገውም፡፡ ወይንም በአስተዳደግ ላይ ብቻ ተመርኩዞ “የሀብታም ልጆች የበሰለ አእምሮ ይኖራቸዋል” ከእንግዲህ አይባልም። “የእንትና ዘር ነኝ” ብቻ ተብሎ የቅድመ አያትን አጥንት ድል በራስ ላይ ስለመደገሙ ማረጋገጥም አያስኬድም፡፡
ስለዚህ እነዚህን ሦስት መሰረታዊና ለንቃተ ህሊና ማደግም ሆነ መቀነስ ከፍ ያለውን ድርሻ ሚወስዱት ምክኒያቶች (archetypes) በተናጠል የኢንተለጀንስ አይነት ሰየሙላቸው፡፡
በትምህርት የሚያድገውን (በትምህርት ቤት የተስተማረውን በመቅሰም የማይታማውን) አይነቱን ንቃተ ህሊና “አናሌቲክ” ብለው አንድ ቡድን ሰጡት፡፡ በአስተዳደጉ ምክኒያት …. ወይንም አስተዳደጉን አሸንፎ ከፍ ወዳለ ንቃተ ህሊና፣ ያለ ትምህርት የሚያድገውን (እንደ ሀገራችን ነጋዴ) “Practica” አሉት፡፡ በፈጠራ አቅም የሚገለፀውን ደግሞ “creative” ብለው ፈረጁት፡፡
እነዚህ ሦስቱ መሰረታዊ ኢንተለጀንስ አይነት ቢሆኑም … በእርስ በራሳቸው ድብልቅ የሚፈጠር ንቃተ ህሊና እና ከታወቀው ውጭ ያለው፣ ገና ያልተመረመረው ደግሞ ፈርጀ ብዙ እና ገና ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ነው።
… ስለዚህ መጀመሪያ የተነሳሁበትን ድምዳሜ … ማለትም “የሰው ልጅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደነቆረ ነው የመጣው” የሚለውን ስሜታዊነቴን ወደ ጎን አድርገን፣ የተጓዝንበትን ብቻ እንደ ሀሳብ መንገድ መቁጠር እንችላለን፡፡ ድንቁርና እና ንቃተ ህሊና ስለ ምንነታቸው ራሱ ያለቀ ትርጉም መስጠት ባልተቻለበት ሁኔታ፣ በአንዱ ወንጭፍ ተጠቅሞ ሌላውን መምታት ወይንም ማንቋሸሽ አይቻልም። ብዙ ጊዜ ከመነሻው የተነሳንበት ሀሳብ ላይ ያሉ ትርጉሞች ግልፅ ሳይሆኑ ወደ ድምዳሜ መሄድ አደገኛ ነው፡፡ ነው … ወይም ይመስለኛል፡፡

Read 1876 times